በቀጣይ ዓመት አልጄሪያ በምታዘጋጀው የአፍሪካ ሀገራት ቻምፒዮን ሺፕ(ቻን) ዋንጫ ለመሳተፍ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በመጨረሻው የማጣሪያ ምእራፍ ላይ ይገኛል፡፡ የመጨረሻው ዙር ማጣሪያ የመጀመሪያ ጨዋታውን ትናንት በገለልተኛ ሜዳ በታንዛኒያ ቤንጃሚን ምካፓ ስታዲየም ሩዋንዳን ገጥሞም አቻ በሆነ ውጤት አጠናቋል፡፡ ጥሩ እንቅስቃሴን በጨዋታው ማሳየት የቻሉት ዋልያዎቹ የሩዋንዳን ግብ መድፈር ባይችሉም የትናንቱን ጨዋታ 0ለ0 ማጠናቀቃቸው ለሶስተኛ ጊዜ በቻን ለመሳተፍ ያላቸውን ተስፋ አያጨልመውም፡፡ ይሁን እንጂ የመጨረሻው የዘጠና ደቂቃ ፍልሚያ ሩዋንዳ በሜዳዋና በደጋፊዋ ፊት የምታደርገው እንደመሆኑ ዋልያዎቹ ቀላል ፈተና አይጠብቃቸውም፡፡
ከዋናው የዋልያዎቹ ስብስብ በግብጽ ሊግ የሚጫወተው አማካይ ሽመልስ በቀለ እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ የሚገኘው የአጥቂ ስፍራ ተጫዋች አቡበከር ናስር በውድድሩ ላይ የማይሰለፉ መሆናቸው የአሰልጣኝ ውበቱን ቡድን በትናንቱ ጨዋታ ግብ ሳያስቆጥር እንዲወጣ አድርጎታል፡፡
በአገር ውስጥ ሊጎች የሚጫወቱ ተጫዋቾች ብቻ በሚሳተፉበትና በካፍ አዘጋጅነት በየሁለት አመቱ የሚደረገው የቻን የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር የማጣሪያ ጨዋታዎች ከነሀሴ ወር መጀመሪያ አንስቶ እየተከናወኑ ይገኛሉ። በቅድመ ማጣሪያ ጨዋታው ከደቡብ ሱዳን ጋር የተደለደለችው የኢትዮጵያ ስቴድየሞች የካፍን መመዘኛ መስፈርት አለማሟላታቸውን ተከትሎ በተጣለው ዕገዳ ልክ እንደ አፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎቿ ሁሉ ይህንንም ጨዋታ ከሜዳዋ ውጪ ታንዛኒያ ላይ ለማድረግ ተገዳለች።
የመጨረሻውን የማጣሪያ ጨዋታም ኢትዮጵያ እና ተጋጣሚዋ ሩዋንዳ የካፍን መስፈርት የሚያሟላ ስታዲየም የሌላቸው መሆኑን ተከትሎ እገዳ ላይ ቢገኙም ሩዋንዳ አንድ ስቴድየሟ ጨዋታ እንዲያስተናግድ ፍቃድ ማግኘቱ ይታወቃል፡፡ ይህንን ተከትሎ ሩዋንዳ ነሐሴ 29 የሚደረገውን የመልስ ጨዋታ በሁዬ ዓለም አቀፍ ስታዲየም እንደምታስተናግድ ይፋ ተደርጓል። ኢትዮጵያ ግን አሁንም ስቴድየሞቿ ፍቃድ ስላላገኙ ከሩዋንዳ ጋር ትናንት ያደረገችውን የመጀመሪያ ጨዋታ በታንዛኒያ ዳሬሰላም ቤንጃሚን ምካፓ ስታዲየም እንደምታደርግ ተገዳለች፡፡
በአፍሪካ ከዋናው አፍሪካ ዋንጫ ቀጥሎ ትልቁ የእግር ኳስ መድረክ የሆነው የቻን ዋንጫ በአገር ውስጥ ሊጎች የሚጫወቱ ተጫዋቾችን ብቻ ለማበረታታት በካፍ አማካኝነት እኤአ በ2007 የተዋወቀ ሲሆን 2009 ላይ በኮትዲቯር አዘጋጅነት ለመጀመሪያ ጊዜ ተካሂዷል። ከጊዜ ወደ ጊዜ በውድድሩ የሚሳተፉ አገራት ቁጥርም እያደገ ሄዶ ትኩረት ከሚሰጣቸው የስፖርት መድረኮች አንዱ ሆኗል። የአለምን እግር ኳስ በበላይነት የሚመራው ፊፋም እኤአ 2010 ላይ ለዚህ ውድድር እውቅና ሰጥቶታል።
ኢትዮጵያ ከሰላሳ አንድ አመታት በኋላ እኤአ 2013 ላይ በደቡብ አፍሪካ አዘጋጅነት በተካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ መሳተፏን ተከትሎ በእግር ኳሱ የተፈጠረው ከፍተኛ መነቃቃት ይታወሳል። የዚያ ትውልድ ታሪካዊ ተጫዋቾችና የዋልያዎቹ አሰልጣኝ የነበሩት ሰውነት ቢሻው ከአፍሪካ ዋንጫው ማግስት በተመሳሳይ ደቡብ አፍሪካ ላይ በተካሄደው የቻን ዋንጫ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ መሳተፍ ችለዋል። ለዚህ ተሳትፎም የመጨረሻውን የማጣሪያ ጨዋታ ከሩዋንዳ ጋር ከሜዳቸው ውጪ ተፋልመው ማለፋቸው አይዘነጋም። በተለይም በዚያ የመጨረሻ የማጣሪያ ፍልሚያ የዋልያዎቹ ቋሚ ግብ ጠባቂ የነበረው ጀማል ጣሰው ጨዋታው በመለያ ምት እንደሚጠናቀቅ ከአሰልጣኙ ጋር ቀደም ብለው በመግባባት የመለያ ምት የማዳን የተሻለ ብቃት ያለው ግብ ጠባቂ ሲሳይ ባንጫ ተቀይሮ እንዲገባ ማድረጋቸው አይዘነጋም። ሲሳይ ባንጫም ተቀይሮ ገብቶ ሁለት የመለያ ምቶችን በማዳን ዋልያዎቹን ለቻን ዋንጫ ያበቃበት ክስተት የሚታወስ ነው።
ዋልያዎቹ በቀጣዩ የቻን ውድድርም በአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ እየተመሩ በጋቦን በተካሄደው ዋንጫ ላይ መሳተፍ ችለዋል። በሁለቱም ብቸኛ ተሳትፏቸው ግን ከምድባቸው ሳያልፉ ቀርተዋል። ዘንድሮም በመጨረሻው የማጣሪያ ጨዋታ በአሰልጣኝ ውበቱ እየተመሩ ለሶስተኛ ጊዜ ለመሳተፍ ሩዋንዳን በሜዳዋ ከሳምንት በኋላ ማሸነፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ማን ያውቃል የሲሳይ ባንጫ ታሪክ በፋሲል ገብረሚካኤል ይደገም ይሆናል፡፡
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 21 /2014