ጀማ ወንዝ ከዓባይ ገባር ወንዞች አንዱ ነው::ከሰሜን ሸዋ አካባቢ የሚፈልቀው ጀማ ወንዝ በሚፈለገው ልክ ጥቅም ላይ ሳይውል ልክ እንደ ዓባይ ወንዝ ለዘመናት ሲፈስ ቆይቷል::ካለፉት ቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን የጀማ ወንዝን ለመስኖ ጥቅም ላይ ለማዋል ጥረት እየተደረገ ይገኛል::ይህን ወንዝ ጥቅም ላይ ለማዋል እየተደረገ ካለው ጥረት አንዱ ማሳያ በዚህ ወንዝ ላይ እየተገነባ ያለው የአጂማ ጫጫ መስኖ ልማት ፕሮጀክት ነው::ይህ ፕሮጀክት በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በአንጎለላ ጠራ ወረዳ እየተገነባ ይገኛል::
ይህ የመስኖ ፕሮጀክት በአማራ ክልል ውስጥ በመገንባት ላይ ካሉ ትልልቅ የልማት ፕሮጀክቶች አንዱ ነው::ግድቡ ከአንድ ዓመት ከመንፈቅ በፊት ጥር 2013 ዓ.ም ግንባታው የተጀመረ ሲሆን፤ የፕሮጀክቱን ግንባታ በሶስት ዓመት ለማጠናቀቅ ታቅዶ ስራው እንደተጀመረ ከመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያሳያል::በዚሁ እቅድ ሰኔ 2016 ዓ.ም ለማጠናቀቅ ታቅዷል::
ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመላክተው፤ ፕሮጀክቱ በ5 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ወጪ የሚከናወን ነው::የግድብና ተያያዥ ስራዎች እና የመስኖና ድሬይኔጅ ግንባታው በመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ባለቤትነት እየተከናወነ ይገኛል፤ ግድቡ 372 ሜትር ርዝመት፣ 45 ነጥብ 5 ሜትር ከፍታ እና 55 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ የመያዝ አቅም አለው::
ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ከአማራ ክልል አጎለላ ጠራና የባሶን ወረዳዎች 10 ቀበሌዎቸ ውስጥ 7 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ እንዲለማ ማድረግ ያስችላል፤ 14 ሺህ እማወራዎችና እና አባወራዎችን ተጠቃሚ የማድረግ አቅም እንዳለው የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር መረጃዎች ያመላክታል::
በግድቡ የሚያዘው ውሃ ወደ ኋላ አምስት ኪሎ ሜትር ድረስ በመተኛት 680 ሄክታር መሬት በመሸፈን ሰው ሰራሽ ሀይቅ ይፈጥራል::ይህ ሰው ሰራሽ ሀይቅ ከመስኖ ልማት በተጨማሪ ለአሳ ልማት እና ለመዝናኛ ሊውል የሚችልም ነው::በዚህም ለአካባቢው ተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ያስገኛል::
የአጂማ- ጫጫ መስኖ ልማት ፕሮጀክት በሶስት ሎቶች ተከፋፍሎ ግንባታው እየተካሄደ ያለው:: የፕሮጀክቱ ዋና ዋና ስራዎች የግድብ ግንባታና ተያያዥ ስራዎች (ሎት- ሶስት)፣ ከወንዙ ቀኝ በኩል 3000 ሄክታር የሚያለማው ዋና ቦይና የመስኖ መሰረተ ልማት ግንባታ (ሎት- አንድ) እንዲሁም ከወንዙ ግራ በኩል 4000 ሄክታር የሚያለማው ዋና ቦይና የመስኖ መሰረተ ልማት ግንባታ ( ሎት- ሁለት ) ናቸው::ሎት-ሶስት በታኅሳስ 2013 ዓ.ም እንዲሁም ሎት አንድ እና ሁለት በ2014 በጀት ዓመት ነው ግንባታቸው የተጀመረው::
በ2014 በጀት ዓመት መጨረሻ ድረስ የፕሮጀክቱ ሎት-አንድ 20 በመቶ ፣ ሎት-ሁለት 20 በመቶ እና ሎት-ሶስት 34 በመቶ ለማከናወን ታቅዶ፤ ሎት አንድ 14 ነጥብ 24 በመቶ ወይም የዕቅዱን 71 ነጥብ 20በመቶ ፣ ሎት ሁለት 2 ነጥብ 14 በመቶ ወይም የዕቅዱን 10 ነጥብ 70 በመቶ እና ሎት ሶስት 18 ነጥብ 81 በመቶ ወይም የዕቅዱን 55 ነጥብ 32 በመቶ በቅደም ተከተል ተግባራዊ ማድረግ መቻሉን ሚኒስቴሩ በቅርቡ ይፋ አድርጓል::
በዚህም መሰረት አጠቃላይ የፕሮጀክቶቹን የግንባታ አፈጻጸም በ2013 በጀት ዓመት መጨረሻ ከነበረበት ሎት-አንድ 0 ነጥብ 50 በመቶ ወደ 14 ነጥብ 74በመቶ ፣ ሎት- ሁለት 2 ነጥብ 14በመቶ (በዚህ ዓመት የተጀመረ) እና ፣ (ሎት- ሶስት) ከ22 ነጥብ 82በመቶ ወደ 41 ነጥብ 63በመቶ በ2014 በጀት ዓመት መጨረሻ ማድረስ መቻሉን የሚኒስቴሩ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ብዙነህ ቶልቻ አብራርተዋል::
ለሎት አንድ የሚያስፈልግ ተጨማሪ የካምፕ ግንባታ ሥራዎች፣ የቀኝ ዋና መስኖ ቦይ ቁፋሮ ሥራ 10 ኪሎ ሜትር ፣ የቀኝ ዋና መስኖ ቦይ የግንብ ሥራ 10 ኪሎ ሜትር ፣የቀኝ ዋና የመስኖ ቦይን ተከትሎ የመዳረሻ መንገድ 10 ኪሎ ሜትር፣ የውሃ ማስተላለፊያ እና ማፋሰሻ ውቅሮች ግንባታ ሥራ መጠናቀቁን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በቅርቡ ይፋ ባደረገው መረጃ አመላክቷል::
ለሎት- ሁለት የሚያስፈልጉ ተጨማሪ የካምፕ ግንባታ ሥራዎች፣ የግራ ዋና መስኖ ቦይ ቁፋሮ ሥራ አራት ነጥብ ሁለት ኪሎ ሜትር፣ የግራ ዋና መስኖ ቦይ የግንብ ሥራ አራት ነጥብ ሁለት ኪሎ ሜትር (በከፊል)፣ የግራ ዋና የመስኖ ቦይን ተከትሎ የመዳረሻ መንገድ 4.2 ኪሎ ሜትር በላይ ተገንብቶ ተጠናቅቋል፡፡
በተጨማሪም (ሎት- ሶስት) በክረምት ወቅት ወንዝ ለመቀልበሻ የሚያገለግለው የግርጌ ግድብ ግንባታ አብዛኛው ሥራ፣ የትርፍ ውሃ ማስወጫ ውቅር ግንባታ አብዛኛው ሥራ፣ የግድብ የታችኛው ውሃ ማስወጪያ ውቅር አብዛኛው ሥራ፣ የመስኖ ውሃ ማስወጪያ ቱቦ ቀበራ ሥራ እና የእግረኛ መተላለፊያ ድልድይ ሥራዎች፣ አብዛኛው የመሰረት ማጠናከሪያ የሲሚንቶ ማጠጣት ሥራ፣ የዋናው ግድብ የታችኛው ክፍል የተወሰነ የድንጋይ ሙሌት ሥራ እና ጊዚያዊ የመዳረሻ መንገድ ግንባታ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡
ፕሮጀክቱን የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር በባለቤትነት እያስገነባ ሲሆን፤ የሶስቱም ሎቶች ፕሮጀክት ስራ ተቋራጭ የአማራ ውሃ ስራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት ነው፤ አማካሪው አማራ ዲዛይንና ቁጥጥር ስራዎች ድርጅት ነው::
ፕሮጀክቱ ገና በግንባታ ላይ እያለ ከአሁኑ ለአካባቢው ማህበረሰብ ትልቅ ጥቅም እያስገኘ ነው:: ለበርካቶች ቋሚ እና ጊዚያዊ የስራ እድል ፈጥሯል::በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በተፈጠረ ቋሚና ጊዚያዊ የሥራ ዕድል 2 ሺህ 885 ወንዶችና 1 ሺህ 754 ሴቶች በድምሩ 4 ሺህ 639 እንዲሁም አንድ ተቋራጭ ድርጅት እና አንድ አማካሪ ድርጅት የስራ እድል ተጠቃሚ መሆናቸውን የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
የፕሮጀክቱ የፋይናንስ አጠቃቀምም መልካም የሚባል ሲሆን የበጀት ዓመቱ የፋይናንስ አጠቃቀም ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ ብር 883,542,563.00 ታቅዶ ብር 808,795,601.16 ወይም የዕቅዱን 91 ነጥብ 54 በመቶ ወጪ ሆኖ ሥራ ላይ መዋሉንም መረጃዎቹ ያመለክታሉ::
ፕሮጀክቱ የተወሰኑ ተግዳሮቶችም አጋጥመውት እንደነበር የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መረጃ ያሳያል::በተቋራጩ የገልባጭ መኪና እጥረት የፕሮጀክቱ አንዱ ተግዳሮት ሆኖ ነበር::በተለይም ሎት ሁለት ላይ ይህ ችግር ታይቷል:: የተቋራጭ ድርጅት መረጣ ሂደት ረጅም ጊዜ የወሰደ እና ተቋራጭ ድርጅቱ በወቅቱ ሥራ ያልጀመረ መሆኑ፣ የመሰረት ማጠናከሪያ ሥራ ቢጀመርም በሚፈለገው ፍጥነት ሥራው እየሄደ አለመሆኑ፣ ወረዳው የካሳ ግምቶችን በወቅቱ አስልቶ ቶሎ ወደ ሚኒስቴር መሰሪያ ቤቱ አለመላኩ ከተግዳሮቶቹ መካከል ይጠቀሳሉ::
እንደ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መረጃ፤ ችግሩን ለመቅረፍ የተለያዩ የማስተካከያ እርምጃዎችም ተወስደዋል::ተቋራጭ ድርጅቱ ያለበትን የገልባጭ መኪናዎች ችግር በፍጥነት እንዲፈታ በደብዳቤ እና በቃል እንዲያውቀው በማድረግ ችግሩን እንዲፈታ እንዲሁም የባከኑ ጊዚያትን ለማካካስ ተቋራጭ ድርጅቱ ተጨማሪ የሰው ሃይል እና ማሽነሪዎችን ወደ ፕሮጀክቱ በማስገባት የማካካሻ ስራዎችን እንዲያከናውን ጥረት ተደርጓል::ከተቋራጭ ድርጅቱ ጋር በመነጋገር እና ችግሮች እንዲፈቱ በማድረግ የግራውቲንግ ስራ ከዚህ በተሻለ ሁኔታ እንዲፈጥን ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ ይገኛል::
የመስኖ ፕሮጀክቱ ለኢትዮጵያዊያን ትርጉሙ ብዙ ነው::ከግድብነት ባሻገር ተጨማሪ መልዕክትም አለው::የግድቡ ግንባታ በፈረንጆቹ ጃንዋሪ 10 በ2021 በተጀመረበት ወቅት የወቅቱ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ እንዳሉት፤ አጂማ ጫጫ የዓባይ ገባር ወንዝ በሆነው ጀማ ወንዝ ላይ የሚገነባ ፕሮጀክት እንደመሆኑ ኢትዮጵያ በውሃ ሃብቷ የመጠቀም መብቷን የትኛውም ምድራዊ ሀይል ሊያስቆመው እንደማይችል አንዱ ማሳያ ነው::አገሪቷ በዓባይ ወንዝ ገባር ወንዞች ላይ የመስኖ ግድቦችን እየገነባች ስለመሆኗ ሌላ ማሳያ ነው::ተመሳሳይ ፕሮጀከቶች በዓባይ ገባሮች እና ሌሎች ወንዞች ላይ በብዛት መገንባታቸው በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ያለውን የህዝብ ብዛት ለመመገብ አማራጭ የሌለው ስራ ነው::
በጀማ ወንዝ አቅራቢያ የሚኖሩ አርሶ አደሮች ወንዙ ሲፈስ እያዩ ከወንዙ ሳይጠቀሙ ለዘመናት ኖረዋል:: ጀማ ወንዝም ለብዙ ዘመናት ከዓባይ ወንዝ ጋር በማበር የኢትዮጵያን ለም አፈር ወደ ጎረቤት አገሮች ሲያግዝ የኖረ ነው::ወንዙን የአካባቢው አርሶ አደሮች ለዘመናት በትካዜ ሲያዩት ኖረዋል::የግድቡ ግንባታ ተጠናቆ ስራ ሲጀመር የአጂማ ወንዝ ሲፈስ የማየት ዘመን ይቀየራል::
ፕሮጀክቱ የአካባቢውን አርሶ አደሮች በዓመት ዝናብ እየጠበቁ ከማልማት ኋላቀር ግብርና አሰራር በማላቀቅ በዓመት ከአንድ ጊዜ በላይ እንዲያለሙ ያስችላቸዋል::የአካባቢውን ማህበረሰብ የኑሮ ደረጃም ከፍ ያደርገዋል::በዓመት አንድ ጊዜ የሚያመርቱ አርሶ አደሮች ከሁለት ጊዜ በላይ ማምረት ሲችሉ በሕይወታቸው ላይ ተጨባጭ ለውጥ ያስመዘግባሉ::ለአገሪቱ ኢኮኖሚም ከፍ ያለ ሚና ይጫወታሉ፡፡
በተለይም አካባቢው የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ መዲና ለሆነችው አዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኝ እንደመሆኑ የአካባቢው አርሶ አደሮች በግድቡ ውሃ የተለያዩ አትክልቶች እና ፍራፍሬዎችን በማምረት ለገበያ ማቅረብ ስለሚችሉ የገበያ ችግር ያጋጥማቸዋል ተብሎ አይሰጋም::
በቀጣይም በሌሎች የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ላይ ሲያጋጥሙ የነበሩ ችግሮች እንዳያጋጥሙ አስፈላጊው ርብርብ ሊደረግ ይገባል::የፕሮጀክቱ ግንባታ በአስቸኳይ እንዲጠናቀቅ ከሚደረግ ጥረት ባሻገር ፕሮጀክቱ እንደተጠናቀቀ በአስቸኳይ ወደ ስራ ለማስገባት ከአሁኑ ዝግጅቶች መደረግ አለባቸው::በተለይም የአካባበቢው ህብረተሰብ ስለመስኖ ልማት ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግ በትኩረት መስራት ይኖርበታል::የአካባቢው አስተዳደር እና ማህበረሰብም የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 21 /2014