የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ አበርክቶ

የኢትዮጵያን መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግርን እውን ለማድረግ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል ተብለው ትኩረት ከተሰጣቸው ተግባራት መካከል የኢንዱስትሪ ፓርኮች (Industrial Parks) ልማት አንዱ ነው። የኢንዱስትሪ ፓርኮች የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት የመሳብ፣ የሥራ እድል ፈጠራን የማስፋት እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን እውን የማድረግ ዋና ዋና መሠረታዊ ተልዕኮዎች አሏቸው። ፓርኮቹ በሚገነቡባቸው አካባቢዎች ለሚኖረው የኅብረተሰብ ክፍል ሥራ በመፍጠርና ከአካባቢ ጋር ተስማሚ የሆነ የሥራ ከባቢ እውን በማድረግ ለሀገራዊ የምጣኔ ሀብት እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ተመራጭ ከሚያደርጓቸው ነገሮች መካከል በርካታ አገልግሎቶችን አንድ ሥፍራ ላይ ሰብሰብ አድርገው የሚያቀርቡ መሆናቸው፣ ተገቢ መሠረተ ልማት የሚገነባላቸው እንዲሁም ከሌሎች አምራቾች ጋርም የሚያገናኙ መሆናቸው ይጠቀሳሉ። ከዚህ አንፃር በኢትዮጵያም ብዙ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በማቋቋም እንዲሁም በአንፃራዊነት ዝቅተኛ ዋጋ የሚከፈልባቸውን የሰውና የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን፣ ማሽኖችን ከቀረጥ ነፃ ማስገባትን፣ የብድር አቅርቦትን፣ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን እና የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን እንደማበረታቻ በማቅረብ ትልልቅ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ፋብሪካዎቻቸውን ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲከፍቱ ጥረቶች ተደርገዋል።

በርግጥም ኢትዮጵያ የአፍሪካ የማምረቻ መናኸሪያ (Manufacturing Hub) እንድትሆን የሚደረገውን ጥረት ለማቀላጠፍ እንዲሁም የሥራ አጥነት ችግርን ለመቅረፍ ላቅ ያለ ሚና ይጫወታል ተብሎ የተጣለበት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ውጤቶች ተገኝተውበታል። በተለይም ኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድሎችን በመፍጠር ቀላል የማይባል አስተዋጽኦ አበርክተዋል። በአሁኑ ወቅት የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣናን ጨምሮ በመላ ሀገሪቱ 13 የኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚገኙ ሲሆን በሥራ እድል ፈጠራ፣ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትና በቴክኖሎጂ ሽግግር ለሀገራዊ ምጣኔ ሀብት እድገት ቀላል የማይባል አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ።

ከእነዚህ የኢንዱስትሪ ፓርኮች መካከል አንዱ በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ታሪክ ፈር ቀዳጅ የሆነው የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ነው። ግዙፉ የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ በማምረቻ ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች ትልቅ እድልን የሚፈጥር ሲሆን፣ በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ የተሰማሩ አምራቾች በፓርኩ በምርት ሥራ ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ።

ኢንዱስትሪ ፓርኩ 52 ሼዶችን የያዘ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል 39 ሼዶች በባለሀብቶች ተይዘዋል። 18 ኩባንያዎች በምርት ሥራ ላይ ይገኛሉ። ከአምራቾቹ መካከል አብዛኞቹ የውጭ ኩባንያዎች ሲሆኑ፣ ሦስቱ የሀገር ውስጥ ድርጅቶች ናቸው። በፓርኩ ውስጥ ከሚገኙት የውጭ ሀገራት ኩባንያዎች መካከል የቻይና፣ የሕንድ፣ የስሪ ላንካ፣ የፈረንሳይ፣ የዩናይትድ ኪንግደምና የኢንዶኔዥያ አምራች ድርጅቶች ይጠቀሳሉ።

የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ማቴዎስ አሸናፊ እንደሚገልጹት፣ ኢንዱስትሪ ፓርኩ በሥራ እድል ፈጠራ፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር እና በውጭ ምንዛሬ ግኝት ለሀገር ኢኮኖሚ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል። ኢንዱስትሪ ፓርኩ መሠረተ ልማቶች (መብራት፣ ውሃ፣ ስልክ፣ የቆሻሻ ማስወገጃ፣ የእሳት አደጋ መቆጣጠሪያ፣ መንገድ…) ተሟልተውለታል። ከዚህ በተጨማሪም ባለሀብቶች የኢንዱስትሪ ሚኒስቴርን፣ የኢንቨስትመንት ኮሚሽንን፣ የኢትዮ-ቴሌኮምን፣ የኤሌክትሪክ ኃይልን፣ የኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳዮች አገልግሎትን፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽንን፣ የባንክና የሌሎች ተቋማትን አገልግሎቶች በተቀናጀ ሁኔታ የሚያገኙበት የአንድ ማዕከል አገልግሎት አለው። ይህ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ባለሀብቶች ለምርት ሥራቸው የሚስፈልጓቸውን አስተዳደራዊና የግብዓት ፍላጎቶች በፍጥነትና በጥራት እንዲያገኙ በማስቻል የሀብት ብክነትን ለመቀነስ ያግዛል።

በአሁኑ ወቅት በኢንዱስትሪ ፓርኩ ከ23ሺ በላይ ሠራተኞች እንደሚገኙ የሚናገሩት አቶ ማቴዎስ፣ ኢንዱስትሪ ፓርኩ ለዜጎች ሥራ እድል መፍጠር ብቻ ሳይሆን፣ ሠራተኞች በቂ የሙያ ክህሎት እንዲያገኙና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እያስቻለ እንደሚገኝ ይገልፃሉ። ‹‹ኢንዱስትሪ ፓርኩ ሥራ ከጀመረ ወዲህ ከ80ሺ በላይ ዜጎች በፓርኩ የሥራ እድል አግኝተው ሰርተዋል። ሠራተኞቹ የሙያ ክህሎት አግኝተዋል፤ በሙያቸው ባገኙት ልምድም ተወዳዳሪ ሆነዋል። ኢትዮጵያውያን በኢንዱስትሪ ፓርኩ ውስጥ የሥራ እድል ማግኘታቸው ለቴክኖሎጂ ሽግግርም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል። በውጭ ሀገራት ዜጎች ሲከናወኑ የነበሩ ሥራዎች በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች መሰራት ችለዋል። ቀደም ሲል ከአንድ ሺ በላይ የውጭ ሀገራት ሠራተኞች ነበሩ፤ አሁን ያሉት 355 ብቻ ናቸው፤ አብዛኞቹ በኢትዮጵያውያን እየተተኩ ነው። ትናንት በድርጅቶች ተቀጥረው ባለሙያ የነበሩ ሰዎች ወደፊት ፓርኩ ውስጥ ሼድ ይዘው አምራች እንዲሆኑ ጥረት ይደረጋል›› በማለት ያስረዳሉ።

ኢንዱስትሪ ፓርኮች የውጭ ምንዛሬ ከማስገኘት ኃላፊነታቸው ባሻገር፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ እንዲመያርቱ በማድረግ ለተኪ ምርቶች ልማት አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት በርካታ ተኪ ምርቶችን እያመረቱ ይገኛሉ። በዚህ ረገድ የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለተኪ ምርቶች ልማት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ የፓርኩ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ማቴዎስ ይናገራሉ። እሳቸው እንደሚሉት፣ ከዚህ ቀደም ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫዎች ከነበሩት የሥራ እድል ፈጠራና የውጭ ምንዛሬ ግኝት ባሻገር ለተኪ ምርት (Import Substitution) እና ትስስር (Linkage) ትኩረት ተሰጥቷል። የፀጥታ ኃይሎች የደንብ ልብስ በሀገር ውስጥ መመረቱም የዚህ ትኩረትና ጥረት ማሳያ ነው።

በውጭ ምንዛሪ ግኝት ደግሞ፣ ኢንዱስትሪ ፓርኩ የገበያ መዳረሻዎችን በማስፋት ላይ እንደሚገኝና በአሁኑ ወቅትም በየወሩ በአማካይ ከአራት ሚሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ ያላቸውን ምርቶች ለውጭ ገበያ እያቀረበ እንደሚገኝም አቶ ማቴዎስ ይገልፃሉ። ‹‹ከዚህ ቀደም አብዛኞቹ አምራቾች የገበያ መዳረሻቸው ወደ አውሮፓና አሜሪካ ነበር፤ አሁን ግን ለሀገር ውስጥ ገበያ ለአፍሪካ ገበያ ትኩረት ተሰጥቷል። በፓርኩ ውስጥ የሚገኙ አምራቾች ለአፍሪካ ገዢዎች ራሳቸውን እያስተዋወቁና የገበያ አማራጮቻቸውን እያሰፉ ይገኛሉ›› ይላሉ።

የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ በፓርኩ ውስጥ የሚመረቱ ምርቶች የአካባቢ ጥበቃ ደረጃዎችን ያሟሉ እንዲሆኑ ያደረጋቸው ጥረቶች ፍሬ አፍርተውለት፣ ሰሞኑን ‹‹Environmental Management System Cer­tificate ISO 14001:2015›› የተሰኘ የጥራት ማረጋገጫ ከኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት አግኝቷል። ይህ የጥራት ማረጋገጫ በፓርኩ የሚመረቱ ምርቶች የምርት ሂደቶቻቸው ዓለም አቀፍ ሕጎችን እና የአካባቢ ጥበቃ ደረጃን ያሟሉ መሆናቸውን እንደሚያሳይና በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ተወዳዳሪነትን የሚጨምር እንደሆነ አቶ ማቴዎስ ያስረዳሉ።

በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የማርኬቲንግ፣ ፕሮሞሽንና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ምክትል ዋና አስፈፃሚ አቶ ዘመን ጆነዲ፣ የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከፍተኛ የሥራ እንቅስቃሴ ከሚታይባቸው ኢንዱስትሪ ፓርኮች መካከል አንዱ መሆኑን ጠቁመው፣ በ2016 የበጀት ዓመት የበጀት ዓመት ለአውሮፓና ለአሜሪካ ገበያዎች ካቀረባቸው የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ምርቶች ከ44 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ እንዳስገኘ ይናገራሉ።

አቶ ዘመን ‹‹የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ልማት ታሪክ ፈር ቀዳጁ ኢንዱስትሪ ፓርክ ነው። ፓርኩ በሥራ እድል ፈጠራ፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና በውጭ ምንዛሬ ግኝት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው። ብዙ ወጣቶች የእውቀትና ክህሎት ሽግግር ተጠቃሚ ሆነው ፓርኩን እያንቀሳቀሱ ይገኛሉ። ጀማሪ ሠራተኛ ሆነው ወደ ፓርኩ የገቡ ወጣቶች ሙያቸው አዳብረው አሁን በአስተዳደርና በሌሎች የሙያ ኃላፊነቶች ላይ እየሰሩ ነው›› በማለት ኢንዱስትሪ ፓርኩ በሥራ እድል ፈጠራና ቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ ያለውን ሚና ያብራራሉ።

ኢትዮጵያ ከአጎዋ (AGOA) ተጠቃሚነቷ መታገዷን ተከትሎ የተፈጠሩ የገበያ ክፍተቶችን ለመሙላት አዳዲስ የገበያ መዳረሻዎችን በማፈላለግ የአምራቾቹን የገበያ ተደራሽነት ማስፋት ስለመቻሉም አቶ ዘመን ይገልፃሉ። ‹‹በአጎዋ መታገድ ምክንያት የተፈጠሩ ክፍተቶችን ለማስተካከል በፓርኮች የሚመረቱ ምርቶች ሌሎች ዓለም አቀፍ ገበያዎችን እንዲያገኙ ተደርጓል። ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር (ሚሲዮኖችንና ኤምባሲዎችን በመጠቀም) ተጨማሪ ገበያዎችን ለማግኘት እየሰራን ነው። የብሪክስ (BRICS) ሀገራት ሰፊ ገበያ አላቸው። የእነዚህን ሀገራት ገበያዎች ለመጠቀም እየተሰራ ነው›› ይላሉ።

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሰላማዊት ካሣ በበኩላቸው፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን አቅም የማጠናከር ተግባር መንግሥት የሀገር ውስጥ ምርትን ለማሳደግ የያዘው የትኩረት አቅጣጫ አካል መሆኑን ይገልፃሉ። እንደ ሚኒስትር ዴኤታዋ ገለፃ፣ መንግሥት የኢንዱስትሪ ፓርኮቹን አቅም በማሳደግ የሥራ እድል ፈጠራን፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርንና የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለመጨመር ለባለሀብቶች ዘርፈ ብዙ ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል። በዚህም በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የሚገኙ አምራቾች ምርታቸውን እያሳደጉና የገበያ መዳረሻዎቻቸውን እያሰፉ ይገኛሉ። ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ሀገራዊ ንቅናቄ፣ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው፣ የህዳሴ ግድብ ተጨማሪ ኃይል ማመንጨቱና ሌሎች ርምጃዎች የኢንዱስትሪው ዘርፍ ትርጉም ያለው እድገት እንዲያስመዘግብ እንደሚያስችሉም ያብራራሉ።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍስሃ ይታገሱ (ዶ/ር)፣ የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ወቅታዊ የምርት ሂደትና አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴ አበረታች መሆኑን ከጥቂት ሳምንታት በፊት መግለፃቸው ይታወሳል።

የሀገሪቱን የምጣኔ ሀብት መዋቅር ከእርሻ መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለማሸጋገር የሚያግዙ በርካታ መልካም አጋጣሚዎችና እድሎች አሉ። ይሁን እንጂ እነዚህን መልካም አጋጣሚዎች በመጠቀም የኢኮኖሚውን መዋቅራዊ ሽግግር ለማሳካት የተከናወኑ ተግባራት ሀገሪቱ ካላት አቅምና ፍላጎት ጋር ተመጣጣኝ አይደሉም። ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ ያላትን አቅም በመጠቀምና ከዚሁ ዘርፍ የሚገኘውን ገቢ በማሳደግ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ የምታደርገውን መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግር ለማሳካት አምራች ዘርፉ አሁን ካለው አፈፃፀም በብዙ እጥፍ እንዲጨምርና እንዲሻሻል ማድረግ ያስፈልጋል።

የአምራች ዘርፉ እድገት ሊሻሻል የሚችለው ከኢንቨስትመንት መስፋፋት ጋር ተያይዞ ነው። የኢንዱስትሪ ፓርኮች ደግሞ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ተግባራዊ በማድረግ ለኢንቨስትመንት መስፋፋት ምቹ ሁኔታዎችን የሚፈጥሩ ናቸው። ስለሆነም መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግሩን ለማሳካት የኢንዱስትሪ ፓርኮችን አፈፃፀም ማሻሻል ይገባል። ይህም ባለሀብቶች ወደ ፓርኮቹ ገብተው ለማምረት የሚያስችሏቸውን የመሠረተ ልማት ግብዓቶች፣ የሰለጠነ የሰው ኃይልና የፋይናንስ አቅርቦት ማሟላትን እንደሚያካትት ሊታወቅ ይገባል።

አንተነህ ቸሬ

አዲስ ዘመን ነሐሴ 30/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You