ኢትዮጵያ ተፈጥሮ የለገሰቻት የማዕድን ሀብት ከፍተኛ ክምችት ያላት ሀገር ብትሆንም ይህ ሀብቷ በተለያዩ ምክንያቶች በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል አልተደረገም። ጥቅም ላይ አለመዋሉ ብቻ ሳይሆን በቅጡ እንዳልተጠናም መረጃዎች ያመላክታሉ። በመሆኑም ቀደም ባሉት ጊዜያት የማዕድን ዘርፉ ትኩረት ተነፍጎት በመቆየቱ የተነሳ እዚህ ግባ የሚባል ሥራ በዘርፍ አልተሰራም። በመሆኑም ሀገሪቷ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም ሳታገኝ ቆይታለች።
ይሁን እንጂ የማዕድኑ ዘርፍ ትኩረት ተሰጥቶት ከተሰራበት ገቢ በማመንጨትና የሥራ እድል በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ከመሆኑም ባሻገር የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት መሆን እንደሚችል ይታመናል። ታዲያ ሀብቱን በአግባብ አውቆና አልምቶ ጥቅም ላይ እንዲውል ከተደረገ አንዱ የኢኮኖሚ መሠረት ሆኖ ሀገር ከድህነት አረንቋ እንድትወጣ የሚያደርግና ወደፊት የሚያሻግር ነው።
ይህን ገና ያልተነካና ብዙም ያልተሰራበትን ሀብት በማልማት ሀገር ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ ብዙ ሥራዎች መሥራትን ይጠይቃል። በተለይ ኢትዮጵያ ያላትን ከፍተኛ የማዕድን ሀብት ክምችት በደንብ አጥንቶ፣ አውቆና ለይቶ ማልማት ከተቻለ የማዕድን ውጤቶችን ኤክስፖርት አድርጋ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ያስችላታል። ማዕድናቱን ወደ ውጭ በመላክ ከምታገኘው የውጭ የምንዛሪ ይልቅ ቅድሚያ ተሰጥቶት ከተሰራበት ከውጭ የምታስመጣውን የማዕድን ውጤቶችን በሀገር ውስጥ በማምረትና መጠቀም፣ ምርቱን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ይበልጥ ተጠቃሚ ልትሆን ትችላለች። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህም መንግሥት ለማዕድን ዘርፉ ትኩረት በመስጠቱ ከአምስቱ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች አንዱ አድርጎ በመወሰድ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ።
በዕለቱ ዝግጅታችንም የማዕድን ዘርፉ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ስለሚኖረው አበርክቶ ስናነሳ የዕለቱን የጳጉሜን 2 ቀን 2016 ዓ.ም መልዕክት ታሳቢ በማድረግ ነው። የጳጉሜን ቀናት በተለያዩ ስያሜዎች የተሰየሙ ሲሆን፤ ዛሬ ጳጉሜን 1 ቀን 2016 ዓ.ም የመሻገር ቀን “የመሻገር ጥሪቶች፤ የአዲስ ብርሃን ወረቶች ” በሚል መሪ ሃሳብ ነው።
ኢትዮጵያ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት ከምታደርጋቸው ዘርፈ ብዙ ጥረቶች መካከል ቁልፍ ሚና የሚጫወተው የማዕድን ዘርፍ እንደሆነ ይታመናል። ሀገሪቷ የማዕድን ሀብቷ ጥቅም ላይ ውሎ ሀገሪቷ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ ከማድረግ ባሻገር የኢኮኖሚ መሠረት ሆኖ ወደፊት መሻገሪያ ድልድይ እንዲሆን ከማድረግ አኳያ ሀገሪቷ ያላትን አቅምና አሁን ላይ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎችን አስመልክቶ የሚከተለውን አሰናድተናል።
መረጃዎች እንደሚያመላክቱት ከሆነ ኢትዮጵያ ከዓለም የማዕድን ክምችት አኳያ ስትመዘን በርካታ የማዕድናት ዓይነቶች ስላለት ስማቸው በአንደኝነት ከሚጠቀሱት መካከል ትገኛለች። ይህን ከፍተኛ የማዕድን ክምችቷን በዓይነት ስንመለከትም ወርቅ፣ የከበሩና ጌጣጌጥ፣ ፖታሽ፣ ሊትየም፣ ኮፐር፣ ማንጋኒዝ፣ ክሮማይት፣ የፎስፌት፣ ኒኬል፣ ጨው፣ ለኢንዱስትሪ (የታንታለም፣ ብረት እና ብረት ነክ ማዕድናት እና ሌሎች)፣ ለኮንስትራክሽን (የድንጋይ ከሰል፣ አሸዋና ሌሎች)) ግብዓት የሚውሉ ማዕድናት፣ የኢነርጂ፣ የጂኦተርማል ማዕድናት፣ በአሁኑ ወቅት በዓለም እጅግ ተፈላጊ የሆኑ እና የሌሎች ማዕድናት ዓይነቶች ይገኙባታል። በተለይም በዓለም ላይ እጅጉን ተፈላጊ የሆኑ አረንጓዴ ቴክኖሎጂን ለማምረት ከፍተኛ አቅም ያላቸው ማዕድናት መገኛ መሆኗን መረጃዎች ያመላክታሉ።
ከማዕድን ሚኒስቴር የተገኙ መረጃዎችም ይህንን የሚያጠናክሩ ናቸው። ሀገሪቱ ያሏት የማዕድን ሀብት ዓይነትም ሆነ ክምችት መጠን በትክክል ስለማይታወቅ ይህን ለማወቅ በየጊዜው ጥናቶች ይካሄዳሉ። ይሁን እንጂ እስካሁን በተደረገው የዳሰሳ ጥናት የክምችት መጠናቸው የታወቀ ማዕድናት መኖራቸው ይጠቁማሉ። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ወርቅ ሲሆን በሀገሪቱ ከ517 ቶን በላይ የወርቅ ክምችት መኖሩ ተረጋግጧል። በከበሩት ማዕድናት ዘርፍ ከ40 ያላነሱ ድንቅ እና ውድ የሆነ ዋጋ ያላቸው ማዕድናት አላት። ሀገሪቱ ከዓለም ግዙፉ ያልለማ የፖታሽ ክምችት ካላቸው ሀገራት አንዷ ናት። በደናክል ተፋሰስ ውስጥ ከ26 ቢሊዮን ቶን በላይ የፖታሽ ሀብት የሚገኝ ሲሆን፤ 540 ሚሊዮን ቶን የሚገመት የፖታሽ ክምችት አላት። የጂኦተርማል አቅሟም እስከ 10ሺ ሜጋ ዋት በላይ ማመንጨት አቅም አላት። በአሁኑ ወቅት ያላት የድንጋይ ከሰል ክምችትም ግማሽ ሚሊዮን ቶን በላይ የሚጠጋ እንደሆነ ይገመታል።
እስካሁን ድረስ በተደረገው የዳሰሳ ጥናት የተለየውን የሀገሪቱ የማዕድን ሀብት ከፍተኛ ክምችት መጠን ስንመለከትም ዘርፉ ገና ያልተነካ፣ ብዙ ሊሰራበት የሚችል እንደሆነ ያመላክታል። ይሁን እንጂ ሀገሪቱ ቀደም ባሉት ጊዜያት ለበርካታ ዓመታት ማዕድኑ እያላት በሀገር ውስጥ በማምረት መጠቀም ሳትችል ቀርታ ከውጭ ሀገር በውድ ዋጋ እያስገባች መቆየቷ ይታወሳል። በተለይ ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች፣ ለብረት፣ ለሴራሚክ፣ ለጨርቃጨርቅ እና ሌሎች ኢንዱስትሪዎችም ለኃይል ምንጭነት የሚውለውን የድንጋይ ከሰል ለማስመጣት ከፍተኛ ወጪ ስታወጣ ኖራለች። ለዚህም በየዓመት ከ300 ሚሊዮን ዶላር በላይ ስትጠየቅ እንደነበር መረጃዎች ያመላክታሉ።
ምንም እንኳን የማዕድን ሀብት ከፍተኛ ኢንቨስትመንትና መዋለ ነዋይ የሚጠይቅ እንደመሆኑ አሁን ላይ በሚፈለገው መጠን ኢንቪስት ተደርጎበት ሀገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ማግኘት ችላለች ባይባልም ዘርፉ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራበት መሆኑ ተስፋ ሰጪ ነው። በመሆኑም ከጊዜ ወደ ጊዜ በዘርፉ ለውጦችና መሻሻሎች እየታየ ይገኛል።
ለዚህ ውጤትም አሁን ላይ ሀገሪቱ ማዕድኑ እያላት ከውጭ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የምታስገባው ማዕድን በሀገር ውስጥ በመተካት ያለመ አሰራር እየተገበረ ይገኛል። ባለፉት ጥቂት ዓመታት መንግሥትም ለዘርፉ ትኩረት በመስጠት ሀገሪቷ ከውጭ የምታስመጣው የማዕድን ሀብት ውጤቶች በሀገር ውስጥ ለመተካት እየተሰሩ ባሉ ሥራዎች ለውጦች እየታዩ ውጤቶች እየተመዘገቡ መጥተዋል። ለአብነትም የድንጋይ ከሰል ምርት ብንመለከት ሙሉ ለሙሉ በአገር ውስጥ የመተካት ሥራውም ተጠናክሮ ቀጥሏል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከውጭ ሀገራት የሚገባው የድንጋይ ከሰል በሀገር ውስጥ በማምረት ለመተካት በተሰሩ ሥራዎች በአሁኑ ወቅት የሲሚንቶ ኢንዱስትሪዎች ለኃይል ምንጭነት እንደዋና ግብዓትነት የሚጠቀሙት የድንጋይ ከሰል 63 በመቶ በሀገር ውስጥ በማምረት መሸፈን ተችሏል። በዚህም ምርቱን በሀገር ውስጥ በመተካት ከ120 በላይ ሚሊዮን ዶላር ዓመታዊ ወጪን ማዳን የተቻለ መሆኑን ከማዕድን ሚኒስቴር የተገኙት መረጃዎች ያመላክታሉ።
እነዚህ የድንጋይ ከሰል ክምችቶችም በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ይገኛሉ። ክምችቱ በቤንሻንጉል ጉምዝ፣ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በደቡብ ምዕራብ እና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች ስለመኖራቸው መረጃዎች ያሳያሉ። ይህም ሀገሪቱ የድንጋይ ከሰልን በሀገር ውስጥ በማምረት ከውጭ የሚመጣውን በማስቀረት ሙሉ ለሙሉ መተካት የሚያስችል አቅም እንዳላት ማሳያ ነው።
በተመሳሳይ ሀገሪቱ እንደ ኦፓል፣ ኤመራልድ፣ ሳፋየር፣ ሩቢ፣ አጌት እና ኳርትዝ የመሳሰሉ በዓለም ላይ እጅግ ተፈላጊ የሆኑ የከበሩና የጌጣጌጥ ማዕድናት እምቅ ሀብት እንዳላትም ይታወቃል።
መረጃዎች እንደሚያመላክቱት አሁን ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ በከበሩና በጌጣጌጥ ማዕድናት ዘርፍ በዓመት 250 እስከ 300 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ሀብት ይንቀሳቀሳል። ይህ ሀብት በኢትዮጵያም እስከ ባለፈው ዓመት ድረስ ከሶስት እስከ አራት ሚሊዮን ዶላር ሀብት ያስገኘ ነው። ይህ የዓለምን ኢኮኖሚ እያንቀሳቀሰ የሚገኘውን ሀብት በሚገባ ለመጠቀም የሚያስችሉ ሥራዎች ከተሰራ አመርቂ ውጤቶችን ማስመዝገብ እንደሚቻል ያመላክታል።
በከበሩና በጌጣጌጥ ማዕድናት ዘርፋም ከባለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ በመንግሥት ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶት ሥራዎች በመሥራታቸው አበረታች ለውጦች እየታዩ መጥተዋል። በተለይ ደግሞ የከበሩና የጌጣጌጥ ማዕድናት ለውጭ ገበያ በመላክ ለኢኮኖሚ ጠቀሜታ እንዲውሉ የማልማት ሥራው ተጠናክሮ ቀጥሏል።
በአሁኑ ወቅት የከበሩና የጌጣጌጥ ማዕድናት ላይ እሴት በመጨመር ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሪን እንዲያመጡ እየተደረገ ይገኛል። ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን የሚበልጠውን ገበያ የያዙት ምንም ዓይነት እሴት ሳይጨመርባቸው በጥሬው የሚላኩት ማዕድናት ናቸው።
የዘርፉን የአምስት ዓመታት የውጭ ገበያ መረጃ ይህንኑ የሚያመላክት ነው። በአምስት ዓመታት ለውጭ ገበያ ከተላኩት የከበሩና የጌጣጌጥ ማዕድናት 95 በመቶ ያህሉ በጥሬው (ምንም ዓይነት እሴት ሳይጨመርባቸው) እየተላኩ ሲሆን፤ ቀሪዎቹ አምስት በመቶ ያህሉ ብቻ እሴት ተጨምሮባቸው የሚላኩ መሆኑን ነው።
የማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ በአንድ ወቅት ስለከበሩ ማዕድናት ሲናገሩ ሀገሪቷ በከበሩ ማዕድናት ዘርፍ የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ በማድረግ ወደ ቀጣይ ምዕራፍ እንዲያሸጋገሩ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በከበሩት ማዕድናት ዘርፍ ከ40 ያላነሱ ማዕድናት ይኖራት እንጂ ሀብቱ በቅጡ ስላልታወቀ ጥቅም ላይ አልዋልም። ለዚህም ደግሞ ዋንኛ ምክንያት እስካሁን በዚህ ዘርፍ እውቅና ያላቸው ባለሙያዎች ስላልነበሩ ያላለቀለትና እሴት ያልተጨመረበትን የከበረ ድንጋይ ለተለያዩ ሀገራት ስናቀርብ ኖረናል ነው ያሉት ሚኒስትሩ። ይህ ደግሞ እንደ ሀገር ማግኘት ያለብን ዋጋ ሳናገኝ፤ በብዙ ሺዎች ቶን እየላክን ከ10 ሚሊዮን ዶላር ያልበለጥ እድገት ስናስመዘገብ ቆይተናል ሲሉ ተናግረዋል።
እንደ ሚኒስትሩ ማብራሪያ፤ ኢትዮጵያ እጅግ በጣም ውድ የሆነ ኦፓል፣ ሳፋየር እና ኤምራልድ የመሳሳሉ ማዕድናት ያላት ሀገር ብትሆንም እውቀት ስለሌለን በኢንዱስትሪ ደረጃ የሚያመርቱ ተቋማት ስለሌሉ ሀብቱ በከንቱ እንዲባክን ሆኗል። በከበሩት ማዕድናት ዘርፍ ከወርቅ ባልተናነሰ ሁኔታ በቢሊዮን ዶላር ኤክስፖርት ማድረግ ትችላለች። በማዕድን ዘርፉ ዋንኛ ኤክስፖርት የሚደረገው ተደርጎ የሚቆጠረው ወርቅ ነው። ነገር ግን በደንብ ከተሰራ የአንድ ኦፓል ዋጋ ከወርቅ ዋጋ በላይ ያወጣል። በመሆኑን ዘርፉን በእውቀትና በቴክኖሎጂ ተደግፎ ሊመራ ይገባል ማለታቸው የሚታወስ ነው።
የማዕድን ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሚሊዮን ማትዮስ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የተለያዩ የማዕድን ሀብቶች ያሏት ሀገር እንደመሆኗ የማዕድን ሀብቷን በማልማት የመጠቀም ሰፊ እድል ያላት መሆኑን ይገልጻሉ።
እሳቸው እንዳሉት፤ የመጀመሪያው ጉዳይ ሀገሪቱ ያላትን ሀብት ለይቶ በማወቅ የማዕድን ሀብቱ በየትኛው አካባቢ በምን ያህል መጠን ሊለማ ይችላል የሚለው ሥራ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል። በመቀጠልም ማዕድን ሀብቱ የሚለማበት ሁኔታ ማመቻቸት ያስፈልጋል።
ሀገሪቷ ከማዕድን ዘርፍ ባላት አቅም ልክ ተጠቃሚ እንድትሆን ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ነው። በተለይ ዘርፉ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሰፊ የሥራ እድል መፍጠር ያስችላል። በ2016 በጀት ዓመት ስምንት ወራት አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ዜጎች በዘርፉ ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙ ጠቅሰው፤ በተዘዋዋሪ ደግሞ ከሰባት ሚሊዮን በላይ የሆኑ ዜጎች ከዘርፉ ተጠቃሚ እንደሆነ መናገራቸው ይታወሳል።
በተለይ በአሁኑ ወቅት ዘርፉ እንዳያንሰራራ እያደረጉ ያሉት ዋንኛ ተግዳሮቶች መካከል አንዱ ሕገወጥነት መሆኑ ይጠቀሳል። እንደሚኒስትር ዴኤታው ማብራሪያ ሕገ ወጥነት በመከላከል ረገድ ከፌዴራል እስከ ክልል ያለው ተቋማት ተቀናጅቶ እንዲስሩ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የሚመራ ሀገራዊ የማዕድን ካውንስል ተቋቁሞ ወደ ተግባር ተገብቷል። ካውንስሉ የክልል ምክትል ፕሬዚዳንቶች፣ ሚኒስትሮችም የተካተቱበት ስለሆነ ከክልልና ከፌዴራል ያሉ አካላት በቅንጅት ሥራዎችን የሚሰሩበት ነው።
የማዕድን ካውንስሉ ቅንጅታዊ አሰራሮችን መከተል በማዕድን ዘርፍ ውጤት ያመጣል ተብሎ ይታሰባል ያሉ ሚኒስትር ዴኤታው፤ በዘርፉ ተንሰራፍቶ ያለውን ኮንትሮባንድ ንግድና ሕገ ወጥነት ለመቅረፍም የክልል እና የፌዴራል የጸጥታ መዋቅሩ ከፖለቲካ አመራሩ ጋር ተቀናጅቶ የሚሰራበትን እድልም የሚፈጥር ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በአጠቃላይ ሀገሪቷ በማዕድን ዘርፉ ያላት ሰፊ የመጠቀም አቅም በተወሰነ መልኩ ለማንሳት ተሞከረ እንጂ እያንዳንዱን የማዕድን በዝርዝር ብንመለከት ሰፊ ጊዜና ሰዓት ይፈጃል። አሁን ላይ እየታዩ ያሉ ጅምሮችም ተጠናክረው ቀጥለው ሀገር ከሀብቱ ተጠቃሚ መሆን እንድትችል የሁሉንም አካላት ርብርብ ይጠይቃልና በተለይም የሚመለከታቸው ሁሉ የየድርሻቸው በመወጣት ዘርፉን ማሻገር ይገባል የዝግጅት ክፍሉ መልዕክት ነው።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 1 /2016 ዓ.ም