የዘመናችን የኔሮ አልጋ ወራሾች፤
ሕወሓት ለኢትዮጵያ መከራ፣ ለሕዝቧ የስቃይ ምንጭ ሆኖ የተተከለ መርገምት ነው። በባዕድ ቋንቋ እንግለጸው ከተባለ “TPLF:- The problem child of Ethiopia” ልንለው እንችላለን። ይህ የሽብር ቡድን ግማሽ ክፍለ ዘመን ለሚጠጋ ዓመታት ኢትዮጵያን ሲያምሳት፣ ምድሪቱን በደም አበላ ሲያጨቀይ፣ የተከበረውን የትግራይ ሕዝብ ማቅ በማልበስ ለመከራና ለእንባ እንደዳረገ “ለነጭ ጸጉር” ሊበቃ ችሏል። ያለ ባሩድ ሽታ መተንፈስና ያለ ደም ግብር መኖር የማይችሉት የዚህ አሸባሪ ቡድን መሪዎች፤ ሰብዓዊነት ለሚሉት “ክብር” ደንታ የሌላቸውና በሞትና በእልቂት የሚስቁ የዘመናችን ኔሮዎች ናቸው ማለት ይቻላል። ሕወሓት የተወከለበት የሮማው መሪ የኔሮ ታሪክ እንደሚከተለው በአጭሩ ይታወሳል።
በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ከጥቂት የሩቅ ምሥራቅ መንግሥታት በስተቀር አብዛኛዎቹ የወቅቱ ሀገራት በሮም አገዛዝ ሥር ወድቀው እንደነበር የዓለም ታሪክ ይነግረናል። የሮማው ገዢ የኔሮ የንግሥናና የገናናነት ዓመታት የሚባሉት ከ54 – 68 ዓ.ም የነበሩት 14 ዓመታት ነበሩ። ኔሮ ጎላ ባለ ሁኔታ የሚታወቀው በግዴለሽነቱ፣ በጨካኝነቱ፣ በአዝማሪ ወዳድነቱና በገንዘብ አባካኝነቱ ነበር። የሕዝቡን ገንዘብ ሲያራቁት ይሉኝታም ሆነ ስጋት ፍጹም በስሜቱ እንደማይዞር ግለ ታሪኩ ይመሰክራል። እያደርም ትዕቢቱና እብሪቱ እየገነነ ሄዶ ሕዝቡን መጨቆንና መግደል ዋናኛ ስራው እስከ መሆን ደረሰ።
በ64 ዓ.ም የሮም ቤተመንግሥትን የሚያስንቅ ወርቃማ ቤት (Golden House) ለራሱ በገጠራማው የከተማዋ ዳርቻ በኤስኩሊን (Esquiline) አስገንብቶ ሲያበቃ የነባሯን የሮም ከተማ የዝና ተቀናቃኝነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲያበቃ ወሰነ። የእብደቱን ድርጊት የፈጸመውም በመጠጥ ኃይል ክፉኛ ሰክሮ በሰገነቱ ላይ ቆሞ እየሳቀ አብዛኛውን የሮም ከተማ ክፍል በእሳት አጋይቶ የዶግ አመድ በማድረግ ነበር። እንዳሰበውም ተሳካቶለት ሮም በአንድ ምሽት ወደ ትቢያነት ተለወጠች።
የተመኘው ወርቃማው ቤተመንግሥቱ ተሰርቶ እንደተጠናቀቀና የሮም ከተማ በወደመች በአጭር ጊዜ ውስጥ ግን ሕዝቡና ሹማምንቱ በሚያስተውሉት የመሪያቸው ጭካኔና የእብደት ድርጊት ትእግስታቸው ስለተሟጠጠ የኔሮ ገናናነትና ፈላጭ ቆራጭነት እያደር እየቀዘቀዘ በመሄድ የሕዝብ ተቃውሞና አመጽ በየክፍለ ሀገራቱ መቀጣጠል ጀመረ። አምርረው የሚቃወሙትንና ከመንበረ ስልጣኑ ሊያስወግዱት ሙከራ ያደረጉትን ለውጥ ፈላጊ ዜጎቹን በአሰቃቂ ሞት እየቀጣ ዕድሜውን ለማራዘም ሙከራ ቢያደርግም የተቀጣጠለው የሕዝብ አመጽ ግን በአጭሩ ሊበርድና ሊገታ አልቻለም።
በመጨረሻም የተቃዋሚዎቹ ቁጣ ገንፍሎ በመውጣት የኔሮ ፍጻሜ መቃረቡ ተረጋገጠ። አንዴ የእብሪቱና የትምክህቱ ዋንጫ ሞልቶ መገንፈል ጀምሯልና የሕዝቡን ቁጣ ማንም ሊያስቆም አልተቻለውም። በራሱ በኔሮ ሠራዊት ውስጥ ሳይቀር ተቃውሞው በከፍተኛ ሁኔታ ከዳር ዳር እንደ ወላፈን በመግለብለቡ ፍጻሜው እየተቻኮለ መገስገስ ጀመረ።
ነገሮች መባባሳቸው ያባነነው ኔሮ ከተቀሰቀሰበት የሕዝብ አመጽ አምልጦ ለመሄድ ሮምን ወደ ኋላው ትቶ በሽሽት ላይ እያለም አንዱን የቅርቡን ሰው አግኝቶ ተማርኬ እጄን ከምሰጥ በአንተ እጅ እንድትገለኝ ብሎ ስላዘዘው በዚሁ የውርደት አሟሟት ሕይወቱ አልፎ አሳፋሪ ታሪኩ ከትውልድ ትውልድ እየተሸጋገር ለማስተማሪያነት ሊውል በቅቷል።
የሕወሓት መሪዎች እኩይ ድርጊት የአንድ ሳንቲም ገጽታ ያህል ከሚቀራረበው የኔሮ ታሪክ ጋር ማመሳሰላችን ቢያንስ እንጂ የሚበዛ አይሆንም። እብሪትና ትምክህት የተጣባቸው የርኩስ መንፈስ ካዳሚዎቹ የዘመናችን የኔሮ አምሳያ የሕወሓት መሪዎች የዚያ ጨካኝ ሮማዊ መሪ መንትያ ወንድሞችና እህቶች ናቸው ብንል ከእውነታ አያርቀንም።
የሰሜን ዕዝን ሠራዊት ከድተው ያንን ሁሉ ግፍ ሲፈጽሙ የሠራዊቱ አባላት የሕዝብ ልጆች መሆናቸውን እንኳን ልብ ያሉት አይመስልም። ልጆቹ በግፍ የተሰውበትና መከራ የወደቀበት የኢትዮጵያ ሕዝብ በቸልታ ያልፈናል ብለው አስበው ከሆነም የጅልነታቸው ቀዳሚ መገለጫ ነው ማለት ይቻላል። ጥቂት የማይባሉት የሕወሓት መሪዎች የእብሪታቸውና የግፋቸው ውጤት ምን እንዳስከተለባቸው የቅርብ ጊዜ ታሪክ ነው። አንዳንድ የአሸባሪው ድርጅት መሪዎችም ልክ እንደ ኔሮ ግፋቸው ሲያቅበዘብዛቸው መና ሆነውና ትቢያ ለብሰው በምድረ በዳ እንደቀሩ የሚረሳ አይደለም።
ከውርደት ሞት የተረፉትም ቢሆኑ በምን ዓይነት ሁኔታ ከጎሬያቸውና ከተሸሸጉበት ዋሻ እጃቸውን ለምርኮ ከፍ አድርገው በመዘርጋታቸው ለነፍሳቸው ትድግና እየተማጸኑ ምህረት እንደጠየቁ ታሪክም እኛም ምስክሮች ነን። ከጥቂት ወራት በፊት እብሪትና የደም ጥማት ያክለፈለፋቸው የሕወሓት ሠራዊት አባላት “ድሉ የሰመረላቸው መስሏቸው” ንጹሐንን እየፈጁ፣ ሺህዎችን እያፈናቀሉና የሕዝብና የመንግሥት ንብረትን እያወደሙ ወደ መሃል ሀገር ሲገሰግሱ በሳተናው ሠራዊታችን፣ በሕዝባዊ ሠራዊትና በሚሊሽያ ጀግኖቻችን ክፉኛ ተመትተው ተረት እንደሆኑ አይዘነጋም።
እብደት ዓይነት አለው። የሕወሓት መሪዎችን እብደት ለመግለጽ ግን ያዳግታል። በአስተሳሰባቸው ብቻም ሳይሆን በህሊናቸው ጭምር ጨርቃቸውን ጥለው የማንነታቸውን እርቃን በማጋለጥ መሳቂያና መሳለቂያ መሆናቸው ለአባባላችን ጥሩ ማስረጃ ይሆናል። እንኳን ሰብዓዊ ፍጡር ቀርቶ የዱር እንስሳት እንኳን የወገናቸውን ሞት ሲመለከቱ በቋንቋቸው ሀዘናቸውን እየገለጹ ያነባሉ፤ ደመ ነፍሳዊው ልባቸውም እንዴት እንደሚሰበር መመልከት የዕለት ተዕለት ክስተት ነው።
በአብዛኞቹ የትግራይ እናቶችና አባቶች ቤት የሞት መርዶ መደመጥ እንግዳ አይደለም። ልጆቻቸው ከጉያቸው እየተነጠቁ በማያምኑበት ጦርነት ተማግደው ከንቱ ሆነው የቀሩት ከብዛታቸው የተነሳ “ይህን ያህል ቁጥር ነው” ብሎ ለመግለጽ እንኳን እንደሚያስቸግር ተደጋግሞ ተገልጿል። እውነታው ለጊዜው የተድበሰበሰ ቢመስልም የታሪክ ዐይን በንስር ስለሚመሰል ነግ ተነገወዲያ የተሰወረው እየተገለጠ፣ የተከደነው እየተከፈተ የአሸባሪው ሕወሓት ገመና ሲፈተሽ ጉድ የሚያሰኙ ግፎች ይፋ ተገልጠው ለአደባባይ እንደሚበቁ ይታመናል። እውነት ተደብቆና ለዘለዓለም ተዳፍኖ ስለማይቀር።
ሕወሓት ከአሁን ቀደም የፈጸመው እብሪትና የግፍ ድርጊት የተረሳ ይመስል ዛሬም የተራረፉ የምስኪን የትግራይ ልጆችን ከፊት አሰልፎ ከቀናት በፊት በሀገሪቱ ላይ ለሦስተኛ ጊዜ ጦርነት መክፈቱ በምን ቋንቋ እንደሚገለጽ ግራ ያጋባል። ከአለት ጋር መላተም ምን ውጤት እንደሚያስከትል መሪዎቹ ጠፍቷቸው ነው ለማለት አያስደፍርም። የትግራይን ምድር ተተኪ አልባና የአኬልዳማ ምድር ማድረጉ ለማንና ለምን እንደሚበጅም ግራ ያጋባል።
የትግራይን ወጣቶች “ግፋ በለው!” እያሰኙ እነርሱና ቤተሰቦቻቸው ግን በተለያዩ ሀገራት ተንደላቀው የሚኖሩት ህሊና ቢሶቹ የስልጡን ሀገራት “የአደባባይ ተንከባላዮች” እንደሚደሰኩሩት “ጦርነት በከበሮ የሚደምቅ ባህላዊ ጭፈራ” ሳይሆን፤ የደም፣ የአካልና የንብረት ምንዳ የሚያስከፍል አሰቃቂ ትራጄዲ ነው። ወጣቱን ወደ እሳት እየማገዱ እነርሱ ግን ጣቶቻቸውን ኮምፒውተር ላይ ሰክተው ሌት ተቀን የሚያራግቡት የሀሰት ትርክትና ፕሮፓጋንዳ ዞሮ ዞሮ የትግራይ ሕዝብ እውነታውን ሲረዳ አፈሙዙን ወደ እነርሱ አዙሮ የኔሮ ታሪክ እንደሚደገምባቸው አልገባቸውም ወይንም ገብቷቸውም ተስፋ ቆርጠዋል።
የትግራይ ሕዝብ በእነዚህ እኩይ ልጆቹ የመከራ እንጀራ እየበላ እስከ መቼ ኑሮውን ይገፋል? እስከ መቼስ ለከንቱ ጦርነት ልጆቹን የአረር ማብረጃ ማገዶ ማድረግን ምርጫው ያደርጋል? መሪ ተብዬዎቹና የቅርብ ጀሌዎቻቸው በውጭ ሀገራትና በሀገር ውስጥ በተንደላቀቀ ኑሮ እየኖሩ ሕዝበ ትግራይን በመከራ ወላፈን ሲያንገበግቡት እንዴት በቃን ብሎ የተገፋው ወገን አቅሙን ማሳየት ይሳነዋል? በእርዳታ የመጣን ነፍስ አድን እህል በምስኪን የትግራይ ወጣቶች ሕይወት እየለወጡ እነርሱ ሲንደላቀቁ ሕዝቡ በነቂስ ተነስቶ ሃይ ላለማለት ለምን እንደማይደፍር ግራ ያጋባል። የሕዝቡ አጠቃላይ ድቀት በምን ሚዛን እየተመዘነ ወይንም እየተነጻጸረ እንደሚገለጽ ለማሰብ ልብን ፍስስ ስለሚያደርግ ከዚህ በላይ ቃላትን አስማምቶ በማሳካት ስሜትን ለመግለጽ መሞከር እጅጉን ይፈትናል።
እርግጥ ነው ምንም ዓይነት እርምጃ በንፁሐን ላይ ለመውሰድ የመሪዎቹ ጭካኔ መጠንም ሆነ ዓይነት እንደሌለው በቅጡ ይታወቃል። ለበቀልም ሆነ ለክፋት ድርጊቶች የወያኔ መሪዎች እንደማይመለሱም ግልጽ ነው። ነገር ግን እስከ መቼ የትግራይ እናቶችና አባቶች ፍርሃት አቆርፍዷቸው እንዳነቡና ከል እንደለበሱ አልቅሰው ኖረው እያለቀሱ ያልፋሉ?
በጽዮን ማርያም ቤተክርስቲያንና በነጃሺ ደጃፍ በፈጣሪ መንበር ሥር የሚፈሰው የሕዝበ ትግራይ እንባስ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚቆመው እንዴትና በምን ብልሃት ነው? ሕዝቡ ፈጣሪውን በመተማመን ኅብረት ፈጥሮ ለመከራ የዳረጉትን ጥቂት ጨካኝ መሪዎች “በቃችሁ!” ብሎ በነቂስ አደባባይ ወጥቶ ለፍርድ አሳልፎ ሊሰጣቸው ይገባል። በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካ ሀገራት እየኖሩ ጦር የሚያሰብቁ የደም ነጋዴ ተቆርቋሪ ነን ባይ “የእንግዴ ልጆቹንም” ሕዝቡ “እምቢዮ! ሞትና መርዶ ሰለቸን! መረረን!” ብሎ “የሕዝብ ድምጽ የእግዜር ድምጽ” እንዲሉ አፋቸውን ሊያዘጓቸው ይገባል።
በሌሎቹ የሀገራችን ክልሎች ስለ ሰላምና ስለ ልማት እየተወራ በትግራይ ምድር ግን ሕዝቡ ሞትና ፍርሃት ከነገሠበት ግዞት ነፃ እንዲወጣ የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ተገቢውን ድጋፍ ሊያደርግ ውዴታ ብቻም ሳይሆን ግዴታውም ጭምር ነው። የትግራይ ሕዝብ ግራ ተጋብቷል። በአንድ በኩል ልጆቼ በሚላቸው እኩዮች ሸክሙ በዝቶ አጉብጦታል። በሌላ በኩልም ከተቀሩት ወንድምና እህት ሕዝቦች ጋር እንዲቆራረጥ በሀሰት ፕሮፓጋንዳ ግራ ተጋብቷል።
በትግራይ ክልል የሚገኙት አብያተ ክርስቲያናት የሚያሰሙት የደውል ድምጽ ፈጣሪ የሚመሰገንበት “የስብሀት ለአምላክ” መወድስ ሳይሆን “ኤሎሄ! ኤሌሄ ላማ ሰበቅተኒ!” የሚል መቃተት ነው። የየመስጊዶቹ አዛንም “ፈጣሪ አምላክ ሆይ!” ለምን ረሳኸን!? ለምንስ በጨካኞች እጅ አሳልፈህ ሰጠኸን” የሚል ምሬት የሚስተጋባበት ነው። ይህን መሰሉ የወገኖቻችን መቃተት ተሰምቶን ሕዝቡን ከተቆራኙት የጨካኝ እጆች አርነት እንዲወጣ በጸሎትም በበጎነትም ልንደገፈው ይገባል።
መንግሥት ሰላምን ለማስፈን በቁርጠኝነት እየሄደበት ያለው ዕቅድ እንዲሳካም አጠናክረን ድጋፋችንን ልንገልጽለትና ልናግዘው ይገባል። እንደዚህ ጸሐፊ እምነት ከምንጊዜውም ይልቅ የትግራይ ሕዝብ የወገኖቹን ድጋፍ በብርቱ የሚፈልግበት ወቅት አሁን ነው። አረመኔዎቹ የሕወሓት መሪዎች ከምድረ ገጽ ጠፍተው ታላቁ የትግራይ ሕዝብ ነፃ እንዲወጣ ዜጎች በመረባረብ አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ ሊያደርጉ ግድ ይላል።
አሸባሪው ቡድን ዳግም የከፈተብን ወረራ በአጭሩ እንደሚቀለበስ ባያጠራጥርም ለመከላከያ ሠራዊታችንና በጎኑ ተሰልፈው መስዋዕትነት ለሚከፍሉት ጀግኖቻችን እንደተለመደው የሞራልና የማቴሪያል ስንቃቸውን አጠናክረን ልንደግፋቸው ይገባል። የትግራይ ሕዝብ ሆይ! መላው የሀገርህ ልጆች በጉዳትህ ማዘናቸው አልቀረም። እነዚህ የታሪክ አራሙቻዎች በፍጥነት ተነቅለው እንደተለመደው በየእምነት ተቋማቱ ደጀ ሰላም ላይ አብረን ፈጣሪን የምናመሰግንበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም።
በሁሉም ዘርፍ የገጠመህን ስብራት ተረባርበን ልንጠግንልህ ዝግጁ ሆነን እየተጠባበቅን ነው። ጦርነት ለማንም እንደማያዋጣ በአሸባሪነቱ ጨክኖ ልቡ ለደነደነው ሕወሓትና ለልበ ድፍኖቹ መሪዎቹ መልእክታችንን በሚገባቸው ቋንቋ አድርስልን። የትግራይ ሕዝብ የኢትዮጵያ ፈርጥ ነው። የተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብም ለትግራይ ውበት ነው። መከራው ያልፋል። እጅ ለእጅ ተያይዘን ፈጣሪን የምናመሰግንበት ጊዜም ሩቅ አይሆንም። የዘመናችን የኔሮ ደቀመዛሙርት የሕወሓቱ መሪዎችና ጋሻ ጃግሬዎች የሚጠፉት በራሳቸው እጅ ወይንም ከራሳቸው በወጣ ኃይል ነው። ይህ መልእክት ትንቢት ሳይሆን እውነት ነው። ለምን ቢሉ ሁሌም ትዕቢት ውድቀትን ይቀድማልና።
ሰላም ይሁን!
በ(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ነሐሴ 21 /2014