ከዓለም ጤና ድርጅት ጋራ የላንሴት ግሎባል ኮሚሽን ኦን ቪዡዋል ኬር የሚባለው ኮሚቴ በየአመቱ ሪፖርት ያወጣል:: በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት መሰረት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ1 ቢሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች የዕይታ ችግር እንዳለባቸው አረጋግጧል:: በኢትዮጵያም ከእይታ ጋር በተያያዘ ችግር ያለባቸው ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ስለመሆኑና በተለይ ደግሞ አገሪቷ በትራኮማ የአይን ህመም ከዓለም ቀዳሚዋ እንደሆነች ይነገራል::
በህብረተሰቡ በኩል ለአይን የሚደረገው ጥንቃቄ ዝቅተኛ መሆን፣ ጥራት ያለውና ሁሉንም ተደራሽ ያደረገ የአይን ህክምና ተቋማት እንደልብ አለመገኘትና የአይን ህክምና ባለሙያዎች ቁጥር አነስተኛ መሆን ደግሞ ለችግሩ መባባስ አይነተኛ ሚና ይጫወታል:: በአሁኑ ጊዜ ግን በመጠኑም ቢሆን የአይን ህክምና ተቋማትና የዘርፉ ባለሙያዎች ቁጥር እየጨመሩ መምጣታቸው ለብዙሃን ተስፋ ሰጥቷል:: ለዚህም ከሰሞኑ በአለርት ሆስፒታል የተከፈተው የአይን መነፅር ማምረቻ ማእከል ተጠቃሽ ነው::
ዶክተር ሰለሞን ቡሳ በአለርት ሆስፒታል የአይን ህክምና ክፍል ኃላፊ ናቸው:: እርሳቸው እንደሚሉት የአይን ህክምና ክፍል በአለርት ሆስፒታል ሲቋቋም በአንድ ክፍል ውስጥ በአንድ ሀኪም ብቻ ነበር:: የአይን ህክምና ክፍሉ ሲጀመር ደግሞ ለስጋ ደዌ ህመምተኞች ተብሎ ነበር:: በዚህ ጊዜ የስጋ ደዌ ታማሚዎችን አይናቸውን ለማዳን በሚል ሲ ቢ ኤም የተባለው የጀርመን ግበረ ሰናይ ድርጅት አንድ ጀርመናዊ የአይን ስፔሻሊስት ልኮ የአይን ህክምናው በአለርት ሆስፒታል እንዲጀመር ተደረገ::
ዛሬ ላይ የአይን ህክምና ክፍሉ እየተስፋፋ ሄዶ ለመላ አገሪቱ ከፍተኛ የአይን ህክምና አገልግሎት የሚሰጥ ለመሆን በቅቷል:: ይህ የአይን ህክምና ተቋም ስምንት የአይን ስፔሻሊስት ሃኪሞችና አራት የመነፅር ባለሙያዎች አሉት:: በአልትራ ሳውንድ፣ ባዮሜትሪክና በመሳሰሉት መሳሪያዎችም የተደራጀ ነው:: ከፍተኛ ቁጥር ያለው የአይን ቀዶ ህክምናም በአይን ህክምና ተቋሙ ይሰራል:: በርካታ የአይን ታካሚዎችም ወደ ተቋሙ መጥተው ይታከማሉ::
ወደዚህ ሆስፒታል ሪፈር ተፅፎላቸው የሚመጡ የአይን ታካሚዎች ሆስፒታሉ ከከተማው ወጣ ያለ በመሆኑ የታካሚዎችን እንግልት ለመቀነስ በእለቱ ህክምናቸውን አግኝተው ይሄዳሉ:: ቀዶ ህክምናም ቢሆን በሁለት ሳምንት ውስጥ ይጠናቀቃል::
እንደ ሃላፊው ገለፃ በሆስፒታሉ የአይን ታካሚዎች በአብዛኛው ድሆች ናቸው:: የጤና መድህን አገልግሎት በመጀመሩ ጥቂት ሰዎች ናቸው የዚህ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆን የቻሉት:: እነዚህም ቢሆኑ እንደ ግላውኮማ የአይን ግፊት የሚፈጥር በሽታ ያለባቸው ሰዎች መድሃኒቱ የማያቋርጥ በመሆኑና የመድሃኒቱ ዋጋም ከፍተኛ በመሆኑ መድሃኒቱን ለመግዛት ሲቸገሩ ይታያል:: ለህክምናውም ከፍተኛ ወጪ ያወጣሉ:: በተጨማሪ ደግሞ የእይታ ችግር ያለባቸው ተማሪዎች፣ ልጆችና አዋቂዎች መነፅር ሲታዘዝላቸው መነፅሩን ለመግዛት አቅም ያንሳቸዋል::
ከዚህ በመነሳት በሆስፒታሉ መነፀር እዛው እንዲሰራና አንድ ሰው መነፅር ሲታዘዝለት እዛው ተሰርቶ እንዲሰጠው የሚያስችል የመነፅር ማምረቻ ማእከል ተከፍቷል:: የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ ያልሆኑ፤ ፍጹም ደሃ የሆኑትና የስጋ ደዌ ተጠቂ የሆኑት ደግሞ የመነፅር አገልግሎቱን በነፃ እንዲያገኙ ይደረጋል::
የመነፅር ማምረቻ ማእከሉ በሚሰራበት ጊዜ ከዚሁ ጋር በማያያዝ ህብረተሰቡን እያሳወረ ያለውን በስኳር በሽታ ምክንያት የሚከሰተውን የሬቲና መድማት፣ ውሃ መቋጠርና የመሳሰሉትን ነገሮች ለመፍታት እየተመረመሩ በጨረር የሚታከሙበት ክፍል ተዘጋጅቷል:: ለዚህ የሚያስፈልገውም መሳሪያ ተሟልቷል::
ከዚህ በተጨማሪም የአይን ዋናውን የመመልከቻ ግድግዳ ሬቲና ደረጃውን የሚመረምርና የሚያሳይ ክፍልም ከነመሳሪያዎቹ ተዘጋጅቷል:: እንዲህ አይነቱ ምርመራ ብዙ ሆስፒታሎች ላይ የሌለ በመሆኑ ይህን አይነቱን የምርመራ አገልግሎት ለሚፈልጉ ታካሚዎች በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኙ እድል የሰጠ ነው::
ማእከሉን ገንብቶ ለማጠናቀቅ አምስት ወራት የፈጀ ሲሆን ለአጠቃላይ ግንባታውም 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ወጪ ሆኗል:: ይህንንም ሙሉ ወጪ የሸፈነው ሲ ቢ ኤም /ክርስቲያን ብላይንድ ሚሽን/ የተሰኘ የጀርመን ግብረሰናይ ድርጅት ነው::
በሬቲና ጨረር ህክምና ክፍል በቀን እስከ 20 የሚጠጉ ታካሚዎች የሚስተናገዱ ሲሆን በመነፅር አገልግሎት ደግሞ እስከ 30 የሚሆኑ ሰዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል::
በአለርት ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር አድማሱ ትብለጥ በበኩላቸው እንደሚናገሩት የመነፅር ማምረቻ ማእከሉ የአይን ህክምና ማስፋፊያ አንዱ አካል እንጂ አዲስ ፕሮጀክት አይደለም:: ከዚህ ቀደም የሬቲና ጨረር ህክምናና ደረጃውን የጠበቁ የመመርመሪያ ክፍሎች አልነበሩም:: ከዚህ አንፃር ከመነፅር ማምረቻው በተጨማሪ እነዚህ የሪቲና ጨረር ህክምናና ምርመራ ክፍሎች ተከፍተዋል::
በተለይ ታካሚዎች መነፅር ሲታዘዝላቸው መነፅር ፍለጋ ሲንገላቱና ለመነፅሩም ከፍተኛ የሆነ ወጪ ሲያወጡ ይታያል:: ከዚህ አንፃር ማዕከሉ ማህበረሰቡ በተለይ ደግሞ ህፃናት ታክመው መነፅር ለማግኘት እንዳይነከራተቱና ከፍተኛ ወጪም እንዳያወጡ ሊያደርግ የሚችልና መነፅሩን እዚሁ አምርቶና ለክቶ ለታካሚዎች ለመስጠት የሚያስችል ነው::
ከሲ ቢ ኤም ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር የሚሰራውና በአዲስ አበባ ከተማ ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ስር ያሉ መጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ያሉ ህፃናት ተማሪዎችን ለማንኛውም የአይን ችግር በመለየት መነፅር የሚስፈልጋቸውን በነፃ ለመስጠትም ጥረት እየተደረገ ነው:: ከዚህ በኋላ የዕይታ ችግር ያለባቸው ህፃናት ተለይተው መነፀር ተዘጋጅቶላቸው የሚሰጣቸው በማእከሉ መጥተው ይሆናል:: ከዚሁ ድርጅት ጋር በመተባበር በቅርቡ ወደ ማህበረስብ ልየታ ለመግባትም ማእከሉ ያግዛል::
ማዕከሉ ህፃናትን ታሳቢ ያደረገና የመነፅር ስራ አገልግሎቱም ለህፃናቱ በነፃ የሚደርስ ነው:: አዋቂዎችም በተመሳሳይ በተመጣጣኝ ዋጋ በማዕከሉ ተጠቃሚ ይሆናሉ:: ዝቀተኛ ገቢ ያላቸው ደግሞ አገልግሎቱን በነፃ እንዲያገኙ ይደረጋል::
ማዕከሉ መነፅሮችን ለማምረት የሚያስችሉ ክፍሎች፣ ማሳያ ክፍሎችና የሬቲና ጨረር ህክምናና የሬቲና ደረጃ መመርመሪያ ክፍሎችን አቅፏል:: ባጠቃላይም በማእከሉ ስምንት የአይን ስፔሻሊስቶች፣ አራት የመነፅር ባለሙያዎችንና ሌሎች ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞችን ይዟል:: በቀጣይም ለሌሎች ባለሙያዎች መነፅሩ እንዴት እንደሚሰራ ስልጠና የሚሰጣቸው ይሆናል::
የዚህ ማእከል ግንባታ ተጠናቆ ወደ ስራ መግባት መንግስት ለህክምናው ዘርፍ የሰጠው ትኩረት አንዱ ማሳያ ነው:: የመንግስት ሆስፒታሎች ባላቸው አቅም ለህብረተሰቡ ለመድረስ ከሚደረገው ጥረት ውስጥም አንዱ ነው:: ሁሉን አቀፍ የአይን ህክምና አገልግሎት ለመስጠት የሚደረገው ጥረት አንዱ አካልም ነው:: በቀጣይ ሃብታምም ሆነ ደሃ፤ ህፃንም ሆነ አዋቂ በማእከሉ መጥቶ ሲታከም መነፅር ሌላ ቦታ ሄዶ እንዳይገዛ የሚግዝ ጭምር ነው::
የአለርት ሆስፒታል ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር እስማኤል ሸምሰዲን እንደሚናገሩት በኢትዮጵያ የእይታ ችግር ያለባቸው በተለይ ደግሞ በትራኮማ የአይን በሽታ የሚሰቃዩ ዜጎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑ ያስቆጫል:: በሌላ በኩል ደግሞ በዚህ ላይ ለመስራት የሚያስችል እድልም አለው:: በአገሪቱ ከዚህ በፊት የሉም ተብለው የሚታሰቡ እንደ ስኳርና ከዚህ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ካታራክትና መሰል የአይን ህመሞች ከፍተኛ ደረጃ እየያዙ መጥተዋል::
ስለአይን ህክምና ሲታሰብ ሁሉን አቀፍ የአይን ህክምና መስጠት የሚችል ተቋም መገንባት ወሳኝ ነው:: ለዚህም አለርት ሆስፒታል የአይን ህክምናን እንደቀዳሚ የትኩረት አቅጣጫ አድርጎ በመውሰድ እየሰራ ይገኛል:: ለዚህም ሲ ቢ ኤም የተሰኘው የጀርመን ግብረሰናይ ድርጅት ድጋፍ ያደርጋል:: ከነዚህም ድጋፎች ውስጥ አንደኛው የክላስተር ፕሮጀክት ነው:: በዚህ ፕሮጀክት አስራ ሶስት ሆስፒታሎችን አለርት እየመራ የአይን ህክምና መሳሪያዎችና ግብአቶችን የሚያገኙበትንና በመላው ኢትዮጵያ ያሉ ህክምናውን ማግኘት የማይችሉ ሰዎችን ለመደገፍ ጥረት ያደርጋል::
ዋና ስራ አስፈፃሚው እንደሚሉት የአይን ችግር ሲባል አዋቂዎችን ብቻ ሳይሆን ህፃናትንም የሚነካ በመሆኑ ይህንኑ መሰረት በማድረግ ከ ሲ ቢ ኤም ጋር በመላው ኢትዮጵያ አስራ ሶስት ሆስፒታሎች የሚሳተፉበት ፕሮግራም አለ:: ይህም በቀጣይ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል::
በሌላ በኩል የአይን ህክምናውን ህፃናት ጋር ለማድረስ አለርት ሆስፒታል የትምህርት ቤት ፕሮግራም ጀምሯል:: በዚህ የትምህርት ቤት ፕሮግራም በርካታ የእይታ ችግር ያለባቸው ህፃናት ተለይተዋል:: አንድ ሺ የሚጠጉ ህፃናት ደግሞ መነፅር ለመውሰድ ተዘጋጅተዋል::
ይህ ፕሮጀክት በሙከራ ደረጃ ያለ ሲሆን በመላው አገሪቱ እንዲስፋፋና አገራዊ ፕሮጀክት ሆኖ ትምህርት ቤቶች የአይን ህክምናው አካል እንዲሆኑ አለርት ሆስፒታል በቀጣይነት ተጠናክሮ ይሰራል::
ከዚህ ባሻገር ከጤና ሚንስቴር በሚደረግ ድጋፍ የጤና ህክምና ለማስፋፋት መሰረታዊ የአይን ህክምና ስልጠና ፕሮግራም በመቅረፅ ከተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች የጤና ባለሙያዎች ወደሆስፒታሉ መጥተው እንዲሰለጥኑና በችገራቸው ጊዜ የማማከር አገልግሎት በቴሌ ሜዲስን እንዲገኙ ለማድረግ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ:: በዚህም በሁለት ዙር በመሰረታዊ የአይን ጤና ህክምና ባለሙያዎችን ማሰልጠን ተችሏል::
አሁን ከተገነባው የአይን መነፅር ማምረቻ ማእከል በተጨማሪ የህፃናት የአይን ህክምና ማዕከል ራሱን ችሎ በቀጣይ የሚገነባ ይሆናል:: ለዚህም በሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ ውስጥ ቦታ ተለይቷል:: ግንባታውም በቅርቡ ይጀመራል ተብሎ ይታሰባል:: እስከዛው ግን አሁን ላይ የተገነቡና ከዚህ ቀደም የነበሩትን የአይን ህክምና ክፍሎች የማጠናከር ስራ ይሰራል:: በቀጣይም አለርት ሆስፒታል በአፍሪካ በተመረጡ የህክምና ዘርፎች መሪና ምሳሌ ሊሆን የሚችል ተቋም እንዲሆን በጥንካሬ ይሰራል::
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 21 /2014