ኢትዮጵያ ያላት የማዕድን ሀብት መጠንና በዘርፉ ልማት ለማካሄድ ያለው የተመቻቸ ሁኔታም ተደጋግሞ ይገለጻል፡፡ ለጌጣጌጥ የሚውሉ የከበሩ እንዲሁም የግንባታና የኢንዱስትሪ ግብአት ማዕድናት በተለያዩ ክልሎች በስፋት የሚገኙ ከመሆናቸው በተጨማሪ ለሀገሪቱም ኢኮኖሚ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ናቸው፡፡
ከከበሩ ማእድናት መካከል አንዱ የሆነው የወርቅ ማዕድን አምራች ከሆኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች አንዱ የኦሮሚያ ክልል ነው፤ በክልሉ ሁለቱ የጉጂ ዞኖች፣ ቦረና እና ሶስቱ የወለጋ ዞኖች እንዲሁም ኢሉባቦር የወርቅ ማእድን በስፋት ይገኛል፡፡ ሻኪሶ ለገደንቢ አካባቢ ደግሞ በወርቅ ሀብቱና ምርቱ በስፋት ይታወቃል፡፡ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልልም የወርቅ ማዕድን በስፋት ከሚገኝባቸው ክልሎች አንዱ ነው፡፡ እነዚህ አካባቢዎች በዋናነት ይጠቀሱ እንጂ፣ መጠኑ የተለያየ የወርቅ ማዕድን በመላ ሀገሪቱ ይገኛል፡፡
በአነዚህ ክልሎች የወርቅ ማእድን የማውጣት ስራ እየተካሄደ ሲሆን፣ ከእዚህም አምራቾቹ፣ ክልሎቹ፣ ማእድናቱ የሚገኙባቸው አካባቢዎች ጭምር ተጠቃሚ እየሆኑ ከመሆናቸው በተጨማሪ ማእድኑ ለውጭ ምንዛሬ ግኝት አስተዋጽኦ እያደረገ ነው፡፡
እንደሚታወቀው፤ ኢትዮጵያ በዓለም ገበያ ላይ አቅርባ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ከምታገኝባቸው ዋና ዋና የውጭ ምርቶች አንዱ ወርቅ ነው፡፡ በመሆኑም የወርቅ ልማቱ ወርቅ የማንጠር ክህሎትን ባላቸው በባህላዊ ወርቅ አምራቾች እና በኩባንያዎች አማካኝነት እየተመረተ ለብሄራዊ ባንክ እንዲገባ ይደረጋል፡፡
በኩባንያ ደረጃ ወርቅ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚያመርቱ ወይም ከሚያለሙ መካከልም ሜድሮክ ኢትዮጵያ የሚጠቀስ ቢሆንም፣ በልማቱ ከፍተኛውን ድርሻ የያዙት ባህላዊ አምራቾች እንደሆኑ ይገለጻል፡፡ ምንም እንኳን ከወርቅ ልማት የሚገኘው ገቢ በዓለም ገበያ ዋጋ ተለዋዋጭነት የሚወሰን ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ ግን ከዘርፉ የምታገኘው ገቢ ካላት እምቅ አቅም ጋር የሚመጣጠን እንዳልሆነ ተደጋግሞ ይነሳል፡፡
ለዚህም እንደ ምክንያት ከሚቀርቡት መካከል የወርቅ ልማቱ ጊዜንና ጉልበትን ቆጣቢ አለመሆኑ፣ በጥራትም አለመመረቱ በአጠቃላይ ልማቱ አለመዘመኑ የሚሉት ይገኙበታል፡፡ ባህላዊ ወርቅ አንጥረኞቹም ቢሆኑ የልፋታቸውን ያህል ዋጋ እንደማያገኙና በዚህም ኑሮአቸው ላይ ለውጥ ማምጣት እንዳልቻሉ ከባለጉዳዩቹ መገንዘብ ይቻላል፡፡
በአብነትም የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከሶስት አመት በፊት ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሸርቆሌ ወረዳ ላይ ተገኝቶ ካሰራጨው ዘገባ ያገኘነውን መረጃ መጥቀስ ይቻላል፡፡ በወቅቱ የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ተብሎ ይጠራ የነበረው ተቋም በክልሉ የወርቅ ልማት ሥራውን ለማዘመን የሚያግዝ በሸርቆሌ ወረዳ ውስጥ የማሽን ተከላ እንዲከናወንና በዚህም ከ50ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር በእቅድ የያዘውን ሥራ በተመለከተ ለመዘገብ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጣቢያ በስፍራው ተገኝቶ ነበር፡፡
በወቅቱም ጣቢያው ካነጋገራቸው ባህላዊ ወርቅ አምራቾች መካከልም አንዳንዶቹ በሰጡት አስተያየት እንዳሉት፤ የቁፋሮ ሥራውን የሚያከናውኑት በግምት ነው፤ በግምት ቁፋሮ ተካሂዶ አፈሩ ከወጣ በኃላ በውሃ አጥቦ የመለየቱ ሥራ ተከናውኖም ማዕድኑ ሊገኝም ላይገኝ ይችላል፡፡ አልሚው በለስ ከቀናው ተደስቶ ጥሬ ወርቁን ለገበያ አውሎ ገቢ ያገኛል፡፡ ካልቀናውም አዝኖ ሌላ ዕድል ይሞክራል፡፡
አልሚው ማዕድኑን እስኪሚያገኝ ድረስ ጥልቅ ጉድጓድ ውስጥ መዝለቅ ይጠበቅበታል፡፡ በዚህ ወቅት ለመተንፈስ አየር ሊያጥረው ይችላል፡፡ በዚህም ለጤና ችግር እና ለሞት አደጋ የመጋለጥ እድሉ ሰፊ ነው፡፡
ረዘም ያለ ጊዜ ወስዶ ቆፍሮ ያወጣውን አፈር በውሃ በማጠብና በባህላዊ ዕቃ እያጠለለ ወርቁን ከአፈሩ ለመለየት በሚያደርገው ጥረትም እንዲሁ ለጤና ጉዳት ተጋልጦ ጊዜና ጉልበትን በሚወስድ አሰራር ውስጥ ሊያልፍ ይችላል፡፡ በዚህ ድካም ውስጥ አልፎ ያገኘውን ወርቅ ሽጦ የሚያገኘው ገቢም ወርቁን ከመሬት ውስጥ ቆፍሮ ያወጣበትን ጊዜና ጉልበቱንም ያፈሰሰበት እንዲሁም ጤናውን ለአደጋ ያጋለጠበትን ሁኔታ የሚያካክስ አለመሆኑን ብቻ አይደለም አስተያየት ሰጭዎቹ በቁጭት የተናገሩት፡፡ አንዴ ያገኘውን ወርቅ ሽጦ ገቢ ካገኘ በኃላ ለተከታታይ ጊዜ ቁፋሮ ላይ ተሰማርቶ ወርቅ የማያገኝበት አጋጣሚ ሊኖር የሚችል መሆኑን ነው፡፡ ቀደም ሲል ያገኘውን ገቢ ለዕለት መተዳደሪያው ስለሚያውለው ገንዘቡ ያልቃል፡፡ ገቢውን ቆጥቦ ኑሮን ለማሻሻል የሚያስችለው ገቢም አይደለም እያገኘ ያለው፡፡ ይህ ደግሞ አምራቾቹ ለውጥ ሳያገኙ በተመሳሳይ ኑሮ ውስጥ እንዲገፉ በማድረጉ ኑሮአቸውን አሰልቺ እንዳደረገው ያስገነዝባል፡፡
ማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስቴር/ የቀድሞውን ማለት ነው/ ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን የሚቆጥብ የወርቅ ማጠቢያ ምሽን በአካባቢያቸው ላይ ተክሎላቸው ከድካማቸው ለማረፍ ተስፋ ቢያደርጉም፣ በተግባር አለማየታቸው አሳዝኗቸዋል፡፡
በቤንሻንጉል ክልል ሸርቆሌ ወረዳ ውስጥ ለመትከል የታቀደው የወርቅ ማጠቢያ ማሽን ፋብሪካ ግንባታ መጓተቱን ነበር በውቀቱ የኢትዮጵያ ቴሌቪዝን ጣቢያ የዘገበው፡፡በወቅቱም በክልሉ 24 የወርቅ ልማት ቦታዎች ተለይተው ለክልሉ ወጣቶች መሰጠታቸውንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
ይህን የቆየ መረጃ መነሻ ማድረግ የወደድነው በባህላዊው የወርቅ ልማት ሥራ ላይ የሚስተዋለው ችግር የቆየ መሆኑንና አሰራሩ አለመዘመኑ ጉዳቱ በተለያየ መንገድ የሚጠቀስ መሆኑን ግንዛቤ እንዲኖር ለማስቻል ነው፡፡
ሀገሪቱ ያላት የወርቅ ሀብት መጠንና ሀብቱ የሚገኝባቸው አካባቢዎችና ያላቸው የወርቅ ማእድን መጠንም በሚገባ ተለይቶ እንደማይታወቅ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ይህን ውድ ሀብት በሚገባ ለማወቅና በተደራጀ የአሰራር ሥርአት ልማቱ እንዲከናወን ለማድረግ ጥናታዊ ሥራዎች እንደሚያስፈልጉ በተለያዩ ወገኖች ምክረሀሳቦች ይሰጣሉ፡፡
የማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ታከለ ኡማ በአንድ ወቅት ከፋና ብሮድካስት ጋር በነበራቸው ቆይታ ኢትዮጵያ የወርቅ ሀብት ቢኖራትም፣ እንደ ደቡብ አፍሪካ፣ታንዛኒያ፣ጋና የመሳሰሉ ሀገራት ስሟ በማእድኑ አይጠቀስም፡፡ እነዚህ ሀገራት ይበልጧታል፡፡ በዚህ ረገድ የዘርፉን ችግሮች ለይቶ በመቅረፍ መሥራት እንደሚጠበቅ በመንግሥት ታምኖበት የተለያዩ እርምጃዎች በመወሰድ ላይ መሆናቸውን አሰታውቀው ነበር፡፡ ሚኒስትሩ በሶስት አመታት ጊዜ ውስጥም 300 ሺ /ሶስት መቶ ሺ/ ኪሎግራም ወርቅ ለማምረት መታቀዱን ነው የተናገሩት፡፡
ሀብቱ የሚገኝባቸው ክልሎችም የየበኩላቸውን ጥረት ለማድረግ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ፡፡ በዚህ በኩልም በባህላዊ መንገድ የሚመረተውን የወርቅ ማዕድን ልማት ለማዘመን የኦሮሚያ ክልል ማዕድን ልማት ባለስልጣን እያከናወነ ያለው እንቅስቃሴ ይጠቀሳል፡፡
የባለሥልጣኑ ዋና ሥራ አስፈጸሚ አቶ ተስፋዬ መገርሣ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት፤ በባህላዊ መንገድ ወርቅ የሚያመርቱ ጉልበታቸውን ከማባከናቸው በተጨማሪ በቁፋሮ ያወጡትን ማዕድን በአግባቡ እያጣሩ አይደለም፡፡ ከአንድ ኪሎ አፈር ውስጥ መቶ በመቶ ማዕድኑን ማውጣት እየተጠበቀባቸው እነሱ ግን አነስተኛ መጠን ያለው ወርቅ ነው የሚያወጡት፡፡ ይሄ ብክነት ነው፡፡
ወርቁን ከአፈር ውስጥ የሚያጣራ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ችግሩን ማስቀረት የሚቻልበትን መንገድ ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ደግሞ መንግስት ስራ ብቻ መሆን የለበትም፤ የግሉም ዘርፍ ቴክኖሎጂውን ለወርቅ አምራች ማህበራት በማቅረብ ማገዝ ይኖርበታል፡፡ አቅርቦቱን ፕሮጀክት ቀርጾ መተግበርም ይቻላል፡፡
እዚህ ላይ ዓለምአቀፍ ድርጅቶችም እንዲተባበሩ ማድረግም ሌላው አማራጭ ነው፡፡በአሁኑ ጊዜም አንድ የካናዳ ድርጅት ወደ ስምንት የወርቅ ማጠቢያ ማሽኖች ለክልሉ በማቅረብ እገዛ አድርጓል ሲሉ ዋና ስራ አስፈጻሚው ያብራራሉ ፡፡
እንደ ኃላፊው ገለጻ፤ እንዲህ ያሉ ማበረታቻዎች አምራቹን ያነቃቃሉ፡፡ አምራቾቹ በቴክኖሎጂ አጠቃቀሙ ላይ ስልጠና ወስደው መጠቀም ከጀመሩና ጥቅሙንም ከተገነዘቡ በኃላ በሂደት በራሳቸው የማጠቢያ ማሽኑን ገዝተው ለመጠቀም እንዲነሳሱ እድል ይፈጥራል፡፡ በዚህ መልኩ አጠናክሮ መቀጠል ከተቻለ ችግሩን በዘላቂነት መፍታት ይቻላል፡፡
እንዲህ ያሉ የመንግሥት እንቅስቃሴዎችን መሠረት በማድረግና ዘርፉ ላይ የሚስተዋለውን ክፍተት በማየት ዘርፉን ለማገዝ፣ ራሳቸውንም በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ አለፍ ብለውም ቴክኖሎጂውን በሀገር ውስጥ በመተካት በቴክኖሎጂው ራስን ለመቻል፣ በሌላ በኩል ደግሞ ለግዥ የሚወጣውን ወጪ ለማስቀረት የወርቅ ማጠቢያ ማሽን በሀገር ውስጥ ለመተካት በእንቅስቃሴ ላይ የሚገኙ ወጣቶችንም በሀገር ውስጥ ማግኘት ተችሏል፡፡
የወርቅ ማጠቢያ ማሽን በመፍጠርና ወደምርትም በማስገባት ተጠቃሚው ዘንድ ተደራሽ ለማድረግ በእንቅስቃሴ ላይ የሚገኙት ወጣቶች አባስ ሲራጅ እና ቢቂላ ዮሐንስ ይባላሉ፡፡ ወጣቶቹ የማጠቢያ ማሽኑን በቡራዩ ከተማ ውስጥ ነው እየሰሩ የሚገኙት፡፡ጓደኛሞቹ ለተወሰነ ጊዜ ለብቻቸው ከሰሩ በኃላ ሁለት ልጆች ቀጥረው አራት ሆነው በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡
ወጣት አባስ ስለወርቅ ማጠቢያ መሣሪያ(ማሽን)ሥራውና ለፈጠራ ሥራው የተነሳሱበትን አጋጣሚ አስመልክቶ እንዳጫወተኝ፤ ወጣቶቹ ሌላው ዓለም ጉልበቱንና ጊዜውን በመቆጠብ የወርቅ ልማትን እንዴት እንደሚያከናውን በውጭ የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ ተመልክተዋል፤ ይህ ‹‹ናሽናል ጆግራፊ››በሚል ዝግጅት ላይ በካናዳ አንድ የወርቅ ማጠቢያ ማሽን ሥራ ትኩረታቸውን ይስበቸዋል፤ ማሽኑ በፋብሪካ ውስጥ ተመርቶ እንዴት ጥቅም ላይ እንደሚውል ይከታተላሉ፡፡
በሀገራቸው ደግሞ ባህላዊ የወርቅ አምራች ወርቅ ለማልማት የሚደርስባቸውን ስቃይ በመገናኛ ብዙሃን ሲቀርብ ብቻ ሳይሆን ልማቱ በሚከናወንበት ቦታም የማየት ዕድሉን አግኝተው ለመገንዘብ ችለዋል፡፡
አምራቾቹ የወርቅ ማጠቢያውን በግዥ ከውጭ አስመጥተው ለመጠቀም አቅሙ እንደማይፈቅድላቸውም ከገበያው ተገንዝበዋል፡፡ ዋጋው የመንግሥትንም የመግዛት አቅም የሚፈታተን ነው፡፡ አነስተኛ የሚባለው ዋጋ ሁለት መቶ ሺ ዶላር እንደሆነም መረጃ ሰብስበዋል።
ወጣቶቹ ይህን ሁሉ ግምት ውስጥ ያስገባ ውሳኔ ላይ በመድረስ ነው ወደ ሥራ ለመግባት የተነሳሱት። በአጋጣሚ ደግሞ ሁለቱም የቴክኒክና ሙያ ሙሩቅ በመሆናቸው ወደሥራው ለመግባት አልተቸገሩም፡፡
ጓደኛው ቢቂላ በኢትዮጵያ ብረታብረት ኢኒጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ውስጥ የመሥራት ዕድል አግኝቷል። ሁለቱም ሙያቸውን መሠረት አድርገው በካናዳ በባለሙያዎች የተሰራውን አስመስለው መሥራቱን ተያያዙት፡፡ ማሽኑን በመስራት ውስጥ አራት አመታትን አስቆጥረዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥም ሰባት የወርቅ ማጠቢያ ማሽኖች ሰርተው ለተጠቃሚው ተደራሽ አድርገዋል፡፡
ሞዴል ያደረጉትን የካናዳን የወርቅ ማጠቢያ ማሽን ሥራ አሁንም ክትትል በማድረግ በየጊዜው ካለው ለውጥ ጋር በመራመድ ሥራቸውን እያሻሻሉ እያቀረቡ ናቸው፡፡ በአሁኑ ጊዜም ማሽኑ በመቆጣጠሪያ (በንዝረት) ኃይል እንዲንቀሳቀስ በማድረግ ለውጥ አምጥተውበታል፡፡
አሁን ደግሞ በካናዳ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለውን የ2022 ሞዴል የወርቅ ማጠቢያ ማሽን በሀገር ውስጥ ለማምረት እየሰሩ ናቸው፡፡ ማሽኑን ሲሰሩ ዲናሞ የሚባለው ግብአት ካልሆነ በስተቀር ሌሎች ግብአቶች ከሀገር ውስጥ ምርት ነው የተጠቀሙት፡፡ አብዛኛው ግብአትም ብረት ነክ ነው፡፡
አንድ የወርቅ ማጠቢያ ማሽን ሰርቶ ለማውጣት እስከ አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊየን ብር ወጭ ይጠይቃል፡፡ ስራው ከ20 እስከ 30 ቀናትም ይወስዳል፡፡ የማሽኑ የአገልግሎት ዘመንም ከ20 አመት በላይ እንዲሆን ተደርጎ ነው የተሰራው፡፡
ማሽኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ እስከ አንድ መቶ ቶን የሚደርስ አፈር በማጠብ ወርቁን የመለየት ሥራ የማከናወን አቅም አለው፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚያከናውነውን ሥራ በጉልበት ሰራተኛ ማከናወን ቢፈለግ አስርና ከዚያ በላይ ሰዎችን ይፈልጋል፡፡ ማሽኑ ከቦታ ቦታ በማንቀሳቀስ እንዲሰራ ተደርጎ የተሰራም ነው፡፡
የወርቅ ማጠቢያ ማሽን ፈጣሪዎቹ ወጣቶች በአሶሳና ሻኪሶ በወርቅ ልማት ላይ ለተሰማሩ አምራቾች በሽያጭ ማቅረባቸውንም የሚናገረው ወጣት አባስ፣ ማሽኑን ለሚገዛቸው በቦታው ድረስ በመገኘት ስለአጠቃቀሙ ስልጠና እንደሚሰጡም ገልጾልኛል፡፡
ወጣት አባስ እንደተናገረው፤ የማሽኑን ሥራ በራሳቸው ወጭ ሰርተው ገበያ ላይ በማዋል አለማምደው ተቀባይነት በማግኘታቸው በአሁኑ ጊዜ በትእዛዝ የሚያሰራ ደንበኛ ማግኘት ችለዋል፡፡ በማህበር የተደራጁ ወርቅ አምራቾችም ጥያቄ ማቅረብ ጀምረዋል፡፡ከጋምቤላ ክልልም ጥያቄ ቀርቦላቸዋል፡፡
የማሽኑ የፈጠራ ሥራ ባለቤትነት ማረጋገጫ እውቅና (ፓተንት ራይት) ለማግኘት በሂደት ላይ ናቸው፡፡ ሥራቸውን የሚያከናውኑበት የቡራዩ ከተማ አስተዳደር እያበረታታቸውና የመስሪያ ቦታም ሊሰጣቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የማዕድን ሚኒስትሩ ታከለ ኡማም በሥራ ቦታቸው ተገኝተው እንዳበረታቷቸውም ነው ወጣት አባስ የነገረኝ፡፡ ብረቶችን ለማጠፍና ለመቁረጥ የሚያገለግል ቶርኖ የሚባል ለሥራቸው የሚያግዛቸው ማሽን ሊዝ ፋይናንሲንግ በሚባል የብድር አገልግሎት ከልማት ባንክ የሚያገኙበትን ሁኔታ ለማመቻቸትም እየሰሩ መሆናቸውን ይገልጻል፡፡ ብድሩ ከተመቻቸላቸው እስከ ዛሬ ለቶርኖማሽን ኪራይ የሚያወጡትን ወጭ እንደሚያስቀርላቸውና ጊዜም እንደሚቆጥብላቸው ተናግሯል፡፡
እኛም በወጣቶቹ የተጀመረው ባህላዊ የወርቅ አመራረት ዘዴን የማዘመን ጥረት ሊበረታታ ይገባል እንላለን፡፡
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 20 /2014