የአሁኑ ዘመን የሃያላኑ አገራት የጉሮሮ ለጉሮሮ ትንቅንቅ በተለይ ሶስት አገራትን ይመለከታል። ሩሲያ እና ቻይና በአንድ በኩል፤ አሜሪካ እና ምእራቡ (አንዳንዶቹ ወጣ ገባም እያሉ ቢሆንም) በሌላኛውና ተቃራኒው ጫፍ። ለምን? ጥያቄው ይሄው ነውና በቀጥታ ወደ እሱው እንሂድ።
ሶቪየት ህብረት ”ፈራረሰች” (ቃሉ በዚህ አይነት መልኩ እንዲገለፅ የምእራቡ አለም ሚዲያ የመሪነቱን ሚና ተጫውቷል) ከመባሉ በፊት ”የዓለም ፖሊሶች ነን” የሚሉት ሁለቱ ነበሩ፤ ሪሲያና አሜሪካ። ሌላው የእነሱ ጀሌ ነበር፤ በወቅቱ ቻይና በከፋ ድህነት ውስጥ ነበረች።
ሶቪየት ህብረት ”ፈራረሰች” ከተባለ በኋላ ያ ሁለትነት ቀረና ብቸኛዋ የዓለም ፖሊስ አሜሪካ ሆነች። በቃ። ሌላው፣ በተለይም ምእራቡ ለሷ መገበር ስራው ሆነ። የዓለም አቀፍ ተቋማቱ መርህም ያልተፃፈውን ሕግ ከማክበርና የአሜሪካን እስትንፋስ ከማስተጋባት፣ ከማክበር፣ ማፅደቅና አጨብጭቦ ወደ ተግባር ከመሸኘት ያለፈ ስራ አልነበራቸውም።
የሷን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከማስፈፀም ያለፈ ምንም ሊያደርጉ አልቻሉም። ለማመን በሚያስቸግር ሁኔታ አለም በአሜሪካ መዳፍ ስር ተጠቃልላ ገባች። የሚጨመቀው እየተጨመቀ፤ የሚጨበጠውም እየተጨበጠ በአሜሪካ እዚህ ተደረሰ። አሁንስ?
አሁን ያለው ሁኔታ የቻይናና ሩሲያ ፍቅር ከፍ ያለ ደረጃ የደረሰበት፤ ግንኙነታቸው ጣራ የነካት፤ በንግድ፣ በዲፕሎማሲ፣ በሰላምና ደህንነት … አንዱን ካንዱ መለየት በሚያስቸግር ሁኔታ አንድ የሆኑበትና በአንድ አካል የበላይነት ተጠፍሮ የቆየውን የዓለም የበላይነት በማስለቀቅ (ባለሙያዎቹ ”Beijing and Moscow as one of pragmatism and based on “balancing” against “U.S.” ይሉታል) የአለማችንን የኃይል ሚዛን ለማስጠበቅ መንቀሳቀስ ጀምረዋል።
እርግጥ ነው ጉዳዩን በጥቅል እናንሳው እንጂ ትንቅንቁ፤ ጉሮሮ ለጉሮሮ የመያያዙ ጉዳይ እንዲህ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ቀዝቃዛው ጦርነት ነው እየተደገመ ያለው የሚሉ ወገኖች መኖራቸው እንዳለ ሆኖ፤ በእነዚህ ኃያላን መካከል ያለው እሰጣገባ መልኩ አንድ አይደለም፤ መገለጫውም የትየለሌ ነው።
የቻይና ሳይታሰብ ከተፍ ማለት፤ በኢኮኖሚ፣ ወታደራዊ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ …. ተገዳዳሪ ሆኖ መገኘት፤ ከሁሉም በላይ በአሜሪካ የዝንጋኤ ወቅት ሰርስራ ወደ አፍሪካ መግባቷና በአህጉሪቱ ከሚገኙ አገራት ከ46 በላይ በሆኑት ቤተሰባዊነቷን ማጠናከሯ … ዛሬ ለአሜሪካ የእግር እሳት በመሆን እያንገበገባት ነው ።
የተከፈለውን ዋጋ ሁሉ ከፍላ አፍሪካን ከቻይና መንጠቅ፤ ወይንም አፍሪካን መልሳ ወደ ራሷ ጉያ ለመክተትና መሪዎቿን ተነስ፣ ቁጭ በል …. ለማለት እየቧጠጠች ያለችው ገደል በቀላሉ የሚታይ፣ የሚዳሰስ፣ የሚሰላ… አይደለም።
የሚያሳዝነው ግን ሁለቱ ዝሆኖች ሲጣሉ ተጎጂው ሳሩ መሆኑ ነው። እነሱማ ይፈራራሉና እስካሁን ከቃላት ጦርነት አልፈው ጦር ሲማዘዙ አልታዩም። በእጅ አዙር ግን …።
የአገራቱ ወታደራዊ ኃይል
በአሁኑ ሰአት ቻይና በአጠቃላይ 3.4 ሚሊዮን የጦር ኃይል (ከአጠቃላይ ህዝቡ 0.2 በመቶው) ሲኖራት፤ ከዚህ ውስጥ 2.1ዱ (በዚህ ቁጥር ከአለም አንደኛ ናት) በቀጥታ ውጊያ ላይ መሳተፍ የሚችል (active)፤ 70 ሰርጓጅ መርከቦች (ሩሲያ 60 ነው ያላት)… አመታዊው የመከላከያ በጀቷም $178 ቢሊዮን ነው። የሩሲያስ?
የCIA ሰነድ (CIA Factbook፣ ጁን 29, 2022) እንደሚያመለክተው ሩሲያ 850,000 ተዋጊ ኃይል (active)፤ 300,000 የምድር ኃይል፤ 40,000 አየር ወለድ፤ 150,000 ባህር ኃይል፤ 160,000 aerospace forces (አየር ኃይል)፤ 70,000 ”ሮኬት ተኳሾች” (strategic rocket forces) አሏት። ገፃችን ውስን በመሆኑ ወደ መሳሪያዎቿ አልገባንም።
ይህ የድሮው ሳይሆን የአሁኑ ዘመን የሁለቱ ወዳጅ አገራት ጡንቻ ነው። ይህንን ጡንቻ በማስተባበር ነው በተሳሳተ መንገድ በዓለም ህዝብ ዘንድ ተቀባይነት አግኝቶና ፀንቶ የኖረውን የአሜሪካንን የበላይነት (ወታደራዊ የበላይነት፣ ጣልቃ ገብነት፣ ጉልበተኛነት) ርእዮት (“of militarism, interventionism and the forcible imposition of U.S. values on other countries.”) ከስሩ መንግሎ ለመጣልና በምትኩ የሁሉንም እኩልነት የምታስተናግድ ዓለም ለመፍጠር እየተንቀሳቀሱ ያሉት።
ተንታኞች እንደሚሉት ከሆነ አልሞት ባይ ተጋዳይነት ካልሆነ በስተቀር የአሜሪካ የበላይነት እንደ ሆነ ከተወሰደ ቆይቷል። በጦርነቱም ከሆነ ሩሲያ በኒውክሌር ጦር መሳሪያዋ የአሜሪካንን ሚሳኤሎች ጭጭ ምጭጭ ማድረግ የሚያቅታት ምንም ነገር የለም። በመሆኑም መፍትሄም አሜሪካ እጅ ወደ መስጠትና አብሮ መስራቱ መምጣት፤ ፌዙን በማቆም፣ ”የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዬ ነው” የምትለው የሷ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የራሷ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ብቻ መሆኑን መገንዘብና ወደ 21ኛው ክፍለ ዘመን አስተሳሰብ መመለስ ብቻ ነው።
ከሲኖ-አሜሪካ ጋር በተያያዘ ናሳ የእስከዛሬው አካሄዴን ቀይሬያለሁ፤ የመጪው ዘመን የዓለማችን ስጋት የሆነችውን፤ የቻይናን እንቅስቃሴ ለመግታት ከተለመደው ክትትሌና አካሄዴ ወጥቻለሁ። ትኩረቴንም ቴክኖሎጂ(ዋ) ላይ አድርጌያለሁ፤ ለዚህም ከፍተኛ በጀት መመደብ ብቻ ሳይሆን በቂ የሰው ኃይልም አዘጋጅቻለሁ …. ሲል ሰሞኑን የለቀቀውን መግለጫም እዚሁ ላይ ከስሩ አስምረንበት ልናልፍ የሚገባን ጉዳይ ነው። (ይህ በቻይና በኩል እንዴት ይታያል? የሚለውን ለሌላ ጊዜ እናቆየው።)
የቻይና ወደ አፍሪካ ዘልቆ መግባትን በተመለከተም፤ ባልተቋረጠ መልኩ ቻይና አፍሪካን በእዳ ትብትብ አድርጋ በመያዝ ዘመናዊ ቅኝ አገዛዝ እየገዛች ነው የሚለው የአሜሪካ ክስ በሁሉም በሚያስብል ደረጃ ተቀባይነት ያገኘ አይመስልም። እንደውም ያለው እውነታ የሚያሳየው ”ከቻይና ጋር ወደፊት!!!” መሆኑን ነው።
ይህ ደግሞ አሜሪካንን ክፉኛ አስቆጥቷታል ብቻ ሳይሆን ራሷን እንድትስት ሁሉ ያደረጋት እስኪመስል ድረስ አበሳጭቷታል። በተለይ አፍሪካ ህብረትን ጨምሮ የአፍሪካ አገራት ”ለፀረ-ሩሲያ አቋሜ ኑ ከጎኔ ቁሙ” ለሚለው ጥሪዋ ምላሽ አለመስጠታቸው በብሊንከን አማካኝነት ቤት ለቤት እየሄደች እንደ ሁኔታው (በማስፈራራት ወይም በማባበል …) በመነጋገር ላይ መገኘቷ እንዳለ ሆኖ ብሊንከን ራሳቸው ለቻይና እዚህ መድረስ ስህተቱ የኛ ነው እስኪሉ ድረስ ሁሉ እንዲሄዱ አድርጓቸዋልና ጉዳዩ የዋዛ አይደለም። በመሆኑም በምትችለው ሁሉ የምትችለውን እያደረገች ትገኛለች። (ዝርዝሩ ብዙ ነው።) ይሳካል፤ አይሳካም … ወደ ፊት የሚታይ ነው የሚሆነው።
ቻይናና ሩሲያን በተመለከተ የሚወጡ ትንተናዎች እንደሚያሳዩት ሁለቱ የሚመሳሰሉባቸው ጉዳዮች በርካታ ሲሆኑ ከሁሉም ቀዳሚው ሁለቱም ራሳቸውን ችለው የኖሩና ረጅም ዘመን የመንግስትነት ልምድ ያላቸው መሆናቸው (autonomous countries with strong state traditions) ነው። አንድነታቸው ከዚህ ይጀምራል። ሌላውን ከወቅቱ ሁኔታ እየተነሳ አንባቢ ሊሞላው ይችላል።
በአጠቃላይ ትንቅንቁ ቀጥሏል። (የ’ኛን፤ በእኛ ላይ እየተደረገ ያለውን ዝም ነው) ጦርነቱ ዩክሬን ላይ ተጀምሯል። ታይዋንን በተመለከተ እየተንደረደሩ መሆኑን እንጂ ስለ መጀመራቸው/አለመጀመራቸው የታወቀ ነገር የለም። በአፍሪካ ምድር የቻይናና ሩሲያ ፖሊሲ ነው የሚቀይረው? አፍሪካ ወደ ኋላ ትመለሳለች? ወይስ፣ አሜሪካ ነች ፖሊሲዋን ወደ ዘመኑ አፎት እንዲገባ ለማድረግ የምትጥረው የሚለው፤ የመጀመሪያውና ሁለተኛው የሚሆን ባይመስልም አጠቃላይ ውጤቱን ግን ወደፊት አብረን የምናየው ይሆናል።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 18 /2014