በዛሬው አዲስ ዘመን ድሮ ዓምዳችን በ1960ዎቹ በተለይም በክረምቱ ወራት ታትመው ለንባብ የበቁ እትሞች ለመቃኘት ሞክረናል፡፡ በክረምቱ ችግኝ ተከላን በሚ መለከት የተሠራን አንድ ዘገባ እንዲሁም በክረምቱ የመብረቅ አደጋ በአንድ ቤት ላይ ባደረሰው አደጋ በሕይወትና በንብረት ላይ ያስከተለውን ጉዳት የሚነግረን ዘገባም ተካቷል። በወቅቱ ያልተለመዱ ወይም ትንግርት የሆኑ ክስተቶችን ያካተተ ዘገባም እነሆ ብለናል።
መብረቅ የ፬ ሰዎች ሕይወት አጠፋ
አገረ ሕይወት (ኢ/ዜ/አ/) በጅባትና ሜጫ አውራጃ ግዛት በኖኖ ወረዳ በማሩ ኢሉ ም/ወረዳ ግዛት ጨንዶ ከሚለው ቀበሌ ባለፈው ወር መጨረሻ ግንቦት ፳፱ ከቀኑ ፲ ሰዓት ላይ በጣለው ኃይለኛ ዝናብ የወደቀው መብረቅ የ፬ ሰዎች ሕይወት አጠፋ።
ይኸው የአቶ ደጀኔ ገብሬ ቤት የወደቀው መብረቅ በቤቱ ውስጥ የነበሩትን ተፈራ ደጀኔ፤ ዳመኑ ደጀኔ፤ ቡሎ ካብትህ ይመርና ቦጋለ ገብረየስ የተባሉትን ሰዎች ሲገድል፤ የሟቾቹንም አስከሬን አስከትሎ በዚሁ አደጋ ከቤቱ ጋር አብሮ መቃጠሉን የወረዳው ግዛት ዋና ጸሐፊ አቶ ተስፋዬ ቡሉ ገልጠዋል፡፡
(ሰኔ 10 ቀን 1961 ዓ.ም ከወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ)
እመት አበቡ በ፩ ጊዜ ፭ ልጆች ወለዱ፤
ደብረ ብርሃን፤ (ኢ.ዜ.አ) በተጉለትና ቡልጋ አውራጃ በተባለው ቀበሌ ኗሪ የሆኑት እመት አበቡ አያኔ ግንቦት ፳፯ ቀን ፷፩ ዓ/ም/ ፫ ወንዶች ልጆችና ፪ ሴቶች ልጆች ተገላገሉ፡፡ ከነዚሁ ከተወለዱት ፭ ህፃናት መካከል ፪ቱ ሲሞቱ፤ ፫ቱ ግን በደኅና ሁኔታ ላይ የሚገኙ መሆናቸውን የወረዳው ግዛት ዋና ፀሐፊ አቶ አበባ ለማ ገልጠዋል፡፡
እነዚሁ የተወለዱት ህፃናት የሚረዱት በክፍሉ መልከኛ በባላምባራስ አንዳርጋቸው ዓዲ መሆኑን ዋና ጸሐፊው ጨምረው አስረድተዋል፡፡ የዲርማ ቀበሌ የሚገኘው በሞረት ወረዳ በኘአ ም/ወረዳ ግዛት ነው፡፡
(ሰኔ 1 ቀን 1961 ዓ.ም ከወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ)
ለጐጃም ጠቅላይ ግዛት ፪ ሚሊዮን የዛፍ ችግኝ ተዘጋጅቷል
ደብረ ማርቆስ፤ (ኢ-ዜ-አ-) የጐጃም ጠቅላይ ግዛት እርሻ ጽ/ቤት በዚህ ዓመት በ፰ የእርሻ ጣቢያዎች ያለማቸውን ፪ ሚሊዮን ፩ሺህ ፩፻፴፭ የዛፍ ችግኞች አስፈላጊ በሆኑ ቦታዎች ማስተከል ጀመረ፡፡
በዚሁ መሠረት በመቻከል ወረዳ በአማኑኤል ከተማ የሚኖረው ሕዝብ ሐምሌ ፲ ቀን ፷፩ ዓ/ም/ በወረዳው ገዢ በአቶ አያሌው አብዲ አማካይነት በከተማው መንገድ ግራና ቀኝ ፬ሺህ ፭፻ ልዩ ልዩ ዓይነት ዛፎችን ተክሏል፡፡ እነዚህ የዛፍ ችግኞች በደምበጫ የችግኝ ማልሚያ ጣቢያ የለሙ መሆናቸው ታውቋል፡፡
በጠቅላላውም ችግኞቹ የለማባቸው የእርሻ ጣቢያዎች ደብረ ማርቆስ፤ ደጀን፤ ደምበጫ፤ ፍኖተ ሰላም፤ ቡሬ፤ ዳንግላ፤ አንዳሳና ቢቸኛ ጣቢያዎች ናቸው፡፡
እነዚህ ጣቢያዎች የለሙት ፲፬ ዓይነት የዛፍ ችግኞች ቀይና ነጭ ባሕር ዛፍ፤ ዋንዛ፤ የሐገር ውስጥና የውጭ አገር ጥድ፤ ኦሜድል፤ ፓይንፓቹላ፤ ፓይን ለዲያታ፤ አርዘሊባስ፤ ዝግባ፤ ኮሶ፤ ክትክታ፤ ግራና ፌጮ የተባሉ ዘሮች መሆናቸውን የጠቅላይ ግዛቱ የርሻ ሥራ ዲሬክተር አቶ ደፋር ታፈሰ ገለጡ፡፡
(ሰኔ 15 ቀን 1961 ዓ.ም ከወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ)
የሸክላ ፋብሪካ በሚሊዮን ብር ተሠራ
አዲስ አበባ፤ (ኢ-ዜ-አ-) በ፩ ሚሊዮን ፭፻ ሺህ ብር ካፒታል የተሠራው የአዲሱ ሸክላ አክሲዮን ፋብሪካ በሚመጣው ታኅሳስ ወር ሥራው ይጀምራል።
በሙሉ አውቶማቲክ የሆነ የሸክላ መሣሪያ የሚኖረው የአዲሱ ሸክላ ፋብሪካ ሥራው በሚጀምርበት ጊዜ በአንድ ቀን 70, 000 ጡቦች (ሸክላዎችን) እየሠራ ለገበያ የሚያቀርብ መሆኑን ሚስተር ዳናሰድ ጂ ሀን ካላፌ የፋብሪካው ሥራ ዋና መሐንዲስ ገልጠዋል፡፡
የፋብሪካው ሕንፃ ሥራ ከተጀመረ ስምንት ወሩ ሲሆን፤ በአሁኑ ጊዜ ከጠቅላላው የፋብሪካ በመቶ ሃምሳው መጠናቀቁን ዋና መሐንዲስ አረጋግጠዋል፡፡
የአዲስ ሸክላ አክሲዮን ማኅበር ከጡብ ሌላ ለቤት ሥራ የሚስፈልጉትን ማንኛውም ዓይነት ሸክላዎችን የሚሠራ በጣም ዘመናዊ ሙሉ አውቶማቲክ የሸክላ መሥሪያ መኪናዎች ያሉት ትልቅ ድርጅት ነው፡፡
(ነሐሴ 11 ቀን 61 ዓ.ም ከወጣው አዲስ ዘመን)
፪ ጭንቅላት ያለው ጥጃ ሞቶ ተወለደ
ጐባ (ኢ.ዜ.አ.) በባሌ ጠቅላይ ግዛት በገናሌ አውራጃ በዶዶላ ወረዳ ግዛት አቤና አንሻ በተባለው ቀበሌ ባለፈው ግንቦት ፳ ቀን ፷፩ ዓ/ም ንብረትነቷ የአቶ ጂሎ ጊጐ የሆነች ላም ልዩ ተፈጥሮ ያለው አንድ ወንድ ጥጃ ወለደች፡፡
ይኸው የተወለደው ጥጃ ሁለት ጭንቅላት፤ ፬ ጆሮ፤ ሁለት አፍ፤ ፬ ዓይን ሁለት ጭራ ያለው ሲሆን የእበት መጣያ ሥፍራ ደግሞ ድፍን መሆኑ ታውቋል። ጥጃው ከላይ በተጠቀሱት የአካል ክፍሎች ከሌሎች እንስሳት የተለየ ቢሆንም፤ እግሮቹና ብልቱ ትክክለኛውን የእንስሳት ተፈጥሮ የያዙ ናቸው፡፡
ይኸው ልዩ ተፈጥሮ ያለው ጥጃ ከመወለዱ በፊት በእናቱ ማህፀን ሞቶ ስለነበር በመንደር ወጌሻ ርዳታ የወጣ መሆኑን የአውራጃው ግዛት ዋና ጸሐፊ አቶ ሙላት ሙሉነህ ገለጠ፡፡
(ሰኔ 1 ቀን 1961 ዓ.ም ከወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ)
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 17 /2014