በክረምት ወቅት ከሚበቅለው ተክል ስሙን የወረሰው በትግራይ አሸንዳ፣ በሰቆጣ ሻደይ (በኸምጣኛ ቋንቋ ‹ለምለም› ማለት ነው)፣ በላሊበላ አሸንድዬ፣ በቆቦ ሶለል ሲባል ዓይንዋ ከሚያምረው ወፍ ‹‹ዓይኒ ዋሪ›› ጋር ልጃገረዶቹን በማነፃፀር በዓሉ በአክሱም ይጠራል፡፡
አሸንዳ፣ አሸንድየ፣ ሻደይ ወይም ሶለል ከነሐሴ 16 እስከ ነሐሴ 18 ቀን ድረስ ይከበራል። ሴቶች ልጃገረዶች በልዕልና የሚታዩበት፣ በነፃነት ነግሠው የሚጫወቱበትም ነው። ከሕፃን እስከ አዋቂ የበዓሉ መገለጫ በሆኑ አልባሳትና ማጋጊያጫዎች የሚታዩት ከነሐሴ አጋማሽ ጀምሮ ነው፡፡ ክብረ በዓላቱ በትግራይና አማራ ጎልተው ይታያሉ፡፡
ነሐሴ 16 ቀን ከሚከበረው የቅድስት ማርያም የፍልሰታ በዓል ጋር የተያያዘው ክብረ በዓል ከዋዜማው እስከ ማግስት ልጃገረዶች የአሸንዳ ቅጠልን አሸርጠው አደባባይ በመውጣትና በየቤቱ በመዞር እየጨፈሩና እያዜሙ ያከብሩታል፡፡ ከሕፃን እስከ አዋቂ የበዓሉ መገለጫ በሆኑ አልባሳትና መጋጊያጫዎች ተውበው ይታዩበታል፡፡ የፀጉር አሠራራቸው ከአልባሶ እስከ ግልብጭ፣ ከጋመ እስከ ድርብ፣ ጋሜ፣ ቁንጮ፣ ሳዱላና ቅርድድ ተሠርተው አደባባይ የሚውሉበት ነው፡፡ ጌጣ ጌጣቸውም ልዩ ልዩ ዓይነት ሕንቆ፣ አልቦ፣ ድሪ፣ ድኮት፣ ጉትቻ፣ ማርዳ፣ መስቀል ሲሆን፣ አለባበሳቸውም በመልጉም /ጥልፍ ቀሚስ/ ፣ ሹፎን፣ ጃርሲ ይታጀባል፡፡
ይህ የልጃገረዶች በዓል በላስታ፣ በዋግ፣ በራያ፣ በተወሰኑ የየጁ አካባቢዎች እንዲሁም በተምቤንና እንደርታ በደመቀ ሁኔታ ይከበራል። ይኼ ዓይነት የባህልም ሆነ የበዓል አከባበር ልማዱን የሚያጠፋ ከመሆኑም በላይ ለዛ እና ውበት የሌለው ነው። አሸንድዬ ልጃገረዶች በየሰፈራቸው በቡድን በቡድን ተከፋፍለው ቤት ለቤት እየዞሩ በጭፈራ፣ በዘፈን፣ በውዳሴ ሰውን እያወደሱ ለተወሰኑ ቀናት ገንዘብ ከሰበሰቡ በኋላ ድግስ ደግሰው በድልቂያ በዘፈን ድግሳቸውን የሚበሉበት የሚቦርቁበት ባህል ነው።
በዋግ ሻደይ ሲባል፣ በላስታ እና በተወሰኑ የራያ አካባቢዎች አሸንድዬና አሸንዳ፣ በየጁ እና በተወሰኑ የራያ አካባቢዎች ደግሞ ሶለል ይባላል።
በእነዚህ አካባቢዎች ልጃገረዶች አምረውና አሸብርቀው የሚታዩት ከጥምቀት ይልቅ በአሸንድዬ ወቅት ነበር። ነሐሴ ሲገባ ጀምረው ልጃገረዶች እርስ በእርስ እየተገናኙ በየእድሜ እርከናቸው ከአቻዎቻቸው ጋር ቡድን መስርተው የአሸንድየው ቀን ነሐሴ 16 እስኪደርስ ድረስ ልባቸው ስቅል ብሎ ይከርማል። ልጃገረዶቹ ለአሸንድዬው ቀን በወገባቸው የሚያስሩት የተጎነጎነ ቅጠል “የአሸንዳ ቅጠል” የሚባል ሲሆን፤ ይኼ ቅጠል በበጋ ወራት የማይገኝ ሲሆን፣ የክረምቱን ዝናብ ተከትሎ በመብቀል በአሸንድዬ ወቅት ለበዓሉ መድረሱ አስገራሚ ያደርገዋል።
የዋዜማው እለት አሸንድየውን ካለበት ቦታ ቆርጠው ካመጡ በኋላ በወገባቸው ልክ በገመድ/በማሰሪያ ከጎነጎኑት በኋላ ለጠዋት እንዳይጠወልግ ጤዛ ሳር ላይ ያሳድሩታል። በነገታው ልጃገረዶች ከቻሉ አዲስ አለበለዚያም ደግሞ የነበራቸውን ልብሶቻቸውን አጥበው ለብሰው፣ ጠጉራቸውን በሚችሉት መልኩ አበጃጅተው፣ እስከቻሉት ድረሰ በሚገባ አምረው እና ተቆነጃጅተው አሸንድዬ፣ ወፌይላላ እያሉ ሲጨፍሩ ሲዘሉ ይውላሉ።
ልጃገረዶች ቀን ቀን የተጎነጎነውን አሸንድዬ ወገባቸው ላይ አስረው በየመንደሩ እየዞሩ የሚጨፍሩ ሲሆን፤ ማታ ማታ ደግሞ የተጎነጎነውን አሸንድዬ ከወገባቸው በመፍታት በሚቀጥለው ቀን ላለው ጭፈራ እንዳይጠወልግ ጤዛ ውስጥ ያሳድሩታል።
አሸንድዬ ባይ ልጃገረዶች ወደሚያወድሱት ቤት ሲገቡ አውጫዋ ልጅ <<እሜቴ አሉ ደህና ወይ>> ስትል ተቀባዬቹ <<አሉ እንጂ ግቡ ይላሉ እንጂ>> ብለው በህብረት ያዜማሉ። ከዚያ አሸንዳዬ፣ ወፌ ይላላ እየተባለ ዜማው/ ዘፈኑ ስጦታውን እስኪቀበሉ ድረስ የተለያዩ የውዳሴ ስንኞች እየተቋጠሩ እንደሚከተለው ይቀጥላል።
አሸንዳዬ
አሃ
አሸንዳ ሆይ
ሽርግፍ አትይሞይ
አሸንዳ ሙሴ
ፍስስ በይ በቀምሴ
አበሙሴ አንቺ አበሙሴ
ሽርግፍ በይ በቀሚሴ
አሸንዳዬ አሸንዳ አበባ
ጠብ እርግፍ እንደ ወለባ
ምድር ጭሬ ጭሬ አወጣሁ ማሰሮ
እሰይ የእኔ እመቤት ድልድል ወይዘሮ
ከሰፌድ ላይ አተር ኮለሌ ኮለሌ
የኔማ እሜቴ አንገተ ብርሌ
ወዘተ ግጥሞችና ስንኞች እየተደረደሩ ጨዋታው ከደራ በኋላ ስጦታውን ሲያገኙ
ምስጋናቸውን እንደሚከተለው
ትሻል እሜትዬ ትሻል
ይሻል ጌትዬው ይሻል
በማለት ይገልጣሉ።
በልጅነታችን ልጃገረዶች አሸንድዬ ሲሉ አንዳንዶቻችን ወንዶቹ ከልጃገረዶቹ ወገባቸው ላይ ያለውን አሸንዳ መንጨት በጣም ከሚያስደስተን ነገር አንዱ ነበር። በተለይ ከሰፈራቸው ውጭ የሚመጡትን ልጃገረዶች አሸንዳ በመንጨት ባዶ ማስቀረት አንዱ የጨዋታው ገጽታ ነው። አንዳንድ አሸንድዬ ባይ ቡድኖች ከእንደዚህ አይነት ነገር ራሳቸውን ለመከላከል ዱላ እና ጅራፍ ይዞ ነጭዎችን የሚከላከል ፈርጠም ያለ ልጅ ያስከትላሉ።
በዚህን ጊዜ አሸንድየውን የሚነጭ ልጅ ካለ ጦርነቱ የሚሆነው ከባለ ዱላው እና ከባለ ጅራፉ ጋር ነው። አንዳንዴም ወንዶች የሰፈራችውን ልጃገረዶች አሸንድዬ ሌሎች እንዳይነጩባቸው ለመጠበቅ ተከትለዋቸው ይጓዛሉ፡፡
ከተለያየ ሰፈር የመጡ የልጃገረዶች ቡድኖች ሲገናኙ በሜዳየ መጣሽ ተባብለው አሽንድያቸውን ይነጫጫሉ። በአንዳንድ አካባቢዎች ልጃገረዶች ላይ ቀበሌና ታች ቀበሌ በሚል ከሁለት ቡድን ተከፍለው ቅልጥ ባለ ሁኔታ አሸንድየ ሲጫወቱ ይውላሉ፡፡ ሆኖም ሴቶች ልጅ ሲወልዱ አሸንድዬ መጫወት ያቆማሉ፡፡ ምክንያቱም ሴት ልጅ ካገባችና ከወለደች ጨዋታው ላይ መሳተፍ ስለማትችል ነው። ልጃገረዶቹም ለትዳራቸው የሚያጫቸው ሰውም በግላጭ የሚያያቸው በዚህ የአሸንድዬ ወቅት ነው።
አሸንድዬ ሲጨፍሩ በቤተሰብ ባል ታጭቶላቸው ድፎ ዳቦና በግ ከአማቶቻቸው በእለቱ የሚመጣላቸውም አይጠፉም። የአሸንድዬ ወቅት ደስ ከሚሉ የዓመቱ ጊዚያት አንዱ ነው፤ የክረምቱ ዝናብ እየቀለለ መሄዱ፣ ክረምቱ የሚፈጥረው ልምላሜ የተዋበ መሆኑ፣ የወንዞቹ ጥራት እና በየቦታው ከሚፈነዱት ምንጮች ጋር ተያይዞ የሚማርክ ጊዜ ነው። ከዚህ በተጨማሪ የአሸንድዬው ጨዋታ፣ የቡሄ፣ የሆያሆየው ድግስ ወዘተ ጋር ተደምሮ ልዩ ጊዜ ያደርገዋል።
«አሸንዳዬ አሸንዳ አበባ
ጠብ እርግፍ እንደ ወለባ»
በየቤቱ፤ በየመዝናኛ ቤቱ፤ አንዳንዴም በየቢሮው ጭምር እየዞሩ የሚያማምሩት ልጃገረዶች ባህላዊ ጨዋታቸው በተለመደባቸው የአገሪቱ አካባቢዎች ሲደረድሩት ከሰሙት ግጥም የአማራ ክልል አባይ ማዶ አካባቢ ነዋሪዋ ወይዘሮ ካሰች በዜ በቃላቸው መያዝ የቻሉት ስንኝ ነው፡፡ ወይዘሮዋ ስለተጫዋቾቹ ውበት እንደሰጡን የአሸንዳዬ ጨዋታ ሳቢና ማራኪ ነው ፤ ልብም ላይ ሀሴት ይፈጥራል፡፡ አለባበሳቸውና ፀጉር አሰራራቸው ልዩ ነው፡፡ በአግራሞትም ያስደምማል። በተለይ ወገባቸው ላይ ያገለደሙት አረንጓዴ ልምላሜ ያልተለየው ጉንጉን የአሸንዳ ቅጠል በተለየ ሁኔታ እንዲደምቁና እንዲታዩ አድርጓቸዋል፡፡
ጨዋታው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራችን መዲና አዲስ አበባና በተለያዩ በአገሪቱ ዋና ዋና ከተሞች እየተለመደ መምጣቱን አስተውለዋል፡፡ መለመዱ ባህሉን ያስተዋውቅና እንዳይዘነጋ ያደርጋልም የሚል ዕምነት አላቸው፡፡ ወይዘሮ ካሰች በዜ እንደነገሩን ጨዋታው አንድ ዓይነት ቢሆንም በተለያየ ስያሜ በመጠራት ይታወቃል፡፡
ለምሳሌ እኔ በተወለድኩበት ሰሜን ወሎ ላሊበላ አካባቢ አሸንድዬ በመባል ነው የሚጠራው ብለውናል። በዚሁ እሳቸው በተወለዱበት አካባቢ በሚገኘው ዋግ ኸምራ ዞን አካባቢ ደግሞ ሻደይ ተብሎ እንደሚጠራም ወይዘሮ ካሰች ነግረውናል፡፡ በዚሁ በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ውስጥ በሚገኘው ቆቦ አካባቢ ሶለል ተብሎ የሚጠራበት ሁኔታ እንዳለም አጫውተውናል፡፡
አጎራባች በሆነችው ትግራይ ክልል አሸንዳ በዚሁ ክልል አክሱም አካባቢም የጨዋታውን ተዋናይ ልጃገረዶች ዓይንዋ ከሚያምረው ወፍ ‹‹ዓይኒ ዋሪ›› ዓይነ ዋሪ ተብሎ እንደሚጠራ አውግተውናል፡፡ ጨዋታው በልጃገረዶቹ አማካኝነት ከነሐሴ 16 እስከ ነሐሴ 18 ቀን ድረስ በሁሉም አካባቢዎች የሚካሄድ መሆኑ እንደሚያመሳስለው ወይዘሮ ካሰች አረጋግጠውልናል፡፡ እንደሳቸው ጨዋታው ሰላማዊ ነው፡፡ ፀብ፤ ክርክር ሌሎች ዝባዝንኬዎች ስለሌሉትና በሳቅ በጨዋታ የታጀበም በመሆኑ በአንድነት አብሮ የመኖር መስተጋብርን ለማጠናከር ይረዳል፡፡ አሁን እየተለመደ እንደመጣው በዋና ዋና የአገሪቱ አካባቢ በሚገኙ ከተሞች እየሰፋ መምጣቱም ባህሉን ከትውልድ ወደ ትውልድ ሳይበረዝ ጠብቆ ከማስተላለፍ ባሻገር ፍቅርን ያጠናክራል፡፡
እኔ በምኖርበት አካባቢ ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ ሳይሆን ለሻደይ ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ ነው የሚባለው ሲሉ ስቀው በማሳቅ አስተያየታቸውን ይጀመራል ወይዘሮ አሰፉ ዋቅሹም ጨዋታው ለዛ ያለውና የፍቅር መገለጫ እንደሆነም ያስረዳሉ፡፡ በልጅነታቸው ለአቅመ ሄዋን እስኪበቁ ጨዋታውን ተጫውተው ማለፋቸውንም ያወሳሉ፡፡ እኛ አምረንና አሸብርቀን የምንታየው በአሸንድዬ ወቅት ነው የሚሉት ወይዘሮ አሰፉ ለጨዋታው ዝግጅት የሚያደርጉት ገና ከነሐሴ መግቢያ ጀምሮ መሆኑንም አውግተውናል፡፡ ከነሐሴ ወር ጀምረን በዕድሜ እኩያ በእኩያ የሆነው ተፈላልገን እርስ በእርስ እንገናኛለን፡፡ ቡድንም እንመሰርታለን፡፡
የሻደዩ ቀን ነሐሴ 16 እስኪደርስ ድረስ ልባችን ስቅል ብሎ ይከርማል። ለሻደዩ ቀን በወገባችን የምናስረውን የተጎነጎነ ቅጠል “የሻደይ ቅጠል” ፍለጋ ስንባዝን ነው የምንከረመው፡፡ ቅጠሉ በቅርብም የሚገኝ ቢሆንም ከቅጠል ቅጠል ውበት ያለውን ለመምረጥ ከአካባቢያችን ብዙ ኪሎ ሜትር ርቀን የምንጓዝበት ጊዜም ብዙ ነው። ይኼ አረንጓዴ ልምላሜን የተላበሰው ቅጠል በበጋ ወራት በፍፁም አይገኝም፡፡ ክረምት ላይ ግን በሁሉም አካባቢዎች ይበቅላል፡፡ ሆኖም አረንጓዴ የተላበሰው ልምላሜው ድምቀት ከቦታ ቦታ ይለያያል፡፡ እርቀን በመሄድ ጊዚያችንን የምናጠፋውም ለዚህ ነው፡፡ ከሚገርመኝ የክረምቱን ዝናብ ተከትሎ በመብቀል ልክ የበጋውን ወራት ተከትላ ብቅ እንደምትለው እንደ አደይ አበባ ሁሉ ቅጠሉ በሻደይ ወቅት ለበዓሉ መድረሱ ነው ብለውናል፡፡ መልካም በዓል!!!
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 17 /2014