እድሜው ከአስር አይበልጥም። በፊቱ ላይ ደማቅ ፈገግታ ይታያል። ከሌሎች አቻ ጓደኞቹ ጋር እንደበፊቱ እየቧረቀ ነው። ደስታው ከልክ አልፎ የናፈቃቸውን የክፍል ጓደኞቹን አሁንም አሁንም ያቅፋቸዋል። ከጓደኞቹ ተለያይቶ ስለከረመ ጊዜውን እንዴትና በምን ሁኔታ እንዳሳለፉ የሚጠይቃቸው ይመስላል።
ጓደኞቹም እርሱን ተመሳሳይ ጥያቄ እየጠየቁት እንደሆነ ያስታውቃል። አይ የልጅ ነገር! ከፊቱ ፈገግታና ደስታው ጋር ተዳምሮ ምንም ነገር የደረሰበት አይመስልም።
ሕፃን ሃምዛ መሀመድ ይባላል። የአስር ዓመት ልጅ ሲሆን፤ የዛሬን አያድርገውና በሰሜን ወሎ ዞን ሀብሩ ወረዳ መርሳ ከተማ የመልካ ጨፌ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የአራተኛ ክፍል ተማሪ ነበር። ምን ያደርጋል አሸባሪው የህውሓት ቡድን ስፍራውን ሲቆጣጠር ትምህርት ቤቱን በማውደሙ ከትምህርት ገበታው ለመፈናቀል ተገዷል። ለስድስት ወራት ያህልም ከሚኖርበት አካባቢ ከቤተሰቦቹ ጋር ሸሽቶ ሌላ ቦታ ቆይቷል።
አሁን ግን የህወሓት አሸባሪ ቡድን በሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ አማራ ልዩ ሃይልና ፋኖ በደረሰበት ጠንካራ ምት አካባቢውን ለቆ ከወጣ በኋላ በፈራረሰ ትምህርት ቤት ውስጥ ባልተመቻቸ ሁኔታ ከስምንት በማይበልጡ ወራቶች ውስጥ የዓመቱን የትምህርት መርሃ ግብር አጠናቋል።
ሆኖም የትምህርት ሚኒስቴር የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ የመገንባት መርሃ ግብር በቅርቡ ሲጀምር ከሚታደሱ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ሕፃን ሃምዛ ሲማርበት የነበረው የመልካ ጨፌ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አንዱ በመሆኑ አዲስና የተሻለ የመማር ተስፋ ጭሮበታል።
መምህርት ደመቁ ሙሄ በሰሜን ወሎ ዞን ሀብሩ ወረዳ የመልካ ጨፌ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የስድስተኛ ክፍል ሳይንስ መምህር ናቸው። ወራሪው የህወሓት ቡድን አካባቢው ከመያዙ በፊት ትምህርት ቤቱ በወረዳው ከ2 ሺህ 250 በላይ የሚሆኑ ተማሪዎችን ተቀብሎ ሲያስተምር እንደነበር ያስታውሳሉ።
በተሟላ የትምህርት መርጃ መሳሪያ ለተማሪዎች ትምህርት ይሰጥ እንደነበርም ያስታውሳሉ። ሆኖም ወራሪው ኃይል ቦታውን ከተቆጣጠረ በኋላ የትምህርት ቤቱን ቤተ ሙከራ፣ መፅሃፍት ቤትና የመማሪያ ክፍሎችን ሙሉ በሙሉ እንዳወደመና አስፈላጊ የሚባሉትን ሌሎች የትምህርት ግብአቶች እንደዘረፈ ይናገራሉ። በዚህም ወራሪ ቡድኑ ተመቶ አካባቢውን ከለቀቀ በኋላ የመማር ማስተማር ሂደቱ ሲጀምር አብዛኛው የትምህርት ቤቱ ንብረት በመውደሙ ተማሪዎችን ለማስተማር እጅግ አስቸጋሪ እንደነበርም ይገልፃሉ።
ከጥር ጀምሮ ከውድመት በተረፈው ትምህርት ቤት ውስጥ ተማሪዎችን እንደገና በመመለስ ማስተማር እንደተጀመረ መምህርት ደመቁ ተናግረው፤ የተሰበሩ ወንበሮችን በመጠገን፣ የትምህርት ቤቱን አጥር በሕብረተሰቡ ድጋፍ በማጠር፣ ከውድመት ተርፈው የወዳደቁ መፅሃፍትን በመልቀምና ለተማሪዎች በመስጠት ትምህርቱ እንዲቀጥል መደረጉን ያስረዳሉ። ይህንንም በማድረግ ከጥር ወር ወዲህ ባሉት ስደስት ወራት ውስጥ የዓመቱን ትምህርት ለተማሪዎቹ በመስጠት ማጠናቀቅ እንደተቻለም ይናገራሉ።
በትምህርት አሰጣጡ ሂደት ተማሪዎች በጦርነቱ ምክንያት ተፈናቅለው የቆዩ በመሆናቸው ስነ ልቦናቸው ተጎድቶ እንቆየ ማየታቸውንና የትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ ተማሪዎቹን በመምከርና በመደገፍ ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉ መደረጉንም ያመለክታሉ።
በወራሪ ቡድኑ የወደመውን ትምህርት ቤት ወደነበረበት ለመመለስ የትምህርት ሚኒስቴር የጀመረውን ተግባር እንደሚያደንቁ መምህርት ደመቁ ግልፀው፤ ከመንግስት በዘለለ ሕብረተሰቡ፣ የግል ድርጅቶችና ባለሃብቶች በመልሶ ግንባታው ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪያቸውን ያቀርባሉ።
የመልካ ጨፌ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ በላይ አስፋው እንደሚናገሩት፤ ወራሪው ቡድን በወረዳው ከገባ በኋላ በትምህርት ቤቱ ያደረሰው ጉዳት እጅግ ከፍተኛ ነው። ሁለት የመማሪያ ክፍሎችን አፍርሷል። በክፍሎቹ ውስጥ የነበሩትን የተማሪዎችን ወንበሮች፣ የመምህራንን ሼልፎች፣ ጠረጴዛዎችንና ወንበሮችን ለማገዶነት አውሏዋል። የማባዣ ማሽኖችን፣ ኮምፒዩተሮችንና ሌሎች የአይ ሲ ቲ መሳሪዎችን በሙሉ ዘርፎ ሄዷል።
የተማሪዎችን መረጃና መዛግብቶችን በሙሉ አውድሟል። የመማሪያ ክፍሎችንም በማፈራረስና የአንድን ብሔር የበላይነት ብቻ የሚገልፅ ፅሁፍ በግድግዳዎቻቸው ላይ በመፃፍ መጥፎ ገፅታ እንዲኖራቸው አንድርጓል። በትምህርት ቤቱ አካባቢ ማህበረሰብ ላይም የስነ ልቦና ጫና አድርሷል። በዚሁ ምክንያት ከወረራው በኋላ የተማሪዎች ቁጥር ከ2 ሺ 250 ወደ 1 ሺ 782 እንዲያሽቆለቁል አድርጓልም ይላሉ።
እንደ ርዕሰ መምህሩ ገለፃ፤ ወራሪ ቡድኑ በትምህርት ቤቱ ላይ ባደረሰው ጉዳት ከ3ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሀብት ወድሟል። ከዚህ አኳያ ትምህርት ቤቱን በአዲስ መልክ መልሶ ለመገንባት ከዚህ የበለጠ ወጪ ይወጣል ተብሎ ይጠበቃል። ትምህርት ሚኒስቴር ባስጀመረው በዚህ የመልሶ ግንባታ መርሃ ግብር በሰዎች ለሰዎች ድርጅት የገንዘብ ድጋፍ አማካኝነት ሁለት የመማሪያ ክፍሎች፣ አንድ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት፣ የአይ ሲ ቲ ክፍል ይገነባሉ ተብሎ ይታመናል። ከዚህ ባለፈ የአይ ሲ ቲ ክፍል ኮምፒውተሮች፣ ማባዣዎች፣ ማተሚያዎች ይሟላሉ ተብሎም ይታሰባል። በተጨማሪም ቤተ ሙከራዎች፣ ቤተ መፅሃፍት፣ የስፖርት መስሪያ ሜዳዎችና ጂምናዚየም በመልሶ ግንባታው ይካተታሉ ተብሏልም።
ከወረራው በፊት ትምህርት ቤቱ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተማሪ ያስተናግድ የነበረ ቢሆንም ከወረራው በኋላ 468ቱ በወረራው ምክንያት ትምህርታቸውን አቋርጠዋል። ለትምህርት አስፈላጊ ግብአቶች ባለመሟላታቸውም የተማሪ መምህር ጥምርታ 1 ለ 60 በመሆኑ ትምህርቱ በበቂ ሁኔታ እንዳይሰጥ ማድረጉንም ይናገራሉ።
ትምህርት ቤቱ በአዲስ መልክ የሚገነባና አስፈላጊ የሆኑ የማስተማሪያ ግብአቶች የሚሟሉለት ከሆነ ቀደም ሲል ከነበረው የተማሪ ቁጥር በላይ ተቀብሎ ሊያስተናግድ ይችላል። ቀደም ሲል በወረራው ምክንያት ያቋረጡ ተማሪዎችን የመመለስ እድልም ይኖራል።
ርዕሰ መምህሩ እንደሚሉት፤ ጦርነቱ ምንም እንኳን የራሱ ተፅዕኖና ጫና ቢኖረውም ከወረራው በኋላ የዓመቱን ትምህርት በስደስት ወራት ውስጥ ቅዳሜና እሁድን ጭምር በማስተማር ማጠናቀቅ ተችሏል። መምህራንና ሌሎች የትምህርት ቤቱ አስተዳደር ሰራተኞች ሙያዊ ግዴታቸውን ለመወጣት የበኩላቸውን ጥረት አድርገዋል።
ትምህርት ቤቱ በጊዜያዊነትም ቢሆን ባለው መሰረተ ልማት ተማሪዎችን መቀበሉን ይቀጥላል። ተማሪ ለመማር ብሎ መጥቶ አይመለስም። ግንባታው ሲጠናቀቅ ደግሞ ቅበላውን በማሳደግ በተሻለ የመማር ማስተማር ከባቢ ላይ ተማሪዎችን ያስተምራል። ከዚህ አንፃር ትምህርት ሁሉንም ባለድርሻ አካላት የሚመለከት እንደመሆኑ ለትምህርት ቤቱ ዳግም ግንባታ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ግለሰቦች፣ ባለሃብቶችና ሕብረተሰቡ የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዲያበርክት ጥሪያቸውን ያስተላልፋሉ።
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በበኩላቸው እንደሚገልፁት፤ ከወረራው ጋር በተያያዘ በሰሜን ወሎ ላይ የደረሰው ችግር ከፍተኛ ነው። ወያኔዎች ከምንም ነገር አስቀድመው መጀመሪያ ማጥፋት የሚፈልጉትም ትምህርትን ነው። የተማረ፣ እውቀት ያለውና ማገናዘብ የሚችል ሰው ደግሞ በቀላሉ አይገዛም፤ ነፃነቱንም ይወዳል። ኃላፊነትን፣ መብትንና ግዴታን አብሮ አያይዞ ያያል። እንዲህ አይነት ሰዎች ያሉበት ሀገር ዝምብሎ በጨበጣና በጉልበት የሚያስተዳድር ኃይል ለረጅም ጊዜ አይቆይም።
በዚህ ምክንያት ወያኔዎች ላለፉት ሰላሳ ዓመታት ከሰሩት ሥራዎች ውስጥ ሁለቱና ዋናዎቹ እንደማህበረሰብ ኢትዮጵያውያንን አብረው እንዳይኖሩ በዘር እየከፋፈሉ እርስበርስ ማባላትና የትምህርት ስርአቱንና ጥራቱን ማጥፋት ናቸው። ‹‹ትምህርት ብዙ ሥራ የሚጠይቅ ነው። አንድ ሀገር ትምህርት ላይ መዋዕለ ነዋይ ላፍስ ሲል ህንፃውን ማቆም አይደለም። ልጆቹ መማር የሚችሉበት አካባቢ መፍጠር ነው።
ከንፅህና ጀምሮ ጭቃ የሌለው ቦታ ኳስ መጫወት የሚችሉ ልጆች፣ በንፅህና ክፍል ውስጥ ገብተው የወደፊቱ ሕይወታቸው ምን ሊሆን እንደሚችል ማየት የሚችሉበት፣ በትምህርት ቤታቸው መጠነኛ እርሻ ቦታ ተዘጋጅቶላቸው ከትምህርት ውጪ ትንሽ ዘመናዊ እርሻ የሚሞክሩበት፣ የእጅ ሥራ የሚማሩበት፣ ከትምህርት ቤት ሲወጡም ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ባይገቡም ማህረሰቡን ቢቀላቀሉ ትንሽ እውቀትና ክህሎት ይዘው የሚሄዱበት የትምህርት ስርአት ለመፍጠር ነው ትምህርት ሚንስቴር የተነሳው። ›› ይላሉም።
እንደ ሚኒስትሩ ገለፃ፤ አዲሱ የኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች ተብሎ የተጀመረው አካሄድ በአንድ ቦታ ላይ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራን፣ ማህበረሰቡና ተማሪዎች የሚገናኙበት አዳራሽ፣ የእጅ ሙያ መስሪያ፣ የእርሻ ቦታ፣ ከእርሻው ደግሞ የሚመረተውን እዛው ተማሪዎችን ማብላትና ትምህርት ቤቱ ውስጥ እንዲቆዩና እውቀትን መከታተል የሚችሉበትን አካባቢን መፍጠርን ያካትታል። የሚቀጥለው ትውልድ የትምህርት መሰረትም ይህ ነው የሚሆነው።
በወረራው ምክንያት በአማራና አፋር ክልል ወደ 1 ሺ 300 የሚሆኑ ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ ፈርሰዋል። እነዚህን ትምህርት ቤቶች በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ውስጥ ለመገንባት እቅድ ተይዟል። ሆኖም ግንባታው ሲካሄድ ከጦርነቱ በፊት የነበረውን ትምህርት ቤት አይነት ማስቀመጥ አይፈለግም። ከዚህ ይልቅ ሙሉ በሙሉ አዲስ የትምህርት ቤት አይነት ነው ለመፍጠር የሚያስፈልገው። ዘመናዊ የኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች የሚባሉትም ለዛ ነው።
ከዚህ አኳያ በወራሪው በቡድኑ የወደመው የመልካ ጨፌ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ታስቦ የተሰራ፤ ከስፖርት ጀምሮ ንፁህ የመማሪያ ክፍሎቹንና መፀዳጃ ቤቶችን፣ የአይ ሲ ቲ ክፍሎችንና ቤተመፅሃፍትን ያካተተ ሙሉ እውቀትንና ትምህርት ለተማሪዎች የሚሰጥበት ቦታ እንዲሆንም ነው። ይህንንም ለማድረግ ትምህርት ሚኒስቴር ብቻውን አይሰራም። አብረው የሚሰሩ ኃይሎች አሉ። ከእነዚህ ውስጥም አንዱ የሰዎች ለሰዎች ድርጅት ነው። የመልካ ጨፌ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታን በገንዘብ የሚደግፈውና የሚገነባውም የሰዎች ለሰዎች ድርጅት እንደሆነም ያነሳሉ።
በዚህ ዓመት ትምህርት ሚኒስቴር ከሚሳራቸው ትምህርት ቤቶች ውስጥ 14ቱን በፋይናንስ የሚደግፈውና የሚገነባውም ይኸው ድርጅት ነው። በዚሁ አካሄድ በኢትጵያ በርካታ የፈረሱ ትምህርት ቤቶችን በአዲስ መልክ ማሰራት የሚለውን ፕሮጀክት የሚደግፉ ሌሎች በርካታ ተቋማት አሉ። ይህን አዲስ አይነት የትምህርት ቤት ሥራ ትምህርት ሚኒስቴር ለመስራት ሲያስብ አጋር አካላት ከሚላቸው ውስጥ ህንጻውንና ሌሎች የትምህርት መሰረቶችን የሚገነባው ሰዎች ለሰዎች ድርጅት ብቻ ሳይሆን ወላጆችም እንደሆኑም ያስረዳሉ።
ወላጆች ትምህርት ቤቶቻቸውን የኛ ብለው ካልያዙትና ትምህርት ቤታቸው የተሻለ እንዲሆን አብረው ከትምህርት ማህበረሰቡ ጋር ካልሰሩ የሚታሰቡትን ተማሪዎች ማፍራት አይቻልም። ከዚህ አንፃር አዲሱ የኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች ማዕከል ወላጆች ናቸው። እንደውም ትምህርት ቤቶቹ የአካባቢው ማህበረሰብ ማዕከል እንዲሆኑ ይፈለጋልም። የአካባቢው ማህረሰብ ከትምህርት ቤቶቹ ጋር ሁሌም ግንኙነት እንዲኖረው ያስፈልጋል።
ሌሎቹ የዚህ አዲስ አይነት የኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች ሥራ አጋሮች መምህራን ሲሆኑ፤ ጥሩ መምህራን እንዲፈሩ አዲሱ የትምህርት ስርዓት መምህራንን ለመደገፍ፣ መምህራን ጥሩ ትምህርት እንዲሰጡ ለማድረግ የሚያስፈልጉ ነገሮችን ለማዘጋጀት ተዘጋጅቶ መጥቷል። በኮምፒዩተር ኦን ላይን የሚሰጡ ትምህርቶችን ለማመቻቸትና ሌሎች የሞያ ማሻሻያ ስልጠናዎችን ለመስጠት ሥራዎች እንደሚሰሩም አስረድተዋል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 16/2014