የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ወሰን ዙሪያ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን በዚህ ሳምንት አሳውቀዋል። የተስማሙባቸው ጉዳዮች ዝርዝር ገና ይፋ ስላልተደረገ ብዙ ማለት ባይቻልም ሁለቱም ተደራዳሪዎች ደስተኛ እንደሆኑ ግን ግልጽ ነው። ሁለቱም አንድ ቀን ፈንድቶ ብዙ ህዝብን እንዲያጠፋ ታስቦ የተጠመደን ቦንብ (ታይም ቦንብ) አምክነናል በማለት የሁነቱን ግዝፈት ለማስረዳት ሞክረዋል። ውሳኔው እንደተባለው ታሪካዊ ቦንብ ማምከን መሆን አለመሆኑን ሰንብተን የምናየው ሆኖ ይህ የወሰን ጉዳይ ግን ብዙ ጣጣዎች ይዞ የተቀመጠ እንደነበር ማወቅ ከባድ አይደለም። ስለዚህም ይህን ችግር ለመፍታት በሁለቱም ወገን እንቅስቃሴ መደረጉ የሚደነቅ ነው።
የሆነ ሆኖ ወደ ዋናው ጉዳይ ስንገባ የእኛ ህዝብ የድንበር ፍቅር ያለው ነው። አጥር ፤ ቅጥር ፤ ወሰን ፤ ድንበር ፤ ይዞታ ምናምን ለሚባሉ ነገሮች ያለው ፍቅር ከፍተኛ ነው። አጥሬን ገፋ በሚል በኩርማን መሬት ሊጋደል ይችላል። 50 ገበሬዎችን የማታኖር መሬት ሀምሳ ሺዎች ለሚሞቱበት ጦርነት መንስኤ ልትሆን ትችላለች። እርግጥ መሬት ዋነኛ ሀብት እና የሀብት ምንጭ በሆነበት አገር ሰው መሬትን ቢወድ እና ድንበርን ቢያጠብቅ አይፈረድበትም። ነገር ግን አንዳንዴ በመሬት እና በድንበር ዙሪያ የምናደርገው ትግል መሬቱ ካለው ጥቅም አንጻር ሳይሆን ስለ መሬት እና ድንበር ካለን እሳቤ አንጻር የተቃኘ ነው። በዚህም የተነሳ የመሬት እና የድንበር ጉዳይ ሁሌም የተጋነነ ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ይህ የድንበር እና የመሬት እሳቤያችን ዛሬ ላይ ዓለም ካለበት ሁኔታ አንጻር ሲታይ ኋላቀር ነው ማለት እንችላለን። ዛሬ ላይ በመላው ዓለም የድንበር እሳቤ እየከሸፈ ነው። ሉዓላዊነት(ግሎባላይዜሽን) አገራት ድንበራቸውን መጠበቅ እንዳይችሉ እንዲያውም ክፍት እንዲያደርጉ አስገድዷቸዋል። በዚህም የተነሳ ዛሬ ላይ ብዙ አገራት የድንበር ሀሳብን ትተው የአስተዳደር ወሰን ማበጀት ላይ ጠንክረዋል። አውሮፓ ብንሄድ የአውሮፓ ህብረት አገራት ድንበሮቻቸውን ክፍት አድርገው አንዱ አባል አገር ዜጋ ወደ ሌሎቹ ከሃያ በላይ አገራት ያለምንም ችግር ይንቀሳቀሳል። አሜሪካ ብንሄድ አንድ አሜሪካዊ 54 ግዛቶችን ያለ ከልካይ መንቀሳቀስ ይችላል። በሌሎች ዓለም ክፍሎችም እንዲህ አይነት ልማድ እየሰፋ ነው። አሁን ላይ አገራት በድንበሮቻቸው ላይ ወታደር እና ዘመናዊ መሳሪያ ሳይሆን መደበኛ ፖሊስ እና የደህንነት ካሜራዎች ብቻ ነው ያላቸው። አንዳንድ አገራት በድንበሮቻቸው ላይ የግለሰብ ቤት በማረፉ የሰውየውን ቤት ሳይነኩ ቀጭን መስመር በማስመር ብቻ ወሰናችን ይሄ ነው ብለው ሲወስኑ እና በሰላም ኑሮራቸውን ሲቀጥሉም አይተናል። ተቋማቶቻቸው አጥር አልባ፤ የዜጎቻቸው መኖሪያም እንዲሁ ቅጽር አልባ ናቸው። በአጭሩ የድንበር ዘመን እያለፈ ነው።
እኛ ጋር ነገሩ በተቃራኒ ነው። ዛሬም ቢሆን ሰዎች ድንበር በጣም ይወዳሉ። ረዣዥም አጥሮች ፤ የአጥር ሽቦ ፤ ተናካሽ ውሾች ወዘተ አሁንም አሉን። ተቋማቶቻችን በፌደራል እና በክልል የጸጥታ ኃይሎች ከዚያም በተቀጣሪ ጥበቃዎች ይጠበቃሉ። በክልሎች መሀል ያለው ድንበር ማለቂያ በሌለው የፍተሻ ኬላ የተሞላ ነው። ከአንዱ ክልል ወደ ሌላው ክልል መሄድ ከአገር ወደ አገር ከመንቀሳቀስም የከበደ ነው። አይደለም በክልሎች መሀከል በአንድ ክልል ውስጥ ያሉ ወረዳዎች እንኳን በግጦሽ መሬት እና በእርሻ ወሰን ይቆራቆዛሉ። አንዳንዶች አቅም አጥተው እንጂ ዶናልድ ትራምፕ በአሜሪካ እና በሜክሲኮ መሀከል ያቆሙትን አይነት የኮንክሪት ድንበር በክልሎች መሀል ቢያቆሙ ደስ ይላቸዋል። ይሄ አደገኛ እና አሳፋሪ ልማድ ነው።
አሁን የሚያስፈልገን ድንበር አይደለም። ወደፊትም የሚያስፈልገን ድንበር አይደለም። የሚስፈልገን የአስተዳደር ወሰን ነው። በተለይም በክልሎች መሀከል የሚያስፈልገን ይሄ ነው። የአዲስ አበባ እና የኦሮሚያ ጉዳይም በዚያ መንፈስ የተቃኘ ነው ተብሏል። ጥሩ ነው። በአዲስ አበባ እና በኦሮሚያ መሀከል ድንበር ኖሮ አያውቅም፤ ሊኖርም አይገባም። ያልነበረው የአስተዳደር ወሰን ነው። የሚያስፈልገውም የአስተዳደር ወሰን ነው። አሁን ተደረገ የተባለውም ይሄ ነው። ይህ ልምድ በአማራ እና በትግራይ ፤ በኦሮሚያ እና በሶማሌ፤ በአፋር እና በሶማሌ ፤ ወዘተ ያስፈልጋል።
አሁን ላይ ለዚያ ትምህርት የሆኑ አንዳንድ ተግባራት በመንግስት ደረጃ እየታዩ ነው። ለምሳሌ ያህል የአብርሆት ቤተ መጻህፍትን እንመልከት። አጥር የለውም። ስለዚህም ድንበሩ የቱጋ እንደሆነ አይታወቅም። ነገር ግን ቤተ መጻህፍቱ ወሰን አለው። በህግ በሚታወቅ ወሰኑ ላይ ቤተ መጻህፍቱ የፈለገውን ልማት ያለማል። ከዚያ ካለፈ የሚመለከተው አካል ይጠይቀዋል። ቤተ መጻህፍቱ የራሱ ወሰን እንዳለው ለማሳወቅ ግን አጥር ማጠር አላስፈለገውም። መሬቱን የሚያስተዳድረው አካልም ቤተ መጻህፍቱ ከወሰኑ አልፎ መንቀሳቀስ አለመንቀሳቀሱን ለማወቅ አጥር አያስፈልገውም። አጥር ሳይገነባ በካርታ ላይ ያለች ቀጭን መስመር ሁሉንም ነገር ግልጽ ታደርጋለች።
ቤተ መጻህፍቱ የድንበር አምሳያ የሚሆነው አጥር ስለሌለው ምን ተጠቀመ? አንደኛ ሳቢ ሆነ፤ ያ ውብ ህንጻ ከነሙሉ ክብሩ እና ከነሙሉ ውበቱ ታየ። አሁን በ4 ኪሎ ያለፈ በሙሉ ዓይኑን ቤተ መጻህፍቱ ላይ ሳያሳርፍ ማለፍ አይችልም። አጥር አልባ መሆኑ ተመልካችን ግቡብኝ ግቡብኝ የሚል ጉጉት ውስጥ እንዲገባ አደረገው። ሁለተኛው ጥቅም፤ አጥር አለመኖሩ የእንቅስቃሴ ነጻነትን ፈጠረ። ተጠቃሚዎች በፈለጉት አቅጣጫ ያለምንም ችግር ይገባሉ ይወጣሉ። ሶስተኛ በአጥር ተከልሎ ይሰራ የነበረ የማይጠቅም እና የማያምር ተግባር በሙሉ ቀርቷል። አላፊ አግዳሚ ስለሚያያቸው የቤተ መጻህፍቱ ሰዎች የማይሆን ነገር ከመስራት ተቆጥበዋል። እንዲህ እያልን ሌሎች ጥቅሞችንም ልንጠቅስ እንችላለን። ይህን እሳቤ ወደ ወረዳዎች ፤ ዞኖች እና ክልሎች ድንበር እናዙረው። እስኪ እነዚህ ክልሎች ድንበር የሚል እሳቤን ትተው ይሄን የማይጠቅም የድንበር ሀሳብ ነፍስ እንዲዘራ ያደረጉትን ኬላዎች፤ ልዩ ኃይሎች ፤ እና መሰል ነገሮች ከድንበር አካባቢ ቢያንቀሳቅሱ ምን ያህል የሀሳብ ፤ የገንዘብ፤ የእውቀት ዝውውር ሊኖር እንደሚችል አስቡት እስኪ።…. የክልሎች ሉዓላዊነት በሚል እሳቤ ክልሎች ድንበር የሚመስል ነገር ገድግደው በክልላቸው ውስጥ የሚሰሩትን ህገወጥ ተግባር ምን ያህል ሊያጋልጠው እንደሚችልም ገምቱ።…. ድንበር ባይኖር ለኗሪዎች ስለለመዱት ብዙም የማይታያቸው የክልሎች እምቅ የተፈጥሮ አቅም ምን ያህል ለሌሎች ፍንትው ብሎ እንደሚታይም አስቡት ።
ለማለት የተፈለገው ነገር አንድ ነው ..እሱም ፤ እንደ አገር የሚያስፈልገን የአስተዳደር ወሰን ነው። አስተዳደር ወሰናችንን ለማሳወቅ ደግሞ ወሰኑን ድንበር የሚያስመስል ነገር ከማድረግ መቆጠብ አለብን። ይህን ለማድረግ ደግሞ የሚያስፈልገን የመጀመሪያው ነገር የድንበርን ሀሳብ ማፍረስ ነው።
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን ነሐሴ 14 /2014