ዓለም አቀፍ ጥናቶች እንደሚያሳዩት 30 ከመቶ ያህሉ የበሽታ ጫና በቀዶ ህክምና አማካኝነት ሊታከም ይችላል። ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው አገራት በአማካይ 0 ነጥብ 03 የህፃናት ቀዶ ሐኪም ለ100 ሺ ህፃናት እንዲሁም አንድ የህፃናት ልዩ ቀዶ ሐኪም ከ3 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ህፃናት እንደሚደርስ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ከዚህ በተቃራኒ ግን ባደጉት አገራት አንድ ልዩ የህፃናት ቀዶ ሐኪም ለ47 ሺ ህፃናት በአማካይ ተደራሽ ይሆናል። ይህም ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎች ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው አገራት አሁንም ድረስ ህፃናት ጥራት ያለው የቀዶ ህክምና እንደማያገኙ ያሳያል።
በኢትዮጵያ ላንቃና ከንፈራቸው ተሰንጥቆ የሚወለዱ ህፃናት ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ በውል የሚያሳይ መረጃ ባይኖርም ቁጥሩ ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ስለመምጣቱ በርካታ ጠቋሚ ምልክቶች እንዳሉ መረጃዎች ያሳያሉ። ይህ የላንቃና ከንፍር መሰጠንቅ ቁጥር እየጨመረ የመጣ ቢሆንም ታዲያ መንግስትም ሆነ ሌሎች የግል ህክምና ተቋማት በሌሎች በሽታዎች ህክምና ላይ ትኩረታቸውን በማድረጋቸው የቀዶ ህክምና አገልግሎቱ ሰፋ ባለና በተሻለ ሁኔታ ሲሰጥ እምብዛም አይታይም።
በእርግጥ መንግስታዊ ባልሆኑ የውጭ ድርጅቶች አማካኝነት አልፎ አልፎ የላንቃና የከንፈር መሰንጠቅ ቀዶ ህክምና አገልግሎት የሚሰጥ ቢሆንም ያን ያህል አጥጋቢ አይደለም። ተደራሽነቱም ቢሆን አጠያያቂ ነው። በዚህም ምክንያት በርካታ ህፃናትና ታዳጊዎች ለስነ-ልቦናና ሌሎች ተያያዥ የጤና ጉዳቶች ሲጋለጡ ይስተዋላል።
ሆኖም ከብዙ ጥረት በኋላ እንዲህ አይነቱ የላንቃ ስንጥቃትና የከንፈር ጉዳት ቀዶ ህክምና አገልግሎት ‹‹ኪድስ ኦር›› እና ‹‹ስማይል ትሬን›› በተሰኙ የግል ድርጅቶችና በጤና ሚኒስቴር ትብብር አዲስ አበባ በሚገኘው አለርት ሆስፒታል ውስጥ በልዩ ሁኔታ ተገንብቶ በቋሚነት አገልግሎቱ መሰጠት መጀመሩ ለወላጆች እፎይታን ለህፃናት ደስታን ፈጥሯል።
የቀዶ ህክምና ማእከሉ መገንባት ከዚሁ የላንቃ ስንጥቃትና የከንፈር መሰንጠቅ ቀዶ ህክምና አገልግሎት ጎን ለጎን ሌሎች የህፃናት ቀዶ ህክምና አገልግሎቶችም በተሻለ መልኩ እንዲሰጡ በር ከፍቷል።
የአለርት ማእከል ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር እስማኤል ሸምሰዲን እንደሚናገሩት በአለርት ሆስፒታል የላንቃና ከንፍር ስንጥቃት ቀዶ ህክምና ክፍል የተገነባው በ‹‹ኪድስ ኦር›› እና ‹‹ስማይል ትሬን›› በተሰኙ መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማትና በጤና ሚኒስቴር ትብብር ሲሆን ቀዶ ህክምና ክፍሉን ገንብቶ ለማጠናቀቅ 8 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ፈጅቷል።
የማእከሉን ግንባታ ለማከናወን አንድ አመት የፈጀ ሲሆን አራት የቀዶ ህክምና ክፍሎችን ያጠቃልላል። አንደኛው በ‹‹ኪድስ ኦር›› እና ‹‹ስማይል ትሬን›› ድጋፍ ሙሉ የህክምና መሳሪያዎች ተሟልቶለት ሙሉ በሙሉ ለህፃናት ብቻ የቀዶ ህክምና አገልግሎት ይሰጣል።
ይህም የፕላስቲክና ሪኮንስትራክቲቭ ቀዶ ህክምናዎችን ማለትም በተፈጥሮ በፊት ላይ፣ እጅና እግር፣ ነርቭና ጅማቶች ላይ የሚደርሱ ጉዳቶች ቀዶ ህክምናዎችን ያጠቃልላል። ከዚሁ ጎን ለጎን የአጥንት ህክምናም ይካሄድበታል። ሶስቱ ክፍሎች ደግሞ የላንቃና የከንፈር ስንጥቃት ቀዶ ህክምና አገልግሎቶችን ይሰጣሉ። በአራቱ የቀዶ ህክምና ክፍሎችም በአንድ ጊዜ አራት ህፃናትን ቀዶ ማከም ይቻላል። በቀን ደግሞ ከ15 እስከ 20 የሚሆኑ ህናፃናትን ቀዶ ለማከም ያስችላል።
የነዚህ የቀዶ ህክምና ክፍሎች መገንባት ቀደም ሲል አገልግሎቱን ሲጠባበቁ የነበሩትን ህፃናት በአፋጣኝ ህክምና እንዲያገኙና የነበረውንም ውዝፍ ወረፋ እንዲቀንስ ያደርጋል። በርካታ ታካሚ ህፃናትንም በአንድ ጊዜ የቀዶ ህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላል። የአልጋ እጥረትና ከቀዶ ህክምና ጋር ተያይዞ ያለውን ችግርም ይቀርፋል። እንደ አገር በቀዶ ህክምና ያለውን ተደራሽነትም ያሰፋል።
የከንፈርና የላንቃ መሰንጠቅ ቀዶ ህክምና ከዚህ ቀደም በተለያየ መልኩ በነፃ ሲሰጥ ቆይቷል። ሆኖም ህክምናው በአለርት ሆስፒታል ውስጥ የራሱ የቀዶ ህክምና ክፍል ተከፍቶለት ስራ መጀመሩ ከዚህ ቀደም በተበጣጠሰና በተቆራረጠ መልኩ ሲሰጥ የነበረውን አገልግሎት በቋሚነት ለመስጠት ያስችላል።
በአለርት ሆስፒታል ፕላስቲክና ሪኮንስትራክቲቭ ሰርጀሪ ክፍል ነርስ ኃላፊ ሲስተር አምሳለ ገላዬ እንደሚናገሩት በ‹‹ኪድስ ኦር›› እና ‹‹ስማይል ትሬን›› ትብብር አስፈላጊ የህክምና መሳሪያዎችን በማሟላት የላንቃና ከንፈር መሰንጠቅ ቀዶ ህክምና ክፍል በአለርት ሆስፒታል ተቋቁሟል።
የቀዶ ህክምና ክፍሉ አራት ትላልቅ የቀዶ ህክምና ክፍሎች ያሉት ሲሆን በነዚህ ክፍሎች ውስጥ የተለያዩ የህፃናት፣ የአጥንት፣ የመልሶ ጥገና ሌሎች የነርቭና የጅማት ቀዶ ህክምና አገልግሎቶች ይሰጣሉ። በቀዶ ህክምና ሂደቱም ከአስራ አምስት እስከ ሃያ የሚደርሱ የጤና ባለሙያዎች ይሳተፋሉ። እነዚህም በፕላስቲክና ሪኮንስትራክቲቭ ቀዶ ህክምና ኢትዮጵያ ውስጥ አሉ ከተባሉት ውስጥ ቀደምቶቹና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም በመምህርነት እያገለገሉ የሚገኙ ናቸው። ስምንት የአጥንት ስፔሻሊስት ሐኪሞችም አሉ።
በተጨማሪም በተለያዩ የአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ሐኪሞችና ጠቅላላ ሐኪሞች በቀዶ ህክምና ክፍሉ ውስጥ ይሰራሉ። አርባ ነርሶችና አስራ ስድስት የሰመመን ባለሙያዎች በዚህ የቀዶ ህክምና ስራ ይሳተፋሉ። በፅዳትና በሌሎች ስራዎች ላይ የሚሳተፉ ሃያ ሰራተኞችም አሉ።
በላንቃና ከንፈር መሰንጠቅ ቀዶ ህክምና አገልገሎት ለማግኘት በርካታ ህፃናት ይመጣሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን በርካታ ውዝፍ ወረፋዎችም በዚሁ አገልግሎት መከፈት ምክንያት ይቀንሳሉ ተብሎም ይታሰባል። በቀን በቀዶ ህክምና ክፍሉ እስከ ሃያ የሚደርሱ ህጻናት የነርቭ፣ የጡንቻ፣ ቃጠሎና የላንቃና የከንፈር መሰንጠቅ አገልግሎቶችን እያገኙ ነው።
ከዚህ ቀደም የላንቃና ከንፈር መሰንጠቅ ቀዶ ህክምና በረጂ የውጭ ድርጅቶች አማካኝነት በዘመቻ መልክ ሲሰጥ የቆየ ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ አገልግሎቱ በቋሚነት በአለርት ሆስፒታል ውስጥ ራሱን ችሎ መሰጠቱ በሁለንተናዊ መልኩ የህፃናትን ጤንነትና እንቅስቃሴ የሚያሻሻል ነው። ለህክምና ባለሙያዎችም ስራው እርካታን ያጎናጽፋል።
የስማይል ትሬን የምስራቅ አፍሪካ ቅርንጫፍ ኃላፊ ወይዘሮ ሲስኒ ዘሚካኤል በበኩላቸው እንደሚገልፁት ስማይል ትሬን እ.ኤ.አ በ1999 በአሜሪካን አገር የተቋቋመ ድርጅት ሲሆን በዋናነት የከንፈርና የላንቃ መሰንጠቅ ነፃ የቀዶ ህክምና አገልግሎት ይሰጣል። በኢትዮጵያም እ.ኤ.አ ከ2006 ጀምሮ ይህንኑ የቀዶ ህክምና አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። በዚህም ወደ 36 ሺ የሚሆኑ ህፃናትና አዋቂዎች የዚህ ነፃ የቀዶ ህክምና አገልግሎት ተጠቃሚ መሆን ችለዋል። አሁንም ድርጅቱ ይህን ነፃ የቀዶ ህክምና አገልግሎት እያስፋፋ ይገኛል።
የከንፈርና ላንቃ መሰንጠቅ ችግር ያለባቸው ህፃናት የአመጋገብ ችግር አለባቸው፤ ለመጥባትም ይቸገራሉ። በዚህም በትንታ፣ በኢንፌክሽንና ሌሎች መሰል ችግሮች ይሰቃያሉ። ባስ ሲልም ከነዚህ ችግሮች ጋር በተያያዘ አምስት አመት ሳይሞላቸው ሕይወታቸው ያልፋል። ነገር ግን ደግሞ ይህ የላንቃና የከንፈር መሰንጠቅ ችግር በቀላል ቀዶ ህክምና በመቅረፍ የህፃናቱን ሕይወት ማስተካከል ይችላል።
በመሆኑም ይህን ቀላል ቀዶ ህክምና ተደራሽ በማድረግ ህፃናቱ ሕይወታቸው እንዳይጎዳ፤ የመናገር፣ የመስማትና ሌሎች የስነ ልቦና ችግሮች እንዳይደርሱባቸው ስማይል ትሬን በርካታ ኢትዮጵያውያንን አግዟል። አሁንም ድርጅቱ ይህንኑ ፕሮግራም በማስፋፋት ሂደት የቀዶ ህክምና የሚካሄድባቸው ክፍሎች ዘመናዊነት እንደሚጎላቸው አረጋግጧል። ቀዶ ህክምና ሲደረግ ለህፃናት የሚስፈልጉ ቁሳቁሶች ካልተሟሉ በቀዶ ህክምና ወቅት ለሚፈጠሩ ችግሮች እንደሚጋለጡም ተመልክቷል።
ይህንኑ ታሳቢ በማድረግም ድርጅቱ የአቅም ግንባታ በማድረግ የህፃናት የላንቃና ከንፈር መሰንጠቅ ቀዶ ህክምና ክፍል ከ300 በላይ በሚሆኑ የቀዶ ህክምና መሳሪያዎች እንዲሟሉ በማድረግ በአለርት ሆስፒታል አዲስ፣ በተለየና ለህፃናት ምቹ በሆነ መልኩ ተገንብቷል።
ይህም ሆስፒታሉ የመንግስት እንደመሆኑ በርካታ ህፃናት ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች መጥተው በተመጣጣኝ ዋጋ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል። ከዚህ አኳያም ቅድሚያ በመስጠት በአለርት ሆስፒታልና የካቲት 12 ሆስፒታል የላንቃና የከንፈር መሰንጠቅ ቀዶ ህክምና ክፍል እንዲገነባ ተደርጓል። ይህም በሚቀጥሉት ሶስት አመታት በትንሹ በሺዎች የሚቆጠሩ ህፃናት ይገለገሉበታል ተብሎ ይታሰባል።
እንደ ኃላፊዋ ገለፃ በክልልም ሆነ በአዲስ አበባ ከተማ ድርጅቱ ለረጅም አመታት የላንቃና የከንፈር መሰንጠቅ ቀዶ ህክምና አገልግሎቱን ለረጅም አመታት ሲሰጥ ቆይቷል። ነገር ግን በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚገለገሉት በመንግስት ህክምና ተቋማት በመሆኑ ከግል ተቋማት ይልቅ የመንግስት ተቋማት በርካታ ድጋፍ ይፈልጋሉ።
ከዚህ አንፃር ድርጅቱ የመንግስት የህክምና ተቋማትን በማጠናከር፤ አሰራራቸውንም በማዘመን ለታካሚዎች ሰፊ የሆነ አገልግሎትን የመስጠት ራዕይ አለው። ከግል ይልቅ የመንግስት የህክምና ተቋማት ብዙ ክፍተቶች ያሉባቸው በመሆኑም በስልጠና፣ በቁሳቁስና የተለያዩ ድጋፎችን ይሰጣል። ያለውን የባለሙያ እጥረት ለመቅረፍም ድርጅቱ የነፃ የትምህርት እድል ፕሮግራሞችን ያመቻቻል።
ድርጅቱ በዋናነት የከንፈርና የላንቃ መሰንጠቅ ቀዶ ህክምና ቢሆንም ስራው ከዚህም ሰፋ ያለ ነው። በአለርት ማእከል የተቋቋመው የቀዶ ህክምና ክፍል ግልጋሎቱ የከንፈርና የላንቃ መሰንጠቅ ለደረሰባቸው ህፃናት ብቻ ሳይሆን ለማንኛውም ቀዶ ህክምና ለሚፈልጉ ህፃናትም ጭምር ነው። ስለዚህ ፕሮግራሙ ሰፊና ታዳሽነት ያለው ነው።
በዚህ በአዲስና በተለየ መልኩ በአለርት ሆስፒታል ውስጥ በተቋቋመው የቀዶ ህክምና ክፍል ውስጥ ከከንፈርና የላንቃ መሰንጠቅ ቀዶ ህክምና በተጓዳኝ ሌሎችም የህፃናት የቀዶ ህክምና አገልግሎቶችም ይሰጣሉ። የቀዶ ህክምና ክፍሉ ለሁሉም የቀዶ ህክምና አገልግሎቶች ሁሌም በሩ ክፍት ቢሆንም ታዲያ የባለሙያና የአልጋ ጉዳይ አብሮ የሚነሳ በመሆኑ እነዚህን ማሟላት ያስፈልጋል።
የቀዶ ህክምና ማገገሚያ ክፍሎችም መስፋት አለባቸው። በዚሁ መሰረትም ሆስፒታሉ በርካታ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል። ከዚህ አኳያ የቀዶ ህክምና ክፍሉ ከዚህ በፊት የነበረውን ችግር በመቅረፍ ረገድ ትልቅ አስተዋፅኦ ቢኖረውም ሌሎች ተጓዳኝ ስራዎች መሰራት አለባቸው። ይህን ማድረግ ከተቻለ ደግሞ የአገልግሎቱን ተደራሽነት ማሳደግ ይቻላል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 14 /2014