እያንዳንዱ ዘመን ትቶት የሚያልፈው የራሱ አሻራ አለው።የትናንቱ ዘመን “እንደ ፈሰሰ ውሃ ላይታፈስ” ታሪክ ሠርቶም ይሁን የተሠራውን አበላሽቶ በትረ ሥልጣኑን ለዛሬ አስረክቦ እብስ ብሎ ተሰናብቷል።ጸጸት፣ ቁጭትና ትዝታ “የተገጠመላቸው ዐይን” የሚመለከተው ትናንትንና የኋላውን ብቻ ሲሆን፤ ተስፋ ደግሞ ትኩር ብሎ “እርምጃውን እያፋጠነ የሚገሰግሰው” በዛሬ ላይ እየተረማመደ ወደ ነገ መዳረሻው ነው።
እያንዳንዱ ግለሰብም የሚኖርበትን ዘመን ይዋጅ ካልሆነ በስተቀር ወደ ኋላው ተዘርግቶም ይሁን ተንጠራርቶ የኃላፊውን ጊዜ አስገብሮ ክፉም ይሁን ደግ አሻራውን ለማሳረፍ ሰብዓዊ ባህርይውም ሆነ አቅሙ አይፈቅድለትም።ባዕዳን ባለብሂሎች “አንድን ወራጅ ወንዝ ሁለቴ አታቋርጠውም” የሚሉት ፈሊጥ አላቸው።ባለቅኔው የክብር ዶ/ር ከበደ ሚካኤል “አዝማሪና የውሃ ሙላት” በሚለው ተወዳጅ ግጥማቸው፡-
“እስኪ ተመለክተው ይህ አወራረድ፣
ያልሰማው ሲመጣ የሰማው ሲሄድ፤
ድምጡን እያውካካ መገሥገሡን ትቶ፣
ማን ይሰማኝ ብልህ ትደክማለህ ከቶ፡፡”
በማለት በግጥማቸው ያስታወሱን ይህንኑ የወንዝ አወራረድ “ተአምራዊ” እውነታ ነው።ዘመንም እንደዚያው ሂያጅ እንጂ ደርሶ ተመላሽ መንገደኛ አይደለም።ቢዘፍኑለትም፣ ቢዘምሩለትም ሆነ ቢዘይሩለት ዘመን እንደ ወንዝ ነው።ሲሄድ ውሎ ሲሄድ የሚያድር፡፡
ሞኝ ሰው አካሉን ዛሬ ላይ አቁሞ፤ ትዝታውን ትናንት ላይ ቸክሎ ሲያብሰለስል፤ ብልህ ሰው ግን ዛሬውን ሊያደምቅ፣ ነገውን ሊያስውብ ይተጋል።“ዘመናችሁን ዋጁት እንጂ ሞኞች አትሁኑ” የሚለው የቅዱስ መጽሐፍ መሪ ጥቅስ ለዚህ ጽሑፍ ማጎልበቻነት ቢጠቀስ ተገቢ ይመስለናል፡፡
እርግጥ ነው ትናንትን በትዝታ መናፈቅ፣ የታለፈውን መልካምም ይሁን አስከፊ ጊዜ እያስታወሱ እንደ ድምጸ መረዋው ዘሜኛ “እህህ” እያሉ መብሰልሰል ሰብዓዊ ተፈጥሯችን እንደሆነ አይካድም።“ያሳለፍነው ዘመን” እየተባለ ቢወደስ ወይንም ቢወቀስ ከአግባብ ማፈንገጥ ተደርጎ ሊታሰብ አይገባም – ምክንያቱም ትዝታ ስለማያረጅ።
“የከሰረ ዐረብ አርጅቶ ከጃጀ በኋላ በወጣትነት ዘመኑ ዱቤ የሰጣቸውን ደንበኞቹን ስም ለመፈለግ አሮጌ መዝገቡን ያገላብጣል” እንዲሉ፤ ትናንትን ረትቶ ለመጣል ግብ ግብ ካልፈጠርኩ ብሎ ወላንሶ በመግጠም ለያዥ ለገራዥ ማስቸገር የአእምሮ ጤንነትን ያጠራጥራል። ቢሞከርስ መች ይቻላል፡፡
ከትናንት ማህደር ውስጥ ታሪክን፣ ተሞክሮን ወይንም ጥፋትን እየመዘዙ “እንዲህ ቢሆን ኖሮ ወይንም እንዲህ በመሆኑ እንዲህ ሆነ …” እየተባለ በትምህርትነቱ መጥቀስም ሆነ መተቸት ይቻል ይሆናል።በየዘመኑ “አጥፊ” ተሰኝተው ትውልድን የበደሉ ግለሰቦችን፣ ቡድኖችንና ሥርዓቶችን በአግባቡ መሄስና መሞገቱ ክፋት የለበትም።ነገር ግን ሞቶ የተቀበረን፣ ተንኮታኩቶ የተሰባበረውን ፍልስፍናና ርዕዮተ ዓለምን በዛሬ ጀንበር እንደ አዲስ በማስተዋወቅ “ተጋግዘን ካላላመጥንና ካላመነዠክት” ብሎ ማስገደዱም ሆነ ማባበሉ “ለራስ አባት ቅድመ አያት ካልሆንኩ” ብሎ የመሟገት ያህል ዋዘኛነት ነው።
ነፍሱ ሄሩ የሥነ ጽሐፍ መምህራችን ደበበ ሰይፉ እነዚህን መሰል ከዘመናቸው ጋር የተኳረፉ የሃሳብ ምንዱባን የገለጻቸው እንዲህ በማለት ነበር፤ “እናንቴ የአባቶቻችሁ ልጆች፤ የአያቶቻችሁ ቅድመ አያቶች” – ግሩም ገለጻ ነው፡
ይሄው የሥነ ጽሑፍ ጎምቱ ባለሙያ መክነፍ እንጂ መስከን ባህርይው ያልሆነውን የጊዜን ዑደት በተባ ብዕሩ የሸነቆጠው እንዲህ በማለት ነው፡፡
ጊዜ በረርክ በረርክ፣
ጊዜ በረርክ በረርክ፣
ግን ምን አተረፍክ
ግን ምን አጎደልክ፣
ሞትን አላሸነፍክ፣
ሕይወትን አልገደልክ፡፡
ዘመን እየከነፈ የሚበረውና የሚጋልበው ከሕይወታችን ላይ ቀናችንንና እድሜያችንን እየቆነጠረ ነው።“ኤዲፐስ ንጉሡ” በሚሰኘው ጥንታዊ የግሪኮች ተውኔት ላይ የሰው ልጅ ዕድሜ የተመሳጠረው በሚከተለው የዕንቆቅልሽ ፍልስፍና ነው።“ጠዋት ላይ በአራት እግሩ የሚሄድ፣ ከሰዓት በሁለት እግሩ የሚራመድ፣ ምሸት ላይ በሦስት እግሩ የሚውተረተር ምንድን ነው?”
መልሱ ያው “ሰው ነው” የሚል ሲሆን፤ ዕንቆቅልሹ ሲፈታ የምሥጢሩ ይዘት የሚከተለውን ይመስላል።“በጠዋት የተመሰለው የአራት እግር እርምጃ ተምሳሌቱ የሕጻንነትን የመዳህ ዘመን የሚያስታውስ ሲሆን፣ የጠዋቱ የሁለት እግር ጉዞ ደግሞ አፍለኛውንና ቢሮጡ የማይደከምበትን የዘመነ ወጣትነት ዕድሜ ያመላክተናል።የዘመነ-ሽበት የእርጅና ወቅት የተነጻጸረው ደግሞ ምርኩዝ ከመጨበጥ ጋር ነው፡፡”
ከዘመን ጋር የማይለወጥ ምናልባትም የተራራ ላይ ቋጥኝ ድንጋይ ሊሆን ይችላል።ገፋ አድርግን ብንመረምር ሌላ የተሻለ ገላጭ ምሳሌ ሊጠፋ እንደማይችል ይገባናል።የድንጋይ ነገር ከተነሳ አይቀር በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ተፈጸመ የሚባልን አንድ ሁኔታ አስታውሰን እንለፍ።በመንገድ ሥራ ላይ የተሰማራ አንድ የኮንስትራከሽ ድርጅት የተራራ ሥር መሹዋለኪያ ለመሥራት በግሬደሩና በመከስከሻዎቹ ግዙፍ ማሽኖቹ አማካይነት ቋጥኙን ድንጋይ እየፈረካከሰና እየከሰከሰ የመንገድ ንጣፉን ሥራ ሲከውን የተመለከቱ የዚያ አካባቢ ተረበኞች እንዲህ በማለት ገጠሙ ይባላል፡፡
“ድንጋይ አይሞት ያሉት ሞት ተፈረደበት፣
እየከሰከሱ መኪና ነዱበት፡፡
ይሄን ብለው ብቻ ቢያበቁ ደግ፤ በመቀባበልም እንዲህ በማለት ትዝብታቸውን ገለጹ ተብሎ ይነገራል፡፡
“እስቲ በል ተቦካ፣ እስቲ በል ተፈጨው
እስቲ በል ትጋገር፣
አንተም ስንፍናውን አብዝተኸው ነበር፡፡
እያንዳንዱ ትውልድ የራሱን ዘመን ዋጅቶ ያስገብር ካልሆነ በስተቀር ወደ ትናንት ተንጠራርቶ “በአደረ አፋሽነት ባለቤት” መሟገት ፋይዳ እንደሌለው ደጋግመን ለማሳየት ሞክረናል።ለዚህ አገላለጻችን በጥሩ አብነት የሚጠቀሰው የሀገራችን ፖለቲካና ተዋናዮች ናቸው።እንዴታው ተደጋግሞ ስለተገለጸ በአጭሩ እናስታውስ፡፡
የ1960ዎቹ የሀገራችን ለውጥ አላሚ ወጣት ፖለቲከኞችን በጥቂት ቃላት እንግለጻቸው ከተባለ “የጥራኝ ጫካው፣ ጥራኝ ዱሩ ናፋቂና አንጎራጓሪዎች” እና “የአስተሳሰብ ግትሮች” ነበሩ ብሎ መደምደሙ “ሃሰት” አያሰኝም፡፡
በአሸባሪነት የተፈረጁት የዛሬዎቹ “የዘመን ጠበኛ” ቡድኖች ተወልደው እትብታቸው የተቀበረው በዚያው በጠቀስነው ዘመን ጫካ ውስጥ እንደነበር የታወቀ ታሪካቸው ነው። ቡድናቸውን ያደራጁትና ያፈረጠሙትም በውይይት፣ በመተማመን፣ በመግባባትና በመቀባበል ሳይሆን እርስ በእርስ ደም እየተቃቡና፣ የተረፉትም እንደ አሜባ እየተበጣጠሱና እርስ በእርስ እየተበላሉ አንዱ አንዱን በመዋጥ ነበር፡፡
ማደሪያቸው ጫካ ነበር ቢባልም እንኳን (ጫካው ምናልባትም የከተማ መሸሸጊያቸውም ሊሆን ይችላል) ከተሸሸጉበት ዱር ይወጡ የነበረው አንድም መንግሥታዊ ተቋማትን ለማውደም አለያም “ጠላት ያሉትን የደመኛቸውን” ሕይወት ለመቅጠፍ እንደነበር ያልመሸበት ታሪካቸው ምስክር ነው፡፡
የእነዚሁ ቡድኖች ቅሬታዎችና የእነርሱ ውላጆች የሆኑት ከግማሽ ክፍለ ዘመን በኋላ ዛሬም ድረስ በቆሙበት እንደተቸከሉ እንጂ ከዘመን ጋር ተለውጠው መቼ አየናቸው? እንኳንስ ርዕዮተ ዓለማቸው በቋንቋ አጠቃቀማቸው እንኳን ሳይቀር አንደበታቸውን ሲገሩ መች ተመለከትናቸው? የኤዲፐስን ዕንቆቅልሽ ደግመን እናስታውስና እነዚህ “የዘመን ኩርፈኞች” የምርኩዝ ዘመናቸውን ነጭ ሽበት እያረከሱ ወደ አራት እግራማነት የዳዴ ዘመን ካልተመለስን ብለው ከዘመንና ከትውልድ ጋር ሲሟገቱ ስለምን ኅሊናቸው እንደማይገስጻቸው አይገባንም።
ዕድሜና የሕይወት ተሞክሮስ እንዴት አይመክራቸውም? “ልጅ ሳለሁ እንደ ልጅ አስብ ነበር፤ ጎልማሳ ስሆን ግን የልጅነት ጠባዬን ሽሬያለሁ” እንዳለው ቅዱስ ጳውሎስ፤ እንደምን ከእውነታ ጋር መታረቅ አቃታቸው? “ድንጋይ አይሞት አሉ” ባዮቹን ሰሜንኞች ደግመን ብናስታውስ አባባሉ በሚገባ ይገልጻቸዋል።
ከአርባ ዓመት በፊት ይቀናቀኑት ከነበረው ሥርዓት ጋር በጠረጴዛ ዙሪያ ተደማምጦና ተደራድሮ መግባባት ስለተሳናቸው በዚያኛውም ወገን ሆነ በእነርሱ በኩል የሆነውን ሁሉ በሚገባ እናስታውሳለን።“ጦርነት ስለማይበጃችሁ ችግራችሁን በሰላምና በድርድር ፍቱ፤ ቆመንለታል ለምትሉት ሕዝብና ሀገር ስትሉም በመካከላችሁ መቀራረብ ተፈጥሮ ተነጋገሩ” በማለት ዛሬም እንደ ትናንቱ ድምጸቱ እንኳን ሳይለይ በርካታ የዓለም መንግሥታት ምክር እየሰጡ ይገኛሉ።እንዴት ኅሊና አለኝ የሚል የግለሰቦች ስብስብ ቆም ብሎ ነገሮችን ግራና ቀኝ በማየት በሰላማዊ መንገድ ለመነጋገር ማሰቢያው ሊደፈን ልቡም ሊደነድን ቻለ?
እንደ ኢትዮጵያ ፖለቲካ ለራሱም ግራ ተጋብቶ ለተቀረው ዓለምም ግራ የሆነ ፖለቲካ ስለ መኖሩ እርግጠኛ መሆን ያዳግታል።ዛሬም እንደ ትናንቱ “ጥራኝ ጫካው፤ ጥራኝ ዱሩ፤ ላንተም ይሻልሃል ብቻ ከማደሩ” እያሉ የሚያቅራሩና “በተመሳሳይ ቅኝት ከበሮ እየደለቁ” ሃምሳ ዓመት ሙሉ በደም ጥማት ሱስ እንዳፋሸኩ ግራ ተጋብተው ግራ ያጋቡ ብጤ “የዘመን ጠበኞች” በሌሎች ሀገራት ይኖሩ ከሆነ የሚያውቁ ቢያሳውቁን አይከፋም፡፡
“ወደ ኋላ ሄደህ በሃሳብ ከማለም
ቀኑ እንዳይመሽብህ ትናንት ዛሬ አይደለም፡፡”
እንዲሉ፤ “ገዳይ ደሞ” ዜማን እያቀነቀኑ ንጹሐንን በመፍጀትና ንብረት እያወደሙ ወደ ሥልጣን ለመምጣት መቃዠት የማያዋጣ ብቻም ሳይሆን እብደትም ጭምር መሆኑን እነ አልሰሜ ቢሰሙ ይበጃቸዋል፡፡
የዛሬይቱ ኢትዮጵያ እንደ ትናንትናው በመሪዎቿ ግትርነት “የፈለገው ዋጋ ይከፈላል እንጂ ወሳኙ ሻምላዬ ነው” ብላ ለመፋለም ፍላጎቱም ሆነ እምነቱ በጭራሽ የላትም።ሰላማዊ ጥሪዋ “ኑና እንዋቀስ” የሚል ነው።መልእክቱ እየተስተጋባ ያለው ደግሞ ሀገራዊ የምክክሩን ወንበር እያበጃጀ ባለው “ብሔራዊ ኮሚሽን” አማካይነት ነው፡፡
ባረጀና ባፈጀ “የተባይ መፈልፈያ” የርእዮተ ዓለም ካፖርት ራሳቸውን የጀቦኑ ተቸካዮችም ሆኑ “ጫካ ውስጥ መሽገው” የንጹሐንን ደም ለማፍሰስ ሰይጣን የተጠናወታቸው “ዘመን አምካኝ” ቡድኖች ወደ ቀልባቸውና ወደ ኅሊናቸው ተመልሰው እንደ ሰብዓዊ ፍጡር “ከእብሪት እንቅልፋቸው ባንነው” ወደ ሰላም ቢመለሱ ይበጃቸዋል።
“ይሄን ያህል ሞተ! ይሄን ያህል ተደመሰሰ!” ቢቸግርና ግድ ቢሆን እንጂ “ሰላምን የሚተካ” ግብ ሊሆን በፍጹም አይችልም።ዘመን የሚዋጀው በዘመነኛው ትውልድ እንጂ፤ ዘመን ከዘመን ተስማምቶ ለመቀባበል ባህርይው አይፈቅድም።ስለዚህ እያንዳንዱ ማለዳ የአዲስ ዘመን መባቻ እንጂ የአሮጌ አስተሳሰብ ኮሮጆ ስላልሆነ “እነ ዘረፌዋ” ወደ ኅሊናቸው ተመልሰው ለሰላም ቢዘምሩ ይሻላቸዋል።ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ነሐሴ 11 /2014