በእድሜ ገደብ የሚካሄዱ ውድድሮች አትሌቶችን ወደ ስኬታማነት የሚያረማምዱ ድልድዮች መሆናቸው ይታመናል። ለኢትዮጵያዊያን የአሮጌው ዓመት መባቻ እና የአዲሱ ዓመት ስጦታ የሆነው ከ20ዓመት በታች አትሌቲክስ ቻምፒዮና በእርግጥም የወጣት አትሌቶችን ብሩህ ነገ የሚያመላክት ነው።
በጥቂት ርቀቶች ተሳትፎ በማጠቃለያው ዕለት ብቻ የተሰበሰቡት 4 ሜዳሊያዎች ዓለምን ሲያስደምሙ፤ ከ19ኙ አትሌቶች 18ቱ ሜዳሊያና ዲፕሎማ ለሃገራቸው ማበርከታቸው ደግሞ የቡድኑን ጥንካሬ ያረጋገጠ ሆኗል።
ታሪክ ሰሪው ቡድን ወደሃገሩ ሲመለስም ከዚህ ቀደም ያልታየ አቀባበልና ማበረታቻ ተደርጎለታል። ይህም ወጣቶቹን አትሌቶች ተተኪና ቀጣይ ሃገራቸውን ተረካቢ እንዲሆኑ ምክንያት እንደሚሆን አመላካች ነው። ታሪካዊና በየትኛውም ውድድር ያልታየውን በርካታ የወርቅ ሜዳሊያ ካስመዘገበው ከዚህ ቡድን በርካታው ስኬት የተመዘገበው ደግሞ በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ፍሬዎች መሆኑም ሌላው አስደናቂ ጉዳይ ነው።
አሰልጣኝ አብዮት ተስፋዬ፤ በ800 እና 1ሺ500 ሜትር የወርቅ እና የብር ሜዳሊያዎችን በማጥለቅ የወደፊት ተስፋውን ያንጸባረቀው አትሌት ኤርሚያስ ግርማ አሰልጣኝ ነው። አትሌቱ በኦሪጎኑ የዓለም ቻምፒዮናም በ800 ሜትር ተሳታፊ መሆኑ አይዘነጋም። በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ አሰልጣኝና የተሳትፎና ውድድር ዳሬክተሩ አብዮት፤ እንደ ቡድን ከውድድሩ አስቀድሞ ጠንካራ ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱ ለውጤት እንዳበቃቸው ይናገራል። እርሱ የሚያሰለጥነው አትሌት ኤርሚያስ አካዳሚውን ከ2010 ዓም ጀምሮ የተቀላቀለ ሲሆን፤ አሁን ላይ ሃገሩን ከማስጠራት ባለፈ በ800 ሜትር በዓለም ፈጣን ከሚባሉ አትሌቶች መካከል አንዱ የሚያደርገውን ሰዓት አስመዝግቧል።
በመሆኑም መሰል ውድድሮች ታዳጊና ወጣት አትሌቶችን ወደተሻለ ብቃት የሚመራቸው በመሆኑ ሊበረታታ እንደሚገባ አሰልጣኙ ይጠቁማል። እርሱ በሚያሰለጥንበት አካዳሚም ቀጣይነት ያለው ተተኪ አትሌቶችን ማፍራት ላይ አተኩሮ እየሰራ ይገኛል። ለዚህም ማሳያ የሚሆነው በዚህ ውድድር ላይ ተሳታፊ ከነበሩት አትሌቶች መካከል በአካዳሚው እንዲሁም በጥሩነሽ ዲባባ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል ሰልጣኞች 4 ወርቅ እና 2 ብር ሜዳሊያዎች መቆጠራቸውን ነው። ይኸውም በአትሌት አዲሱ ይሁኔ፣ መልኬነህ አዘዘ፣ ሳሙኤል ድጉና፣ ሳሙኤል ፍሬው፣ ድሪባ ግርማ፣ መብሪት መኮንን የተገኙ ናቸው። በመሆኑም አካዳሚው የውድድር ተሳትፎ ላይ ብቻም ሳይሆን ውጤታማነት ላይም እየሰራ እንደሚገኝ አመላካች መሆኑን ያረጋግጣል።
ከአካዳሚው የተገኙት የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት የሆኑ አቴሌቶችም ለዚህ ስኬት ያበቃቸውና በቀጣይም ሃገራቸውንና ህዝባቸውን ለማኩራት ያላቸውን ዕቅድ ለአዲስ ዘመን እንደሚከተለው ገልጸዋል። በ5ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ማጥለቅ የቻለው አትሌት አዲሱ ይሁኔ፤ በውድድሩ አሸናፊ ለመሆን አቅዶ ወደ ካሊ ማቅናቱን ያስታውሳል። በኦሪጎን በተካሄደው የዓለም ቻምፒዮና ኢትዮጵያ ያስመዘገበችው ውጤት ለተወዳዳሪዎች የሞራል ስንቅ ሲሆን፤ ተነሳሽነትን አሳድሮባቸዋል። አትሌቶች ከአሰልጣኞች እንዲሁም ከሌሎች የቡድን አባላት ጋር የነበራቸው ግንኙነትም መልካም መሆኑ አስተዋጽኦ ነበረው። እርሱና ጓደኞቹ የወደፊት ተተኪ አትሌት እንደመሆናቸው በቀጣይም ጠንክረው እንደሚሰሩም አትሌቱ ይጠቁማል።
ሌላኛው የ 3ሺ ሜትር ሜዳሊያ ባለቤት መሆን የቻለው አትሌት መልኬነህ አዘዘ፤ ባለፈው ዓመት ኬንያ ላይ በተካሄደው ቻምፒዮና በ1ሺ500 ሜትር የነሃስ ሜዳሊያ ነበር ያስመዘገበው። ክረምቱ አስቸጋሪ ቢያደርገውም ሲያደርጉ የቆዩት ዝግጅት ለውጤት የሚያበቃ እንደሆነ ይገልጻል። በውድድር ወቅትም ከአሰልጣኞች ጋር በመመካከር መሳተፋቸው በርካታና ታሪካዊ ሜዳሊያ እንዲገኝ ምክንያት ሆኗል። በቀጣይም በዓለም ቻምፒዮና እንዲሁም በኦሊምፒክ መድረኮች ተሳትፎ ሜዳሊያ የማስመዝገብ እቅድም አለው።
የ1ሺ500 ሜትር አሸናፊዋና የርቀቱን ክረወሰን የሰበረችው አትሌት ብርቄ ሃየሎም በተመሳሳይ ያደረገችው ዝግጅት ለአሸናፊነት እንዳበቃት ገልጻለች። ከዚህ በኋላ እንደ ኦሊምፒክ ባሉ ትልልቅ ውድድሮች ላይ ተሳትፋ ለሃገሯ የወርቅ ሜዳሊያ የማስመዝገብ ተስፋም ሰንቃለች።
ከዚህ ቻምፒዮና በመነሳት ሃገሯን በተለያዩ ውድድሮች ላይ ካስጠሩት አንጋፋ አትሌቶች መካከል አንዷ መሰለች መልካሙ ናት። አትሌቷ በቡድን መሪነት ወደ ኮሎምቢያ የተጓዘች ሲሆን፤ በካሊ የነበረው የአየር ሁኔታ ከኢትዮጵያ ጋር የሚመሳሰል መሆኑ አትሌቶች ብዙም ሳይቸገሩ አሸናፊ እንዲሆኑ እገዛ እንዳደረገላቸው ገልጻለች። ቡድኑ ወደ ሃገሩ ሲመለስም ከዚህ ቀደም ከነበረው የደመቀ አቀባበል የተደረገለት መሆኑ አበረታች ነው። ወደፊት ተተኪ የሚሆኑ አትሌቶችን በዚህ መልክ መደገፍ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁማለች።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 10 /2014