በድርሰት ስሌት የሰዎችን አመለካከት የተጋነነ ወይም የተዛባ አመለካከት አያደርጉትም :: የሚቀርቡት ፅንሰ ሀሳቦች አንድ ዓይነት ጽንሰ-ሀሳብ ቢመስሉም በውስጣቸው ግን ቅርፅ እና ቀለማቸው ሥዕላዊ መግለጫዎች ሆነው የራሳቸው ትኩረት አግኝተው “የነጥብ ርዕስ” ይሆናሉ:: እንዲህ አይነት አፃፃፎች አብዛኛውን ጊዜ የራሳቸው የሆነ ቅንጡ ትርጉም ያላቸው ሰፊ ርዕሶችን የሚዳስሱ የአዕምሮ ስነ-ጥበብ ናቸው::
የስነ-ጥበብ አፈጣጠር ጌጣጌጦች የደራሲውን የአዕምሮ ደረጃ አካላዊ ብቃት ጭምር መግለጫዎችም ናቸው። ስለዚህ የእኔም “የነጥብ ርዕስ” ደራሲ ሔኖክ ስዩም የፈጠራ ስራዎች ውስጥ ከተካተቱ እምቅ ሐሳቦች ውስጥ አንድ ሁለቱን ብቻ ከመፅሀፉ አካል መርጬ መመልከቱ ጠቃሚ ነው ብየ ስለወደድኩ፤ የካቲት ልጆች ለአድዋ ሰዎች የተፃፈችው መልዕት ነፍሴ ገዝታዋለችና የምለውን ልበል።
ከዚያ በፊት ስለደራሲው ትንሽ መስመሮች ማለት እፈልጋለሁ። ይህ የተጏዡ ጋዜጠኛ የሔኖክ ስዩም “ወደ ኢትዮጵያ ሰዎች” የሚለው ትውልድ ጠያቂ ታሪካዊ መፅሀፍ በቃላት እና በቋንቋ አጠቃቀም ላይ ብቻ የተመሠረተ ሳይሆን የአካዳሚክ ርዕሰ-ጉዳይን ባሕልንና ሐገራዊ አብሮነትን ታሪክን የሚዳስስ ዥረት ነው:: ደራሲው ሀሳቡን፣ ስሜቱን፣ ልምዱን ወይንም ታሪኩን ባልተለመደ ወይም በባህላዊ መንገድ ለመግለፅ ጎላ አድርጎ የመፅሀፉን ውበት እንዲጠብቅ በማሰብ ልዩ የቋንቋ ችሎታውን ተጠቅሟል።
ወርቃማውን ዘመን የኖሩትን አባቶታችንን የኖሩበትን ጊዜ እና ቦታ መርጦ ዘመንን ተሻግረን በአይነ ሕሊናችን አድዋ ላይ እሳት በሚተፉት መትረየሶች፣ አንገት የሚቀሉ ሰይፍና ጎራዴ ከታጠቁ ጀግኖች ጋር ያጨባብጠናል። ስለዚህ ትውልዱን በማነቃቃትና ወደማይታሰቡ ቦታዎችና ዘመናት ወደዃላ ጨልፎ ከወራት የካቲትን መርጦ ብራናውን ይገልጥልናል። ደራሲው የመረጠው ርዕስ ህይወትን የሚያረጋጋ ሲሆን፤ መጽሐፉ ደግሞ ታአምራትን እየሰራ እንደመጣ ጀግና ትውልድን ይጠይቃል። ደራሲው በምሬትና በቁጭት የሚገልፃቸው እውነተኛ ታሪኮች ሕይወት ያላቸው ቋሚ ምስክሮች ሆነው ነቃሽ እየቆጠረ ሲተርካቸው ቁጭቱ አጥንት ድረስ ዘልቆ ይሰማል::
አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታዎች ያህል የሚያስደነግጡ የትውልድ ስህተቶችን ነቅሶ በብዕር ይፋለማቸዋል:: በብዕር ፍትህ ይጠይቅባቸዋል:: በብዕር ዳኝነት ይሰጥባቸዋል። ደራሲው ሔኖክ ስዩም በመሬት ስበት እና በውቅያኖስ ማዕበል ላይ ለውጥ ያስከተለ እስከሚመስል ድረስ ትውልዱ በሀይለኛ የዘረኝነት ሱናሚ እየተመታ ባለበት በዚህ ክፉ ጊዜ የምፅዓት ቀን ከመምጣቱ በፊት መከላከያ የሚሆናቸውን ኢትዮጵያኒዝም ጃኖ እንዲያጠልቁ ይህንን “ወደ ኢትዮጵያ ሰዎች” የተሰኜ መፅሀፍን አበርክቶልናል።
ደራሲው መፅሀፉን የጀግኖችን ሥነ-ልቦና፣ የፍቅር የጓደኝነት እና አገራዊ የተስፋ ታሪክን እንዲያሳይ አድርጎ ከትቦታል። ተገዡ ጋዜጠኛ ሔኖክ ስዩም በድርሰት ችሎታው በሐገራችን ቀደም ሲል ከነበሩት በጣም ምርጥ ታዋቂ ጸሐፊዎች መካከል እንደነ በአሉ ግርማ፤ እንደ ብርሀኑ ዘሪሁን፣ እንደ ተክለ ፃድቅ መኩሪያ፣ እንደ ሀዲስ አለማየሁ፣ እንደ ጳውሎስ ኞኞ፣ እንደ ፀጋዬ ገብረመድህን፣ እንደ ስብሀት ገ/ እግዚአብሔር፣ እንደ ማሞ ውድነህ የመሳሰሉ አሻራቸውን ትተው ካለፉት፤ አሁንም በህይወት ካሉት እንደ አለማየሁ ገላጋይ፣ አዳም ረታ፣ እንዳለ ጌታ ከበደ፣ ወዘተ ከመሳሰሉ ዝነኛ የኢትዮጵያ ክላሲክ የሆኑ ፀሀፊዎች እግር ከእግር እየተከተለ የሚጓዝ ብቃት ያለው ወጣት ደራሲ ሲሆን፤ አንድ ቀን ከነዚህ ታላላቅ ደራሲዎች ተርታ ስሙን በወርቅ ቀለም እንደሚያፅፍ እርግጠኛ ነኝ።
ቀደም ባሉት ጊዜያት የተጓዡ ጋዜጠኛ ሔኖክ. ስዩምን ሁለቱን፣ መፃህፍቶችን አንብቢያለሁ:: ይህኛው ሶስተኛየ መሆኑ ነው። የደራሲው ብዕር የሰውን ነፍስ ሥነ-ልቦና በዘዴ የሚያሳዩ እፁብ ድንቅ ሥራዎች በመሆናቸው የተዋጣላቸው የመንፈስ ምግቦች ናቸው:: በተለይ ሶስተኛው የተጓዡ ጋዜጠኛ መፅሀፍ “ወደ ኢትዮጵያ ሠዎች” በአርበኝነት ጦርነት ወቅት ስለ ኢትዮጵያ ክቡር ሕይወታቸውን ሲገብሩ የኖሩትን የአድዋ ትውልዶች ይዘክራል።
“ሰው ወድቆ ሐገር ቆሟል:: በዚያ ጀግና አፈር በልቶ የሐገር ክብር አፈርን አራግፎ ህያው ሆኖል”:: የወደቁት በወደቁበት አልቀሩም:: ስማችንና ዘመናችንን ይዘው ተነሱ:: ሞት ለጀግኖች ሲሆን ትንሳኤው ግን ለኛ ሆነ፤” በማለት መፅሀፉ መጠነ ሰፊ ሥራውን በብዙ የታሪክ መስመሮችን አካቶ ይዟል::
በመፃፉ ውስጥ የሚያነሳቸው የአድዋ ጀግኖች ታሪካቸው ነፍስ ዘርቶ ህያው ገድል ሲሰሩ ጥቁሩን የሱናሜ ንጉስ እምዬ ምኒልክ እና ብርሀን ዘኢትዮጵያ እቴጌ ጣይቱ ብጡልን ጠቅሶ የውጊያ ትዕይንቶቻቸውን በምናብ ያሳየናል። የዛሬዋ ኢትዮጵያ እንዴት እንደቆሞች የሙታን አፅም(በጀግንነት የወደቁትን) አነጋግሮ አፈር የማያበላሸውን ታሪካቸውን አገላብጦ ትውልድን እየጠየቀ ታሪኩን ይዘክራል::
በዚህም “ሰው ተከፍሎ ለሰው ሀገር በማኖሩ አህጉር ያስመካ ድል እውን ሆኖ በዚያ ድል አንዲት ሐገር ብቻ ሳትሆን ፍትህ የሚጋሯት ሁሉ ቀና ብለዋል::” ይልና፤ በታላቅ ንጉስ መሪነት የጥቁር ድል በጥቁር ሕዝቦች ተፃፈ፤ የካቲትም ብራናው ሆነች፤ ኢትዮጵያዊነትም ቀለም ሆነ፤” በማለት ህያው ምስክርነት ይሰጣል። በተለይ “ጥቃት”ን ሐገራዊ ፋይዳ በመስጠት ሂደት ውስጥ በሰዎች እና በአካባቢ ላይ ሊደርስ የሚችልን ጉዳት እንዳይደርስ መከላከል ስለመሆኑ በማንሳት፤ የዘር ፖለቲካ እንደምስጥ አንክቶ በበላው ቂላ ቂል ከንቱ ትውልድ ውስጥ ደራሲው ቁጭቱን እንኳን የሚገልፅበት አቅም ሲያጣ ይስተዋላል።
“ከአድዋ ጀግኖች አልተማርንም:: ለየ ብቻችን ቆመን ግን ተሸነፍን!:: ለየብቻ ቆመን የታገልንባቸው አውደ ውጊያዎች ኪሳራ እንጅ ክብር አልነበራቸውም። አድዋ ግን እንደ ዜጋ አልተገለለም:: ንጉሰነገስቱ ሁሉን ጠሩ:: ሁሉም ባለቤት ነበረ:: ሁሉም ባለቤት ሲሆን ድል አለ። አድዋ የባለቤትነት ውጤት ነው፤” ይለናል። በአሁኑ ኑባሬያችን እየተቆጨም፤ አሁን ግን ተባብረን ማድረግ የምንችለውን ሳናደርግ እንደ ሐገር ተያይዘን ወድቀን ተያይዘን መነሳት አቅቶን እርስበእርስ ስንገዳደል የአይን ምስክር ሆኖ ለትውልዱ አቤት ይላል::
የአድዋ ልጆች የአለም መሳቂያ ለማኞች ሆነናል:: በቁጭት ስሜት ብቻ ተስፋ ቆርጠን ከዛሬ ይልቅ ነገም የተሻለ ቀን እንዳለ ማሰብ ስለአቃተን በዘርና በቋንቋ ኮሮጆ ውስጥ ተደብቀን መሰማማት አቃተን። ከወደቅንበት እጅ ለእጅ ተያይዞ መነሳትና አንድ ሆነን መቆም አቃተን። … እያለ በመዘርዘር ደራሲው በአድዋ መንፈስ ይቀናል። ይሄንንም ሲያብራራ “እኔ አድዋን ባሰብኩ ጊዜ ነፍስም አይቀርልኝ:: “ስለምን” ብትሉ፤ እቀናለሁ:: በመንፈሳችንም እቀናለሁ። ልትቀኑ የሚገባው ለሐገር በተከፈለ ተግባር ነው። የአድዋ መንፈስ ያስቀናል። አድዋ ለዘላለም ተቆፍሮ የሚወጣ ነዳጃችን ነው:: ዘላለም ተነግሮ የማይጠገብ፤… እያለ ይቀጥላል።
በየካቲት እውን የሆነችው ድል የአንድ ግንባር ጦርነት ፍፃሜ ብቻ ሳትሆን ዘመን ድንበር የማያበጅላት የነፃነት ዘለአለም ናት። ምክንያቱም በዚያ ዘመን እውነት ሀሰትን አሸንፋለች፤ በዚያ ሰው ወድቆ ሐገር ቆሟል፤ በዚያ ጀግና አፈር በልቶ የሐገር ክብር አፈሩን አራግፎ ህያው ሆኗል:: እናም ደራሲው ይህንን ሁሉ ቁጭቱን ሲናገር እንዲህ ይላል፡- እናንተ የሐገሬ ሰዎች… ይህንን ድምፅ እንደ አንድ የራሴን ልጩህ ብሎ እንደወጣ ድምፅ ቁጠሩት፤ በምድረበዳ ሳይሆን በመካከላችሁ እንዳለ ድምፅ ጆሮ ስጡት፤” በማለት ለትውልዱ እየቃተተ መፅሀፉ ላይ በ ፊደል ታግዞ ምሬቱን ያስተጋባል።
እኔም እላችዃለሁ እናንተ የሐገሬ ልጆች ምናልባት ይህንን መፅሀፍ ስታነቡ የደራሲውን ጩኸት በትክክል ልትረዱት ትችላላችሁ፤ ለእኔ አይነቱ በሰው ሐገር በሰው ታሪክ መንፈሱ ለሚረበሽ ትውልድ ግን ደራሲው ከሕይወት እድሜው ቆንጥሮ እንደለገሰን አድርጌ እቆጥረዋለሁ::
ከዚህም ባለፈ፣ ሔኖክ ስዩም “ወደ ኢትዮጵያ ሰዎች” በሚለው መፅሐፉ አዲሱንም ሆነ ቀጣዩ ትውልድ በማይነጥፍ ጥበብ እንደገና ምርኩዝ ሆኖ መርቷልና ኮምፓስ ሆኖ አቅጣጫ አሳይቶናልና ምስጋናዬ ባለህበት ይድረስልኝ። ለዛሬው በዚሁ አበቃሁ በሌላ ዝግጅት እስክንገናኝ ቸር ይግጠመን።
ከአለባቸው ደሳለኝ አበሻ (ለንደን)
አዲስ ዘመን ነሐሴ 10 /2014