ትምህርት የዜጎችን ሁለንተናዊ አቅም የመለወጥ አቅም አለው:: ይህ የሚሆነው ግን በአግባቡ ከተሰጠና ቅቡልነቱ ከተረጋገጠ ነው:: እናም ይህንን ለማረጋገጥ እንደአገር ብዙ ተግባራት መከወን እንዳለባችው እሙን ነው:: አንዱና ዋነኛው ግን ብቃት የተላበሰ ተማሪ ከማንኛውም ተቋም ውስጥ ማውጣት ነው:: በተለይም ዩኒቨርሲቲ ላይ ብቃት ያለውን ተማሪ ማውጣት ካልተቻለ በብቃት የሚሰራ ባለሙያ በሁሉም ዘርፍ ለማግኘት ይቸግራል::
በብዙዎች ዘንድ አሁን ላይ እየታየ ያለውም ይኸው ነው:: ችግሩ በዋነኝኘት በትምህርት ዘርፉ ውስጥ ያሉ አካላት ላይ ማነጣጠሩ አይቀሬ ነው:: ነገም ቢሆን ከታች ጀምሮ በጥራቱና ብቃት ላይ ያለው ክፍተት ካልተደፈነ ጣት መጠቋቆሙ መቀጠሉ የሚቀር አይሆንም:: እናም ለዚህ መፍትሄ ያሸዋልና እንደአገር እቅድ ተይዞላቸው የተለያዩ ተግባራት መከናወን ጀምረዋል:: ከእነዚህ ተግባራት አንዱ ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ ይተገበራል የተባለለት የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና ነው:: ለመሆኑ ይህ ፈተና መሰጠቱ ምን አይነት እድሎችን ይዞ ይመጣል ስንል የተለያዩ የዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ ኃላፊዎችን አነጋግረናል::
በመጀመሪያ ሃሳባቸውን ያጋሩን የአምቦ ዩኒቨርሲቲ የአስተማሪዎችና የተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ሰለሞን አለሙ ሲሆኑ፤ መውጫ ፈተና በርካታ መልካም ጎኖች እንዳሉት ይናገራሉ:: አንዱ ተማሪዎች በትምህርታቸው ላይ እንዲያተኩሩና ተግተው እንዲማሩ የሚያደርግ ስርዓት መሆኑ ነው:: በተማሪዎች መካከል ያለን የመወዳደር ስሜት የመጨመሪያ መንገድም ነው:: ምክንያቱም የመውጫ ፈተናውን ካላለፉ ሥራ ጭምር ማግኘት እንደማይችሉ ያውቃሉና ቀድመው እንዲዘጋጁ፤ ከጓደኞቻቸው በበለጠ ጠንክረው እንዲያጠኑና የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ያስችላቸዋል::
የጥራት ጉዳይ ተመርቆ ከወጣና ሥራ ላይ ከገባ በኋላ ጭምር የሚታይ ሆኗል:: እናም የመውጪያ ፈተናው ይህንን ከመቀነስ አኳያ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል:: ምክንያቱም ተማሪዎች መውጪያ ፈተናውን ሲያስቡ ከክፍል ፈተናው ባለፈ አገራዊ ፈተናውን አስበው በቂ እውቀት ለመጨመጥ እንዲጥሩ ይሆናሉ:: ተወዳድረው ለመመረጥ ደግሞ አንዱ መስፈርት የሚሆንበት አጋጣሚ ይኖራልና ይህንን እውን ለማድረግም ትጉ እንዲሆኑም ያስችላቸዋል:: ከዚህ ትይዩ ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡትንም ሆነ ለመመረቅ የተቃረቡትን ከገቡበት ዓመት ጀምሮ እስከሚመረቁበት ዓመት ድረስ ያለውን ጊዜ በአግባቡ እንዲጠቀሙና በቂ እውቀት ጨብጠው እንዲወጡ ከማስቻሉም አኳያ የማይተካ ሚና እንደሚኖረው ይናገራሉ::
ዩኒቨርሲቲዎች ዓለም አቀፍ ውድድሩን ለመሸከም የሚያስችል ዕውቀት ማፍሪያ ማዕከል እንዲሆኑም እድል የሚሰጥ ነው የሚሉት ዶክተር ሰለሞን፤ ከትምህርት ጥራቱ ይልቅ ቁጥሩ የሰፋበትን አጋጣሚም ለማመጣጠን ይህ እድል ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል:: በተመሳሳይ ዩኒቨርሲቲዎች ጥሩ ዕውቀት ያላቸው ተማሪዎች ማፍራት ብቻ ሳይሆን ጥሩ ዜጎችም የሚገኙበት ተቋም እንዲሆን ያስችላል:: ከዚያም ሻገር ሲል ተማሪዎች በመጨረሻ ፈተና እንደሚወስዱ አውቀው ቀድመው በአካል፣ በስነ-አዕምሮና በስነ- ልቦና በመዘጋጀት ጠንክረው እንዲሰሩ እንደሚያደርጋቸውም ያነሳሉ::
የመውጪያ ፈተና ከአምስት በመቶ በላይ መድገም የለባቸውም የሚለውን የዩኒቨርሲቲዎች አሰራርም የሚያስቆም ነው:: ብቃት ከሌላቸው መመረቅ እንዳይችሉ ያደርጋል:: የዚህን ጊዜ በመውጫው ፈተና የማሳለፍ ምጣኔ መሰረት በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በትምህርት ክፍልና በመምህር ጭምር ተጠያቂነት እንዲኖርና የመወዳደር ስሜት እንዲፈጠር እድል እንደሚሰጥም ይናገራሉ::
አሰራሩ ከዚህ ቀደም በህግ እና ጤና ትምህርት ክፍል እንደነበር የሚጠቅሱት ዶክተር ሰለሞን፤ አሁን ልዩነቱ ሁሉም ላይ መሆኑ ነው:: ጥራቱ ላይ በሁለቱ የትምህርት መስኮች የታየውንም ይደግመዋል እንጂ ተማሪው ላይ የሚፈጥረው አሉታዊ ተጽዕኖ አይኖርም:: ስለሆነም ተማሪዎች እኛ ላይ ችግር ለመፍጠር አስበው ነው በሚል ሳይጨናነቁ ትምህርታቸው ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ያሳስባሉ:: ለዚህ ደግሞ ዩኒቨርሲቲያቸው ከወዲሁ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል::
እንደ አገር ፈተናው የሚሰጥ ከሆነ አንዳንድ ክፍተቶች ሊኖሩ ይችላሉ:: ምክንያቱም በተማሪዎችና በዩኒቨርሲቲዎች መካከል እንደ ትውልድ(ጀነሬሽን) ልዩነቶች ተፈጥረዋል:: ለምሳሌ፡- ዩኒቨርሲቲ ሲገቡ ከፍተኛ ውጤት ያመጡት የመጀመሪያ ምርጫቸው ይከበርላቸዋል:: በዚህም የመጀመሪያ ትውልድ (ጀነሬሽን) የሚባሉት አቅም ያላቸውን ተማሪዎች የመሰብሰብ አጋጣሚ ይፈጠርላቸዋል:: እናም ሌሎቹ እንደአምቦ ዩኒቨርሲቲ የመሳሰሉት ላይ ይገባሉ:: ይህ ደግሞ የተማሪዎች የብቃት ልዩነት እንዲኖር ያደርጋል:: በተጨማሪም በግብዓት አቅርቦት እኩል ሊወዳደሩ አይችሉም:: ስለሆነም ቀጣዮቹ እየተስተካከሉ ሊመጡ እንደሚችሉ አመላካች ነገሮች በመኖራቸው የአሁኑ ላይ ግን ብዙ ጥንቃቄ እንደሚፈልግ ይናገራሉ::
የደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ክንዴ ገበየሁ እንደሚያምኑበት በትውልድ(ጀነሬሽን)መካከል የሚመጣ ልዩነት መኖሩ አይካድም:: ይሁን እንጂ የመውጪያው ፈተና ሙያ ተኮር በመሆኑ ያንን ማለፍ ካልቻሉ የትውልዱ ልዩነት ነው ልንል የምንችልበት ሁኔታ አይኖርም:: ተማሪዎቹ ባለሙያ ሆነው አገራቸውን በሚጠቅሙበት ልክ መውጣት አለባቸው:: ምክንያቱም ሲወጡ የእንትና ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሳይሆን የሚባሉት በዚህ ሙያ የተመረቀ ተማሪ ነው:: እናም በሁሉም የአገሪቱ ክፍል እንደሚመደቡ ይታወቃልና ለሙያው ብቃት ያላቸው ተማሪ መሆን ግዴታቸው ነው:: ለሥራ ብቁ ሳይሆኑ ማስመረቅ ደግሞ አደጋው ምን ያህል እንደሆነ እንደሀገር ተመልክተነዋል ይላሉ:: ስለሆነም ይህንን አስቦ መሥራት እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ::
የመውጫ ፈተናው ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ ብቸኛ ባይሆንም ወሳኝ ጉዳይ እንደሆነ የምንገነዘበው ተማሪዎቻችን ብሔራዊ ፈተናውን ተፈትነው ሲያልፉ ነው:: ይህንን ደግሞ ዩኒቨርሲቲያችን ከዚህ ቀደም ያገኛቸው ነገሮች አሉትና ያንን እናስቀጥላለን የሚሉት ዶክተር ክንዴ፤ በጤናው ዘርፍ እስካሁን ያስመረቅናቸው ተማሪዎች በስነምግባርም ሆነ በብቃት የተሻሉ ለመሆናቸው መንስኤው ብሔራዊ ፈተና ወስደው በብቃት በማለፋቸው ነው:: አሁንም የመውጪያ ፈተና እንዳለባቸው አውቀው በቂ እውቀት ለመጨበጥ እየተጉ ይገኛሉ:: በተለይም እንደዩኒቨርሲቲ ብቃታቸውን ለመለካት ተደጋጋሚ ፈተናዎችን ያለማመድን በመሆኑ አሁን በተሞክሮ እንድንጓዝም ያደርገናል::
በሁሉም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ መውጫ ፈተና መጀመሩ እንዳስደሰታቸው ያነሳሉ:: በሌሎች ብቃት ያላቸውን ባለሙያዎች ለማፍራት ጥሩ አጋጣሚ እንደሆነም ያስረዳሉ::
እንደመጀመሪያ ብዙ ነገሮች ፈተና እንደሚሆኑ ያልካዱት ዶክተር ክንዴ፤ ቀጣዮቹን ብሩህ ተስፋ ለማየት ይህ እድል አስፈላጊ ነው:: ስህተታችን ምን ላይ እንደሆነ እንድናይም ያደርገናል:: በተመሳሳይ አብዝቶ መትጋትን ለዩኒቨርሲቲዎች፤ ለተማሪዎችና ለመምህራኑ የሚያስተምር ነውና ጥሩና ቀጣይነት ያለውን ስርዓት ለመፍጠርም ያስችላልና ሁሉም አወንታዊ ጎኑን በማየት መስራት እንዳለበት ይጠቁማሉ::
አገራዊ ውድድር ሲታሰብ የበለጠ መትጋት ግድ እንደሆነ የሚያነሱት ዶክተር ክንዴ፤ የምናስመርቃቸው ተማሪዎችን ልዩ ትኩረት እንድናደርግባቸው ያስችለናል:: አገራችንን አስበንም እንድንንቀሳቀስ ያደርገናል:: ምክንያቱም አስመርቀን ለአገራችን የምናበረክታቸው ተማሪዎች ብቁ ባለሙያ እንዲሆኑ ማስቻል አለብንና ነው:: ከአገር አልፎ አለም ላይ የሚወዳደርና የአገሩን ስም ከፍ የሚያደርግ ትውልድ እንድንፈጥርም ይህ የመውጪያ ፈተና ትልቅ አቅም ይኖረዋልም ብለዋል::
እንደ ዶክተር ክንዴ ገለጻ፤ የመውጪያ ፈተና ሲታሰብ ኮርጆና በሌላ ላይ ተንጠልጥሎ ማለፍንም የሚያስቀር ነው:: ምክንያቱም ነገ ብቻውን የሚፈተንበት አገራዊ ፈተና እንዳለ ያስረዳዋል:: ስለዚህም ትምህርቱን በአግባቡ መከታተል ብቻ ሳይሆን በቂ እውቀት ለመጨበጥ ይጥራል:: ይህ ደግሞ መንግስትን ጠባቂ ከማድረግም ይታደጋል:: ተቀጥሬ የሚለውን ስሜትም ያጠፋል:: ምክንያቱም በጨበጠው እውቀት የራሱን የሥራ እድል በራሱ ለመፍጠር ይሞክራል:: እናም አገርን ከፍ የሚያደርጉ በራሳቸው ጭምር የሚሰሩ ባለሙያዎችን ከማፍራት አንጻር መውጫ ፈተናው ትልቅ አቅም ይኖረዋል::
የአፈጻጸም ችግሮች ካልገጠሙ በስተቀር የመውጪያ ፈተናው ከምንም በላይ ለተማሪዎች የሚጠቅምበት ሁኔታ በራስ የመተማመን አቅም እንዲኖራቸው ማድረጉ ነው:: ገና እየተማረ ባለበት ሁኔታ ለወደፊት ህይወቱ ቀድሞ እንዲዘጋጅ፤ ተወዳዳሪ እሆናለሁ የሚል ወኔ ውስጥ እንዲገባና በየትኛውም ደረጃና አካባቢ ቢመደብ ፈተና እንደማይጥለው እንዲያስብ ያደርገዋል:: አለፍ ሲልም ፍላጎቱን መሰረት ያደረጉ ሥራዎችን እንዲመርጥና እንዲሰራ ይሆናል:: ይህንን ሲያደርግ ደግሞ በአገራዊ ስሜትና በደስታ ሁኔታዎችን እንዲፈጽም እድል ይፈጥርለታልም ይላሉ::
የዶክተር ክንዴን ሀሳብ የሚደግፉት የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዳምጠው ዳንሳ በበኩላቸው እንዳሉት፤ የመውጪያ ፈተና በእኛ አገር ብቻ ሳይሆን በሌሎች አገራት ጭምር የሚደረግና ውጤት ያመጣ ሥራ ነው:: እኛ ጋርም በተለያዩ መስኮች ሲደረግ ውጤቱ ምን እንደሚመስል ታይቷል:: አሁን በሁሉም የትምህርት መስኮች መደረጉ ደግሞ የትምህርት ጥራቱን ከማረጋገጥ አኳያ ብቸኛ ባይሆንም ትልቅ መፍትሄ የሚያጎናጽፍ ነው::
የመውጪያ ፈተናው እንደ አገር ሁለት አይነት ውድድሮችን እንድናጎላቸው ያደርገናል:: የመጀመሪያው ከአቻ ጋር የሚደረግ ውድድር ሲሆን፤ ተማሪዎች በሚመረቁበት ሙያ የሚያደርጉት ፍልሚያን ያሳየናል:: ዩኒቨርሲቲዎችም እንዲሁ:: ይህ ደግሞ ለተማሪውም ለአገርም የመሥራት አቅምን የሚጨምር ነው:: ሁለተኛው የመስፈርት ወይም ከስታንዳርድ ጋር የሚደረገው አይነት ሲሆን፤ ተማሪና ተቋማት ወይም ዩኒቨርሲቲዎች ለተሰጠው መስፈርት ብቁ መሆናቸውን የሚያረጋግጡበት ውድድር ነው:: እናም የመውጫ ፈተና በሁለቱም መልኩ የሚለካ በመሆኑ አገርን ከመጥቀም አኳያ የማይተካ ሚናን ይጫወታል ይላሉ::
የመውጪያ ፈተናው ይሰጣል ከተባለ ቆይቶ እንደነበር የሚያነሱት ዶክተር ዳምጠው፤ በኮቪድና መሰል ነገሮች ቆሞ እንጂ ውጤቱን አሁን ላይ እንመለከተው ነበር:: አሁንም ቢሆን ውጤታማ እንደሚያደርገን አምነን ልንሰራበት ይገባል:: የተለየ ነገር አድርጎ በአሉታዊ መመልከቱ ዋጋ ያስከፍላል እንጂ ብቃት ያለው ተማሪን እንድናፈራ አያደርገንም:: ስለሆነም ዩኒቨርሲቲዎች ያንን አስበው ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባም አስረድተዋል::
ከመውጪያ ፈተናው በኋላ ጥራት ያለው ተማሪ ማፍራት የማይችሉ፣ ደረጃውን የጠበቀ ምርምር የማያካሂዱና የአካባቢውን ማህበረሰብ የማይጠቅሙ ዩኒቨርሲቲዎች ሊዘጉ እንደሚችሉ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ሲናገሩም ነበርና ዩኒቨርሲቲዎች ለዚህ የሚተጉበትን አማራጭ መቀየስ እንዳለባቸው የሚያሳስቡት ዶክተር ዳምጠው፤ እንደ አገር ብቁ ዜጋን ማፍራት እንዳይዘጋ ብሎ መሥራት አይደለም::
ግዴታና የዩኒቨርሲቲዎች ዋና ተልእኮ ነው:: ስለሆነም እንደእኛ ዩኒቨርሲቲ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ተግባሩ እየተከናወነ ቀጥሏል:: ዝግጅቶቻችንም ከሞላ ጎደል ጥሩ እየሄደ ነው:: እናም ሁሉም ዩኒቨርሲቲ ከተሰጠው ተልእኮ አንጻር እያየ መሥራት ይጠበቅበታል:: በተለይም በቂ ባለሙያን አፍርቶ ለአገር ጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ ላይ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል:: እኛም ምክረ ሃሳቦቹ ጠቃሚ በመሆናቸው ተማሪዎቹም ሆኑ ዩኒቨርሲቲዎቹ ቢጠቀሙባቸው ጎልተው ሊወጡ ያስችሏቸዋል እያልን ለዛሬ ሃሳባችንን ቋጨን:: ሰላም!!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ነሃሴ 9/2014