የህዝባችን የፖለቲካ እውቀት ቀን በቀን እያደገ ነው:: ፖለቲካውን የሚተነትነው ሰው ቁጥር ከኑሮ በፈጠነ ሁኔታ ቀን ከቀን እያሻቀበ ነው:: በቅርቡ ሀገራችን በፖለቲካ ተንታኞች በኩል ራሷን እንደምትችልም ምንም ጥርጥር የለውም:: ይሄ ቀላል እመርታ አይደለም:: ፖለቲካና ኮረንቲ በሩቁ ነው በሚባልበት ሀገር እንዲህ ሰዎች ራሳቸውን የፖለቲካ ተንታኝ አድርገው የሚሾሙበት ሁኔታ መፈጠሩ አስገራሚ ነው:: ችግሩ ብዙው ትንታኔ በትንታ የሚገድል መሆኑ ነው:: በህይወታቸው አንድም ነገር አስተዳድረው የማያውቁ ሰዎች ሀገር አንዴት መተዳደር እንዳለባት ያለምንም ችግር ሲተነትኑ መስማት አስገራሚ ነገር አለው:: አንድ መጽሀፍ አንብበው የማያውቁ ሰዎች በማንኛውም ጉዳይ ላይ አስተያየት ሲሰነዝሩ ማየትም አስቂኝ ነው::
የዛሬው ጉዳዬ ግን ፖለቲካ ለምን ተተነተነ አይደለም:: እሱ መብት ነው:: ገባህም አልገባህም ፤ ትክክል ሆንክም አልሆንክም የመናገር ነጻነት ህገ መንግስታዊ መብት እስከሆነ ድረስ የታየን መናገር አይከለከልም:: ችግር የሚሆነው ግን መንግስት በንግግሬ ምክንያት እኔን እየፈለገኝ ነው የሚል እምነት ከተፈጠረ ነው:: ደግሞም ተፈጥሯል:: እርግጥ ይህ እሳቤ ሀሰት ነው ማለት አይቻልም:: በእኛም ሀገር በሌሎችም ሀገራት ያለ ነገር ነው:: የስለላ መዋቅሩ የሀገርን ደህንነት ስጋት ውስጥ የሚከት መረጃ ያሰራጫሉ የሚላቸውን አካላት ይከታተላል ፤ ያስቆማል ፤ በቁጥጥር ስር ያውላል ፤ ይከሳል ፤ ያስፈርዳል:: ይሄ መደበኛ ሂደት ነው::
ነገር ግን በእርግጥ በዚያ ልክ አንገብጋቢ የሆነ እና ሀገርን አደጋ ውስጥ የሚከትት መረጃ ያላቸው እና የሚያሰራጩት እነማን ናቸው ሲባል ብዙውን ጊዜ እነዚያ አካላት በጣም ጥቂት ሆነው ይገኛሉ:: ሌላው ግን በአብዛኛው አእምሮው ውስጥ ያለውን መረጃ የሚተነፍስ እና ያን ያህልም ተጨባጭ መረጃ የሌለው ህዝብ ነው:: ይህን መንግስትም የደህንነት መዋቅሩም ያውቀዋል:: ታዲያ ለምን እነሱን ይከታተላል? አይከታተልም:: ብዙ ሰው ግን እንደዚያ ይመስለዋል:: ”ምንድን ነው ስልካችን እየተጠለፈ ነው እንዴ?” ይልሀል በስልክ ስታወራው:: ከመሬት ተነስቶ “ፌስቡኬን ሀክ ሊያደርጉት ነው” ይልሀል:: ”መንገድ ላይ ሲከተሉኝ ነበር” ይልሀል::
እንዲህ አይነቱ ቅዥት ከብዙ ነገር ሊመነጭ ይችላል:: አንደኛው ለራስ ከሚሰጥ የተጋነነ ግምት ነው:: አንዳንዱ ሰው በማህበራዊ ሚዲያ ብዙ ተከታይ ሲኖረው በጣም ተጽእኖ ፈጣሪ እንደሆነ እና መንግስትን ሁሉ እስከመቀየር የሚደርስ ጉልበት እንዳለው ይሰማዋል:: እንዲህ አይነት ሰዎች በፊትም አሁንም አሉ:: በአንድ ወቅት አንድ ሰባኪ በጣም ከተማው ላይ ዝነኛ ከመሆኑ የተነሳ እኔና ፓትርያርኩ እኩል ሰው ነው የምናሰልፈው ብሎ ተናግሮ ነበር:: ዛሬ ላይ ያን ያለው ሰው ማንም የማይሰለፍለት መደበኛ ሰው ሆኖ እየኖረ ነው:: በቅርቡም በሀገሪቱ ሁለት መንግስት ነው ያለው የሚል ሰው ነበር:: አንደኛው መንግስት አሁንም አለ:: ሁለተኛው ግን አልተገኘም:: እንዲህ አይነት ለራስ የሚሰጥ የተጋነነ ምልክታ እየተሰለልኩ ነው ፤ እየተከታተሉኝ ነው ምናምን ወደሚል እሳቤ ይመራል::
ሁለተኛው የእንደዚህ አይነት እሳቤ መንስኤ ከአእምሮ ጤና መዛባት የሚመነጭ ነው:: የስነ ልቡና ባለሙያዎች ሺዞፈርኒያ ይሉታል:: እውነታን መረዳት ከሚገባን በተቃራኒው ገልብጦ የመረዳት ችግር ነው:: ይህ ገልብጦ የመረዳት ችግር ቅዥትን እና ብዥታን ይፈጥራል:: የሌለ ነገር እንዲታየን ፤ ስጋት ያልሆነ ነገር ስጋት እንዲሆንብን ፤ ተጠራጣሪነት እንዲወርሰን ወዘተ..በር ይከፍታል:: ከዚያ በኋላ ያልታየ ነገር ሁሉ እየታየን በራሳችን ጥላ የምንደነግጥ እንሆናለን:: ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው በእውነተኛ ታሪክ ላይ ተመስርቶ የተሰራው ኤ ቢውቲፉል ማይንድ የተሰኘ ፊልም ነው::
ይህ ፊልም የሂሳብ ሊቅ ስለሆነው ጆን ናሽ የሚያወራ ነው:: ናሽ በሂሳብ ዘርፍ አለምአቅፍ እውቅና ያስገኘለት ትልቅ ሂሳባዊ ግኝት ቢያገኝም የሩሲያ ሰላዮች እየተከተሉኝ ነው የሚለው ቅዠቱ ግን ከእውቀቱ በላይ ዋነኛ መታወቂያው ሆኗል:: ናሽ ገና በጊዜ የዚህ ህምም ተጠቂ መሆኑ ታወቆለት እርዳታ ሲያገኝ የኖረ ሲሆን በእኛ ሀገር ግን ስለነገሩም ያለን ግንዛቤ አነስተኛ በመሆኑ ብዙ ሺህ ሰለባ የሆኑ ሰዎች ልታሰር ነው ፤ እየተከተሉኝ ነው ሲሉ አብረናቸው እየተከተልን እናብዳለን:: እነዚህ ሰዎች አንዳንዴም በሀይማኖት ተቋማት ውስጥ ገብተው ራእይ ታየን ፤ ትንቢት ተነገረን ፤ እንዲህ ሊመጣ ነው ፤ እንዲህ ልንሆን ነው እያሉ ህዝብን ያስጨንቃሉ:: የሆነ ሆኖ ግን ብዙውን ጊዜ ተግባራቸው በአደባባይ የሚታይ በመሆኑ እነሱን የሚከተል ሰላይም ሆነ ሌላ የለም::
ሶስተኛው እና ዋነኛው ጉዳይ ብዙዎች እንዲዚህ የሚሉት የሚኖሩበትን ሀገር ከመርሳት ነው:: የምንኖረው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው:: ኢትዮጵያ ደግሞ በየደቂቃው አዳዲስ ጠላቶች ተፈልፍለው የሚያድሩባት ሀገር ናት:: እስኪ ዙሪያችንን እንመልከት ፤ በምስራቅ አልሸባብ አለ:: አልሻባብ የቀን እና የሌሊት ምኞቱ የአፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ ገብቶ ቦንብ አፈንድቶ የቻለውን ያህል ኢትዮጵያዊ መፍጀት እና የዜና ርእስ መሆን ነው:: በምእራብ ኦንግ ሽኔ ፤ የጋምቤላ ነጻ አውጪ ፤ የቤኒሻንጉል ነጻ አውጪ ወዘተ አሉ:: የእነዚህ ምኞት ደግሞ ኢትዮጵያን ማፍረስ ነው:: በሰሜን ህወሀት አለ:: ከዚያ ደግሞ የግብጽ እና ሌሎች የኢትየጵያ ጠላቶች ከነተላላኪዎቻቸው አሉ::
ሌሎች ወዳጅ ነን የሚሉ ሀገራትም እንደ አቅማቸው ለራሳቸው ጉዳይ አስፈጻሚነት የሚያሰማሯቸው ብዙ ሀይሎች አሉ:: በመንግስት ውስጥ ተሰግስገው ለጠላት መረጃ የሚያቀብሉ ባንዳዎችም በስፋት አሉ:: ታዲያ እነዚህ ሁሉ ባሉበት መንግስት እንዳንተ አይነቱን የፌስቡክ አርበኛ ሲከታተል የሚውልበት ምን ምክንያት አለው ያለንበትን ሀገር እና ሀገራችን ያሏትን ጠላቶች ብዛት እና የጥፋት እቅድ ብናውቅ እንዲህ አይነት ቅዥት ውስጥ አንገባም::
ሲጠቃለል ፤ ለማለት የተፈለገው ፤ ወገኔ ሆይ በሌለ ነገር ራስህን አታስጨንቅ:: ከመጻፍ እና ከመናገር ያለፈ ሀገርን የሚጎዳ ነገር ውስጥ እስካልገባህ ድረስ ጀርባህን አይክበድህ:: ዘና ብለህ ኑር::
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን ነሃሴ 9/2014