እንደ የዓለም የቱሪዝም ድርጅት መረጃ፣ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ትልቅ፣ ውስብስብ እና ለብዙ ሰው የስራ እድል መፍጠር የሚችል ነው። ከቱሪዝም ኢንዱስትሪው ሁለንተናዊ ጥቅም ለማግኘት አገራት ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው የሰለጠነ የሰው ኃይል ለመፍጠር ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ ይገኛሉ።
አገራችን ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ ብዙ ችግር ይስተዋልባታል። የአገራችን የቱሪዝምና ሆቴሉ ዘርፍ ስር የሰደደ የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ከሚስተዋልባቸው ዘርፎች መካከል አንዱ መሆኑን በዘርፉ የተካሄደ ጥናት ያመላክታል።
በሰባተኛው ብሄራዊ የጥናትና ምርምር ጉባኤ ላይ የቀረበው ጥናት እንደሚያሳየው፤ በዘርፉ ከተሰማሩ ሰራተኞች መካከል 33 በመቶው ብቻ ናቸው በዘርፉ ስልጠና ያገኙት። በአገራችን በቱሪዝም ሆነ በሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ለሰለጠነ የሰው ኃይል የሚሰጠው ቦታ ዝቅተኛ ነው። በስራ ላይ ካሉት ባለሙያዎች መካከል በትክክል ስልጠናውን አግኝተው ምዘናውን አልፈው ስራ የያዙት 14 ነጥብ 4 በመቶ ብቻ ናቸው።
ከዘርፉ ፈጣን እድገት አንፃር የስልጠናው ዘርፍ አብሮ ያለመፍጠን ጥናቱ ከዳሰሳቸው ችግሮች አብዩ ነው። ይህንን እና መሰል ችግሮችን ለመቅረፍ ጥረት እየተደረገ ነው። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በአገር አቀፍና በክልሎች ደረጃ በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ውስጥ እየሰሩ ላሉ ባለሙያዎች ስልጠናዎች እየተሰጡ ነው።
በኦሮሚያ ክልል በአዳማ ከተማ በሚገኙ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ውስጥ አገልግሎት በመስጠት ላይ ለሚገኙ ባለሙያዎች በቅርቡ የሶስት ቀናት ስልጠና ተሰጥቷቸው ተመርቀዋል። ባለሙያዎቹም ከአንድ ሪዞርት እና 34 ሆቴሎች የተወጣጡ ሲሆኑ፣ በአጠቃላይ ከ35 ተቋማት የተወጣጡ 729 ባለሙያዎች ናቸው ስልጠናውን በመከታተል ያጠናቀቁት።
በምረቃው ስርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት የኦሮሚያ ክልል የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሁንዴ ከበደ እንደተናገሩት፤ በኦሮሚያ ክልል ሆቴል ተብለው የሚታወቁ ተቋማት ብዛት 2 ሺ 200 ይደርሳል። ከዚህ ውስጥ የኮከብ ደረጃ ያላቸው ሆቴሎች ብዛት 66 ነው። ከዚህ በተጨማሪም በቅርቡ ለኮከብ ደረጃ የታጩና ለምዘና የተዘጋጁ በርካታ ተቋማትም አሉ። በአጠቃላይ የክልሉ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ብዛት ሆቴል፣ ካፌና ሌሎችን ጨምሮ 18ሺህ 72 ናቸው። በነዚህ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ወደ 82 ሺህ ሰዎች እያገለገሉ ይገኛሉ።
ምክትል የቢሮ ኃላፊው እንዳሉት፤ ስልጠናው በቢሾፍቱ እና በአዳማ የተሰጠ ሲሆን፤ በአጠቃላይ ወደ 1500 ያህል ባለሙያዎች ተከታትለውታል። በቀጣይነት በባቱ ከተማ፣ በምዕራብ አርሲ ዞን ሻሸመኔ ከተሞች ለአንድ ሺህ ሰልጣኞች ስልጠናው ይሰጣል። በአጠቃላይ 2500 የሚሆኑ ባለሙያዎች ስልጠናውን ያገኛሉ።
የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሰዓዳ ኡስማን በበኩላቸው እንዳብራሩት፤ የኦሮሚያ ክልል ለቱሪዝም ግብዓት የሚሆን ብዙ ያልታወቀ የቱሪስት መስህቦች ያሉበት ቢሆንም፣ መስህቦቹ በሚፈለገው ልክ ጥቅም ላይ ሳይውሉ ቆይተዋል። እስከ ለውጡ ድረስ ለቱሪዝም ዘርፍ ተገቢው ትኩረት ሳይሰጠው ቆይቶ የነበረ ሲሆን፤ ከለውጡ በኋላ ግን ለቱሪዝም ዘርፍም በትኩረት እየተሰራ ነው። ከተሰሩት ስራዎች መካከል የቱሪዝም መዋቅር ከፌዴራል እስከ ቀበሌ መዘርጋቱ ነው። የቱሪዝም ዘርፍን የሚመለከቱ ፖሊሲዎች እንዲሻሻሉ ተደርጓል።
በአሁኑ ወቅትም የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ። የኦሮሚያ ክልል መንግስት ለዚህ ዘርፍ ትልቅ ትኩረት በመስጠት የቱሪዝም ተቋማትን የማጠናከር አገልግሎቶችን ተደራሽ የማድረግ እና የማዘመን ስራዎች እየተሰሩ ናቸው። ባለሃብቶች እና ባለሙያዎች ተገቢውን የቱሪዝም አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ድጋፍ እየተደረገ ነው ሲሉ ወይዘሮ ሰዓዳ ያብራራሉ።
አገሪቱ ተጠቃሚ መሆን የምትችለው በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች ጥሩ አገልግሎት ማቅረብ ሲችሉ ነው ያሉት ወይዘሮ ሰዓዳ፤ ጥራት ያለው አገልግሎት ማቅረብ ካልተቻለ ቱሪስቶችን መሳብ፣ ማቆየትም ሆነ ገቢ ማግኘት አይቻልም። አገሪቱ ተጠቃሚ መሆን እንድትችል የአገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ሰራተኞች አቅም መገንባት፣ ማሳደግ፣ ማጎልበት ይገባልና ድጋፍ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ከተሞች በአገልግሎት መስጫ ተቋማት ውስጥ ለተሰማሩ ባለሙያዎች ስልጠናዎች እየተሰጠ መሆኑን ገልጸው፣ በአዳማ በሚገኙ አገልግሎት መስጫዎች ውስጥ ለሚያገለግሉ ባለሙያዎች የተሰጠው ስልጠናም የዚሁ አካል ነው ብለዋል። 729 ባለሙያዎች ሰልጥነው በአንድ ጊዜ ሲመረቁ በኦሮሚያ ክልል ደረጃ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ደረጃም የመጀመሪያው መሆኑን ጠቁመዋል። ከፍተኛ ቁጥር ያለው ባለሙያ ማሰልጠን መቻሉ የቱሪዝም ዘርፉን ለማዘመን እየተደረገ ላለው ጥረት ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።
እንደ ወይዘሮ ሰዓዳ ማብራሪያ፤ ስልጠናው በራሱ ግብ አይደለም። ለታሰበው ግብ መዳረሻ ግን ይሆናል። ለክልሉ የቱሪዝም ዘርፍ ተጨማሪ አቅም ለመፍጠር ታስቦ የተሰጠ ነው። ባለሙያዎቹ በስልጠና ያገኙትን እውቀት እና ክህሎት በመጠቀም ለአገልግሎት መሻሻል የበኩላቸውን መወጣት አለባቸው። ባለሙያዎቹም አንዴ ሰልጥነናል ብለው መዘናጋት የለባቸውም፤ በየጊዜው ክህሎታቸውን እያሳደጉ መቀጠል አለባቸው።
ከሌሎች ድጋፍ ሰጪ ተቋማት ጋር በመተባበር መሰል ስልጠናዎችን የመስጠቱ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል። የአሁኑ የመጀመሪያ ስልጠና መሆኑን ጠቅሰው፣ ተጠናክሮ ጠቁመዋል።
በክልሉ ከ15ሺህ በላይ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት መኖራቸውን የጠቆሙት ወይዘሮ ሰዓዳ፣ በተወሰኑ ከተሞች ለሚገኙ ባለሙያዎች እየተሰጠ ያለው ስልጠና ካሉት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ባለሙያዎች ጋር ሲነጻጸር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም ብለዋል።
እንደ ቢሮ ኃላፊዋ ገለጻ፤ የቱሪዝም ዘርፍ ባለሙያዎችን በማሰልጠን ረገድ መሰራት ካለበት ስራ አንጻር የሰው ኃይልን በማሰልጠን ረገድ ገና አልተነካም፤ አሁን ያለውን የሰው ኃይል ብቻ ይዞ የቱሪዝም ዘርፉን የታሰበበት ደረጃ ማድረስ አይቻልም። ስለዚህ በዘርፉ ድጋፍ የሚሰጡ አካላት የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት ረገድ ድርሻቸው ትልቅ ስለሆነ በቀጣይ ቢሯቸው ከድጋፍ ሰጪ ተቋማት ጋር በጋራ ለመስራት ዝግጁ ነው።
የኢፌዴሪ ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስለሺ ግርማ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በርካታ የቱሪስት መስህቦች መገኛ መሆንዋን ጠቅሰው፤ ከኢትዮጵያ ውስጥም ኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ የቱሪስት መስህቦች ያለበት መሆኑን አስታውቀዋል። እነዚህን የቱሪስት መስህቦች አልምቶ ውጤት ለማምጣት አንዱ መሰረታዊ ነገር የሰው ሀብት ልማት ላይ የሚሰራው ስራ ነው። የቱሪዝም ዘርፍ የሰው ሀብት ልማት ላይ የተሰራው ስራ እጅግ በጣም አነስተኛ ነው ይላሉ።
በአሁኑ ወቅት በተለይም በኦሮሚያ ክልል የሆቴሎች፣ ሪዞርቶች፣ ካፌዎች እና ሬስቶራንቶች ቁጥር እያደገ መጥቷል። ይህ ይበል የሚያሰኝ እድገት ነው። ለዘርፉ እድገት ባለሃብቶች ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። ይህም ይበል የሚያሰኝ ነው። በዘርፉ የሚደረገው ኢንቨስትመንትም ማደጉን መቀጠል አለበት።
ባለሃብቶች ኢንቨስትመንታቸውን ሊያስፋፉ ይገባል ያሉት አቶ ስለሺ፣ በተለይም በተቋሞቻቸው ውስጥ የቀጠሯቸውን ሁሉንም ሰፈራተኞች ማብቃት እጅግ በጣም አስፈላጊ መሆኑን መገንዘብ እንዳለባቸው አስታውቀዋል። አብዛኛው ኢንቨስትመንታቸው ከህንጻ ግንባታ ጎን ለጎን ሰው ሀብት ልማት ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለበት ጠቁመዋል።
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ፤ የቱሪዝም ሀብቶች ተጠቃሚ ለመሆን ከዚህ ቀደም በአገር አቀፍ ደረጃ በአሜሪካና በአውሮፓ ላይ ተንጠልጥሎ የነበረውን የቱሪዝም ንግድ በኤዢያ፣ በአፍሪካ እና በመካከለኛው ምስራቅ ጭምር ለማስፋት ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ነው። በዚህም የቱሪስት ቁጥርን በከፍተኛ ደረጃ መጨመር ይቻላል። ከነዚህ ቱሪስቶች አገሪቱ ማግኘት ያለባትን ጥቅም ማግኘት እንድትችል ሰለጠነ የሰው ኃይል ያስፈልጋታል።
አገሪቱ ሰራተኞችን፣ ወጣቶችን በተለይም ሴቶችን ወደ አረብ አገራት ከመላክ ይልቅ እያሰለጠነች በቱሪዝም ዘርፍ የምትጠቀምበት እና በተለያዩ ማህበራት በመደራጀት ለአገር ኢኮኖሚ ልማት የበኩላቸውን እንዲወጡ ማድረግ እንዳለባት ያስገነዝባሉ። በዚሁ መሰረትም ሊሰራ ይገባል።
በአገር አቀፍ ደረጃ የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ እቅድ መያዙን የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በአስር ዓመት ውስጥ ከቱሪዝም ዘርፉ ከ20 ቢሊየን ዶላር በላይ ለማግኘት መታቀዱን አብራርተዋል። በዚህ ዘርፍ ከሚሊየን በላይ የሚሆኑ ዜጎች በተለያዩ የሙያ ዘርፎች የስራ እድል ይፈጠርላቸዋል ብለዋል።
የዘርፉ እድገት የዘርፉ ባለሙያዎች በሚሰጡት የአገልግሎት ጥራት የሚወሰን ነው ያሉት አቶ ስለሺ፤ የዘርፉ እጣ ፋንታ የዘርፉ ባለሙያዎች በሚያቀርቡት አገልግሎት፣ በሚኖራቸው ስነምግባርና የተግባቦት ክህሎት እንደሚወሰን ገልጸዋል። እነዚህ የዘርፉ ምሩቃንም የዘርፉን እጣ ፋንታ የመወሰን አቅም ካለው ኃይል መካከል መሆናቸውን አውቀው እንዲሰሩ አሳስበዋል።
በስልጠናው የተሳተፉ ባለሙያዎች በበኩላቸው ስልጠናው ብዙ ልምድና ክህሎት ያገኙበት መሆኑን በመጠቀስ፣ በስልጠናው ያገኙትን እውቀትና ልምድ ወደ ስራ ሲመለሱ እንደሚያግዛቸው ጠቁመዋል። መሰል ስልጠናዎች በተከታታይ ሊሰጡ እንደሚገባም ተናግረዋል።
ስልጠናውን ጨርሰው ከተመረቁት መካከል ዓለምብርሃን በየነ አንዱ ነው። ዓለምብርሃን የምግብ ዝግጅት ባለሙያ ነው። በስልጠናው ብዙ የማያውቃቸውን ነገሮች እንዳወቀበት ነው የተናገረው። በስልጠናው ያገኘው እውቀት ስራውን ለማዘመን ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥርለት ተናግሯል። ስልጠናው ሶስት ቀን ብቻ መሆን እንዳልነበረበት ተናግሮ፣ ሰፊ ስልጠና ቢሰጥ መልካም ነው ብሏል።
የፈረቃ ቡድን መሪ መሆኑን የጠቆመው ዓለምብርሃን፣ በስልጠናው ወቅት ያገኘውን ተጨማሪ እውቀትና ክህሎት ከሱ ጋር አብረው ለሚሰሩት እንደሚያጋራም ተናግሯል።
ሜላት ተፈራ የፍሮንት ኦፊስ ሰራተኛ ነች። በስልጠናው ያገኘቺው ልምድና ክህሎት ስራዋን በተሻለ መንገድ ለመስራት የሚያስችላት መሆኑን ነው የተናገረቺው። ወደ ስራዋ ስትመለስም እንደሚረዳት ተናግራለች። ስራዋን በተሻለ መንገድ ለመስራት እና ፕሮፌሽናል ለማድረግ እንደምትሰራ ተናግራ፤ ስለጠናውን ለባልደረቦቿ እንደምታጋራ ተናግራለች።
ሰዓዳ አማን በአዳማ ሂልሳይድ ሆቴል ሰራተኛ ነው። ስልጠናውን በአጭር ቀን ውስጥ የተሰጠ ቢሆንም፣ ብዙ ልምድና ክህሎት የቀሰመበት፣ በጣም ሲጠብቀው እንደነበር ጠቁሟል። ስልጠናው ለቀጣይ ስራው ብዙ እንደሚያግዘው ጠቁሞ፤ ለስራው የበለጠ እንዲነሳሳ እና ከቀድሞ በተሻለ እንዲሰራ እንዳነሳሳው ተናግሯል። የሚያሰለጥነው አካልም በሆቴል ኢንዱስትሪ ውስጥ ያለውን ክፍተት በመለየት በማሰልጠኑ እንደተደሰተ ተናግሯል።
በኢትዮጵያ ውስጥ በብዙ ሰዎች ወደ ስራ የሚገቡት በዘርፉ ሰልጥነው በቂ እውቀት ይዘው ሳይሆን በእድል እና በገጠመኝ ነው። በእድል እና በገጠመኝ ወደ ሆቴል እና ቱሪዝም ዘርፍ የሚገቡ ሰዎች እንዲህ አይነት ስልጠና ማግኘታቸው የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ እንደሚረዳም ጠቁሟል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 8 /2014