የቅደመ ስኳር በሽታ (Pre-Diabetes) ምንድነው?
በደም ውስጥ ያለ ግሉኮስ መጠን ሲጨምር ነገር ግን የስኳር በሽታን ያህል ከፍተኛ ካልሆነ ቅድመ ስኳር በሽታ ወይም ፕሪ ዳያቤቲስ (pre-diabetes) ይባላል። በደም ጉሉኮስ (በባዶ ሆድ) ምርመራ ላይ 100 እስከ 125 ሚሊግራም በዴሲሊትር ወይም በኤዋንሲ(A1C) ምርመራ ከ 5.7% – 6.4% ያሳያል።።
በጤና ላይ የሚያስከትለው ችግር
የደም ግሉኮሱን ካልተቆጣጠረ ቅድመ ስኳር በሽታ ያለበት ሰው ለስኳር በሽታ በከፍተኛ ደረጀ የተጋለጠ ነው። በተለይ ከ60 አመት እድሜ በታች ከሆነ፣ ውፍረት ካለ፣ በእርግዝና ጊዜ የደም ግሉኮስ ከፍተኛ ከነበረ ወደስኳር በሽታ የመለወጥ እድሉ ከፍተኛ ነው።
በምርመራ ይህ የታወቀለት ሰው እራሱን እንደ እድለኛ መቁጠር ይችላል። ምክንያቱም ህመሙ ከፍቶ በስኳር በሽታ ሰበብ የሚመጡ በሽታዎች ሳይከሰቱ በፊት የጤናውን ሁኔታ ማወቅ ችሏል። ሳይቃጠል በቅጠል እንዲሉ፤ አመጋገቡን በማስተካከል፤ የአካል እንቅስቃሴ በማድረግ፣ የሃኪሙን ምክር በመከተል ቅድመ ስኳር በሽታ ወደ ስኳር በሽታ እንዳይሄድ ለማድረግ እድል አለው።
ምልክቶች
በዚህ ደረጃ ላይ እያለ ህመምተኛው ምንም ምልክት ላያሳይ ይችላል። አንዳንድ ሰዎች አንገታቸው፣ ብብታቸው፣ ጉልበታቸው፣ ክርናቸው፣ ወይም የጣታቸው መተጣጠፊያ ላይ የሚገኝ ቆዳቸው በተለየ መልኩ ይጠቁራል። ይህ ጥቁረት አንዳንዴ እድፍ ይመስላል። ነገር ግን እንደእድፍ በመታጠብ አይለቅም። ከዚህ ውጭ የማይረካ የውሃ ጥም፣ ቶሎ ቶሎ የረሃብ ስሜት ሲሰማዎ፣ እና አሁንም አሁንም የውሃ ሽንት የሚለው ከሆነ ህመሙ ወደስኳር በሽታ መለወጡን ጠርጥረው ለሃኪም ማማከር ተገቢ ነው።
ህክምና
የቅድመ ስኳር በሽታ ያለበት ሰው፤ እንደዶክተሩ ምክር የደም ግሉኮሱን በየግዜው መታየት አለበት። የደም ግፊት ወይም እና ኮሌስትሮል ካለ በቂ ህክምና ማድረግ ለህመምተኛው ጤና ይመከራል። አንዳንድ ዶክተሮች የህመምተኛውን አጠቃላይ ጤና በማየት ሜትፎርሚን የተባለ ክኒን ያዛሉ። ይህ መድሃኒት የስኳር በሽታን ለማዘግየት እንዲሁም የደም ግሉኮስን ለመቀነስ ለብዙ ስኳር በሽተኞች ይታዘዛል። ምንም መድሃኒት ባይታዘዝ እንኳን አመጋገብ መለወጥ እና የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግ ለወደፊቱ ጤንነትዎ አስፈላጊ መሆኑን አይዘንጉ።
ሜትፎርሚን ለምን በሽታ ይታዘዛል?
ሜትፎርሚን አይነት 2 ስኳር በሽታ (Type II diabetes mellitus) ያለባቸው ሰዎች፤ በደማቸው ያለውን የግሉኮስ መጠን ለማስተካከል የሚታዘዝ መድሃኒት ነው።
በተጨማሪ፤ ሜትፎርሚን ለሌሎች ህመሞች ሊታዘዝ ይችላል። ቅድመ ስኳር በሽታ(Pre-diabetes)፣ በእርግዝና ጊዜ ለሚከሰት የስኳር በሽታ(Gestational Diabetes)፣ ፓሊሲስቲክ ኦቫሪ ሲንድሮም(Polycystic ovary syndrome) ለተባለ የሴቶች የማህጸን ህመምን እንደምሳሌ መጥቀስ ይቻላል።
ሜትፎርሚን እንዴት ነው የሚሰራው?
ሜትፎርሚን በደም ውስጥ ያለውን ግሉኮስ በተለያየ መንገድ ይቀንሳል።
- ኢንሱሊንን በመርዳት ከደም ውስጥ ወደጡንቻ ህዋስ የሚገባውን ግሉኮስ መጠን ይጨምራል።
- ጉበት ውስጥ የተከማቸውን ግላይኮጅን(glycogen) ወደግሉኮስ እንዳይለወጥ ይረዳል። ይህም ከጉበት ወደ ደም የሚገባውን የግሉኮስ መጠን እንዲቀንስ ያደርገዋል።
- በምግብ ልማት ከትንሿ አንጀት የተገኘውን ግሉኮስ ወደ ደም ስርአት ሲገባ እንዲቀነስ ያደርገዋል።
እነዚህን መንገዶች ተጠቅሞ በደም ውስጥ ያለውን የግሉኮስ መጠን እንዲቀንስ ያደርጋል። ሜትፎርሚን፤ የስኳር በሽታን ይቆጣጠራል እንጂ አያድንም። የደም ግሉኮስ መጠን ቢስተካከል እንኳን፤ መድሃኒትዎን መውስድ እንዳያቋርጡ። አመጋገብን መቆጣጠር እንዲሁም የሰውነት እንቅስቃሴ ማዘውተር፤ የስኳር በሽታ ህክምና አካል መሆኑን አይዘንጉ።
ሜትፎርሚን በምን መልኩ ታሽጎ ይመረታል?
በአፍ የሚወሰድ ክኒን(tablet) ወይም በብጥብጥ ፈሳሽ (solution) መልክ ይዘጋጃል። የሜትፎርሚን ክኒን ቶሎ የሚሰራ(immediate release) ወይም ዘግይቶ የሚሰራ(long acting or extended release) ሊሆን ይችላል። ከተዋጡ በኋላ ዘግይተው የሚሰሩ (long acting or extended release) መድሃኒቶችን መስበር፣ ማኘክ፣ ወይም መዳመጥ የለብዎትም።
ከመጠቀምዎ በፊት ማወቅ ያለብዎት ምንድነው?
- እርጉዝ ሴት ከሆኑ፦ ሜትፎርሚን በጽንስም ሆነ በነፍሰጡር ሴት ጤና ላይ ችግር አያስከትልም።
- የሚያጠቡ እናት ከሆኑ፦ ሜትፎርሚን በጡት ወተት ውስጥ ስለሚኖር አማራጭ መንገድ ለመፈለግ ዶክተርዎን ያማክሩ።
- ሜትፎርሚንን በሚወስዱበት ጊዜ አልኮል መጠጣት አይመከርም።
- ለረጅም ጊዜ ሜትፎርሚን የሚወስዱ ሰዎች የቫይታሚን ቢ12 ማነስ ሊያጋጥማቸው ይችላል። ይህ ቫይታሚን የአእምሮ እና የደም ጤንነት ላይ አሉታዊ ሚና አለው። ብዙ ጊዜ ቫይታሚን ቢ12 ከአሳ፣ ከእንቁላል፣ እና ከስጋ ምግቦች ይገኛል። ነገር ግን ሜትፎርሚን የሚወስዱ ሰዎች፤ ቫይታሚኑ ከአንጀታቸው ወደሰውነታቸው በሚገባ መልኩ አይሰርግላቸውም። ዶክተርዎ የምርመራ ውጤትዎን አይቶ ካስፈለገ ይህን ቫይታሚን በክኒን መልክ ሊያዝልዎት ይችላል።
የሜትፎርሚን ትክክለኛ አወሳሰድ
የሀኪምዎን ትእዛዝ በጥንቃቄ ይከተሉ። የሚወስዱበት ሰአት፦ ዘግይቶ የሚሰራ (Extended Release, Long Acting) ሜትፎርሚን ከሆነ በእራት ሰአት ይውሰዱ። የተቀሩት የሜትፎርሚን አይነቶች ቀንም ሆነ ማታ መውሰድ ይቻላል። በየእለቱ በተመሳሳይ ሰአት መዋጥ መድሃኒትዎን ሳይረሱ እንዲወስዱ ይረዳዎታል።ሜትፎርሚንን ከምግብ ጋር መውሰድ ይመከራል።
መድሃኒቴን መዋጥ ከረሳሁ ምን ማድረግ አለብኝ?
ወዲያው እንዳስታወሱ ይውሰዱ። ብዙ ሰአት ካለፈ ይተውት እና በሚቀጥለው የመድሃኒት መውሰጃ ጊዜዎ የተለመደውን መጠን ይዋጡ። የረሱትን ጨምረው ለመዋጥ እንዳይሞክሩ።
በዚህ መድሃኒት ምክንያት ሊከሰቱ የሚችሉ የጤና ችግሮች
ሜትፎርሚን የሚወስዱ ሰዎች ብዙ ጊዜ ይስማማቸዋል። ነገር ግን አንዳንድ ሰዎች ሜትፎርሚን ሲወስዱ የሆድ ህመም ሊያጋጥማቸው ይችላል። ለምሳሌ ያህል ተቅማጥ/ድርቀት፣ የምግብ አለመንሸራሸር፣ ፈስ(flatulence/gas ) እና ሆድ መጮህ፣ አፍ ላይ የብረት ጣእም እንዲሁም ሆድን የመጭነቅ ስሜት ሊሰማቸው ይችላል። ይህ ምልክት ከጊዜ በኋላ ይጠፋል። ከምግብ ጋር መውሰድ እነዚህን ምልክቶችን ለመቀነስ ይረዳል። ከሚችሉት በላይ ከሆነ ግን ሃኪምዎን ያማክሩ።
አንዳንድ ዘግይቶ የሚሰራ (ግሉኮፌጅ ኤክስ-አር (Glucophage XR)፣ ፎርታሜት (Fortamet) ወይም ግሉሜትዛ (Glumetza)) የተባሉት የሜትፎርሚን መድሀኒቶች የሚወስዱ ሰዎች በሰገራ ውስጥ ክኒን የሚመስል ነገር ሊያዩ ይችላሉ። ይህ ምንም ችግር የለውም። እነዚህ መድሃኒቶች በ24 ሰአት ውስጥ መድሃኒቱን ቀስ በቀስ እንዲለቁ የሚያደርጋቸው የሚጠቀለሉበት ነው። ይህ ለየት ያለ መጠቅለያ በጨጓራም ሆነ በአንጀት ላይብላላ ይችላል። መድሃኒቱን ግን እንደማጥለያ ቀስ እያለ ማሳለፍ ይችላል። ስለዚህ በሰገራ ውስጥ ክኒኑ እንዳለ የወጣ ይመስላል። ውስጡ መድሃኒት የለም፤ ባዶ ቀፎ ነው።
ለዚህ መድሃኒት የሃኪም ክትትል ያስፈልገኛል?
እንደዶክተርዎ ምክር፣ በአመት አንድ ጊዜ ወይም በየመንፈቁ፣ አንዳንዴ በየሶስት ወሩ ሀኪምዎ ጋር መሄድ ያስፈልጋል። የኩላሊትዎን ጤንነት እና በደምዎ ያለውን ቫይታሚን ቢ12 በየጊዜው መመርመር ሜትፎርሚንን ለጤናዎ ጥቅም እንጂ ጉዳት እያስከተለ እንዳልሆነ ለማረጋገጥ ይረዳል። በተጨማሪ የደም ግሉኮስ እና ኤዋንሲ(A1C) በየጊዜው መለካት ያስፈልጋል።
መድሃኒቱ መቀመጥ ያለበት ቦታ
መድሃኒትዎን፤ ሙቀት እና ቅዝቃዜ የማይበዛበት፤ ደረቅ ቦታ ያስቀምጡ። መድሃኒትን መታጠቢያ ቤት ማስቀመጥ አግባብ አይደለም። ህጻናት እና የቤት እንስሳት የማይደርሱበት ቦታ ያስቀምጡ።
የላክቲክ አሲዶሲስ(Lactic Acidosis) ማስጠንቀቂያ
የኩላሊት ህመም ያለባቸው ሰዎች፤ ሜትፎርሚንን ከሰውነታቸው በሚገባ መልኩ አያስወግዱም። ሜትፎርሚን በሰውነት ሲከማች ለጤና አስጊ የሆነ ላክቲክ አሲዶሲስ የተባለ ህመም ሊከሰት ይችላል። ይህ የሚከሰተው እጅግ አልፎ አልፎ ቢሆንም፤ ምልክቶቹን እና ቢከሰት ምን ማድረግ እንዳለብዎ ማወቅ አይከፋም።
የላክቲክ አሲዶሲስ ምልክቶች የጡንቻ ህመም፣ የመተንፈሻ አካላት መጨናነቅ፣ በጭንቅ መተንፈስ፣ ቶሎ ቶሎ አየር መሳብ፣ ጥልቅ ድካም መሰማት፣ማንቀላፋት፣ እና የሆድ መጨነቅ ናቸው።
ለመከላከል
ቅድመ ስኳር በሽታን ለመከላከል የሚረዱ እርምጃዎች ቅድመ ስኳር በሽታ ወደ ስኳር በሽታ እንዳይሄድ ከሚረዱት ጋር ተመሳሳይ ናቸው። እነዚህም፣ የተመጣጠነ ጤናማ ምግብ መመገብ፣ በሳምንት ቢያንስ 150 ደቂቃ (በየእለቱ ቢያንስ ሃያ ደቂቃ) እንደሩጫ ያለ ስፖርት መስራት፣ ውፍረት መቀነስ፣ የሚያጨሱ ከሆነ መተው፣ እንዲሁም ከፍተኛ የደም ግፊት ወይም ኮሌስትሮል ካለብዎ ህክምና መከታተል ናቸው።
አዲስ ዘመን ነሐሴ 7 /2014