የ2014 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሴቶች እግር ኳስ ክለብ ታንዛኒያ በሚካሄደው የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ ክለቦች ቻምፒዮና ላይ ለመሳተፍ ትናንት ወደ ታንዛኒያ አቅንቷል።
በኢትዮጵያ ሴቶች እግር ኳስ ውድድር ታሪክ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ በርካታ ጊዜ በማንሳት ስኬታማ የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቡድን ታንዛኒያ በሚካሄደው የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ ክለቦች ቻምፒዮና ላይ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ መዘጋጀቱ ታውቋል። “ጀግኖች አትሌቶቻችን የአገራቸውን ስም በዓለም አቀፍ መድረክ ከፍ እንዳደረጉት ሁሉ እኛም እንደ አትሌቶቹ የአገራችንን ስም በመልካም ለማስጠራት ተዘጋጅተናል” ሲሉም የቡድኑ አባላት ወደ ታንዛኒያ ከማቅናታቸው በፊት ገልፀዋል።
ቡድኑ ከቀናት በፊት በተዘጋጀለት የሽኝት ሥነ ሥርአት ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ፣ የእግር ኳስ ክለቡ በውድድሩ ላይ የተሳካ ጊዜ እንዲያሳልፍ በመመኘት ለስኬት እንዲበቃም አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል። በሥነ ሥርአቱ ላይ የክለቡ አሠልጣኝ እና አምበል ከባንኩ ፕሬዝዳንት የባንዲራ ርክክብ በማድረግ በድል ለመመለስ ቃል ገብተዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች እግር ኳስ ክለብ በምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ ክለቦች ቻምፒዮና ላይ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ይረዳው ዘንድ ስድስት ተጫዋቾችን ከአገር ውስጥ ክለቦች ማስፈረሙ የሚታወስ ነው። ክለቡ ከነሐሴ 7 እስከ 22 ቀን 2014 ዓ.ም በሚካሄድው ቻምፒዮና ላይ ውጤታማ ለመሆን አራያት ኦዶንግ፣ ኒቦኚ የን፣ ቅድስት ዘለቀ፣ መሳይ ተመስገን፣ ብርቄ አማረ እና ናርዶስ ጌትነትን ማስፈረሙ ይታወቃል።
ዘንድሮ ለ2ኛ ጊዜ በሚካሄደው በምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ ክለቦች ቻምፒዮና ላይ ስምንት ክለቦች ተሳታፊ ይሆናሉ። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አንደኛው ተሳታፊ ክለብ ሲሆን የዩጋንዳው ሺ ኮርፖሬትቷ የታንዛኒያው ሲምባ ኩዊንስ፣ የደቡብ ሱዳኑ ዬ ጆይንት ስታርስ፣ የዛንዚባሩ ዋሪየር ኩዊንስ፣ የቡሩንዲው ፎፊላ ፒ ኤፍ፣ የሩዋንዳው ኤኤስ ኪጋሊ፣ የጅቡቲው ጂአር ኤፍሲ በውድድሩ እንደሚሳተፉ ታውቋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በውድድሩ በምድብ አንድ ከዛንዚባሩ ዋሪየርስ እንዲሁም ከብሩንዲው ፎፊላ እና ከሩዋንዳው ኤኤስ ኪጋሊ ጋር ተደልድሏል። የመጀመሪያ ጨዋታቸውንም ከዛንዚባሩ ክለብ ዋሪየርስ ጋር ያደርጋሉ።
ንግድ ባንኮች ቀሪ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታቸውን ደግሞ ከብሩንዲው ፎፊላ እና ከሩዋንዳው ኤኤስ ኪጋሊ ጋር በተከታታይ የሚያደርጉ ይሆናል። በ2022 ወርሃ ጥቅምት ሞሮኮ ለምታስተናገደው የአፍሪካ የሴቶች ቻምፒየንስ ሊግ ውድድር ለማለፍ በሚደረገው የምስራቅ አፍሪካ ክለቦች ማጣሪያም ንግድ ባንኮች ውድድራቸውን በበላይነት ካጠናቀቁ በአፍሪካ የሴቶች የክለቦች ውድድር የሚሳተፉ ይሆናሉ።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን ኬኒያ ላይ ተዘጋጅቶ በነበረው የመጀመሪያው የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ ክለቦች ቻምፒዮና ላይ የ2ኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ ይታወሳል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 6 /2014