
አዲስ አበባ፡- ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አሁን ያለበት ደረጃ የኢትዮጵያ ብልፅግና እውን የሚሆንና ማንም ሊያስቆመው እንደማይችል ማሳያ መሆኑን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትናንትናው እለት በጉባ ተገኝተው የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን የሁለተኛ ዩኒት ኃይል ማመንጨት ባስጀመሩበትና አጠቃላይ የህዳሴ ግድብ የስራ ውጤትን በማስመልከት ለኢትዮጵያውያን ባስተላለፉት የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታቸው፣ በታሪክ ውስጥ ማለፍ ዕድል እንደሆነ ነገር ግን ታሪክ ሠርቶ ማለፍ ዕድልም ድልም መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ይህም የዛሬይቱ የኢትዮጵያውያን ለአንድ ሺህ ዓመታት ሲታለም በቆየው፣ በርካቶችም ሲመኙት የነበረው የአባይን ውሃ የመጠቀም መሻት በዓይኑ ያየ፣ በእጁም የዳሰሰ እንዲሁም በእግሩ መርገጥ የቻለ ባለዕድል ትውልድ ስለሚያደርገው መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በርካታ ኢትዮጵያውያን ገንዘባቸውንና እውቀታቸውን ከዚህም አልፎ ሕይወታቸውን የገበሩለት ፕሮጀክት እንደሆነ ገልጸው፤ ስራው በዚህ ፍጥነት እንዳይከናወን ከፍተኛ ተግዳሮቶች የገጠሙትና የፀጥታ አካላትም በዚህ ልክ ብዙ ዋጋ የከፈሉበት መሆኑን አውስተዋል፡፡ በመሆኑም በዚህ ስፍራ በድል መቆማችንን አቅልለን ሳንመለከት ለላቀው ድል ደግሞ ዜጎች ከዚህ ይበልጥ እንዲነሳሱ አሳስበዋል፡፡
አባቶቻችን ይህንን ግድብ ለመገንባት አስበዋል፣ አልመዋል፣ እንዲሁም ብዙ ቁጭት አስተናግደዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ነገር ግን እኛ የታለመውንና የታሰበውን ግድብ ከሃሳብ ወደ ተግባር፣ ከመገደብና ከበርካታ ፈተናዎች ውስጥ አልፎ በዚህ ወቅት ሁለተኛውን ዩኒት ኃይል ማመንጨት ወደሚችልበት ደረጃ ማድረስ መቻላችን ተረት የነበረውን ታሪክ ማድረጋችንን ያሳያል ብለዋል፡፡
ከዚህም አልፎ አይቻልም የተባለውን ተችሎ በማየታችን እንደ ዜጎች የምንኮራ ሲሆን፤ ከዚህ በላይ ግን የአባቶቻችንን ትልምና ፍላጎት በማሳካት ሀገራችንን በፀና መሰረት ላይ ማቆም የዚህ ትውልድ ዋነኛ ኃላፊነት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያን የፀናችና የበለፀገች ሀገር ማቆየት ከቻልን ሀገሪቱ ባፈራችው ሀብት ትውልድ የሚጠቀም በመሆኑ ሀገርን የማፅናትና የማበልፀግ ጥረት ውስጥ አቅም በፈቀደ ሁሉ ተሳታፊ መሆን ከሁሉም ዜጎች የሚጠበቅ ይሆናል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት በተለይም ሱዳንና ግብፅ ኢትዮጵያ ኃይል በማመንጨት ኢኮኖሚዋን ማሻሻል፣ በጭለማ ውስጥ የሚኖሩ ዜጎችን ብርሃን እንዲያገኙ ከመፈለግ ውጪ ሀገራቱን የመጉዳት ዓላማ እንደሌላት በተደጋጋሚ ስትገልጽ መቆየቷንም አውስተዋል፡፡
በዚህ ዓመት ሶስተኛውን የውሃ ሙሌት ያረጋገጠው 22 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ገደማ ውሃ መያዝ የሚችል ስራ እንዲሁም ሁለት ዩኒት ማመንጨት የሚችል ስራ ሲሰራ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ላይ ምንም አይነት የውሃ እጥረት እንዳያጋጥምና ውሃው ኃይል እያመነጨን አንድም ቀን ሳይቋረጥ እንዲሄድ የተደረገ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በመሆኑም የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ይህን እውነታ በመገንዘብ በስምምነት ውስጥ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ከልብ በማመን ለዚህም እንዲተጉ ገልጸው፤ ከዚህ ውጪ ያለው ማንኛውም አማራጭ የጀመርነውን ስራ የማያስቆም መሆኑን ተገንዝበው ወደ ሰላም፣ ወደ ድርድርና በጋራ ወደማደግ እንዲመጡ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አሁን ያለበት ደረጃ የሚያሳየው የኢትዮጵያ ብልፅግና እውን የሚሆንና ማንም ሊያስቆመው እንደማይችል ተናግረው፤ በወቅቱ በመከወን፣ በብቃት በመጨረስ፣ ወደሚቀጥለው ደረጃ የሚያድግ መሆኑን ማሳያ እንደሆነም አመላክተዋል፡፡
የአመቱን እቅድ ከአስር ቀን በፊት ቀድሞ መከወን የተቻለው በብዙ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ጥረት በመሆኑ ያሰብነውን ማሳካት ብቻ ሳይሆን ቀድመን ማሳካት መቻላችንን ያሳየ ነው ብለዋል፡፡ በመሆኑም መላው ኢትዮጵያውያን ወደ ብልጽግና ለሚደረገው ጉዞ የራሳቸውን አሻራ እንዲያስቀምጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በዚህ ስራ ውስጥ በገንዘባቸው፣ በዕውቀታቸው እንዲሁም በቦታው በመገኘት ስራው በታቀደለት መሰረት እንዲከወን ጥረት ያደረጉ አካላትንም አመስግነዋል፡፡
ፍቃዱ ዴሬሳ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 6 ቀን 2014 ዓ.ም