
አዲስ አበባ፡- የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ለዕኩይ ዓላማቸው ድጋፍ ለማሰባሰብ ቢንቀሳቀሱም የግድቡ ሥራ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ሉአላዊ መብት በመሆኑ በድል ታጅቦ መቀጠሉን ኢንጂነር ፈቂ አህመድ ነጋሽ ገለጹ፡፡
የሕዳሴው ግድብ ተደራዳሪ ቡድን አባል የነበሩት ኢንጂነር ፈቂ አህመድ ነጋሽ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ሙሌት ከመካሄዱ በፊት ከፍተኛ ተቃውሞ ሲያሰሙ ነው የቆዩት፡፡ ጉዳዩን ወደ ጸጥታው ምክር ቤት በመውሰድና ድጋፎችን በማሰባሰብ የግድቡን ሥራም ሆነ ሙሌት ለማደናቀፍ ሲሠሩ ነበር፡፡ ሆኖም የግድቡ ሥራ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ሉአላዊ መብት በመሆኑ በድል ታጅቦ ቀጥሏል፡፡
የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ከፍተኛ ጉዳት ያደርስብናል በሚል የሕዳሴው ግድብ ግንባታንም ሆነ የግድቡን ሙሌት ወደ ጸጥታው ምክር ቤት ሲወስዱ መቆየታቸውን የጠቀሱት ኢንጂነር ፈቂ አህመድ፤ ጉዳዩን ዓለም አቀፍ ስጋት ለማስመሰልም እንቅስቃሴ ሲያደርጉ መቆየታቸውና በተለይም ግብፅ የአባል ሀገራቱን ስምምነት በሚጥስ መልኩ አሁንም ጉዳዩን ወደ ጸጥታው ምክር ቤት እየወሰደች እንደምትገኝ ተናግረዋል፡፡
ሆኖም አሁን ኢትዮጵያ በሕዳሴ ግድቧ የምትይዘው ውሃ በታችኛው የውሃው ተፋሰስ ሀገራት ላይ ጉዳት እንደማያደርስ የሚያረጋግጥና በጋራ ከሀገራቱ ጋር በመመካከር መስራት እንደሚቻል ነው የገለጹት፡፡
የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ሕዝባቸውን በአሉባልታ ሲያደናግሩ ስለቆዩ ግድቡ ከሞላ በኋላ ጉዳት ሳያደርስ ሲቀር በሕዝባቸው ትዝብት ውስጥ ላለመግባት በሌላ መንገድ ሊቀጥሉ ይችላሉ ያሉት ኢንጂነሩ፤ የዚህ ግዙፍ ግድብ ትልቁ ተግባር ኃይል ማመንጨት በመሆኑ ስጋት ውስጥ ሊከታቸው እንደማይገባ አብራርተዋል፡፡
እንደ ኢንጂነር ፈቂ አህመድ ገለፃ፤ ሀገራት በድንበር ተሻጋሪ ወንዞቻቸው አለመግባባትና መፋጠጥ ላይ ይደርሳሉ፤ መጨረሻ ላይ ግን ወደ ትብብርና ወደ ስምምነት ነው የሚሄዱት፡፡ በቅርቡ ግብፅ የሀገራቱን ስምምነት ጥሳ ወደ ጸጥታው ምክር ቤት የወሰደችውን ጉዳይ አሁንም ምክር ቤቱ እንደተለመደው ወደ አፍሪካ ሕብረት ይመልሰዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ያም ሆኖ በኢትዮጵያ ደረጃ ብዙ የዲፕሎማሲና የተግባቦት ሥራዎች መሠራት አለባቸው፡፡
በኢትዮጵያ በኩል በንቃት ሊሠሩ ይገባል ያሏቸውን ጉዳዮችም ኢንጂነሩ ተናግረዋል፡፡ በተለይም ግብፅ ወደ ጸጥታው ምክር ቤት የላከችውን ክስ አስመልክቶ ወደ ተለያዩ ሀገራት በመሄድና የኢትዮጵያን አቋም በማሳወቅ ድጋፍ የሚገኝባቸው ሁኔታዎች ላይ ብዙ መሠራት ያለባቸው ሥራዎች አሉ ብለዋል፡፡
በተግባቦትና ዲፕሎማሲ ላይ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት ግብፅ ወደ ጸጥታው ምክር ቤት የወሰደችውን የሕዳሴው ግድብን ጉዳይ ወደ አፍሪካ ሕብረት ማስመለስ ይቻላል የሚል እምነት እንዳላቸውም አክለው ገልጸዋል፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በተጎሳቆለ አኗኗር ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ሕይወት እንደሚቀይርም አንስተዋል፡፡ ከግድቡ የሚገኘው የኤሌክትሪክ ኃይል በሀገር ውስጥ እና ለውጭ ሀገራት ተሸጦ ከፍተኛ ገቢ እንደሚያስገኝና የኢንዱስትሪዎችን የኃይል ፍላጎት እና የውሃና ጤና ተቋማትን ፍላጎት በማሟላት የሀገሪቱን ዕድገት ከፍ እንደሚያደርግ ብሎም በየቤተሰቡ ውስጥ የኑሮ መሻሻልን የሚፈጥር መሆኑን ኢንጅነሩ አብራርተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት የሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ተርባይን ኃይል ማመንጨት መጀመር ማብሰሪያ ሥነ ሥርዓት በትናንትናው ዕለት ተከናውኗል፡፡
ውብሸት ሰንደቁ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 6 ቀን 2014 ዓ.ም