የወዳጅነት ትርጓሜው ምንድን ነው? ወዳጅ ምንድን ነው? ወዳጅ ሊሆን የሚችልስ ማን ነው? እነዚህ ጥያቄዎች የሚጤኑ ናቸው። ሥነ ልቡናን መርምሮና ስለ ማኅበራዊ ኑሮ ጠልቆ ፍተሻ ያደረገ ብቻ አይደለም ለእነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ ለማግኘት የሚችለው። መቼም ሰው ሺህ ጠላት ቢኖረው እንኳ አንድ ወዳጅ አያጣም። ወዳጅነት የተሰኘውን ቃል ከነትርጓሜው የማያውቅ ሰብዓዊ ፍጡር ይገኛል ለማለት አንደፍርም። ምናልባት ችግሩ በአተረጓጎሙም ላይ ይሆናል እንጂ እኔ ስለ ወዳጅነት ምንም አላውቅም የሚል አይኖርም።
ጎረቤት፣ የሥራ ባልደረባ፣ የቀለም ባልንጀራ፣ ማህበርተኛ፣ የጦር ሜዳ ጓደኛ፣ የትምህርት ቤት ጓደኛ፣ እድርተኛ ወዘተ ከእነዚህ ሁሉ እየተመረጠ ወዳጅ ይያዛል። ምሥጢር የሚያካፍሉት፣ ብሶት የሚያዋዩት፣ የልብ የሚያጫውቱት ሰው ይያዛል። ለክፉ ቀን የሚደርስ፣ የሚታደግ፣ የሚዋስ ወዳጅ ይያዛል።
በሀገራችን ከጥንት ጀምሮ የወዳጅነት ትርጓሜ በቀላል የሚታይ አይደለም። የቀረው ቀርቶ ሰው የወለደው ልጁንና ከአብራኩ የወጣውን ሲያናግር እንኳ ልጄ ወዳጄ ይላል። አባቴ ወዳጄ ማለትም የተለመደ ነበር። ይህ የሚያስረዳው እንግዲህ የወዳጅነት ትርጓሜ የቱን ያህል የጠለቀ ሊሆን እንደበቃ ነው። አባቴ፣ ወንድሜ፣ ልጄ ብቻ ብሎ መጻፉ፣ ወይም መጥራቱ፣ ይድረሱን የከበደ ስለማያደርገው መውደድን ሲጨመር ግን የልብ ሰውነትን፣ የአንጀት ፍቅረኛነትን ስለሚገልጽና ለስጋ ልደት የበለጠ ጉልበት ስለሚቸረው ወዳጅ ታክሎበት ተገኝቷል።
በሥጋ ልደትም ሆነ በጋብቻ ውህደት ያልተዛመደውም ቢሆን «ወንድሜ ወዳጄ» ሲባል ሰምተናል። ፍቅር በሥጋ መተሳሰርን በጅማት መቋጠርን አይጠይቅምና። ለመሆኑ ወዳጅ በዛሬ ጊዜ አለ ወይ? ዓይነቱስ? መልኩ ጥቂት ቀየርየር ያለ ቢሆንም ወዳጅነት ዛሬም በኅብረተሰባችን አለ። እንደ ጊዜው መሠልጠን፣ እንደ ኑሮው መዘመን ይሁን እንጂ አይጠፋም። ብሎም ቢሆን ከሸበተው ዘመን ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው ወንድ ከወንድ፣ ሴት ከሴት ጋር ብቻ፣ የሚለው አሮጌ የወዳጅነት መመሪያ ዛሬም በኅብረተሰባችን ዘንድ ይታያል።
ከአንድ እናትና አባት ከተወለደ ይበልጥ የሚፋቀሩ የልብ ወዳጆች አሉ። የሚያስቀኑ «ከዓይን ይሰውራችሁ» የሚያሰኙ የልብ ወዳጆች ሞልተዋል። ግና ዳሩ በተመሳሳይ ጾታዎች በዙ እንጂ በተቃራኒዎቹ መካከል እንዲያው ወዳጅ የተባሉ ከስንት አንድ ናቸው። «የሉም» ማለቱ ይቀላል።
«የወንድና የሴት ወዳጅነት» ከተባለ ያው «ወሲባዊ ግንኙነት» ብቻ መሆኑን በአሳዛኝ ሁኔታ እንመለከታለን። በተባዕቱና በእንስቷ መካከል ያለው ዝምድና ከወሲብ አኳያ ብቻ ሊጤን መብቃቱ የአመለካከትን ብልሹነት፣ የአስተሳሰብን ደካማነት ሳይነግረን አያልፍም።
ወሲብ ራሱን የቻለ፣ ክብርም የሆነ የአካላዊ አንድነት የምሥራች ነው እንጂ እንዲሁ የትምና ከማንም ጋር የሚካሄድ ተራ ነገር አይደለም። ጽዱ ወዳጅነትም የራሱ የሆነ በእጅጉም የከበደ ሚዛን አለው። ታዲያ እነዚህን ሁለት የተለያዩ ጉዳዮች ግራና ቀኝ አድርጎ ማየት ለምን አይቻልም? ለምን አንዱን ከሌላው ነጥሎ መመልከት አይቻልም? ጉዳዩ ብዙ የሚያወያይ ነው።
በአንድ መሥሪያ ቤት የሚሠሩ፣ ቢሮ የሚጋሩ፣ ወንድና ሴት እንኳን ከድርጅቱ ውጪ ኩርፈኞች ሆነው የታዩበት አሳዛኝ ወቅት አልታጣም። ያው «ወሲብ» በማሠሪያነት ቀርቦ ካላዛመዳቸው በቀር ወዳጅነት ስለተባለው ጽዱ ወዳጅነት ስለተሰኘው ያወቁም፣ የሰሙም፣ አይመስሉም።
ከተመሳሳይ ጾታ ጋር ወዳጅ ሊኮን እንደሚቻል ሁሉ ከተቃራኒውም ጾታ ጋር ወሲብ ሳይጨመር መወዳጀት የማይቻልበት ምክንያት ግን ምንድን ነው? ምንስ የሚያግድ ነገር አለ? አንዳንዶች ይህን ኋላ ቀር የሆነ ጊዜ የሻረውን፣ ዘመን የጣለውን አመለካከት እየኮነኑና ልባቸውንም ክፍት አድርገው ፅዱ ወዳጅነት ከተቃራኒው ጾታ ጋር ለመመሥረት ይሻሉ።ግና የሚወርድባቸውን የአሉባልታ ማዕበል በመፍራት ብቻ ያሰቡትን ሳይፈጽሙት ይቀራሉ።«እገሌ ከእገሊት ጋር ታየ» ከተባለ ያም ያም ተነስቶ፣ ሀገር ምድሩን በአሉባልታ ውሽንፍር ይመታዋል። ከመሬት ብድግ ብሎ ሳይጠይቅ ጭፍን ምስክርነቱን ይሰጣል። እንዲሁም ሲሆን ወንድ ከሴት፤ ሴት ከወንድ ጋር ያላት ግንኙነት የራቀና የሻከረ ሆኖ ይቀራል። ተባዕቱ እንስቷን ለመቅረብ እስዋም ከእርሱ ጋር ለመቀራረብ ያላቸውን ፍላጎት ርግፍ አድርገው ይተውታል። ማኅበራዊ ግንኙነት ይወይባል። ወንድም ከእህቱ ጋር ለመሄድ እንኳን በአደባባይ ይፈራል። የአሉባልተኞች ምላስ ከጦር ይሾላልና።
በቁጥር ጥቂት ያልሆኑ ወንዶችና ሴቶች ከጊዜ በኋላ ሥራ ይዘውና አግብተው በሚገኙበት ወቅት እንኳን ድሮ በትምህርት ቤት የሚያውቁትን ተቃራኒ ጾታ በመንገድ ሲያገኙት ሰላምታ አይሰጡትም። እያወቁ እንዳላወቁ ይሆናሉ። ይሸሹታልም። አዲሱ ፍቅረኛ ፤ አዲሱ ባል እንዳያይ ወይም ትኩስዋ ሚስት እንዳታይ ተብሎ ለመታሰቢያነት የተቀመጠ ፎቶ ግራፍ ሳይቀር ከአልበም እየተገነጠለ ይቀደዳል። ይቃጠላል። ከተቃራኒ ጾታ የመጣ ደብዳቤ ሁሉ ይበጫጨቃል። ይሸረካከታል። ይጣላል። ይህ የሚሆነው የፍቅረኛን ቅናት በመጠኑ ለማጠውለግና ከጭቅጭቅ ለመዳን ሲባል ነው። ነገር ግን እነዚህ ደብዳቤዎች ሁሉ «የወደድኩሽ የሞትኩልሽ» መልዕክቶች ናቸው ወይ? የሞት ፍርድ የተበየነባቸው ፎቶግራፎችስ ሁሉ የፍቅረኛ ሥዕሎች ነበሩ ወይ? ወይስ የተቃራኒ ጾታ ምስሎች በመሆናቸው ብቻ ነው? እንግዲህ እነዚህን ጥያቄዎች በምንፈትሽበት ወቅት የነገሩን ግሩምነት በጉልህ እንመለከታለን።
መቼም ፍጡር ሆኖ፣ ያውም ሰው ሆኖ በአንድ ወቅት ከአንዱ ወይም ከአንዲቷ ጋር በወሲብ ያልተገናኘ፣ በአካል ያልተቆራኘ አይኖርም። መናኝ ወይም ስንኩል ካልሆነ በቀር ተፈጥሯውን ሕግ ያላደረሰ የለም። ለአቅመ አዳምና ለአቅመ ሔዋን ደርሶ ስሜታዊ ፍላጎቱን ማሟላትን እንደ ወንጀል አይቆጠርም። ብሎም ቢሆን ካገኙት ጋር ሁሉ እገሌ ተእገሌ ሳይባል ወሲባዊ ግንኙነት ይከናወናል ማለት አይደለም። ታዲያ ፅዱ ወዳጅነት ስለሚባለው ቃል ለምን ለማወቅ የተሳነን እንሆናለን? ምላሹ የከበደ አይደለም። ስሜታዊ ብስለት የሌለውና ወሲባዊ ሥነ ምግባር ምን እንደሚመስል የማያውቅ የወዳጅነትን ትርጓሜ በአንድ አቅጣጫ ብቻ ይመለከታል። ብያኔው የተዛባ ምስክርነቱም የተሳሳተ ነው።
እዚህ ላይ ግን አንባቢ ሊረዳ የሚገባው ጉዳይ አለ። ይኸውም «ፍቅር ይጥፋ፣ ወሲባዊ ግንኙነት ይውደም» ለማለት ያልቃጣሁ መሆኑን ነው። ፍቅር መኖር አለበት። ወሲባዊ ግንኙነትም በአካላዊ አንድነትና በመንፈሳዊ ውህደት ጠንክሮ በፍቅር ማሠሪያነት ሕያው ሆኖ መኖር ይገባዋል።
ይሁንና ፍቅር ሲባል በእጅጉ የከበረ፣ ምሥጢሩም የረቀቀ እንጂ እንደ ስኳር መቁነን ተሠርቶለት ሁሉን ለማቃመስ እንዲችል በራሽን የሚታደል መኖ አይደለም። ወሲብም የአንድነትና የውህደት ብሥራቱ እንጂ ካገኙት ጋር የሚወጠን አይደለም። ፍቅርና ወሲብ በየቀኑና በየሰዓቱ፣ በየወሩ፣ በየሳምንቱ ለተለያዩ ግለሰቦች እንደ ሳንቲም እየተመነዘረ የሚበተን አይደለም። እንደ ቁጠባ ሂሳብ «ዛሬ ይህን ያህል ፍቅር ተቀምጦ» እንደ ንግድ ቤትም “ዛሬ ይህንን ያህል ፍቅር ለገቢ ተይዞ፣ ሰንብቶና ከራርሞ፣ ካስቀመጡበትና ካለበት ቦታ አራጣና ትርፍ የሚሰባሰቡበት አይደለም። ሁሉም «አይደለም» ነው።
ስለዚህም አንድ ፍቅረኛ በወዳጅነት ይዞ ቀሪውን በፅዱ ወዳጅነት መንከባከብ ያሻል። እንዲህም ሲሆን የወዳጅነት ትርጓሜ ሳይወላገድ በርቱዕነት ጸንቶ ይኖራል። ወዳጅነትም የከበረ ሊሆን ይበቃል።
በሥልጡኑ ክፍለ ዓለም የወዳጅነት ትርጓሜ እጅግም የተጣመመ አመለካከት አይታይበትም። በሀገራችን ግን ይህ ገና ረዥም መንገድ የሚቀረው ይመስላል። በአንድ ቤት (አፓርታማ) ውስጥ በደባልነት የሚኖሩ ወንድና ሴት ሞልተዋል። በፅዱ ወዳጅነት። ግና ዳሩ እነዚህ ሰዎች ወደ ሀገራችን ለጉብኝት እንኳ ቢመጡ «ባልና ሚስት» ይባላሉ። ሲጋቡ ያየ ግን የለም። ምስክርነቱም የጭፍን ነው። «አረ ምኔም አይደለም፣ ፅዱ ወዳጆች ነን» ቢል ይስቁበታል። በዋሾነት ይጠረጥሩታል። «ርግጥ ይሆናል» የሚል እንኳ የሚገኝ አይመለስለኝም። ወንድና ሴት አብረው ከታዩ ሮጦ የወሲብ እማኝ መሆን ብቻ ነው።
በፅዱ ወዳጅነት የመፈላለጉ ጉዳይ አስቸጋሪ እየሆነ መሄዱን ዘወትር ከተለያየ አቅጣጫ በሚከሰተው ሁኔታ ለመረዳት አያዳግትም። «እስቲ ዛሬ ምሳ ልጋብዝሽ፣ ቡና ላጠጣሽ» ብሎ ጉብሉ ወይዘሪቷን በንጹሕ ልቦና ቢጠይቅ እንኳ ነገሩን በቶሎ በወሲብ ላይ ታንጠላጥልና በመፍራት ግብዣውን «አሻፈረኝ» ትላለች ወይም ትቀበላለች። አንዳንዶቹ ግብዣውን እሺ ካሉ በኋላ ወሲብ ያልታከለበት መሆኑን ሲረዱም የሻጉራ ማየት ይጀምራሉ። «ቢንቀኝ ነው እንጂ» የሚሉም አሉ። በእነርሱ ቤት እንግዲህ «ክብርት» የሆነችው ለወሲብ የተፈለገች ብቻ ነች ማለት ነው። ፅዱ ወዳጅነት ስለሚለው ግን ሊሰሙም ሊረዱም አይፈቅዱም። ነገሩን እኔም ለማውዛት አልኩ እንጂ ወሲብ ከሌለበት ሴት የሚጋብዝ ከስንት አንድ ቢገኝ ነው።
በአንድ ወቅት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የኅብረ ትርዒት ፕሮግራም በተከታታይ ለተመልካች የቀረበ ጭውውት ትዝ ይለኛል። ለሁለት ወይም ለሦስት ተከታታይ ዕሑዶች ሳያሰልስ በረፋዱ ሰዓት የመጣው የስልክ ጥሪ ባል ሚስቲቱን ያጨቃጭቃል። እንስቷ ደዋይ የወንድ ድምፅ ካልሰማች ስልኩን መልሳ ትዘጋዋለች። ያኔ ሞባይል አልነበረምና ስልኩ ሲያቃጭል ሚስት እንደገና ተነስታ «ሀሎ» ስትል ድርግም ይላል። በዚሁ ምክንያት ባልና ሚስት ተነታረኩ፣ ብዙ ተዳረሱ።
በአንድ ጋዜጠኛ የተደረሰው ያ ጭውውት የኅብረተሰባችንን የወዳጅነትን ትርጓሜ በተገቢው መንገድ የመፈተሸ ባህሉ ገና ያልዳበረ መሆኑን ያመላክት ነበር። ደዋይዋ ለምን ሚስቱን በቀጥታ አታነጋግርም ነበር። ምናልባት ፅዱ መወዳጅነትን የተመረኮዘ፣ በባልደረብነት ላይ የተንተራሰ ትውውቅ ሊሆንም ይችላል። ሚስትየዋስ ገና የደዋይዋን ምንነት ሳታውቅ ከሜዳ ነገር ቋጥራ፣ በጥርጣሬ ተወጥራ አራስ ነብር ሆና መገኘትን ምን አመጣው? ይህ እንግዲህ ዘወትር በአመዛኙ ትዳር ውስጥ የሚታይ አስከፊ መልክ ነው።
ይህንና እነዚህን የመሳሰሉትን ሁኔታዎች በጥልቀት ስንመረምር ዘመናዊ ተብለው ለጊዜው መሰልጠን፣ ለወቅቱ መዘመን ምስክር ሊሆኑ ይበቃሉ የሚባሉት አንዳንድ ሰዎች እንኳ ገና የትናንት ወዲያ አዝጋሚዎች ሆነው እናገኛቸዋለን። አለባበስንና ቋንቋን ብቻ ይዘው የተቀመጡ በእሳቤና በግንዛቤ ግን የኮሰመኑ የመሰከኑ።
በውኑ የሚያሳሰብ ብዙም የሚያነጋግር ጉዳይ ነው። እንዴት የወዳጅነት ትርጎሜ ተወለጋግዶ ይቅር? ማቃናትስ አይቻልም ወይ?
ስለዚህ በመጀመሪያ ልናውቅ የሚገባን ግዙፉ ጉዳይ ‹‹የወንድ የሴት ግንኙነት›› ሲባል የግድ ‹‹ወሲባዊ›› ተብሎ መተርጉም እንደማይኖርበት ነው። ከዚህ ጠባብ እሳቤ ራሳችንን ነፃ ማድረግ ይኖርብናል።
ፍቅረኛ ሊኖር ይገባል። የሕይወት ተካፋይ የኑሮ ተጎዳኝ ማግኘት ይገባል። በዚያው ልክ ደግሞ የሚወዱት፤ የሚዋዋሉት፤ የልብ የሚያጫውቱት፤ ‹‹ወዳጅ›› ከየትኛውም ጾታ ሊኖር ይገባል። ሁሉንም በየፈርጁ መልበስ እንጂ ማዘበራረቅ ከንቱ ነው።
የወዳጅነትን ትርጎሜ የማወቅና መረዳት ጉልበታችን የጠነከረ መሆን ይኖርበታል። እንዲያው በአንድ አቅጣጫ ብቻ እየተመለከቱ ወልጋዳ ዳኝነትና የሐሰት ምስክርነት መስጠቱ ግን የትም ሊያደርሰን አይችልም።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 21/2011
ወዳጅ ማለት ምን ማለት ነው?