ዓለም የደረሰበት የሥልጣኔ ደረጃ ነገሮችን ከማቅለል ባሻገር ሰዎች ስራ ላይ የሚያሳልፉትን ጊዜና ጉልበት የሚቀንስ ሆኗል። እንደማሳያም “በይነ መረብ” ሰዎች ሥራዎችን በቤታቸው ወይም ባሉበት ቦታ ሆነው መስራት የሚችሉበትን እድል ፈጥሯል። በቅርብ ጊዜ የወጡ ጥናቶች እንደሚያሳዩት 16 በመቶ የሚሆኑ የዓለማችን ድርጅቶች የበይነ መረብ ስራዎችን የሚያሰሩ ናቸው። እነዚህና መሰል የስራ አጋጣሚዎች የአኗኗር ስልትን ማዘመን፣ የተሻለ ገቢን ማስገኘትና ለሌሎች ማሕበራዊ ጉዳዮች በቂ ጊዜ ማግኘትን ጨምሮ ብዙ ጠቀሜታዎች ይኖራቸዋል።
የበይነ መረብ ፋይዳ በተለይ በኮቪድ ወቅት በሚገባ ታይቷል፤ ወቅቱ ከቤት አትውጡ ይባል የነበረበት እንደመሆኑ ስራና ሰራተኛ የተቆራረጡበት ወቅት ቢባል ማጋነን አይሆንም። በዚያ ወቅት ግን ምስጋና ለቴክኖሎጂ ከቤታቸው ሆነው ስራቸውን የሚያከናውኑ ጥቂት አልነበሩም። ስራ ማከናወኛው መንገድ ደግሞ በየነ መረብ ነበር። አንዳንድ ሰራተኞች ቤታቸው ስራቸውን እየሰሩ በበይነ መረብ አማካይነት ወደ ተቋማቸው ይልኩ ነበር።
ሰዎች ከቤት በማይወጡበት፣ ብዙዎች በከሰሩበት በዚያ ወቅት በይነ መረብ ተጠቃሚዎች ግን ትርፋማ ሆነው እንደነበር በወቅቱ ሲዘገብም ነበር።
በበይነ መረብ የሚከናወኑ ስራዎች የተለያየ ፋይዳዎች ያላቸው መሆኑ ቢታመንም፣ ተአማኒነታቸውና ቀጣይነታቸው አጠራጣሪ የሚሆኑባቸው አጋጣሚዎችም ይስተዋላሉ። አጠራጣሪ ብቻም ሳይሆን ሕገወጥ የሚሆኑበት ሁኔታም ጥቂት አይደለም። በሀገራችን በእዚህ አይነት መንገድ በተደረጉ ግብይቶች ብዙ ሰዎች ገንዘባቸውን አጥተዋል። ለመሆኑ እነዚህ ግብይቶች እንዴት ነው የሚሰሩት።
ዲጂታል ገንዘብ
ዘመናችን ካመጣቸው አበይት ክስተቶች መካከል የክሪፕቶከረንሲ ቴክኖሎጂ አንዱ ነው። ክሪፕቶከረንሲ በዋነኝነት ቢትኮይን የሚባለው የብሎክቼን ስርዓት የሚጠቀም ቴክኖሎጂ ሲሆን፤ ሳቶሺ ናካማቶ በሚባል ማንነቱ እስካሁን ድረስ በግልጽ ባልታወቀ ሰው አማካኝነት እ.ኤ.አ በ2008 የተፈጠረ ነው። በ2009 ደግሞ ገበያ ላይ ለሁሉም ሰው ተደራሽ መሆን በሚችል መልኩ የተለቀቀ ሲሆን፤ ራሱን በራሱ መቆጣጠር በሚያስችል መልኩ እንዲሰራ ተደርጎ የተሰራ የዲጂታል ገንዘብ ሥርዓት ነው። ይህም የሃርድ ከረንሲ ወይም የወረቀት ገንዘብን በመተካት ከንክኪ ውጪ የሆነ ምናባዊ የገንዘብ ሥርዓት የፈጠረ ሲሆን፤ በዓለማችን የገንዘብ ሥርዓት ላይ የራሱን ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከት የቻለ ቴክኖሎጂ ነው።
ስለዲጂታል የገንዘብ ሥርዓት
የዲጂታል የገንዘብ ሥርዓት በሁለት ሰዎች መካከል የሚደረገውን የገንዘብ ልውውጥ ሥርዓት (ትራንዛክሽን) ለሚቆጣጠሩ ሰዎች ሥርዓቱ የሚሸልመው የተወሰነ ቢትኮይን ስላለ የኮምፒውተር እውቀት፣ የተሻለ አቅም ያለው ኮምፒውተር፣ የተሻለ የኤሌክትሪክ ኃይል እና የኢንተርኔት ፍጥነት ያለው ማንኛውም ሰው ቢትኮይኑን በመጠቀም ገንዘብ መስራት እንዲችል ተደርጓል።
አሜሪካ፣ አውሮፓ፣ ካናዳ፣ አውስትራሊያ፣ ፈረንሳይ፣ ጃፓን፣ እንግሊዝ፣ ስፔን፣ ሜክሲኮ እና ማዕከላዊ የአፍሪካ ሪፐብሊክ የቢትኮይን ሕጋዊ የገንዘብ ሥርዓት ከተፈቀደባቸው አገራት መካከል ሲጠቀሱ፤ በተቃራኒው ደግሞ ቻይና፣ ኢራቅ፣ አልጄሪያ፣ ሞሮኮ፣ ቱኒዚያ፣ ባንግላዴሽና ግብፅ ቢትኮይን በአገራቸው የመገበያያ ገንዘብ እንዳይሆን ከሚከለክሉ አገራት መካከል ይጠቀሳሉ።
በሀገራችን ደግሞ የቢትኮይን ጉዳይ ያሳሰበው ብሄራዊ ባንክ በዚህ ዲጂታል ግብይት መገበያየትም ሆነ ክፍያ መፈጸምን ሕገወጥ ሲል በቅርቡ መግለጫ አውጥቶበታል። ምናባዊ ገንዘብን ወይም ንብረትን ከግብይት ወይም ለክፍያ መጠቀም በኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ እውቅና ያልተሰጠው ድርጊት መሆኑን በመግለጽ ሕብረተሰቡ ከዚህ እይነት ድርጊት ራሱን እንዲጠብቅ አስገንዝቧል፤ ይህን ድርጊት በሚፈጽሙት ላይም ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቋል።
የክሪፕቶከረንሲ ተጠቃሚዎች ትርፍ ከሚያገኙባቸው በርካታ መንገዶች መካከል፤ አንዳንድ ተቋማት ደምበኛን ለመሳብ በስጦታ መልክ ሲያበረክቱ ሲሆን፤ ሌሎች ደግሞ የክሪፕቶከረንሲን በየጊዜው የዋጋ ለውጥ ማሳየትን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ገዝተው በማስቀመጥና ሲወደድ በመሸጥ ነው።
የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት፣ ክሪፕቶከረንሲ መንግሥት በጥሬ በሚያትመው ገንዘብ ምክንያት የሚፈጠረውን የዋጋ ግሽበት ለመከላከል የሚያግዝ መሆኑ እንደ መልካም አጋጣሚ የሚነሳ ሲሆን፤ በተቃራኒው ደግሞ የባንኮችን ሥራ መገዳደሩ እና የደሕንነት ስጋቶች መነሳታቸው እንደ መጥፎ ጎን የሚነሱበት ናቸው።
የዲጂታል ገንዘብ ማጭበርበር
ስለዲጂታል የገንዘብ ሥርዓት እንደሚሰራ ያህል ካየን፤ የዲጂታል/የክሪፕቶከረንሲ ማጭበርበር እንዴት እንደሚሰራ ለማየት እንሞክር። የዲጂታል ገንዘብ ሥርዓት ሥራው ብዙ ጊዜ በቡድን በተደራጁ ባለሙያዎች የሚሰራ ሲሆን፤ የፒራሚድ ሥርዓት ያለውና ከላይ ያሉት ሰዎች ከስራቸው ሰዎችን እያስገቡ ግብይቱን የሚያሳድጉበት ሂደት ነው። በዚህም ከስር የገባው ሰው ከሚፈጽመው ክፍያ በየደረጃው ከላይ ያሉ አባላት ገንዘብ እንዲያገኙ የሚደረግበት ሥርዓት ነው።
ይህም አሳማኝ ይሆን ዘንድ ማሕበራዊ የትስስር ገጽን የሚጠቀሙ ሲሆን፤ ለዚህ የተዘጋጁት ግለሰቦች ገንዘብ እንዴት እያገኙ እንደሆነና ሕይወታቸው እንዴት እየተቀየረ እንደሆነ በመተረክና በማስመሰል የተሳሳተ ተሞክሯቸውን ቪዲዮ በመስራት ሌሎችን ለማሳመን ይሞክራሉ። በተጨማሪም ገንዘብ ከፍለው ለገቡ አዳዲስ አባላት ከከፈሉት ገንዘብ በጥቂቱ በወኪሎቻቸው በኩል ወደ የባንክ አካውንታቸው እንዲገባ በማድረግ በጉዳዩ ላይ ያላቸው እምነት እንዲጨምርና ሌሎች ሰዎችንም ወደ ሥርዓቱ እንዲያስገቡ የሚያደርጉበትም ሁኔታ እንዳለ ማንነታቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የጉዳዩ ሰለባ የሆኑ ምንጮች ይገልጻሉ።
በቅርቡ ደግሞ ፊያስ (fias777.com) በሚል ስያሜ በሚጠራ ድርጅት ምክንያት ብዙዎች ለኪሳራ መዳረጋቸው እንዲሁም ተስፋ መቁረጥ ደረጃ መድረሳቸው እየተሰማ ይገኛል። እኛም ከዚሁ ላይ በማተኮር፣ ፊያስ ምንድነው? ምን አይነት የገበያ ሥርዓት ነው? ማን ማንን ተጠቃሚ ያደርጋል? እንዲሁም ተአማኒነቱስ ምን ያህል ነው? የሚሉ ተያያዥ ጥያቄዎችን በዚህ ጽሁፍ ውስጥ ለመዳሰስ እንሞክራለን።
“ኢትዮጵያ ቼክ” በማሕበራዊ ሚዲያ እና በመደበኛ ሚዲያዎች የሚቀርቡ ሀሰተኛ መረጃዎችን የሚያጣራ ዌብሳይት ፊያስ በተባለው ድርጅት ላይ ባደረገው ማጣራት፤ ድርጅቱ ራሱን የኮሚሽን ስራ የሚሰራ የማስታወቂያ ድርጅት ብሎ እንደሚጠራና አሰራሩም ቀላልና ክሊክ ማድረግን (መጠቆምን) ብቻ የሚጠይቅ፣ አባላቱም የሚሰጣቸው የስራ ብዛትና የሚያገኙት የገቢ መጠን እንደየደረጃው እንደሚለያይ ከቪ.አይ.ፒ ዜሮ (0) እስከ ቪ.አይ.ፒ አምስት (5) የደረጃ አይነቶች እንዳሉ ያብራራል።
ለምሳሌ፣ በቪ.አይ.ፒ 4 ደረጃ የሚገኝ አባል በቀን ውስጥ ከሚሰጡት 17 ስራዎች በአንዱ 18 ብር በመሰብሰብ በቀን 306 በወር ደግሞ 9ሺህ 180 ብር ማግኘት የሚያስችል መሆኑን ድርጅቱ ያስረዳል። በተጨማሪም ድርጅቱ ኢትዮጵያ ውስጥ 2 ሚሊዮን የሚሆኑ ተጠቃሚዎች እንዳሉት የሚገልጽ ሲሆን፤ በሕዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት እንዳገኘም ይጠቁማል።
“ኢትዮጵያ ቼክ” ባደረገው ማጣራት ግን ድርጅቱ ስለ አሰራሩ ከገለጸው በተቃራኒ ሆኖ ነው የተገኘው። ድርጅቱ እንደ QuestNet እና Tiens የፒራሚድ ስሌት ያለው አሰራር እንደሚጠቀም ‹‹ኢትዮጵያ ቼክ›› አረጋግጧል። እነዚህን አይነት ድርጅቶች ከዚህ ቀደም በሚከተሉት የፒራሚድ ስሌት አሰራር ብዙዎችን በማጭበርበራቸው ምክንያት ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይሰሩ እገዳ የተጣለባቸው መሆኑ ይታወሳል።
የፒራሚድ ንግድ ስሌት የሚባለው አንድ ሰው በስሩ ብዙ ሰዎችን በማስገባት እነርሱም ሌሎች ሰዎችን እንዲሁ በስራቸው በማስገባት ሰንሰለቱ የሚቀጥልበት አሰራር ነው። በዚህ ሰንሰለት ውስጥ ደግሞ ከላይ ያሉት አባላት ተጠቃሚ ሲሆኑ፤ ብዙዎች ግን ተጭበርብረው ይቀራሉ። ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ ቼክ የድርጅቱ አባላት የሆኑ ሰዎችን አነጋግሮ ባገኘው መረጃ መሰረት ድርጅቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ምዝገባም ሆነ ቢሮ እንደሌለው አረጋግጧል፤ ከዚህም አባላቱ ባለቤቶቹን የማወቅ እና የመጠየቅ መብት እንደሌላቸው መረዳት ይቻላል። ምንም እንኳን ድርጅቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ምዝገባ አካሂጃለሁ ሕጋዊ ነኝ ቢልም፤ በንግድ ሚኒስቴር የንግድ ምዝገባ ጽ/ቤት ግን እንዳልተመዘገበ ኢትዮጵያ ቼክ ማጣራቱን ይገልጻል።
ከኢትዮጵያ ቼክ በተጨማሪም የማጭበርበር ድርጊቶችን ከሚከታተሉት አንዱ የሆነው ScamAdvisor ስለ ፊያስ ባደረገው ማጣራት ድርጅቱ ተዓማኒነቱ በጣም የወረደ መሆኑንና ማጭበርበር ሊሆን እንደሚችል፤ እንዲሁም ይህንን ዌብሳይት በሚጠቀሙበት ጊዜ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ያሳስባል።
በአንድ ወቅት ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በሰራው ዘገባ ላይ እንዳመለከተው፤ በቲያንስ /Tiens/ አማካኝነት ሲተገበር የነበረው የአጋዥ ምግቦች የፒራሚድ ንግድ በ2008 ዓ.ም እገዳ ተጥሎበት ተቋርጦ ነበር። ሆኖም ግን ከ3 ዓመታት በኋላ ይህ አይነት የንግድ ስልት በ2011 መጨረሻ በድጋሚ ተመልሷል። ቲያንስ የተባለው ድርጅት አጋዥ ምግቦችን የሚሸጥ የነበረ ሲሆን፤ ሕገወጥ በሆነው የፒራሚድ ስልት በመጠቀሙ እና 200ሺህ የሚሆኑ አባላቱን አክስሮ በ2008 ዓ.ም ከተቋረጠ በኋላ ዳግም በ2011 ዓ.ም “ሪል ራይዝ ትሬዲንግ” በተባለው ጅምላ አከፋፋይ እና የችርቻሮ አከፋፋይ በሆነው በዊዝደም ኢምፓየር አማካኝነት ወደ ንግድ ሥርዓቱ መመለሱን ዘገባው ያስረዳል። ዊዝደም ኢምፓየር የተባለው ድርጅት የተባለውን አይነት ፒራሚዳዊ የንግድ ስልት እንደማይጠቀምና ከቲያንስ (Tiens) ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌለው ቢያሳውቅም፤ የተሰበሰቡት ማስረጃዎች ግን ይህንን ውድቅ የሚያደርጉ ሆነው ተገኝተዋል።
እነዚህ ከላይ የተመለከትናቸው ማሳያዎች እንደሚያሳዩት እንደ ፊያስ ያሉ የክሪፕቶከረንሲ ወይም የመስመር ላይ ስራዎች ተዓማኒነታቸው እጅግ አጠያያቂ በመሆኑ ሰዎች አባል ከመሆናቸው ወይም ስራውን ከመጀመራቸው በፊት አስፈላጊውን ማጣራት እንዲያደርጉ እና ራሳቸውን ከመጭበርበር ድርጊቶች እንዲከላከሉ ለመጠቆም እንወዳለን። ይሄም “ቀድሞ ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ አሁን ምን ያደርጋል ድስት ጥዶ ማልቀስ!” የሚለውን ተረት በራስ ላይ ከመተረት የሚታደግ አስፈላጊ ጥንቃቄ ነው።
ዳናት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሐሴ 4 /2014