ማክሮ ኢኮኖሚ የአገር ውስጥ ምርት፣ አገራዊ ገቢ፣ የሥራ ዕድል እና ሥራ አጥነትን እንዲሁም የኑሮ ውድነትን እንደሚያካትት የተለያዩ መረጃዎች ያመለክታሉ። በኢትዮጵያም የብሔራዊ ማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ ባደረገው ግምገማ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ2014 በጀት ዓመት በተለያዩ መመዘኛዎች ስኬት ማስመዝገቡ መግባባት ላይ ተደርሷል።
ግምገማው በተካሔደበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ እንደገለጹት፤ በወጪ ንግድ ዘንድሮ ከ10 ነጥብ 2 እና 3 ቢሊዮን ዶላር በላይ ከአገልግሎት ዘርፍ ብቻ ማግኘት ተችሏል። ይህ የሆነው ከዳያስፖራ የሚላከው እና የወጪ ቀጥተኛ ንግድ ኢንቨስትመንት ሳይጨመር ነው። ሁለቱ ሲጨመሩ ወደ 20 ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል። ይህ ለኢትዮጵያ ትልቅ አይደለም። ኢትዮጵያ ከዚህም በላይ ከዚህ አምስት እና ስድስት ሰባት እጥፍ ማግኘት እና ማደግ ትችላለች፤ ነገር ግን ኢትዮጵያ ከነበረችበት ሁኔታ አንፃር ይህ በጣም ትልቅ እምርታ ነው።
ይህ ውጤት አንድም በበጀት ዓመቱ ከውጪ የሚገቡ የግብርና ምርቶች በአገር ውስጥ እንዲመረቱ ማድረግ በመቻሉ እና የግብርናው ዘርፍ ዕድገት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በማስመዝገብ ረገድ ከፍተኛ ውጤት በማምጣቱ መሆኑን የሚገልጹት ደግሞ የግብርና ሚኒስቴር ዑመር ሁሴን ናቸው።
እንደሚኒስትሩ ማብራሪያ፤ በአራት ነገር ላይ ትኩረት በማድረግ የወጪ ምርትን ብቻ ሳይሆን ወደ አገር የሚገባ ምርትን የመተካት ሥራ ተሠርቷል ። በዚህ ውስጥ የአርሶ አደሩን ገቢ ማሳደግ እና የሥራ ዕድል መፍጠርም ሌላኛው ትኩረት ሆኖ ሲሠራበት ከርሟል። በተለይ የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ገቢ አብዛኛው ከቡና ምርት በመሆኑ ቡናን በጥራት ለዓለም ገበያ ለማቅረብ በተሠራው ሥራ ከዚህ ቀደም ሲነሱ የነበሩ ችግሮችን መፍታት ተችሏል።
ሁልጊዜ ለዓመታት የተተከለው የቡና እግር ላይ ብቻ ከማተኮር ይልቅ ከአረንጓዴ ልማቱ ጎን ለጎን በተለያዩ ክልሎች ከሶስት ሚሊዮን ችግኝ በላይ ተተክሏል። ይህም ከአራት ዓመት በኋላ በአስተማማኝ መልኩ እንዲቀጥል በሚያስችል መልኩ እየተሠራ መሆኑን ያመለክታል።
ሌላው ማክሮ ኢኮኖሚው ላይ ስኬት እንዲገኝ በማስቻል በኩል ተጠቃሹ የትራንስፖርት ዘርፍ ነው። የአገሪቱን የወጪ እና የገቢ ንግድ በማሳለጥ ለተጠቃሚው እንዲደርስ በማድረግ ረገድ የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክ ሚኒስቴር ከፍተኛ ውጤት የተመዘገበባቸውን ሥራዎች ሰርተዋል የሚሉት የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክ ሚኒስትሯ ዳግማዊት ሞገስ ናቸው።
እንደሚኒስትሯ ማብራሪያ፤ የማዳበሪያ አቅርቦትን በጊዜው በማድረስ የተገኘውን ስኬት በማሳያነት ሊጠቀስ የሚችል ነው። ከወጪ እና ከገቢ ንግድ ጋር ተያይዞ የተመሰረቱ ምርቶችን ለዓለም ገበያ ለማቅረብ፤ ከውጭም የሚገቡትን ምርቶችን ወደ አገር አምጥቶ እስከ መጨረሻው ተጠቃሚ ከማድረስ አንፃር የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክ ሚናውን በአግባቡ ተወጥቷል።
በዚህ ዓመት ከ 13 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በላይ ወደ አገር የሚገባ ምርት ነበር። ከዚህ ውስጥ የማዳበሪያ ግብዓትን ማንሳት ይቻላል። ኢትዮጵያ በጅቡቲ ወደብ ላይ ብቻ ጥገኛ በመሆኗ በወጪ እና ገቢ ንግድ ዘርፍ በርካታ ችግሮች እንደነበሩ የሚታወስ ቢሆንም፤ ተጨማሪ ወደቦችን መጠቀም በመቻሉ የመርከቦችን የቆይታ ጊዜ እና የውጭ ምንዛሪ ወጪን መቀነስ ተችሏል። የጅቡቲ ወደብ አጠቃቀም 98 እና 99 በመቶ ይደርስ የነበረ ቢሆንም፤ በእዚህ ዓመት ግን ወደ 84 በመቶ ማውረድ ተችሏል። ይህ የሆነው የታጁራ ወደብን የመጠቀም ድርሻ ከዘጠኝ በመቶ በላይ ከፍ ማድረግ በመቻሉ እና የበርበራ ወደብንም እንደዚሁ መጠቀም በመቻሉ መሆኑን አመላክተዋል።
ሌላው ኢትዮጵያ በማክሮ ኢኮኖሚ የተሻለ አፈፃፀም እንዲታይባት ካስቻሉት መካከል የባንኩ ዘርፍ ሌላኛው ነው። ባንክን በተመለከተ በተቀማጭ የሀብት መጠን ብድር በማስመለስ ምጣኔ እና በሌሎች የጤናማነት መለኪያዎች የተሻለ አፈፃፀም ማስመዝገብ መቻሉ ታውቋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ ዶክተር ይናገር ደሴ እንደሚናገሩት፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የባንኮች ተቀማጭ ሀብት አንድ ነጥብ ሰባት ትሪሊዮን ብር ደርሷል። ይሄ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር 26 ነጥብ 7 በመቶ አድጓል። ባለፈው አንድ ዓመት ባንኮች ብድር የማስመለስ አቅማቸውን በ48 ነጥብ 7 በመቶ ማሳደግ ችለዋል። ለግሉ ዘርፍ የሚያቀርቡት የብድር ምጣኔም በከፍተኛ መጠን የጨመረ ሲሆን ይህም በአጠቃላይ የባንኩ ዘርፍ በተሻለ አፈፃፀም ላይ መሆኑን የሚያመላክት ነው።
በዓለምም ሆነ በአገር ደረጃ አንዳንድ ነገሮች ቢያጋጥሙም የፋይናንስ ዘርፉ ጤናማ ዕድገት አሳይቷል። በ2014 በጀት ዓመት የፋይናንስ ዘርፉ አፈፃፀሙ በጥሩ ሁኔታ አልቋል። ለግል ዘርፉ የሚቀርበው የውጭ ምንዛሬ መጠንም በከፍተኛ መጠን ጨምሯል። በሌላ በኩል የቴሌ ብር ወደ ሥራ መግባቱን ተከትሎ ዲጂታል ፋይናንስ ሥርዓት እየጎለበተ መጥቷል። ይህም ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርን እና ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር የዋጋ ግሽበት እንዲረጋጋ እንደሚያግዝም ተናግረዋል። ይህ ሁሉ ቢሆንም ለግል ዘርፉ የሚቀርበው የውጭ ምንዛሬ መጠን በቂ አለመሆኑ አሁንም በድክመት የሚነሳ ነው።
የንግዱ ማሕበረሰብ እና አጠቃላይ የግል ዘርፉ የውጭ ምንዛሪን በሚፈልገው መጠን ማግኘት ባለመቻሉ የውጭ ምንዛሪ ተመኑ በባንኮች እና በውጭ በሚመነዘረው መካከል በየጊዜው እየሰፋ መሆኑ ታይቷል። ይህንን ለመቀነስ የውጭ ምንዛሪ ማግኛ መንገዶች ላይ በስፋት መሠራት እንዳለበት ጠቁመዋል።
የብሔራዊ ማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ አባል አቶ ተክለወልድ አጥናፉ በበኩላቸው፤ የፋይናንስ ዘርፉን ለማሻሻል የተከናወኑ የለውጥ ሥራዎች ዘርፉን ከውድቀት እንደታደጉት በመጠቆም፤ ለአብነት ባለፉት 4 ዓመታት የባንኮች ቅርንጫፍ ቁጥር በ30 በመቶ ማደጉን ይገልጻሉ። በዚህ ምክንያት ቅርንጫፎቹ 8 ሺህ ደርሰዋል። 82 ሚሊዮን ዜጎች የቁጠባ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ መሰራቱንም አብራርተዋል። ነገር ግን ከዓለም አቀፉ ጂኦ ፖለቲካ መለወጥ ጋር ተያይዞ የዋጋ ንረት አሁንም የኢትዮጵያ ፈተና ሆኖ መቀጠሉን በማስታወስ፤ ተጎጂዎችን ለመታደግ ግብርና መስኖ እንዲሁም ለመንገድ በአጠቃላይ የመንግሥትን በጀት 59 በመቶ የሚሆነውን ወጪ በማውጣት ሕብረተሰቡ የኑሮ ሁኔታው እንዲረጋጋ እየተሠራ መሆኑን አመላክተዋል።
መንግሥት የኑሮ ውድነቱን ለማቃለል ከቀረጥ ነፃ በማስገባት ማግኘት ከሚገባው ገቢ እስከ 50 ቢሊዮን ብር ነው ያጣው፤ ችግሩን ለማቃለል ከሚፈለገው በላይ ገንዘብ ወደ ገበያ እንዳይገባ መቆጣጠር እና ድህነትን የሚቀንሱ የልማት ሥራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት፤ በአገር ውስጥ ያለውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት ያስችላል።
በቀጣይ የወጪ ንግድ ላይ ምን ያህል ትኩረት መሠጠት እንዳበት እና የወጪ ንግድም ዋነኛው መሠረት መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በምሳሌ አስደግፈው ሲያብራሩ ‹‹የወጪ ንግድ መታየት ያለበት እንደወተት ነው። ወተት በዕለቱ ይጠጣል፤ ይሸጣል። ሲያድር ይረጋል፤ እርጎውም ይሸጣል፤ ይጠጣል። በመቆየቱ ዋጋው አይቀንስም። እርጎ መሸጥ ያልፈለገ ሰው አይብ አድርጎ ይሸጠዋል። ወይም ቂቤ ያወጣል። አሬራው ሳይቀር ይጠጣል። የወጪ ንግድ እንደዚህ ነው። ዛሬ አራት ሚሊዮን ዶላር ቢመጣ ዕዳ እና የፍጆታ ፍላጎትን መሸፈን ይቻላል። ከፊሉን ተጠቅመን ከፊሉን እናቆየው እና መጠባበቂያ ይሁን ካተባለም በማንኛውም ሰዓት የሚመነዘር በመሆኑ ማቆየት ይቻላል።›› በማለት ለማክሮ ኢኮኖሚ የወጪ ንግድ ዘርፉ ምን ያህል የደም ስር እንደሆነ ያስረዳሉ። የተከማቸ ዕዳ ለመቀነስ እና አዳዲስ ፕሮጀክት ለመጀመር እና የገበያ መረጋጋት ለመፍጠር ለሁሉም የወጪ ንግድ አስፈላጊ ነው ይላሉ።
የወጪ ንግድ ላይ ያልተሳካለት ኢኮኖሚ በብዙ ምክንያት ማደግ አይችልም። ምንም እንኳ የማክሮ አመላካቾች ብዙ ቢሆኑም ዋናው ግን በወጪ ንግድ ምን አመጣሁ? የሚለው ነው። እርሱ ሲስተካከል ብዙዎቹን አመላካቾችን መቀየር ማደግ እና ማስተካከል ይቻላል ብለዋል።
እንደጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ፤ ለምሳሌ በውጭ ምንዛሪ ግብርና ማደግ ይችላል። አርሶ አደሩ ማሽኖችን ካስገባን እና መስኖ እንዲሠራ ካገዝነው ‹‹ምርቴን አሳድጋለሁ›› ይላል። ስለዚህ የወጪ ንግድ ካደገ እና ገንዘብ ካለ ግብርናን መደገፍ ይቻላል። አርሶ አደሩ የሎጀስቲክ ጥያቄ ካቀረበ እና መንገድ ካልሠራችሁልኝ መኪና ካላመጣችሁልኝ እንዴት ችግሬን እፈታለሁ? ካለ ምላሽ መስጠት የሚቻለው የውጭ ምንዛሪ ካለ ብቻ ነው። ስለዚህ በወጪ ንግድ ላይ እድገት መጣ ማለት ሌሎቹን ዘርፎች እየደገፈ የሚፈለገውን ውጤት መምጣት ይቻላል። የወጪ ንግድ ላይ ሳይሳካ የግብርና ምርት ቢያድግም 20 እጥፍም ቢሆን በውስጥ ችግር ባይኖርም አስተማማኝ ማድረግ አይቻልም።
የወጪ ንግድ ላይ መኖር ያለበት ዕይታ ልክ እንደወተቱ ነው። በማንኛውም ጊዜ የማይወድቅ የሚበላ የሚሸጥ የሚጠቅም መሆኑ መዘንጋት የለበትም። የተሻለ እምርታ የመጡት የወጪ ንግድን ያሳደጉ አገራት ብቻ ናቸው ፤ ይህ መሆኑ በደንብ መያዝ እና በዚህ ሃሳብ ላይ መሰራት አለበት። ይህ ሲባል የግብርና ምርትን ወደ ውጪ በመላክ ብቻ ሳይሆን እንደቱሪዝም ያሉ ሌሎች ዘርፎች ላይም ትኩረት ተሰጥቶ መሠራት እንዳለበት ያብራራሉ።
ከቱሪዝም አንፃር እንደ ኢትዮጵያ ሊሸጥ የሚችል ሀብት ያለው አገር እንደሌለ በመጥቀስ፤ ታሪክ፣ ታይተው የማይጠገቡ ሰንሰለታማ ተራሮች እንዲሁም የዱር አራዊት እና ሌሎችም የአገሪቷ መልከዓ ምድር ያቀፋቸው ሀብቶች ቢኖሩም የአገልግሎት ኢንዱስትሪው ዘምኖ መሸጥ ካልቻለ መጠቀም እንደማይቻል ያስረዳሉ።
በቱሪዝም ሌሎች አገራት ፀሃይ፣ አሸዋ እና ባህር ብቻ ይዘው አሸዋ ላይ ዛፍ በመትከል ውሃውን ገፍተው አስደማሚ ሪዞርት በመገንባት ብዙ እያገኙ መሆኑን በማስታወስ፤ ባህርዳር እና ጎርጎራ መሃከል ላይ ያለውን ደጋ እስጢፋኖስን በማስጎብኘት ዛሬም ድረስ አፅማቸው ሳይበሰብስ የቆዩትን ነገሥታት እና በዚያ ዘመን ከ500 ዓመት በፊት በምን ዓይነት ዕቃ የነገሥታቱን አፅም ማቆየት እንደተቻለ ማሳየት ቢቻል ትልልቅ ውጤቶችን ማግኘት ይቻላል ይላሉ።
የህዳሴው ግድብ አካባቢም ብዙ የከፍታ ቦታዎች በመኖራቸው፤ አንድ ከፍታ ለአንድ ሪዞርት በማለት ብዙ መጠቀም እንደሚቻል እና እንደውም የቆየ ውሃ እና ባህር ሳይሆን ትኩስ ውሃ ላይ መዝናኛን በመፍጠር ብዙ መጠቀም እንደሚቻል ለዚህም ብዙ አቅም መኖሩን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል።
ከሁሉ በላይ ግን የሰው ሃይልን መጠቀም ነው ካሉ በኋላ፤ ብዙ አገራት መቀጠል የቻሉት በቂ የሰው ሃይል ስለነበራቸው መሆኑን ገልፀዋል። ነገር ግን ቁጥራቸው አነስተኛ ሆኖ በጣም በርካታ ሰውን ከውጪ ያመጡ አገራት የውጪው ሰው ጥሎ ሲሔድ ወደቡም ሆቴሉም ዝግ እንደሚሆን በማስታወስ፤ አገሬ ብሎ ሞትን የሚጋፈጥ ሰውን በማሰማራት፣ በማስተማር እና በማቅናት ሕዝቡን ሥራ ወዳድ ማድረግ ከተቻለ ትልቅ ለውጥ የሚመጣ መሆኑን ገልፀዋል።
በተቃራኒው በከፍተኛ ደረጃ እርዳታ የሚጠብቅ እና የልመና ባህልን የተለማመደ ትውልድ እየተፈጠረ ከቀጠለ ለብልፅግና ፀር መሆኑን ጠቁመዋል። ቁጭ ብሎ በሰበብ አስባቡ ችግር ተናግሮ መረዳት የሚያስብ ሃይል ሳይሆን ሰርቶ ደክሞ ለውጥ የሚያመጣ ሃይል መፈጠር ከተቻለ የማክሮ ኢኮኖሚው ስኬት ከዚህም በላይ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል። ሃይል እና ማዕድን ኢንዱስትሪን በጣም ስለሚያግዙ ሁለቱ ላይ ለየት ያለ ሥራ በቀጣይ መስራት እንደሚኖርበትም አክለዋል።
ሚኒስትሯ ዳግማዊት ሞገስ በበኩላቸው በ2014 በጀት ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ የሞያሌ ኮሊደርን የሞምባሳ ወደብን በመጠቀም ምርቶችን ወደ ሀገር ቤት ማስገባት የተቻለ ቢሆንም፤ በ2015 በጀት ዓመት ከዚህ የላቀ ስኬት ለማስመዝገብ እንደሚሠሩ እና ትልቅ ውጤት ይገኛል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሃሳብ በሚደግፍ መልኩ የተናገሩት ዶክተር ይናገር ደሴም በቀጣይ የወጪ ንግድን ጨምሮ የውጭ ምንዛሬን ግኝቱን የሚያሻሽሉ ተግባራትን በማከናወን የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ችግርን ለመቅረፍ ይሠራል የሚል እምነት እንዳላቸው በመጠቆም፤ በ2015 በጀት ዓመት በወጪ ንግድ ላይ ከፍተኛ ርብርብ ለማድረግ የተለጠጠ ዕቅድ መታቀዱን እና በግብርናና በማኑፋክቸሪንግ እንዲሁም በማዕድን እና በቱሪዝም ላይ ትልልቅ ሥራዎችን በመሥራት የውጭ ምንዛሪ ሊገኝባቸው የሚችሉ አማራጮች በማስፋት ከዚህ የተሻለ ውጤት ለማምጣት መታቀዱን አመላክተዋል።
ምህረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 3/2014 ዓ.ም