የዘንድሮው የውድድር አመት ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ የተለየ ሆኖ እየተገባደደ ይገኛል። ከሳምንታት በፊት በ18ኛው የኦሪገን የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና አስደናቂ ውጤት በማስመዝገብ አሜሪካንን ተከትሎ በታሪኩ ሁለተኛ ሆኖ ያጠናቀቀው የኢትዮጵያ ቡድን ጣፋጭ ድል ሳይረሳ ሌላ ተጨማሪ አስደሳች ውጤት ተመዝግቧል። የኦሪገን ቻምፒዮና በተጠናቀቀ ማግስት ወደ ደቡብ አሜሪካዋ ኮሎምቢያ ያቀናው የኢትዮጵያ ወጣት የአትሌቲክስ ቡድን በካሊ የዓለም ከ20 አመት በታች የዓለም ቻምፒዮና ሌላ ታሪክ ማስመዝገብ ችሏል።
በውድድሩ ታሪክ ስድስት ወርቅ፣ አምስት ብርና አንድ የነሐስ ሜዳሊያ በማስመዝገብም ከዓለም ሦስተኛ ከአፍሪካ ደግሞ ቀዳሚ ሆኖ ማጠናቀቅ ችሏል። ላለፉት ስድስት ተከታታይ ቀናት ሲካሄድ በሰነበተው የዓለም ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ቻምፒዮና በ19 አትሌቶች በሁለቱም ፆታ በ10 የውድድር ተግባራት ብቻ የተሳተፈው የአትሌቲክስ ቡድን በድምሩ በ12 ሜዳሊያዎች ከዓለም አገራት አሜሪካንን እና ጃማይካን ተከትሎ 3ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል። ይህም ውጤት እስከ ዛሬ ከተካሄዱት የዓለም ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ቻምፒዮናዎች ከፍተኛው ሲሆን ከተሳተፉበት ውስን ውድድሮች አንፃር ውጤቱ በርካቶችን ያስደሰተ ሆኗል።
በውድድሩ ኢትዮጵያ ይዛ ካጠናቀቀችው ደረጃ ባሻገር አራት ወርቆችና ሁለት የብር ሜዳሊያዎች ቻምፒዮናው ከትናንት በስቲያ ሌሊት ሲጠናቀቅ የተመዘገቡበት መንገድ በርካቶችን አስደስቷል። እነዚህ ሜዳሊያዎች በአንድ ሌሊት አንድ ሰዓት ባልሞላ ሰዓት ውስጥ ሲመዘገቡ በወንዶች ስምንት መቶ ሜትር ወርቅ፣ በወንዶች 3ሺ ሜትር መሰናክል ወርቅና ብር፣ በሴቶች 1500 ሜትር ወርቅና በሴቶች አምስት ሺ ሜትር ወርቅና ብር የኢትዮጵያ ሆኗል።
ከቀናት በፊት በ1500 ሜትር የብር ሜዳሊያ ያጠለቀው ወጣቱ አትሌት ኤርሚያስ ግርማ በ800 ሜትር ተጨማሪ ወርቅ በማጥለቅ በቻምፒዮናው የጎላ ኢትዮጵያዊ አትሌት ሆኗል። በ3ሺ ሜትር መሰናክል ወንዶች ሳሙኤል ዱጉና የወርቅ ሜዳሊያውን ሲያጠልቅ ሌላኛው ኢትዮጵያዊ ወጣት አትሌት ሳሙኤል ፍሬው በድንቅ ብቃት የብር ሜዳሊያውን ወስዷል። ከባድ ፉክክር ባስተናገደው በ5ሺ ሜትር ሴቶች ውድድር መዲና ኢሳ እና መልክናት ውዱ በተመሳሳይ ወርቅ እና ብር ሜዳሊያ ሲያጠልቁ፣ በ1500ሜ ሴቶች ደግሞ በአትሌት ብርቄ ሀየሎም (4:04.27) የቻምፒዮናውን ክብረወሰን በማሻሻል ጭምር የወርቅ ሜዳሊያ ማሸነፍ ችላለች።
ከፍጻሜው ቀን አስቀድሞ በነበሩ ሌሎች ውድድሮች ኢትዮጵያ በ5 እና 3ሺ ሜትር ወንዶች በአዲሱ ይሁኔ እና መልኬነህ አዘዝ የወርቅ፣ በ3ሺ ሜ መሠናክል ሴቶች በሲምቦ አለማየሁ፣ በ1500 ሜትር ወንዶች በኤርሚያስ ግርማ እና በ3ሺ ሜትር ሴቶች በፅዮን አበበ የብር ሜዳሊያዎችን ያሸነፈች ሲሆን፣ በተጨማሪም በሴቶች 3ሺ ሜትር መሰናክል በአትሌት መሠረት የሻነህ የነሐስ ሜዳሊያ ማግኘቷ ይታወቃል።
ይህንን ውጤት ተከትሎም ኢትዮጵያ በሜዳሊያ ሰንጠረዡ በስድስት ወርቅ፣ አምስት ብር እና አንድ የነሐስ በድምሩ በ12 ሜዳሊያዎች፡ ከአሜሪካ እና ጃማይካ በመቀጠል ከዓለም ሦስተኛ ከአፍሪካ ደግሞ በቀዳሚነት ውድድሯን ፈጽማለች። በ19 ወጣት አትሌቶች እና በ10 የውድድር ዓይነቶች ተሳትፎ ብቻ የተገኘው ይህ አስደናቂ ውጤት በቻምፒዮናው ታሪክ የኢትዮጵያ የምንጊዜም ከፍተኛው ሆኖ ተመዝግቧል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 2 ቀን 2014 ዓ.ም