እንደ አገር የትምህርት ተደራሽነቱ የሰፋ ቢሆንም የጥራቱ ጉዳይ ግን ሁሉንም የሚያነጋግርና የሚያሳስብ ከሆነ ሰነባብቷል። ከዚህ ጋር ተያይዞም ችግሩን የተረዳው የትምህርት ሚኒስቴር የተለያዩ ሥራዎችን እየከወነ ነው። ከእነዚህ መካከልም የአመራር ለውጥ ላይ መሥራትና ጥራት ያለው ትምህርትቤት መገንባት አንዱ ሲሆን፤ እንደ ክልል ተልእኮው ተሰጥቶ እየተከወነም ይገኛል። እኛም ለዛሬ ለትምህርት ጥራት አጋዥ የሆነውን ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት ቤት በመገንባት በብዛት ሲያስመርቅ ያየነውን የኦሮምያ ክልልን በመምረጥ ምን ምን ተግባራት እየተከወኑ እንዳሉ ለመዳሰስ ሞክረናል። በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡን የክልሉን ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቶላ በሪሶን የጋበዝን ሲሆን፤ ያደረግነውን ቆይታም እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
አዲስ ዘመን፡- በኦሮሚያ ክልል ያለው የመማር ማስተማር አጠቃላይ ገጽታ ምን ይመስላል?
ዶክተር ቶላ፡- አጠቃላይ ገጽታውን ለመግለጽ መጀመሪያ ቀደም ሲል የነበረውን ተግባርና እንቅስቃሴ ማንሳት ያስፈልጋል። በተለይ የለውጥ አመራሩ በ2010 ዓ.ም ከገባ በኋላ ምን ለውጦችን እያመጣ ሄደ የሚለውን መዳሰስ ግድ ይሆናል። ለዚህ ደግሞ መነሻ የሚሆነው አመራሩ ሲመጣ መጀመሪያ ምን ሰራ የሚለው ነው። እናም ለዚህ ጥያቄ ምላሽ የሚሆነው የቀደሙ ችግሮችን ለማወቅ ጥናት ያደረገ ሲሆን፤ ይህ ጥናትም የኦሮምያ ክልል የትምህርት ችግሮች በብዛት ያሳየና ለመፍትሄው ያነሳሳ ነው። ዋና ዋና የተባሉ ችግሮችን እንድንፈታ የሆንበትም ነው ተብሎ መወሰድ ይችላል።
ከችግሮቹ በመነሳት ከአመራር ለውጥ ጀምሮ ሥራዎች ተከናውነዋል። የመምህራንና የተማሪዎች ችግርም በስፋት ታይተው መፍትሄ የሚያገኙበት ሁኔታ ውስጥም ተገብቷል። ይህ ሥራ ሲሰራም የክፍል ደረጃን ጭምር በለየ መልኩ ነው። ማለትም ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ እስከ መሰናዶ ድረስ ያሉት እንዲሁም ልዩ ትምህርትቤቶችና አዳሪ ትምህርትቤቶች ተቃኝተውበታል። በዚህም እንደ ክልል ብዙ ለውጦች የመጡበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
አዲስ ዘመን፡- የትምህር ጥራትን ለማሻሻል እንደ ክልል ምን አይነት ተግባራት እየተከናወኑ ናቸው?
ዶክተር ቶላ፡- የትምህርት ችግር ሰው አይቶ የሚረዳው አይደለም። እጅግ ውስብስብና ጥልቅ ነው። እናም ችግሮቹን ለመፍታት ጊዜና በጀት እንዲሁም የአመራር ጥበብን ይጠይቃል። በዚህም በዋናነት አራት ተግባራትን ለመከወን እቅድ ይዘን ወደ ተግባሩ ገብተናል። ለዚህ ደግሞ በጀት ዋነኛ ጉዳይ በመሆኑ 65 ቢሊዬን ብር እንደሚያስፈልገንም በጥናት አረጋግጠንም ነው የገባነው። ነገር ግን በወቅቱ ክልሉ እንኳን የተመደበለት በጀት 54 ቢሊዬን ነበር። ስለዚህም ለእኛ 65 ቢሊዮን ብር ሊመድብ አይችልም።በመሆኑም ስፋት ያላቸው ሥራዎችን ለማከናወን ሌላ አቅጣጫ መከተል ግድ መሆኑን አምነን በሁለት መንገድ ተግባሩ እንዲከናወን ሆኗል። በመንግስት አቅምና በማህበረሰቡ እገዛ።
የመጀመሪያ ትኩረት ያደረግነው ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገቡ ተማሪዎች ላይ ሲሆን፤ በቁጥርም ሆነ በውጤት አናሳ ናቸውና ለምን ሆነ የሚል ጥያቄ ይዘን ተነሳን። ታችኛው ክፍል ላይ 10 ሚሊዬን የሚሆን ተማሪዎች አሉ። ሆኖም የሁለተኛ ደረጃ ተማሪው ቢበዛ ሁለቱን ሚሊዬን ብቻ ነው የሚሸፍነው። ከአጠቃላይ የኢትዮጵያ ተማሪዎች አንድ ሶስተኛውን የሚይዘው ክልል ኦሮምያ ነው። ነገር ግን በክልሉ የሚመዘገበው ከፍተኛ ውጤት በተለይ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ከዘጠኝ አይበልጡም። ዩኒቨርሲቲ የሚገቡትም ጥቂቶች ናቸው። ስለዚህም ተማሪዎችን በጥራት ለማስተማር ጥራት ያላቸውን ትምህርትቤቶች መገንባት አንዱ የመፍትሄ መንገድ በመሆኑ ወደ ሥራ ለመግባት ችለናል። የትምህርትቤቶች ምቹ አለመሆንም እንዲሁ ተማሪዎች ውጤታማ እንዳይሆኑ የሚያደርጋቸው ነውና ይህንን ለመቀየርም ብዙ ተግባራት ተከናውነዋል። ለአብነት ብዙ የዳስ ትምህርትቤቶችን ወደ ትምህርትቤት መቀየርና የክፍል ተማሪ ጥምርታውን ማሻሻል አንዱ ነበርም።
ሌላው በጥናት የተለየው ችግር ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ክፍል የሚማሩ ተማሪዎች ጉዳይ ሲሆን፤ ማንበብና መጻፍ የማይችሉ ነበሩ። ለዚህ ደግሞ መንስኤው የቅድመ መደበኛ ትምህርትቤቶች በክልሉ ላይ አለመኖራቸው ነበር። ቢኖሩም በግል የሚሰሩ እንጂ በመንግስት የሚተዳደሩ አይደሉምና አቅም ለሌለው ሰው አይሆኑም። በዚያ ላይ በፖሊሲም አልተደገፈም። እናም ይህንን በመፍታትም በኩል ትልልቅ የሚባሉ ተግባራት ተከውነዋል።
ሌላው የተለየው መምህራን ላይ የነበረው ችግር ሲሆን፤ በወቅቱ 13 ኮሌጆች ቢኖሩም በማሰልጠኛዎቹ ውስጥ መምህራን ተገቢውን ስልጠና ሳያገኙ ይወጣሉ። ይህ ደግሞ መማር ማስተማሩን በእጅጉ ሲጎዳው የቆየ ጉዳይ ሆነዋል። በጣም ብዙ ቁጥር ያላቸው መምህራንን በኤክስቴንሽን ጭምር በማስገባት ይማራሉ ።ብቃታቸው ግን እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም። እንደውም ሲኦሲ ሲፈተኑ እንኳን የሚያልፉት በጣት የሚቆጠሩ ናቸው። ስለዚህም ኤክስቴንሽን የሚባል ነገር እንዲቆምና መምህራንም ወደ ስልጠና ተቋሙ ሲገቡ በብቃት ተለይተው መሆን እንዳለበት ተወስኖ ወደሥራ ተገብቷል። በዚህም 90 በመቶው ሲኦሲ እንዲያልፉ አድርጓል። ጥራት ያለው የመማር ማስተማር ሥራም ተፈጥሯል።
ትምህርት የጀመሩትን ምንም ማድረግ ስለማይቻል በተሸለ አካሂድ እየተመራ እንዲያጠናቅቁና ውጤታማ እንዲሆኑም ተደርጓል። ከሶስት ሺህ በላይ መምህራንም ማስመረቅ የተቻለው በዚህ መንገድ በመኬዱ ነው። አሁንም ቢሆን የቅድመ መደበኛ ትምህርትን የሚያስተምሩ ስድስት ሺህ መምህራንን በመመልመል እንዲሰለጥኑ እየተደረገ ነው። በተጨማሪ ቅድመ መደበኛ ትምህርትን የሚከታተሉ ተማሪዎች በእድሜም ሆነ በትምህርት ብቃታቸው የተሻሉ ሆነው እንዲወጡ ብዙ ማሻሻያዎች ተደርገዋል። አንዱ ሁለት ዓመት በዚህ እንዲቆዩ መደረጉ ሲሆን፤ ሁለተኛው አምስት ዓመት ሳይሞላቸው መግባት አለመቻላቸው ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከትምህርትቤት ግንባታ ጋር በተያያዘ የሪፎርም ሥራዎችን እያከናወናችሁ እንደሆነ ተሰምቷል። መነሻችሁ ምን ነበረ? ምን ያህሉስ ተገነቡ?
ዶክተር ቶላ፡- ከላይ እንዳልኩት መነሻችን ጥናት ነው። ምን ያህል ያስፈልጋሉ በምን ያህል በጀት የሚለው ነው። በዚህም ለመንግስትና ለህብረተሰቡ ተከፋፍሎ ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርትቤቶችንና አዳሪ ትምህርትቤቶችን መንግስት እንደሚሰራ የተሰጠ ሲሆን፤ ቅድመ መደበኛውንና ተጨማሪ ትምህርትቤቶችን ደግሞ በሕዝቡ ተሳትፎ የሚሰራበትን መንገድ ፈጥረናል። በዚህም በሕዝብ ተሳትፎ ብቻ ከሦስት ሺህ በላይ ትምህርትቤቶች በዓመት ውስጥ ማጠናቀቅ ችለናል። ለዚህ ደግሞ በሕዝቡ ገንዘብ መዋጮነት የተመሰረተው በኦሮምኛው ተጃጅለ ለሙማ (የዜግነት አገልግሎት) ተሳትፎ ትልቁን ድርሻ የሚወስድ ነበር።
የመጀመሪያ ሙከራ የተካሄደው በተጨማሪ ክፍሎች ላይ ሲሆን፤ 30 ሺህ ትምህርትቤት ለመገንባት አቅደን 34 ሺህ ትምህርትቤቶችን ገንብቶ አስረክቦናል። በተጨማሪም መጸሐፍትን ማሰባሰብና ተማሪዎችን ማገዝ ላይም ትልቅ ሥራ ማከናወንም ተችሎበታል። ለአብነት መጸሀፍ የመጀመሪያ ዓመት 2 ሚሊዬን ቀጣይ ሶስት እያለ እስከ አምስት ሚሊዬን መጸሐፍ መሰብሰብና ማገዝ ተችሏል።
ሕዝቡ ሦስት ሺህ አቅደን ከዚያ በላ የሠራም ነው። ይህም ሰባት ነጥብ አምስት ቢሊዬን ብር ወጪ የተደረገበት ሲሆን፤ በሦስት ዓመት ውስጥ 12ሺህ ያስፈልገናልና ይህንን ለማሳካትም እየተጋ ነው። ስድስት ሺህ በዚህ ክረምት ለማጠናቀቅም እየተሰራ ነው። በመጪው ዓመት ደግሞ የቀረውን 2300 እንደምንጨርስም እምነት አለኝ። አሁን ያለው የወጪ መጠን 30 ቢሊዬን ብር ሲሆን፤ አንዱ የሚሰራው አምስት ቢሊዬን ነው። ይህ ወጪ ግን ለሕዝቡ ከብዶት እንደማያውቅ እያሳየ ነውና ሊመሰገን ይገበዋል።
ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቤትን በተመለከተ ለጨፌው ቀርቦ ውሰኔ ተሰጥቶት 100 ትምህርትቤቶች ተፈቅደው ተጠናቀዋል። ስድስት ቢሊዬን በመመደብም ነው ተግባሩ የተከናወነው። ይህ ሲሆን ደግሞ የትምህርትቤቱን ምቹነት በማምጣትና ለብዙ ዓመት እንዲያገለግል ሆኖ ነው የተገነባው። ለምሳሌ፡- ሁለተኛ ደረጃ ትምህርትቤት ሲገነባ 12 ሄክታር ላይ ማረፍ አለበት የሚል ውሳኔ ተላልፏል። በኋላም ተጨማሪ ክፍል ሲያስፈልግ በዚያው መልኩ የሚሰራ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- ደረጃውን የጠበቀ ትምህርትቤት ለመገንባት ጥናት እንደተካሄደ ተሰምቷል። ውጤቶቹ ምን ይመስሉ ነበር? ከተማሪ፣ ከመምህራንና ማህበረሰቡ ጠቀሜታ አንጻርስ ጥናቱ ምን አመጣ?
ዶክተር ቶላ፡- በክልሉ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርትቤትን ብቻ ብናነሳ ቀደም ሲል 1400 ትምህርትቤቶች ነበሩ። አሁን የተሰሩት ደግሞ 100 ናቸው። ሁለቱን ስናነጻጽር በፊት የነበሩት በብዙ መልኩ ጥራት የላቸውም። እናም በቀላሉ ስለሚፈርሱ ለተማሪም ሆነ ለመምህራኑ ምቹ አይደሉም። የተሟላ ቤተሙከራና ቤተ መፀሐፍት በሌለበት ማስተማርም መሆነ መማር በምንም መልኩ ውጤታማ ሊያደርግ አይችልም። ለሥራም ቢሆን ማራኪነት የላቸውም። በዚያ ላይ እነርሱን ለመገንባት ዓመታት ተቆጥረዋል። እናም የተሻለ እንጂ ከዚህ የወረደ ትምህርቤት እንደማይገነባም ተወስኗል።
100 ትምህርትቤት መሥራት ብዙ ለውጥ ያመጣል ተብሎ አይታሰብም። ሆኖም በርካታ ጥቅሞች እንዳሉት ግን አይካድም። ምክንያቱም ተማሪንና መምህራንን ብቻ ሳይሆን ማህበረሰቡንም ጭምር የሚጠቅም ሆኖ ተገንብቷል። ጥቅሙን ከመነሻው ጀምሮ ብናነሳውም አንዱ የሥራ እድል መፍጠሩ ነው። 150ሺህ ሰው የተጠቀመበት ሆኖ አልፏል። ወደ ሁለት መቶ ሺህ ተማሪን በእነዚህ ትምህርትቤቶች ማካተት ደግሞ ከተማሪው ጥቅም አንጻር ስናየው ዘርፈ ብዙ ጥቅም አለው። አንዱ ረጅም መንገድ ሳይሄዱ የሚፈልጉትን ነገር እያደረጉ እንዲማሩ ማስቻሉ ሲሆን፤ ከተጨማሪ ወጪም ይታደጋቸዋል።
ምቹ የመማር ማስተማር ሥርዓትና አየር መፍጠር በራሱ ትልቅ እድል የሚሰጥም ነው። ምክንያቱም ተማሪም ሆነ መምህራኑ ወደ ትምህርትቤት ሲመጡ ፈልገው እንጂ ተገደው አይሆንም። ደስተኛ ሆነው ጊዜያቸውን በዚያ እንዲያሳልፉም ይሆናሉ። የተሸለ የመወዳደር እድል እንዲኖራቸውም ያደርጋቸዋል።
አዲስ ዘመን፡- ከሸኔ የሽብር እነቅስቃሴ ጋር በተያያዘ የወደሙ ትምህርት ቤቶች ምን ያህል ናቸው ? ከዋና ግባችሁ ባሻገር በጦርነት የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መገንባት ላይስ ምን አይነት እንቅስቃሴ እያደረጋችሁ ነው?
ዶክተር ቶላ፡- እንደአገር ችግር ነው ብዬ የማነሳው ጉዳይ መንፈሳዊ ቅናት አለመኖሩን ነው። የአመለካከት ችግር እጅግ በአገር ላይ ሰፍቷል። ከዚህ ካልተወጣም ውድድር ይኖራል ብዬ አላምንም። ምክንያቱም እንደ ክልል ሥራዎች ሲሰሩ ተሞክሮችን ከመቀስም ይልቅ ማጥላላት ይቀድማል። እንደውም አልሙ፤ ከጦርነቱ ባሻገር ሥራ ስሩና አገርን በጋራ እንለውጥ ሲባል ‹‹ያልተነካ ግልግል ያውቃል›› የሚሉም አይጠፉም። ምክንያታቸው ደግሞ ኦሮምያ ምንም አይነት ችግር እያስተናገደች አይደለም የሚለው ነው። ይህ ግን ትክክል እንዳልሆነ ልባቸው ያውቀዋል። በሸኔ ከዓመት እስከዓመት ስቃዩን የሚበላው የኦሮምያ ክልል ነው።
ኦሮምያ ክልል ምንም አይነት መና አልወረደለትም። ክልሉ በራሱ አቅም በጀቱን እንያሳደገ የሚሳራ ነው። አሁንም ይህንኑ ከማድረግ ወደኋላ አይልም። ችግር ከተባለ ኦሮምያ በሚያጎራብታቸው ሁሉ ተፈትኗል። የተፈናቀሉም በጣም በርካታ ናቸው። የሞቱም እንዲሁ። ጉዳያችን ትምህርት በመሆኑ እርሱን ብቻ እንኳን ብናነሳ ከባድ የሚባሉ ፈተናዎችን እንደ ክልል ተጋፍጠን አልፈናል።
በአሁኑ ወቅት ብቻ የወደሙ ትምህርቤቶች ከ1000 በላይ ናቸው። የተዘረፉትም በዚያው ልክ ይሆናሉ። መዝረፍ ካልቻሉ ደግሞ ያቃጠሏቸውም እንዲሁ ቀላል አልነበሩም። እነዚህን መገንባት ደግሞ ግዴታ ነውና በተቻለ መልኩ እየተሰራባቸው ይገኛል። በእርግጥ የፈረሱ ትምህርትቤቶች ግንባታን በሚመለከት ትምህርትሚኒስቴር ወስዷል። ስለዚህም በቢሮው በኩል የሚደረጉ ነገሮች ተማሪዎችን ባሉበት ሁኔታ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ማስቻል ነው። ይህም እየተደረገ ይገኛል። ከስነልቦና ማማከር ሥራ ጀምሮ ተግባራቱ እየተከናወኑም ናቸው። በተጨማሪም በክልሉ ማህበረሰብ ተሳትፎ እንዲኖር ለማድረግ ገንዘብ የማሰባሰቡ ተግባር ቀጥሏል።
ለምሳሌ፡- ከሱማሌ ክልል ብቻ አንድ ሚሊዬን ሰው ተፈናቅሎ ፤ በባሌ በኩልም ከዚህ ተመጣጣኝ የሚሆን ሰው ቤት ንብረቱን ትቶ ክልሉን ችግር ውስጥ ከቶት ነበር። በተመሳሳይ በወለጋ በኩል ደግሞ ከሦስት መቶ ሺህ በላይ ሰው ተፈናቅሏል፤ በጉጂና ጌዲዮ እንዲሁ ያህል ሰው ከቀየው ወጥቷል። እናም እነዚያን የማቋቋምና ተማሪዎቹን የማገዝ ሥራ የቢሮውም ኃላፊነት ስለነበር አድርጎታል። በቀጣይም ብዙ ሥራዎች እንዳሉበት ይታመናል። ቤተሰብ ሳይቀር የሚታገዝበትን መንገድ እየፈጠርን የሸኔን አላማ አክሽፈናል።
ሸኔ በፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ስድስት ትምህርቤቶችን መገንባት አልተቻለም። ለዚህም ማሳያው ምዕራብ ሸዋ፣ ምዕራብ ጉጂ፣ ምዕራብ ወለጋ ናቸው። ይሁን እንጂ ይህም ሆኖ ሥራ አልቆመም። ማንኛውም ችግር መፍትሄ አለው ብለን እናምናለንና በሌሎች አካባቢዎች ተግባራቶቹ ወደፊት እንዲጓዙ አድርገናል። በእቅዱ መሰረትም እየሄዱ ናቸው። ለምሳሌ፡- ሥራው ከመጀመሩ በፊት አምስት ግቦችን ለማሳካት በዕቅድ ተይዞ ተሰርቷል።
እነዚህ እቅዶች የመጀመሪያው በትምህርትቤቶቹ ግንባታ ወቅት 150 ሺህ ወጣቶች የሥራ እድል ያገኛሉ የሚለው ነው። ሌላው ይህ ክልል ገና ብዙ ፕሮጀክት ይሰራል። ለዚህ ደግሞ ብቃት ያላቸውን ኮንትራክተሮች መፍጠር ይገባልና በትምህርት ቤቶች ግንባታ ውስጥ ወጣቶች ሙያ እንዲቀስሙ ተደርጓል። ሦስተኛው አቅም ያለው አማካሪ ድርጅትን መለየትና ለቀጣይ ለመጠቀም ማመቻቸት ሲሆን፤ ይህንንም ማሳካት ተችሏል። አራተኛው አንድን ፕሮጀክት በጥራትና በጊዜ እንዲሁም በተቀመጠው በጀት ማጠናቀቅ መቻል ሲሆን፤ ስኬታማ የሆንበት ተግባር ነበር።
አምስተኛው ለአገልግሎት ብቁ የሆነውን ትምህርትቤት ግብዓቱን አሟልቶ ወደ ሥራ ማስገባት ሲሆን፤ ሁሉም በሚባል ደረጃ ተሟልተው ለ2015 ዝግጁ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- እንደ አጠቃላይ በጉዳዩ ላይ የሚያስተላልፉት መልክት ካለ ?
ዶክተር ቶላ፡- መልእክቶቼ ሁለት ነገሮች ብቻ ናቸው። አንደኛው አወንታዊ ተመልካች እንሁን ፤ የአስተሳሰብ ችግራችንን እንፍታ የሚለው ሲሆን፤ ሁለተኛው በመንፈሳዊ ቅንኣት ተመርተን እርስ በእርስ በልማቱ በመወዳደር አገራችንን እናሳድግ የሚለው ነው። ሁሉም ጋር ችግርም መፍትሄም አለና ያንን እያዩ በእኩል መራመድ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡ ስለሰጡን ማብራሪያ በድርጅቱ ስም እጅግ አድርገን እናመሰግናለን
ዶክተር ቶላ፡- እኔም እንግዳ ስላደረጋችሁኝ አመሰግናለሁ።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 2 ቀን 2014 ዓ.ም