በሀገራችን የመጀመሪያው ባለጥቁርና ነጭ ቀለም ፊልም «ሂሩት አባቷ ማን ነው» የተሰኘውን ነው። ይህ ፊልም «የሀገር ፊልምና ማስታወቂያ ሥራ ማህበር» በንግድ ሚኒስቴር የሥራ ፈቃድ ተሰጥቶት የታሪካዊው ሂሩት አባቷ ማነው? ባለታሪክ ፊልም ሆኗል። የፊልሙ ፀሐፊ አቶ ኢላላ ኢብሳንም በሃገራችን የሲኒማ ታሪክ ተቀዳሚ ሰው አድርጓቸዋል።
የሃገራችን የሲኒማ ታሪክ በግማሽ ምዕተ ዓመት ዕድሜ አስቆጥሯል። በዚህ ዕድሜው እንዳይሰፈር በመሃል ፊልምና ፊልም ሠሪዎች ተራርቀው ክፍተቱን አስፍተውት ቆይተዋል። አሁን ደግሞ ፊልምና ፊልም ሠሪዎችን የሚያቀራርብ መልካም አጋጣሚ ተፈጠረና ካለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ወዲህ በብዛትም ሆነ በጥራት ሻል ያሉ ፊልሞች መመረት ጀምረዋል።
የሃገራችን የፊልም ኢዱስትሪ(ኢንዱስትሪ ከተባለ) ከዕድሜው የሚመጥን ሥራ እየሠራ ባይሆንም ከዕድሜው በላይ በቁጥር በርካታ ሥራዎችን እየሠራ መሆኑ አይካድም። ምክንያቱም በአንደ ዓመት ውስጥ ከአሜሪካው ሆሊውድ፣ ከህንዱ ቦሊውድ እንዲሁም የአህጉራችን ናይጀሪያ ኒዎውድ ጋር በቁጥር የሚመጣጠኑ አንዳንዴም በቁጥር የሚበልጡ ፊልሞች በመመረት ላይ መሆናቸው ይታወቃል።
በብዛቱ ተፎካካሪ እየሆነ የመጣው የፊልም ኢንዱስትሪ ወደ ጥራቱ ስንመጣ ግን ዛሬም በጥያቄ ምልክት ውስጥ እናስቀምጠዋለን። ምክንያቱም እንደ አሸን ከፈሉት ፊልሞቻችን መካከል ሚዛን የሚደፉትና የተመልካችን ቀልብ ገዝተው አብረው የሚያዘልቁት ቁጥር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ያም ሆነ ይህ ፊልሞቻችን ሀገራዊ ቃና ኖሯቸው ሞራልንና ስነ ምግባርን በማነፅና የሃገራችንን መልካም ገፅታ ከመገንባት አንፃር፤ እንዲሁም ሃገራዊ ፍቅርን በመስበክ ብቃታቸው ሲቃኙ የሚጠበቅባቸውን አስተዋፅኦ አበርክተዋል ለማለት አይደፈረም።
አንዳንዶች የፊልሞች ሚና ማዝናናት እንጂ ማስተማር አይደለም ይላሉ። ይሁን አንጅ በሲኒማ ታሪክ ግምባር ቀደም ተጠቃሽ በሆነው ሆሊውድ የተቋቋመው ታላቅ የሚሏትን አሜሪካን ጥቅም ሊያስከብርና ታላቅነቷን ለመላው ዓለም ለማሳወቅ ታስቦ እንደነበር መረጃዎች መላክታሉ።
ወደ ሃገራችን ስንመለስ ስለኢትዮጵያ ፊልሞች ብዙ ጋዜጦችና መጽሔቶች ብዙ ብለዋል። ከመገናኛ ብዙኃኑ በተጨማሪም ስለጉዳዩ በሚያስወሩ መድረኮች ሁሉ ብዙ ተብሎበታል። ይሄ ሁሉ ሲሆን ግን አወዳደቁን እንጂ አነሳሱን አይዳስሱም። ወቀሳ ከሚበዛባቸው ጉዳዮች ሁሉ የኢትዮጵያ ፊልም ግንባር ቀደሙ መሆኑ አልቀረም። ከተመልካች እስከ ባለሙያ፣ ከመንግሥት እስከ ፊልሙ ባለቤት ‹‹የአገራችን ፊልም የወደቀ ነው›› የማይል የለም። ፊልሙን የገፈተረው ግን ይሄው ወቃሹ አካል መሆኑ አይካድም። ‹‹እኮ እንዴት?›› ብሎ ለሚጠይቅ መልሶቹ እነዚህ ሊሆኑ ይችላሉ።
መንግሥት ኪነ ጥበብን እንደ ጉዳይ ዓይቶት አያውቅም። እሱን የሚነካ የኪነ ጥበብ ሥራ ሲሠራ ግን የንስር ዓይን አለኝ ይላል። በሌላ በኩል ደግሞ ራሱ ለሚያዘጋጃቸው መድረኮች ሲሆን ደግሞ ‹‹ነገር በኪነ ጥበብ ነው የሚያምረው!›› ይላል። የራሱ ሲሆን ኪነ ጥበብ ኃይል እንዳለው ያምናል ማለት ነው። ይህን ኃይል ነው ራሱ ገፍትሮ የጣለው።
እዚህ ጋ ደግሞ ራሱ የኪነ ጥበብ ባለሙያው አለላችሁ። ስለኢትዮጵያ ፊልም ሲጠየቅ ‹‹የኢትዮጵያ ፊልም የሞተ ነው›› ይላል፤ ማነው የገደለው? ቢባል ግን ራሱ እንደገደለው አይረዳም። ለምንድነው ሁልጊዜ የስካርና የዝሙት ፊልም ብቻ የምትሠሩት ሲባል ‹‹ተመልካቹ የሚወደው ይሄንን ነው›› ይላል። ግን የፊልም ዓላማስ ይሄ ነውን? ተመልካቹንስ መቅረጽ የለበትም ነበር?
ራሱ ተመልካቹም የፊልሙ ውድቀት አካል ነው። ስካርና ዝሙት ያለበት ፊልም ሲያሳድድ እየዋለ ነው ‹‹ምን ፊልም አለና ነው!›› የሚለው። ይሄ ‹‹አንድ ዓይነት ብቻ ናቸው›› እያለ የሚወቅስ ሁሉ ምን ምን ፊልም ዓይተሃል ቢባል የሚናገረው
ጥቂቶችን ነው። በታሪክና ባህል ላይ የተሠሩ ፊልሞች አሉ፤ ግን እነዚያ ፊልሞች የተመልካች ድርቅ የመታቸው ናቸው። ስለነዚያ ፊልሞች ዳሰሳ አልተሠራም፤ በመድረክ አልተወራላቸውም፤ ሕዝብ ሲያደንቃቸው አልታየም። ስለዚህ የኪነ ጥበብ ባለሙያው እንዲህ ዓይነት ፊልም ቢሠራ ሊከስር ነው ማለት እኮ ነው። እዚህ ላይ የገንዘብ ጉዳይም ልብ መባል አለበት፤ የሚሠራው ለጽድቅ አይደለም። ፊልሙ አገርና ባህልን ሲያስተዋወቅ ሠሪውም ተጠቃሚ መሆን አለበት። እነዚያ ፊልሞች ደግሞ ከፍተኛ ወጪ የወጣባቸው ናቸው። ጭፈራ ቤትና ስካር ቤት አይደለም የተቀረፁት። ብዙ ጥናት ተደርጎባቸውና ብዙ ወጪ ወጥቶባቸው ነው የሚሠሩት።
የፊልሙ ሰዎች ምን ይላሉ?
የፊልም ባለሙያው ብርሃኑ ሽብሩ እንደሚለው ታሪካዊ ፊልሞችን ለመሥራት የበጀትም የዕውቀትም ችግር አለ። ሃሳቡን ሲያጠናክር አንድ ገጠመኝ ያስታውሳል። የኮሎኔል አብዲሳ አጋ ፊልም ለመሥራት ሃሳብ ይዘው ወደ እርሱ መጡ፤ እንደማይችሉ ነገራቸው። ምክንያቱም የኮሎኔል አብዲሳን ታሪክ ለመሥራት የሚያስችል የዕውቀትም የገንዘብም አቅም የለም። እንደ መድረክ ቴአትር በሜካፕ ብቻ ቀብቶ መሥራት አይቻልም። ገንዘብ ስላለ ብቻም አይሆንም። የጣሊያንንና የኢትዮጵያን ታሪክ ጠንቅቆ የሚያውቅ ባለሙያ ያስፈልጋል።ይህን ትልቅ ሃሳብ ወደ ፊልም ለመቀየር ሰፊ ጥናት ያስፈልጋል። የሁለቱም ሀገራት ቀና ትብብርንም ይጠይቃል።
ታሪካዊ ብቻ ሳይሆን ባህላዊ ነገሮችንም ለመሥራት የአካባቢውን ባህል ማወቅ ያስፈልጋል። እንደ ጎብኚ አንድ ጊዜ ሄዶ ፏፏቴ ሥር መቀረጽ አይደለም፤ አካባቢውን በጥልቀት ማወቅን ይጠይቃል። ለዚህ ደግሞ በዘርፉ በብቃት የተማረ የሰው ኃይል የለም። እነዚህ ነገሮች የሚስተካከሉት ደግሞ መንግሥትና የሚመለከታቸው አካላት ከፍተኛ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሲወጡ ብቻ ነው። ፖሊሲ ማውጣት ብቻውን በቂ አይሆንም። ማስፈፀሚያዎቹ ደምብና መመሪያዎች ያስፈልጋሉ። ለዚህ ደግሞ የፊልም ሠሪዎች ማህበራት ሚናቸው ከፍተኛ በመሆኑ ክትትል ማድረግ እንዳለባቸው ያሳስባል – የፊልም ባለሙያው ብርሃኑ ሽብሩ።
በፊልም ሠሪዎች ማህበር የህዝብ ግንኙነትና የጥናትና ምርምር ኃላፊ አርቲስት ደሳለኝ ኃይሉ ፊልም ለምን መሠራት አንዳለበት ይነግረናል። ፊልም የሚሠራው ግለሰቡ ያሰበውን
ሃሳብ በነፃነት ለማሳየት ሊሆን ይችላል፤ ገንዘብ ለማግኘት ተብሎም ሊሆን ይችላል። በፊልም ዘርፍ ያደጉ አገሮች ደግሞ አገርንና ሃሳብንም ያስተዋውቁበታል። ዜጎችንም ይቀርፁበታል፤ የገንዘብ ምንጭም ነው።
ለመሆኑ የኢትዮጵያ ፊልም ከየትኛው ነው? አገር አስተዋወቀ ወይስ ገንዘብ አስገኘ? የኢትዮጵያ ፊልም በሁለቱም በኩል እንዳልተሳካለት ነው የደሳለኝ አስተያየት የሚያሳየን። የፊልም ኢንዱስትሪውን አሽመድምዶ የጣለው ደግሞ መንግሥት ነው። አስፈፃሚው አካል የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ነው። ይሄ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ግን ለጉዳዩ ተቆርቋሪ በሆኑ ሰዎች አልተመራም። በቦታው የሚቀመጡት ኃላፊዎች ለብሄር የኮታ ማሟያነት ነው። በዚህ ሁኔታ ለፊልም ዘርፍ ሊቆረቆሩ አይችሉም፤ ለሙያውም ቅርበት ያላቸው ሰዎች አይደሉም። በመሆኑም ሙያና ሙያተኛን የሚያገናኙ አልሆኑም ይላል አርቲስት ደሳለኝ።
በዚህ ሁሉ ውስጥ አርቲስት ደሳለኝ አንድ ተስፋ አለው። አሁን ያለው የዶክተር ዐብይ መንግሥት ለኪነ ጥበብ ትኩረት የሰጠ ይመስላል። የዘርፉን ሰዎችም አወያይተዋል። የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩትም ከስነ ጽሑፍ የመጡ ስለሆነ ዘርፉ ተስፋ ሊኖረው ይችላል።
ለመሆኑ ይሄ ሁሉ ሲሆን የኪነ ጥበብ ሰዎችስ የት ነበሩ? መንግሥት ሲያሽደምደው ዝም ማለት ነበረባቸው? እርግጥ ነው የኪነ ጥበብ ሰዎችም የዘርፉን መውደቅ ከመናዘዝ በስተቀር እንዴት ይነሳ የሚል ጥረት ላይ ደካማ ናቸው። ይሁን እንጂ አንድ ነገር አድርገዋል። የፊልም ሠሪዎች ማህበር አካላት የፊልም ፖሊሲ እንዲወጣ አድርገዋል። በነገራችን ላይ ፖሊሲው ላይ ያሉት ቢተገበሩ የኢትዮጵያ ፊልም የዓለም ተወዳዳሪ እንደሚሆን ይታመናል። የመጀመሪዎቹን አንቀጾች እንኳን ብናይ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል እንዲኖር የሚያስችል ነው። ምንም እንኳን ፖሊሲው ከወጣ ገና አንድ ዓመት ቢሆነውም ለውጥ እየታየ ነው የሚባል ምልክት ግን አላየንም (የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የሚለንን ስንደርስበት እናየዋለን)።
ታሪካዊና ሳይንሳዊ ፊልሞች የማይሠሩት ዕውቀቱ ስለሌለ ነው። አርቲስት ደሳለኝ ደግሞ ምናልባትም ምቹ ሁኔታ ስለሌለ ተደብቀውም ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አለው። ይሄ ነገር እውነት ሊሆን ይችላል። የመጽሐፍ፣ የፊልምም ይሁን
የሆነ የውይይት መድረክ ላይ ያስተዋልኩትን አንድ ምሳሌ ልጨምር።ያልጠበቃችሁት ሰው ታገኛለችሁ። በአገራችን ደግሞ አንድ ችግር አለ፤ ዕውቀት ያላቸው ሰዎች ብዙም ልታይ ልታይ አይሉም፤ አንድ ጊዜ ሚዲያ ላይ የቀረቡ ሰዎች ደግሞ ይደጋገሙና አዋቂ እነርሱ ብቻ ይመስሉናል። የአርቲስት ደሳለኝ ኃይሉ ስጋት ትክክል ሊሆን ይችላል ለማለት ነው።
የመንግሥት የተጠናከረ ድጋፍ ቢኖር ግን ይሄም ችግር ይቀረፍ ነበር። አንድ ጠንካራ የፊልም ተቋም ቢኖር እኮ እነዚህን ሰዎች ካሉበት አፈላልጎ ማግኘት ይቻላል። አለመፈለግ ሳይሆን ተስፋ ቆርጠው የተውትም ሊሆኑ ይችላሉ። የታሪክም ሆነ የሳይንስ ተመራማሪዎች እኮ አሉን። ዳሩ ግን እነዚህ ምሁራን የሚነግሩን ስለውጭ ፊልም ብቃት ብቻ መሆኑ ነው የሚከፋው።
ታሪካዊና ሳይንሳዊ ፊልም ቢሠራም ተመልካቹ አይፈልግም የሚለው የፊልም ሰዎች ድምዳሜ ድክመትን መሸፈኛ ወይስ እውነትም ተመልካቹ አይፈልግም? ይሄ ሃሳብ ለደሳለኝ አይሞቀውም አይበርደውም። ምክንያቱም መጀመሪያውኑም እውቀቱም ስነ ምግባሩም በሌላቸው ሰዎች የሚሠራ ፊልም የማምለጫ ምክንያቱ ይሄ ነው የሚሆን። ታሪካዊና ሳይንሳዊ ፊልም ተሠርቶ ተመልካች ያጣ የለም። ለመቶ ሚሊዮን ህዝብ መቶ ሲኒማ ቤት እንኳን የለም። ይሄ በሌለበት ሠሪውም አይነሳሳም።
የኢትዮጵያን ፊልም ለማሳደግ ምን ይደረግ? ለሚለው ወሳኝ ጥያቄ የደሳለኝ የመፍትሔ ሃሳብ አንድ ዓረፍተ ነገር ነው።«ፖሊሲውን መተግበር!»
በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የባህል ኢንዱስትሪ ልማትና ትብብር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ይስማ ጽጌ ከሃሳብ ነፃነት ጋር አያይዘው ይናገራሉ። ሰዎች የሃሳብ ነፃነት በህገ መንግሥት የተሰጣቸው ነው። እነርሱ የፈጠራ ነፃነታቸውን ተጠቅመው ባሰቡት መንገድ ይሠሩታል። ስለዚህ እንዲህ አድርጉ፤ ይህን ዓይነት ፊልም አትሥሩ አይባልም።
ስለዚህ መሆን ያለበት ማህበረሰቡን የሚቀርጽ፣ የአገርን ባህልና ወግ የሚያስተዋውቅ እንድ ሥራ በሽልማትና በሌሎች ነገሮች ማበረታታት እንደሚሻል ነው ዳይሬክተሩ የሚናገሩት። በሌላ በኩል ከኪነ ጥበብ ሰዎች ጋር በመሆን ግንዛቤ መፍጠር እንጂ ለምን እንዲህ ሠራችሁ ብሎ ለመቆጣጠር የሚያስችል የህግ ማዕቀፍም የለም። ትውልድን የሚቀርጽ ነው፤ የአገር ባህልና ወግን ያስተዋወቀ ነው የተባለውን መሸለምና ማበረታታት ሌሎችንም ለመሳብ ይረዳል።
የፊልም ፖሊሲው ክፍል ሁለት 2.3 ‹‹ለ›› ላይ እንዲህ ይላል። ‹‹የአገርን ደህንነትና ጥቅም የሚጎዱ፣ የማህበረሰቡንና የወጣቱን ሞራል፣ ስነ ምግባርና ማህበራዊ እሴቶችን የሚያዘቅጡ፣ ለባህል ወረራ የሚያጋልጡ ይዘት ያላቸው የፊልም ምርቶች እንዳይቀርቡ ይረጋገጣል›› ፖሊሲው ይህንን ሲል የባህል ኢንዱስትሪ ዳይሬክተሩ ደግሞ ‹‹የባህል ወረራ የሚመጣው በፊልም ብቻ አይደለም››ይላሉ። ግን ከፊልም በላይ የባህል ወረራ የሚያስከትል ምን ይኖር ይሆን?
የወጣው ፖሊሲ ገና አንድ ዓመቱ ነው፤ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቂ ውይይትም አልተደረገበትም። በቀጣይ ግን ከዘርፉ ባለሙያዎች ጋር በትብብር እንደሚሠራ አቶ ይስማ ይገልፃሉ። ይሄውም ተገቢውን የሰው ኃይል ከማሟላት ጀምሮ ለቀረጻ የሚያስፈልጋቸውን ነገር እስከማሟላት አብሮ ይሠራል።
ፖሊሲው ይተገበር ዘንድ የፊልሙ ሰዎች ግፊት ማድረግ አለባቸው። መንግሥትም ተገቢውን እገዛ ማድረግ አለበት። የዘርፉ ሰዎች ምን እንደሚያስፈልግ ያውቃሉ፤ ያንን አንድ ሁለት ብለው አብረው ይሥሩ። ከአርቲስቶች ጋር የተወያየው የዶክተር አብይ መንግሥትም በተግባር ያሳይ!
አንድ ጥያቄ ግን አሁንም ጥያቄ ሆኖ እንደቀጠለ ነው። ዕውነት በፊልሙ ውስጥ ያሉ ሰዎች የአገራቸውን ታሪክ የሚያውቁ ናቸው? ታሪካዊ ፊልም የመሥራት ብቃቱ አላቸው? ሳይንሳዊ ፊልም ጭራሹንስ ይታሰባል? በፊልም ኢንዱስትሪው ውስጥ ለውጥ እንዲመጣ ከተፈለገ እነዚህ ጥያቄዎች መመለስ አለባቸው።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 21/2011
በዋለልኝ አየለ