ሰላም ልጆች እንዴት ሰነበታችሁ፤ ሳምንቱ እንዴት አለፈ? መቼም ጥሩ ነው እንደምትሉኝ አልጠራጠርም:: ምክንያቱም ይህንን የእረፍት ጊዜያችሁን ከቤተሰቦቻችሁ ጋር በመሆን በተለያዩ ተግባራት እያሳለፋችሁ እንደሆነ አምናለሁና ነው:: ለማንኛውም ልጆች ይህንን ጊዜያችሁን በአግባቡ መጠቀም አለባችሁ:: አለዚያ ግን የሚያመልጣችሁ ነገር ብዙ ይሆናል:: ልጆች ይህ ጊዜ በተለይም ተሰጥዖዋችሁን የምታሳድጉበት ቢሆን የተመረጠ ነው:: ምን እፈልጋለሁ የሚለውን በተግባር ለማረጋገጥም ያግዛችኋል::
ለመሆኑ ልጆች የእናንተ ፍላጎት ምን መሆን ነው? ዘረዘራችሁልኝ አይደል? ጎበዞች! ታዲያ ለዚያ ፍላጎታችሁ ስኬት ምን ያህል ለፍታችኋል? ጥረት ካላደረጋችሁ የምትፈልጉትን አትሆኑም:: እናም አሁን ጀምራችሁ መሆን ለምትፈልጉት ነገር አስፈላጊ ነው የምትሉትን እንቅስቃሴ ማድረግ አለባችሁ::
የመጀመሪያው ግን ከትምህርታችሁ ጋር የሚገናኘውን ጉዳይ አጥብቃችሁ መያዝ ነው:: ከዚያ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን ቤተሰባችሁ እንዲገዛላችሁ በማሳመን በአወቃችሁት ልክ መሥራት መጀመር ነው:: በልምምድ የማይመጣ ነገር የለምና ሁልጊዜ ለዚያ ፍላጎታችሁ ስኬት መታተርም ይጠበቅባችኋል:: እንደምታደርጉት ደግሞ አምናለሁ::
ዛሬ ይዤላችሁ የቀረብኩት ይህንንኑ ጉዳይ ይመለከታል:: ባለተሰጥዎቹ ልጆች በዚህ በእረፍት ጊዜያቸው ምን እያደረጉ እንደሆነ የሚነግራችሁ ነው:: ለዚህ ደግሞ ቤተሰቦቻቸው እንዳገዟቸው ነግረውናል:: ልጆቹ በሰርከስ ትርኢት ላይ የተሰማሩ ሲሆን፤ እኔ ያገኘኋቸው ደግሞ የልፋታቸውን ውጤት በሚያቀርቡበት ወቅት ነው::
ልጆች መጀመሪያ ግን ስለልጆቹ ከመንገሬ በፊት ስለ ሰርከስ ምንነት ጥቂት ልበላችሁ:: የሰርከስ ሥነ ጥበብ ልዩነትን ፣ ብሩህነትን እና አስገራሚነትን የሚያሳይ ትርኢት ነው:: በጣም ውስብስብ ብልሃቶች የሚመራ ሲሆን፤ ለብዙዎች ደስታ መፍጠሪያ ነው:: አስቂኝ ቀልድ ሌሎችን ማዝናናት በሚችልበት ሁኔታ የሚቃኝም ነው:: ብዙ ስልጠናንም ይፈልጋል:: ያለ ፍርሃት መሞከርን የሚያስቀድም እንዲሁም በችሎታ የሚሰራም ነው::
ልጆች በኢትዮጵያ የሰርከስ ስፖርት ከተጀመረ 28 ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን፤ በእነዚህ ዓመታት ውስጥም ኢትዮጵያውያን የሰርከስ አርቲስቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ የተለያዩ ሥራዎቻቸውን በማቅረብ የሜዳሊያ ሽልማት ከማምጣት ባለፈ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ ሆነዋል:: ለአብነት በተለያዩ ሀገራት ሥራዎቹን በማቅረብ በሚታወቀውና መቀመጫውን ካናዳ ባደረገው በስመ ገናናው ሰርከስ ዲሰሌ በርካታ ኢትዮጵያውያን መሳተፋቸው አንዱ ነው::
የሰርከስ አርቲስቶች ኮንትራት ተሰጥቷቸው ጭምር በተለያዩ የዓለም ሀገራት እየዞሩ ሥራዎቻቸውን ያቀርባሉ። ይህ ደግሞ በዓለም አደባባይ የኢትዮጵያን ስም በማስጠራት ፣ የሥራ እድል በመፍጠር እና ከሱስ የጸዳ ወጣት በማፍራት ትልቅ ሚና እንደተጫወተ ይነገርለታል:: ልጆች ሌላው የሰርከስ እድሉ የተለያየ አካል ጉዳት ያለባቸው ልጆች ማሳተፉ ሲሆን፤ ራሳቸውን በተለያዩ የጥበብ ዘርፎች እንዲያበቁ ያደርጋቸዋል:: በዚያም የሥራ እድል የሚያገኙበትን ሁኔታ ይፈጥርላቸዋል:: በተለይም በሙዚቃ፣ በዳንስ ጥሩ አቅማቸውን እንዲያሳዩ የሚያደርጋቸው ነው::
ልጆች ልጆቹን የት እንዳገኘኋቸው አልነገርኳችሁም አይደል? በደሴ ከተማ ሆጤ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት ውስጥ ነው:: የሰርከስ ትምህርታቸውን እንዴት እንደጀመሩና ወደፊት በሙያው ምን መሆን እንደሚፈልጉ ነግረውኛል:: በመጀመሪያ ሀሳቧን ያጋራቺኝ ተማሪ ዳግማዊት ሰለሞን ትባላለች:: የሰባተኛ ክፍል ተማሪ ናት:: በትምህርቷ በጣም ጎበዝ ስትሆን ጎን ለጎን ሰርከስ ትርኢት ላይ ትሳተፋለች:: ሰርከስ ደሴ ውስጥ የገባችው በአባቷ ገፋፊነት ሲሆን፤ ልዩ ተሰጥዖዋን እንድትረዳው አስችሏታል:: ከዚያ በተጨማሪ ደግሞ ትምህርት ቤት ላይ በተለያየ ወቅት ግጥም በመጻፍ ታቀርባለች:: ጎበዝም በመሆኗ ተሸልማለች::
ወደ ሰርከስ እንድትገባ የመራት የተለያዩ ክበባት ውስጥ መሳተፏ እንደሆነ ያጫወተችን ዳግማዊት፤ ሰርከስ ዝም ብሎ የሚሠራ አይደለም:: ብዙ ልምምድ ይጠይቃል:: ሁልጊዜ ተግባራዊ ልምምድን ይፈልጋል:: ከብዙ ልምምድ በኋላም ነው የሚመጣው:: እናም ልጆች ሰርከስ ከመሥራታችሁ በፊት በቂ ልምምድ ማድረጋችሁን አረጋግጡ:: ለምን ቶሎ አልቻልኩትም ማለት የለባቸውም ስትልም ትመክራለች::
ሰርከስ ፍላጎትንም ይፈልጋል የምትለው ዳግማዊት፤ ልጆች ከእኔ አንድ ነገር ልምድ ቢወስዱ ደስ ይለኛል ትላለች:: ይህም ሰው በሚላቸው ሳይሆን አዕምሯቸው በሚፈቅደው ላይ ተንተርሰው መሥራት አለባቸው የሚለው ነው:: የዚህን ጊዜ ፍላጎታቸውን ግብ እንዲመታ ያደርጉታል:: ይህ ሲባል ግን ወላጆቻችሁን አትስሙ ማለት እንዳልሆነም ታስረዳለች:: ምክንያቱም የተባልነውን የማንሰማ ከሆነ ያልሆነ መንገድ እንድንከተልና ፍላጎታችንን እንዳናሳካ እንሆናለን:: እናም ፍላጎታችሁን ምን እንደሆነ እናንተው ለዩ ለማለት እንጂ ሌሎችን አትስሙ ለማለት ፈልጋም እንዳልተናገረችው ትገልጻለች::
ሌላዋ ያነጋገርኳት ልጅ ቢታኒያ አሸናፊ ስትሆን፤ የስድስተኛ ክፍል ተማሪ ናት:: የምትማረው ደግሞ ትግል ፍሬ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው:: ሰርከስ ደሴን የተቀላቀለችው በራሷ ፍላጎት ሲሆን፤ ቤተሰቦቿ ግን በፈለገችው መልኩ ያግዟታል:: እርሷ ሙያውን ስለምትወደውና ስጦታዬ ነው ብላ ስለምታስብም በየጊዜው ልምምድም ሆነ ተሳትፎ ታደርጋለች:: ከዚያ ሻገር ስትልም ትርኢቶችን ታቀርባለች:: ግን ይህንን ስታደርግ ትምህርቷን በሚነካ መልኩ አይደለም::
ቤተሰቦቿን በማስፈቀድ ቡድኑ ውስጥ ስትገባም መስፈርቷ ቅድሚያ ለትምህርት የሚል ነው:: ምክንያቱም ብዙ ጊዜዋን ለዚያ ከሰጠች በእውቀት የበለጸገ የሰርከስ አርቲስት መሆን አትችልም:: እርሷ ደግሞ ፍላጎቷ የተማረ የሰርከስ አርቲስት መሆን ነው:: እናም ይህ እንዳይጣረስባት በርትታ ታጠናለች:: ጎን ለጎንም ለሰርከስ አርቲስትነቱ የሚያበቃትን ተግባር ትከውናለች::
ልጆች ማንኛውም ነገር ያለ ድፍረት እንደማይመጣ መረዳት አለባቸው የምትለው ቢታኒያ፤ እችለዋለሁ ማለትን አስቀድመው ለራሳቸው መንገር አለባቸው:: ይህ ደግሞ ችሎታቸውን ለማውጣትና እንደሚችሉት ለማረጋገጥ ያስችላቸዋል:: እናም መሆን ለሚፈልጉት ነገር ሥራ እንጂ ወሬ አያስፈልግምና ሁልጊዜ ተግባርና ልምምድን አጥብቀው ሊይዙ እንደሚገባ ትመክራለች:: ልጆች ከአቀረብናቸው ልጆች ብዙ ሀሳብ እንደቀሰማችሁ እምነት አለኝ:: በቀጣይ ደግሞ ሌላ ጉዳይ ይዤላችሁ የምቀርብ ሲሆን፤ ለዛሬ በዚህ ተሰናበትኳችሁ:: መልካም ሳምንት!!!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ነሐሴ 1 ቀን 2014 ዓ.ም