
እነሆ ነሐሴ ወር ገባ::በዚህ ወር ካጣናቸው ታላላቅ ሰዎች መካከል ደግሞ አንዱ ታላቁ ገጣሚ ሙሉጌታ ተስፋዬ ነው:: ሙሉጌታ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ነሐሴ 29 ቀን 1996 ዓ.ም ነው:: ሰውየው የከተማ መናኝ ነበር:: አኗኗሩ ሁሉ ከሰው ለየት ያለ:: እዚህ ጋር ነው ቤቱ ፤ እነ እገሌ ናቸው ዘመዶቹ የማይባልለት:: እሱ ራሱ ሲናገር “የኔ ሀገርና መዳረሻ የሰው ልጅ ልብ ነው” ይል ነበር:: የሆነው ሆኖ ነገርን ከስሩ ውሀን ከጥሩ ነውና ወደኋላ መለስ ብለን ከትውልዱ አንስቶ ከተለያዩ ምንጮች የሰበሰብነውን ይዘን እናውጋ::
በ1992 ለወጣው ፈርጥ መጽሔት ትንሽ ስለ አስተዳደጉ ፍንጭ ሰጥቶ ነበር፣ ያን ዕለት ለጋዜጠኛ ተፈራ መኮንን እንዲህ አለው…:: “…ምን መሰለህ፣ እኔ ዲቃላ ነኝ፤ አባቴ ትግሬ ናቸው፤ እናቴ የዋድላ ደላንታ ሴት ናት:: ወልዲያ ውስጥ ሙጋድ የሚባል ቦታ እናቴ ከፊት ለፊት ጠላ ትሸጥ ነበር:: አባቴ ደግሞ በጓሮ በኩል ጨው ይሸጣል:: እናቴ ጠላውን እየሸጠች ታንጎራጉራለች:: እንጉርጉሮዋ የኚህን ቄስ ቀልብ ጠለፈ:: ቄሱ ሽማግሌ ቢልኩ አይሆንም ይባላሉ:: እናቴና አባቴን የምታገናኝ አንዲት በር ነበረች:: ቄሱ አይሆንም ሲባሉ በሯን ገንጥለው ገቡ:: እኔ ተወለድኩ::…”:: አባቱ ስማቸው አለቃ ተስፋዬ ገ/ኪዳን ሲባል እናቱ ደግሞ ወ/ሮ እታገኝ ንጋቱ ይባላሉ:: የተወደለበት ቀንም ሚያዝያ 19 ቀን 1946 ነው:: የተማረው እቴጌ ጣይቱ ትምህርት ቤት ነው:: መምህራኑ የአሜሪካ ፒስ ኮርፕ አባላት ናቸው:: 1962 የወልድያ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ሲከፈት እዚያ ገብቶ ነው የተማረው:: አያ ሙሌ በልጅነቱ አንዴ ሊስትሮ ሌላ ጊዜም አስጎብኚ፣ ሌላም ጊዜ ሌላ ሆኖ ነው የኖረው:: መጀመሪያም ድሀም በኋላም ድሀ ሆኜ ነው ያደግኩት ይላል ኑሮውን::
‹‹ካህሊል ጂብራን ያልጨረሰውን ልጨርስ ነው የመጣሁት።›› የሚለው ባለቅኔው ሙሉጌታ ተስፋዬ ድንቅ ገጣሚ ነው:: በአንድ ወቅት በአለባቸው ተካ አለቤ ሾው ላይ ቀርቦ ሲናገር እንዲህ አለ:: ‹‹ግጥም ለመጻፍ እንባ ይፈልጋል ፤ ጣር ይፈልጋል ፤ ስቃይ ይፈልጋል:: ከታመመው ጋር አብረህ የምትታመም ከሆነ ፤ ከሚደሰተውም ጋር አብረህ የምትደሰት ከሆነ ኅብረተሰቡን በትክክል የምታውቀው ከሆነ ጥሩ ገጣሚ ይወጣሀል ብዬ አስባለሁ››:: እሱም ኑሮ እንደዚያው ነበር:: እንደ ሕዝቡ መስሎ ፤ ተራውን ሕዝብ ሆኖ ስለኖረ የሕዝብን ልብ ሰርስረው የገቡ ድንቅ ቅኔዎችን ተቀኝቷል:: ብዙ ወፋፍራም ሙዚቃዎችን ሰርቷል:: ለሙዚቃው የተሰጠ ነበር:: ስለሙዚቃ አጀማመሩ ሲናገር ድሮ ሰፈራችን ቴፕ ስላልነበር ከደሴ እና ከመቀሌ የሚመጡ መኪኖች ላይ ያሉ ዘፈኖችን በመስማት ነው ያደግኩት ይላል:: ያኔ ሀገር አቋራጭ መኪኖች አናታቸው ላይ ስፒከር ነበራቸውና ከውስጥ የተከፈተው ሙዚቃ ለደጁም ይሰማ ነበር:: በዚያ ነው አያ ሙሌ ጆሮውን የሞረደው::
በአበበ ተካ የተዜመችውን ‹‹ወፊቱ›› የተሰኘች የራሱ ድንቅ ብዕር ያረፈባትንና ከሥራዎቼ ሁሉ አብልጬ እወዳታለሁ የሚላትን ዜማ ‹‹መቃብሬ ውስጥ ሆኜ እሰማታለሁ›› ይላት ነበረ . . . ይህቺን ግጥም ጨምሮ ሙሉ የ “ሰው ጥሩ” አልበም ግጥሞች ለአበበ ተካ የሰጠው ሲሆን . . . ብጽአት ስዩም ‹‹አደራ ልጄን አደራ›› እያለች በእንባ የምታዜመውን ግጥምና እነ “ገዳዬን”፣ ለፀደንያ ገ/ማርቆስ – “ገዴ”፣ ለዣን ሥዩም፣ ለታምራት ደስታ – “ሐኪሜ ነሽ”፣ ለመሰረት በለጠ – “ጉም ጉም”፣ ለሀና ሸንቁጤ፣ ለማርታ ኃይሉ፣ ለአበበ ብርሀኔ፣ ለፍቅረአዲስ ነቅዓጥበብ፣ ለኩኩ ሰብስቤ እያልን ብንቀጥል ማቆሚያ የለንም። ቆንጥሮ እየሰጠ አንበሽብሿቸዋል፤ ፍዝ ሆኖ አድምቋቸዋል። እነሱን የዝና ማማ ላይ ሰቅሎ እሱ እታች ወርዶ ይተኛል። የአያ ሙሌ ሕይወቱም ሲበዛ ዥንጉርጉር ናት።
ሙሌ የጻፈውን ጥሎት ይሄዳል፤ ዞሮም አያየው። ዘፋኞች ግን ከሥር ከሥሩ የሚጥለውን እያነሱ ይከብራሉ። እጅግ ተወዳጅ የ80ዎቹ እና 90ዎቹ ሙዚቃዎች የርሱ አሻራ ያረፈባቸው ሆነው ሳሉ አብዛኞቹ ግጥሞቹ በሌላ ሰዎች ስም ወይም የገጣሚው ስም ሳይጻፍባቸው እና ተገቢውን ክፍያ ሳያገኝባቸው በመዜማቸው ግዜ ቅር የተሰኘው አያ ሙሌ፦‹‹ያለኝን ለሕዝብ ልስጥ ብዬ እንጂ . . . ዘፋኞች ማለት ‘ከምላስ ላይ ምራቅ’ ፣ ‘ከቅንድብ ላይ ኩል’ የሚሰርቁ ጉዶች ናቸው። ይኼ አካሄድ በኔ ማብቃት አለበት። ወደፊት እያንዳንዳቸው ሳይወዱ በግዳቸው ይናዘዟታል!›› ብሎ ነበር።
አያ ሙሌ በኢሕአፓ ፖለቲካ ውስጥ ተወልዶ፣ በማርክሲዝም ሌኒኒዝም ነዶ፣ በብአዴን በስሎ፣ በትልቅ ደመወዝ ከብሮ፣ በኢሕአዴግ ላዕላይ ምክር ቤት በመግባት በቤተ-መንግሥት ከፍተኛ የመንግሥት ስብሰባዎች ላይ በመሳተፍ ግጥሞችን ያቀርብ ነበር:: መንግሥታዊ መጽሔትና ጋዜጣ ላይ ሂሳዊ ጽሑፎችን እያቀረበ በጋዜጠኝነት ሠርቶ፣ ከመንግሥት አፓርታማ ተበርክቶለት የተደላደለ ኑሮ ሲኖር የቆየ ሰው ነው። ከዕለታት አንድ ቀን ግን ድንገት ከኢሕአዴግ ሰዎች ራቀ። ሽጉጡን አስረክቦ፣ መንግሥት የሰጠውን ቤት ጥሎ ጎዳና ወጣ። ላይመለስ። ዘበኛ፣ ኩሊ፣ ወዛደር፣ ጎዳና ተዳዳሪ . . . ወዘተ ሆኖ ኖረ።
የሆነ ቀን ላይ ወዳጆቹ ፈልገው አፈላልገው ሕይወቱን በ”ኬሻ በጠረባ” ወዳደረገው አያ ሙሌ ደመወዙን ይዘውለት ቢመጡ “ያልሠራሁበትን አልበላም።” በማለት ሳይቀበላቸው መልሷቸዋል።
ሌላ ጊዜ የሆነ መልዕክተኛ ታምራት ላይኔ በጥብቅ እንደሚፈልገውና እርሱም ሊያደርሰው እንደመጣ ሲነግረው አያ ሙሌ ‹‹አመሰግናለሁ፤ መንገዴን ለይቻለሁ!›› ሲል አጭር መልስ በመስጠት መልሶታል።
እንዲሁም በሌላ ጊዜ ደግሞ የማስታወቂያ ሚኒስቴር የነበረው በረከት ስምኦን አያ ሙሌ ያለበት ድረስ ደፍሮ በመምጣት ‹‹እንዲህ ለመሆን ነው ሥራህን የተውከው? በል ወደ ሥራህ ተመለስ፣ ቢያንስ ጥለሃት የመጣሃትን የ11 ዓመት ሕጻን ልጅህ አታሳዝንህም?›› ቢለው አያ ሙሌ ቱግ ብሎ “የኔ ልጅ ሕጻን አይደለችም፣ አንተን በአንድ ዓመት ትበልጥሃለች።” በማለት ነበር ምላሽ የሰጠው።
የከተማ ባሕታዊው አያ ሙሌ ከአፍቅሮተ ነዋይ የራቀ የከተማ መናኝ ነበር። መታወቂያ፣ ስልክ፣ እድር፣ የመኖሪያ ቤትም ሆነ ቋሚ አድራሻ አልነበረውም። ወገን ዘመድ የሚለው ሰውም እንዲሁ። የሚኖረውም በእምነት ነው ‹‹እንደ ወፊቱ ልዋል›› ይል ነበር አዘውትሮ። ከሥራዎቹ ሁሉ ‘ወፊቱን’ አብልጦ የሚወዳት ለዚሁ ይሆን?
የአያ ሙሌን “የባለቅኔው ምሕላ”ን የግጥም ስብስብ ሰብስባ ያሳተመችው ስንዱ አበበ ናት። ይህን ያደረገችው ሙሉጌታ በሚገባው ልክ ለሥራው እውቅና እንደተሰጠው ስለማታምን እንደሆነ ተናግራለች:: “የባለቅኔው ኑዛዜ” ፣ “የነቢያት ጉባኤ”ን እና “ኢትዮጵያዊነት እምነት” የተሰኙትን ሦስት መጽሐፍት ደግሞ አሰናድቶ ያስነበበን ፋሲካ ከበደ ነው።
ሙሌ ድሮ ድሮ እንደ ኢሕአፓም እንደ ብአዴን አድርጎት ነበር:: ምን አድርጎት ነበር ብቻ! ቆራጥ ታጋይ ነበር እንጂ:: በኢሕአዴግ አምናለሁ ይል ነበር፣ አፍ አውጥቶ:: ከተበላሹም አለቃቸውም እያለ ይዝት ነበር:: እነ በረከት፣ እነታምራት ላይኔ፣ እነ ሕላዌ ዮሴፍ የሙሌ ግጥም ነፍሳቸው ነበር:: ሙሌ የወልዲያ ልጅ ይሁን እንጂ አባቱ የትግራይ ሰው ናቸው:: ለትግልና ለታጋዮች የቀረበውም ለዚሁ ሳይሆን አይቀርም::
ስለ ሙሉጌታ ስብሀት ገ/እግዚአብሄር የተናገረውን በማስፈር ጉዳያችንን እንጠቅልል:: በነገራችን ላይ ስብሀት ሙሉጌታን የኔ ሼክስፒር ነው ይለዋል::ወዶ አይደለም::በአማርኛ የሚራቀቀውን ያህል ሙሉጌታ በእንግሊዝኛም ድንቅ የሆኑ ቅኔዎችን ተቀኝቷል::የሆነ ሆኖ የስብሀት ንግግር እነሆ
“ሙሉጌታ ግን ከቅዳሴ እስከ ቅኔ፣ ከዛም ተሻግሮ ቁርዓን፣ ሀዲስንና መንዙማን የሚያውቅ ምሑር ነው:: ይህም ባንዳንዶቹ ግጥሞቹ ውስጥ ይታያል:: እግዜርንም ሸይጣንንም በእኩል ንቀት እየገረመመ ሲያናግራቸው እንደ ዳኛ ነው:: ምንም ምክንያት ሳላገኝለት እውስጤ የሰረፀ ጥርጣሬ አለኝ:: በሞተበት ቦታና ሰዓት ከሰይጣን ጋር እየተፋጠጠ፣ እየተናነቀ ነበር ይሆን…እዝጌርም ሰይጣንም የለም የሚሉ አንባብያን ሁሉ፣ እዝጌርም ሰይጣኑም የመለሱለት የራሱ ሕሊና የፈጠረቻቸው ሕልም ወይም ቅዠት ናት በሉ:: ሌላ ማለት ብትፈልጉም መብታችሁ በሕገ-መንግስቱ የተጠበቀ ነው::”
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን ነሐሴ 1 ቀን 2014 ዓ.ም