ሳቅ እና ጨዋታ ብቻ የሚታይባት፣ ‹‹አቦ ፈታ በል!›› እያለ የተከፋውን ሁሉ ፈገግ የሚያሰኝ ሕዝብ ያላት ድሬዳዋ ከዛሬ 16 ዓመታት በፊት ኃዘን ጥላውን ጣለባት:: የድሬ ኃዘንም የመላው ኢትዮጵያውያን ኃዘን ሆነ:: የሬዲዮ ጣቢያዎች በዋሽንት አሳዛኝ ዜማ ልብ ሰባሪ ድምጽ ሲያወጡ ሰነበቱ:: ከዕለት ወደ ዕለት የሚሰማው ዜና የሟቾች ቁጥር እና የጠፉ ቤተሰቦች ቁጥር ብዛት ሆነ:: ያቺ የደስታ ምንጭ ድሬዳዋ ለወራት በኃዘን ድባብ ተዋጠች::
በዛሬው ሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችን የድሬዳዋን የጎርፍ አደጋ እናስታውሳለን:: በነገራችን ላይ በድሬዳዋ የጎርፍ አደጋ ላይ ፊልሞች እና ዘጋቢ ፊልሞች ተሠርተዋል:: የመታሰቢያ ፕሮግራሞች ተካሂደዋል:: ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ በችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ሲታወስ ቆይቷል:: እስኪ ክስተቱን እናስታውስ!
ሐምሌ 28 ቀን 1998 ዓ.ም ነው:: ሌሊቱን እጅግ ከባድ ዝናብ ጣለ:: የጣለው ከባድ ዝናብም ከባድ የጎርፍ አደጋ አስከተለ:: በወቅቱ በኢትዮጵያ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አልነበሩም:: መረጃው ለመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድ ጊዜ የመድረስ ዕድል አልነበረውም::
አደጋው የደረሰው ሐምሌ 28 ሌሊት ለሐምሌ 29 አጥቢያ ነው:: ሐምሌ 29 ቀን 1998 ዓ.ም ጠዋት በጥቂት የቴሌቪዥን ተጠቃሚዎችና በብዙ የሬዲዮ ተጠቃሚዎች ዘንድ ይህ አሳዛኝ ዜና መሰማት ጀመረ:: የድሬዳዋ የጎርፍ አደጋ! በሁለተኛው፣ ሦስተኛውና አራተኛው ቀን… እያለ ግን በሕትመት መገናኛ ዘዴዎችም ተጨማሪ ሐተታዎችን ጨምሮ ተደራሽነቱ እየሰፋ መጣ::
ከአደጋው ክስተት መሰማት በኋላ አኃዛዊ መረጃዎችም መውጣት ጀመሩ:: 200 ያህል ሰዎች ሕይወታቸው አልፎ ተገኘ፤ 300 ያህል ሰዎች የደረሱበት ሳይታወቅ ቀረ:: 3 ሺህ ያህል ሰዎች ደግሞ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቀሉ::
የውጭ መገናኛ ብዙኃን በወቅቱ እንደዘገቡት አደጋው በምሥራቅ አፍሪካ ከፍተኛ የተባለ አደጋ ነበር:: አደጋው የ15 ሚሊዮን ዜጎችን ሕይወት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እንደሚነካ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ድጋፍ ጉዳዮች ትብብር ጽሕፈት ቤት(UN Office for the Coordination of Humanitarian Affairs) መረጃ ያመለክታል::
ከሐምሌ 30 ቀን ጀምሮ የእርዳታ ሰጪ ድርጅቶች (የዓለም የምግብ ፕሮግራም፣ ዩኒሴፍ የመሳሰሉት) እና መንግሥት ወደ ቦታው መድረስ ጀመሩ:: የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋትና ዝግጁነት ኤጄንሲ የእርዳታ ዝርዝር ሒደቶችን ማሳወቅ ጀመረ:: ኤጀንሲው ሐምሌ 30 ቀን አስቸኳይ የምግብና ቁሳቁስ እርዳታዎችን ይዞ በቦታው እንደደረሰ የOCHA መረጃ ያመለክታል::
ከሐምሌ 30 በኋላ በተደረጉ ምርመራዎች ደግሞ የተፈናቃዮችና የሟቾች ቁጥር እየጨመረ መጣ:: 200 የነበረው የሟቾች ቁጥር በምርመራ የተረጋገጠው ብቻ 250 ደረሰ:: አጠቃላይ በአደጋው የተፈናቀሉት ደግሞ ከ10 ሺህ በላይ እንደሆነ የወቅቱ መረጃዎች ያሳያሉ:: በወቅቱ የነበረው የድሬዳዋ ሕዝብ ብዛት ከ398 ሺህ በላይ እንደነበር በ1997 ዓ.ም የተደረገው የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ መረጃ ያመለክታል:: ምናልባትም 400 ሺህ ሊሆን ይችላል::
ታሪክን ስናስታውስ በወቅቱ የነበሩ ሁነቶችን ጭምር ይነግረናል:: የድሬዳዋ የጎርፍ አደጋ የመድረሱ ዜና በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ከተሰማ በኋላ የድጋፍ ትብብሮች ተደርገዋል:: የወቅቱ የመንግሥት አካላት እና የተለያዩ ሲቪክ ማኅበራት ኃዘናቸውን ገልጸዋል::
ነሐሴ 1 ቀን 1998 ዓ.ም የታተመ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ባገኘነው መረጃ፤ የወቅቱ የድሬዳዋ ከተማ ጊዜያዊ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ፍስሐ ዘሪሁን ሐምሌ 30 ቀን 1998 ዓ.ም ድሬዳዋ ለደረሱ ጋዜጠኞች ስለአደጋው ሁኔታ መግለጫ ሰጥተዋል:: ከንቲባው በሰጡት መግለጫ፤ አደጋው የደረሰው ከሌሊት 7፡00 እስከ 9፡00 ባለው ነው::
ሌሊት 9፡00 ላይ ፖሊሶች ደርሰው ጥይት ወደ ሰማይ በመተኮስ እንቅልፍ የተኛ ሕዝብ እንዲነቃ አድርገዋል:: በሚተኮሰው ጥይት እና በሰዎች ጩኸት ለጊዜው አደጋው ያልደረሰባቸው የተገኙ ሰዎች ራሳቸውን እንዲያድኑ እና ሌሎችንም እንዲያድኑ ተደርጓል:: የተጎዱትንም ሕይወታቸውን ለማትረፍ ፖሊሶች በሌሊት ጥሪ አስተላልፈዋል::
የፌዴራል ፖሊስ እና የመከላከያ ሠራዊት አባላት በቦታው ሲደርሱ፤ የአካባቢው ነዋሪዎች ራሳቸውን ለማዳን በየጣሪያውና አጥሩ ላይ ወጥተዋል:: የፖሊስና የመከላከያ ሠራዊቱ አባላት እነዚህን በየጣሪያውና አጥሩ ላይ የወጡ ዜጎችን በማውረድ ወደ ሌላ አካባቢ አንቀሳቅሰዋል፤ የተጎዱትን ወደ ሆስፒታል ወስደዋል:: ተጎጂዎችን ማስተናገድ ከድሬዳዋ ድል ጮራ ሆስፒታል አቅም በላይ ስለነበር በከተማዋ የሚገኙ ሁሉም ክሊኒኮች አገልግሎት እንዲሰጡና መንግሥት ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው ጥሪ ተላልፏል:: ከመንግሥት በተጨማሪ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ባለሀብቶችም በወቅቱ ርብርብ አድርገዋል::
የጎርፍ አደጋው ደርሶ የነበረው በከተማዋ ስድስት ቀበሌዎችና በገጠር ደግሞ ጭሪ ሚጢ፣ በኬሐሎና ኢጀአነኒ ቀበሌዎች ነበር::
የድሬዳዋ የጎርፍ አደጋ በወቅቱ የነበሩ ተቋማትን ሁሉ ወደ አስቸኳይ ሥራ እንዲገቡ ያደረገ ነበር:: በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ብዙዎችን ይነካካል የተባለውም ለዚህ ነው:: የፌዴራል ተቋማት እንደየሥራ ድርሻቸው ተሰማርተዋል:: ለምሳሌ፤ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በጎርፍ አደጋው የፈራረሱ መንገዶችን በአፋጣኝ ጠግኖ ለእርዳታ ለሚገቡ ተሽከርካሪዎች ምቹ ማድረጉን በወቅቱ በነበሩ ዜናዎች ተነግሯል::
ነሐሴ 1 ቀን 1998 ዓ.ም የወቅቱ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ በድሬዳዋ ተገኝተው ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች ጎበኙ:: የአካባቢው ማኅበረሰብ ያደረገውን መደጋገፍ አድንቀው መንግሥት ተገቢውን ድጋፍና ጥበቃ እንደሚያደርግ ለተጎጂዎች ገልጸዋል:: የአካባቢው ነዋሪዎችም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ውይይት አድርገዋል::
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት በኋላ የፌዴራል አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኤጄንሲ በጎርፍ የተጎዱ ወገኖችን ለመደገፍ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሒሳብ ቁጥር ተከፈተ:: የሒሳብ ቁጥሩ በመገናኛ ብዙኃን ይፋ የተደረገ ሲሆን የሒሳብ ቁጥሩም 0171806845300 ነበር::
የድጋፍ ጥሪው እንደተደረገ ከግለሰቦች ጀምሮ ተቋማትና ባለሀብቶች ርብርብ አድርገዋል:: ለምሳሌ፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 200 ሺህ ብር፣ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ 150 ሺህ ብር፣ የሐረሪ ክልል 100 ሺህ ብር፣ የአዳማ ከተማ 100 ሺህ፣ በአጠቃላይ 550 ሺህ ብር ድጋፍ የተደረገው እስከ ነሐሴ 2 ቀን ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ ነበር::
ከዚያ በኋላ ባሉት ቀናት፣ ሳምንታት እና ወራት ውስጥ የእርዳታዎች ቁጥር እየጨመረ ሄደ:: የተለያዩ ተቋማት፣ ኃላፊነታቸው የተወሰነ የግል ኩባንያዎች፣ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኙ የተለያዩ ማህበራት እርዳታ እያሰባሰቡ ማስረከብ ጀመሩ:: የተለያዩ ተቋማት ሠራተኞች ደግሞ ከ10 እስከ 30 በመቶ የሚሆን የአንድ ወር ደሞዛቸውን ለግሰው እንደነበር ታሪክ አስቀምጦላቸዋል::
ኢትዮጵያውያን በአደጋ ጊዜ እንዲህ ናቸው:: መረዳዳት ባህላችን መሆኑን እንዲህ አይነት የታሪክ አጋጣሚዎች ያሳዩናል:: ባለሀብቶችና ተቋማት ላደረጉት ድጋፍ የተጠቀሱት የገንዘብ መጠኖች ከ16 ዓመታት በፊት መሆኑን ልብ እያልን:: ከ16 ዓመታት በፊት ከባለሀብቶችና ከተለያዩ ተቋማት በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ድጋፍ ማድረግ ትልቅ ነገር ነው::
በነገራችን ላይ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ‹‹በጎርፍ የተጎዱ ወገኖቻችን ሁሌም እናስባለን፤ ስጋቱንም ለመቀነስ ተግተን እንሠራለን›› በሚል መሪ ቃል ክስተቱን ያስታውሰዋል፤ በተለይም በ2008 ዓ.ም 10ኛ ዓመቱ ሲታወስ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና የመንግሥት አካላት በተገኙበት ነው:: ዳግም እንዲህ አይነት አደጋ እንዳይከሰት የጥንቃቄ ሥራዎች ይሠራሉ::
ከጥንቃቄዎች አንዱ ደግሞ ችግኝ መትከል ነው:: የድሬ ነዋሪዎች፣ የመከላከያ ሠራዊት አባላት፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን እና የተለያዩ አካላት ተሳትፈውበታል:: በየዓመቱ በችግኝ ተከላ ይታወሳል:: ባለፈው ዓመት በአንድ ቀን ብቻ 500 ሺህ ችግኞች ተተክለዋል::
ዛሬ ያ የመከራ ጊዜ አልፏል:: ‹‹አልፎ ለማዋየት ያብቃኝ›› ይላሉ አበው ችግር ሲያጋጥማቸው:: አልፎ ለማዋየት ያብቃኝ ማለት ያጋጠማቸው ችግር አልፎ በታሪክነቱ ብቻ ማስታወስ ማለት ነው:: ለዚህም ነው የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ቀኑን ሲያስታውስ ‹‹‹በጎርፍ የተጎዱ ወገኖቻችን ሁሌም እናስባለን፤ ስጋቱንም ለመቀነስ ተግተን እንሠራለን›› የሚለው:: ዳግም ችግሩ እንዳያጋጥም ሥራዎች ይሠራሉ ማለት ነው::
ለዚህም ችግኞች እየተተከሉ ነው:: አሁን በድሬዳዋ በ5 ሚሊዮን ብር የተገነባ የችግኝ ጣቢያ አለ:: በድሬዳዋ የሚዘጋጁ ችግኞች ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ ከጅቡቲ መንግሥት ጋር ያላትን ሁሉን አቀፍ ግንኙነት የሚያጠናከሩ መሆናቸውም ተነግሯል::
የድሬዳዋ አስተዳደር የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን የደን ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ማስረሻ ይመር ባለፈው ግንቦት ወር ውስጥ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት፤ ዘንድሮ ለአራተኛ ጊዜ በሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ ልማት ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ የደንና የፍራፍሬ ችግኞች በድሬዳዋ ይተከላሉ:: ባለፉት ሦስት ዓመታት በድሬዳዋ ከተተከሉት 4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ችግኞች ውስጥ በአማካይ 62 በመቶ የሚሆኑት ጸድቀዋል ተብሏል::
መጥፎ ታሪኮችን እንዲህ በበጎ መቀየር ይቻላል፤ ከዚህ በኋላ የድሬዳዋውን የጎርፍ አደጋ የምናስታውሰው በታሪክነቱ ብቻ ነው:: ምክንያቱም ዳግም እንደዚያ አይነት አደጋ እንዳያጋጥም ተደርጓል:: ይህ ጥንቃቄ ተጠናክሮ ይቀጥል እንላለን::
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 1 ቀን 2014 ዓ.ም