ቅድመ – ታሪክ
ለእሱ ልጅነቱ በብዙ መንገድ ተቃኝቷል። ሕፃን ሳለ ከእናቱ ጉያ አልተነጠለም። ቤት ካፈራው፣ ጓሮ ካሸተው እየተለየ ሲመረጥለት ቆይቷል። በፍቅር የሚያዩት ወላጆቹ ከሚገባው ሁሉ አላጎደሉም። የፈለገውን እየሰጡ፤ የአቅማቸውን እያሟሉ አሳደጉት። እዕድሜው ከፍ ሲል እንደ እኩዮቹ ደብተር ይዞ ቀለም አልቆጠረም። በቤተክርስቲያን አጸድ እየዋለ የቄስ ትምህርት መቅሰም ፍላጎቱ ሆነ።
አቅሙ ሲጠነክርና እግሮቹ ሲበረቱ በየሰፈሩ እየዞረ «በእንተስሟለማርያም» ማለት ጀመረ። የቆሎ ተማሪው እስክንድር ደበሎውን ለብሶ ከሰው በራፍ ሲቆም «ቁራሽ ተጋራኸን» ባዮቹ የመንደር ውሾች ያሯሩጡት ያዙ። ይሄኔ ለምኖ በማደር ተንከራቶ መዋልን አወቀ።
አንድ ቀን እስክንድር ዕውቀቱን በተሻለ ለማነጽ ካለበት ርቆ ተጓዘ። ድቁናውን ለመቀበል ከሀገሩ ወልቃይት ተሻግሮ በአክሱም ጽዮን ከተመ። በየደብሩ ከቅዳሴው ታድሞ ከማህሌቱ ሲቆም ለሌላ ዕድል ምርጫ ሰጠው። ካለበት ሳይርቅ የቅስናን ማዕረግ በክብር ተቀበለ። እንዲህ መሆኑ ራሱን በገቢ እንዲደጉም ማንነቱን በአንቱታ እንዲያስከብር ረዳው።
ቄስ እስክንድር አሁን በዕድሜና በዕውቀቱ በስሏል። የቆሎ ተማሪነት ጉዞው በበርካታ መንገዶች አመላልሶም ካሰበበት አድርሶታል። ይህ ብቻ ግን ለውስጠቱ በቂ አልሆነም። አሻግሮ የሚያስበው ልቡ የከተማን ህይወት ናፈቀ። የተሻለ ኑሮን መሻቱም መረጋጋት ነሳው። በዚህ ስሜት ውስጥ ሳለ ባህር ማዶ የቆየው ታላቅ ወንድሙ አገር ቤት መመለሱ ተሰማ። አሁን የልቡ ምኞት እንደሚሳካ ገመተ። ጓዙን ሸክፎም ወንድሙ ወዳረፈበት አዲስ አበባ አቀና። ይህ አጋጣሚ እስክንድርን ወደነበረበት አልመለሰውም። ከአዲስ አበባ ጋር በቀላሉ ተላመደ። ወንድሙን ሸኝቶ ኑሮውን በሸገር አደላደለ።
ከተሜነትን በቀላሉ የለመደው ወጣት ህይወቱን ለመቀየር ጊዜ አልፈጀበትም። የአዲስ አበባ ኑሮ ቀላል አለመሆኑን ያውቃል። ገንዘብ ካለና ቀልጣፋ ከሆኑ ግን ማደግና መለወጥ እንደሚቻል ለራሱ ነግሮታል። ይህን አቋሙን ለማጠንከር ደግሞ በየጊዜው ከወንድሙ የሚላክለት ዶላር ምክንያት ሆነው። በአጭር ጊዜም መኪኖችን ገዝቶ እየሸጠ ማትረፍ ጀመረ። ገንዘብ ሲይዝ ሀብት አፈራ። በተሻለ ቤት እየኖረ ዘመናዊነትን ሲላመድ ራሱን ለመለወጥ ፈጠነ።
አሁን በወንድሙ አጋዥነት የጀመረው የንግድ ሥራ በእጅጉ እየጣመው ነው። ከብዙዎች ጋር ያስተዋወቀው የመኪና ሽያጭ ከበርካታ ቢሮዎች ደጃፍ ሲያመላልሰው ይውላል። ይህ አጋጣሚ ደግሞ የጉዳይ ማስፈጸሙን ሥራ ጠንቅቆ እንዲያውቅ ረድቶታል። ለእስክንድር የእያንዳንዷን ሰነድ መነሻና መድረሻ፣ የእያንዳንዱን ኃላፊም የሥራ ድርሻና ግዴታ ማወቁ ቀላል የሚባል ሆነ።
አንድ ቀን እስክንድር ከነበረበት መኖሪያው ቀይሮ ቦሌ አካባቢ «ሚኒስትሮች ሰፈር» ወደሚባል አካባቢ ተከራይቶ ገባ። ቀልጣፋው ነጋዴ ፈጥኖ ከአከራዮቹ ለመግባባት ጊዜ አልወሰደም። ቤተኛ ለመሆንም ቀናትን አልቆጠረም። አከራዮቹ በአቀራረቡ መልካምነት ወደዱት። እሱም ቢሆን ለተሰጠው ምላሽ ልዩ አክብሮትን አልነፈገም። ውሎ ሲያድር ቀረቤታቸው ከሰላምታ ዘለለ። ምስጢርን አውቆ ችግርን ለመፍታትም የሚያህለው ጠፋ።
አከራዩ አቶ ቢልልኝ ውሎ ሲያድር የሆዳቸውን አወጉት። ቤቱ የወንድማቸው መሆኑን፣ ሰውዬው ከሀገር ውጪ እንደሚኖሩና ውክልናውን እሳቸው እንደወሰዱ ዘረዘሩለት። ይህን የሰማው እስክንድር ለአቶ ቢልልኝ አንዳንድ ጥያቄዎችን አቀረበ።
ሰውዬው ቤቱ በአዲስ የቤት ቁጥር እንደተመዘገበ ነገሩት። ይሄኔ እስክንድር ጥቂት አሰበ። ለይዞታው ስጋት ይሆናል የሚለውን ጉዳይም በማሳያ እያብራራና በምሳሌ እያጣቀሰ አስቀመጠላቸው።
ቤቱ ቁጥር ካልተሰጠው ቀበሌዎች በህግ እንደሚጠይቁ፣ ማስረዳት ሲጀምር ሰውዬው በሃሳብ ተከዙ። በተለይ ደግሞ የካርታው አለመታደስ ችግር እንደሚሆን ሲያሳምናቸው ይበልጥ ስጋት ገባቸው። ሰውዬው ጆሮ ሰጥተው የማዳመጣቸውን ያህል መፍትሔውንም ከእሱ ጠበቁ። «ምን ይበጃል?» ሲሉም ለጥያቄያቸው ፈጣን ምላሽን ናፈቁ።
እስክንድር ሁሉን ካወቀ በኋላ የመጀመሪያ መፍትሔ ያለውን መላ ነገራቸው። እሳቸው በውጣውረድ መድከም ስለማይኖርባቸው ሙሉ ውክልና እንዲሰጡትና ካርታውን በማሳደስ የሚገባውን ሁሉ እንዲፈጽም አሳወቃቸው። በርካታ ሰዎችን እንደሚያውቅና ጉዳዩን ለመፈጸም ለእሱ ቀላል መሆኑን ሲያስረዳቸው ባገኙት ምላሹ ተደሰቱ። የሚያሳጋቸው ችግር ከመድረሱ በፊት መፍትሔ በማግኘታቸውም ተከራያቸውን ከልብ አመሰገኑ።
ከቀናት በኋላ አቶ ቢልልኝ የቤቱን ተገቢ ማስረጃዎች በመያዝ ወደ ውልና ማስረጃ ቢሮ አቀኑ። ተከራያቸው እስክንድር በነገራቸው መሰረትም የእሱን ስም በማስፈር ሙሉ ውክልና እንዲሰጠው ወደውና ፈቅደው በፊርማቸው አረጋገጡ። ሙሉ ውክልናውን የወሰደው እስክንድር ሰነዱን ከእጃቸው ሲረከብ ቤቱን አስመልክቶ መሸጥና መለወጥ የሚሉ ቃላቶች ስለመኖራቸው አረጋገጠ። ይህ ከሆነ ከጊዜያት በኋላ እስክንድር ቀሪዎቹን ሰነዶች ተቀብሎ ጉዳዩን ለማስፈጸም ደፋ ቀና ማለቱን ጀመረ።
ማለዳ ወጥቶ በጨረቃ የሚመለሰው ተከራይ እንደወትሮው ለዓይን አልታይ አለ። በየምክንያቱ ከቤታቸው ሳሎን ወጣ ገባ የሚለው ሰው በድንገት እግሩን መሰብሰቡ ድንገተኛ ሆነ። በሥራ ብዛት ሰበብ ድምጹን ያጠፋው ተናፋቂ ሰውዬውን ቢያስገርም ደጅ ደጁን እያዩ መዋልን ለመዱት። ከግቢው እየተመላለሱም ዘበኛውን በጥያቄ ወተወቱ «ደህና ነው» ከመባል በቀር ምላሽ አላገኙም። ውሎ ሲያድር ምንም ተጨባጭ እውነትን ያለማምጣቱ ውል ሰጪውን ያሳስባቸው ያዘ።
አሁን አቶ ቢልልኝ ከወትሮው በተለየ ሃሳብ ገብቷቸዋል። ያደረባቸው ጥርጣሬም ዕንቅልፍ ይነሳቸው ጀምሯል። ጭንቀታቸውን ያከፈሏቸው በርካቶች ደግሞ ቤቱን ሊሸጠው እንደሆነ በመንገር ውክልናቸውን ማንሳት እንዳለባቸው እየመከሯቸው ነው። ይህን ሲሰሙ ውል ሰጪው ለደቂቃ አልዘገዩም። ቀሪውን ሰነዳቸውን ይዘው ወደ ውልና ማስረጃ ገሰገሱ። ሰጥተውት የነበረውን ውክልና አንስተውም የተሰጣቸውን ማረጋገጫ ተቀበሉ። በዚህ ብቻ አልቆሙም። ቤቱ እንዳይሸጥና እንዳይለወጥ የሚያዘውን የፍርድቤት እግድ ከእጃቸው አስገቡ።
እስክንድር የሆነውን ሁሉ በሰማ ጊዜ ንዴትና ብስጭት ያዘው። ሰውዬው የፈጸሙት ድርጊት ያላሰበው ቢሆንም በመቀደም ስሜት ተስፋ አልቆረጠም። በእጁ የሚገኘውን ህጋዊ ውክልና እያስተዋለ ቀጣዩን ዕቅድ ነደፈ። የሚያስፈልጉት ማስረጃዎች ሲሰበሰብ የትኛው ከየትኛው መቅደም እንዳለበት አልዘነጋም። መለኛ እጆቹን ሁሌም ቢሆን ያምናቸዋል። ከእግሮቹ ቀድመው ብዙ አራምደውታል። በጥንቃቄ ተጉዘው ከስኬት አድርሰውታል።
አሁንም በፍርድ ሂደት የሚያዋጣውንና የሚረታበትን ሰነድ በጥንቃቄ ለይቷል። ይህን ሁሉ በአግባቡ ካጠናቀቀ በኋላ ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ ለማለፍ መንገዱ ሁሉ ቀና ሆነለት። በእስክንድር እጆች የሚገኙት ህጋዊ የሚመስሉ ማህተሞች፣ የፊርማ ናሙናዎችና የተቋማት ዓርማዎች ሁሉ ያሰበውን ድርጊት ለመፈጸም ተቀዳሚ አጋሮቹ ናቸው። የእነዚህ
ጠቃሚ ጉዳዮች አብረውት መሆን ሲቃዥበት የቆየውን ህልሙን እውን እንደሚያደርጉለት እርግጠኛ ከሆነ ሰንብቷል። እናም የመጀመሪያውን ዕርምጃ አንድ ሲል የጀመረው አቶ ቢልልኝ በፍርድቤት ያስወሰኑትን የመሸጥ የመለወጥ የእግድ ትዕዛዝን ማሰረዝ ላይ ሆነ።
አሁን በውል ሰጪው ጥያቄና በፍርድ ቤቱ የማስወሰኛ ትዕዛዝ እግድ የተሰጠበት ውሳኔ በእጁ ይገኛል።ይህ የእግድ ትዕዛዝ በመዘገብ ቁጥር 165253 በቀን 22/07/02 ከፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የተላለፈ መመሪያ ነው። ትዕዛዙ ቤቱን መሸጥና መለወጥን ጨምሮ ለሌላ ሦስተኛ ወገን ማስተላለፍ እንደማይቻል በአግባቡ ያስረዳል።
ይህን የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሙሉ ለሙሉ የሚሽረውና በቀን 16/ 09/ 02 በእስክንድር ህገወጥ ማህተምና ቲተር ህጋዊ ሆኖ በአግባቡ የተዘጋጀው ጽሑፍ ደግሞ እግዱ ስለመነሳቱና ደብዳቤው ከተጻፈበት ጀምሮ ትዕዛዙ ተፈጻሚ እንደሚሆን ይገልጻል። ለዚህም ማስረጃ ይሆን ዘንድ የፍርድቤቱ የተለመደ ማህተምና የመዝገብ ቁጥር 13525 ያረፈበት ይዘት ያረጋግጣል። የወቅቱ የችሎት ኃላፊ ፊርማ ያረፈበት የወጪ ደብዳቤም ታግዶ የቆየው እግድ በትዕዛዝ መሻሩን ያመለክታል።
እስክንድር ይህን ደብዳቤ አዘጋጅቶ በእጁ ከያዘ በኋላ ወሳኝነት ያለውን የመጀመሪያ መንገድ ቀየሰ። ጉዞውን ወደሰነዶችና ማረጋገጫ ጽሕፈት ቤት አድርጎም ቀጣዩን ዕርምጃ ወደ ቦሌ ክፍለከተማ መሬት አስተዳደርና ግንባታ ፈቃድ ጽህፈት ቤት አፋጠነ። በእነዚህ ተቋማት ደርሶ ያሰበውን ለመከወን ፈጽሞ አልተቸገረም። ለእሱ ዓላማና ግብ ህጋዊ የሚመስሉት ማስረጃዎች በሙሉ ለየደረሱባቸው ተቋማት ተገቢና በቂ ነበሩ።
አሁን እስክንድር ከመንግሥታዊ ተቋማት ጋር ሊያገናኘው የሚችለውን ተጠያቂነት አግባብ በሚመስል ሰነድ አያይዟል። ከዚህ በኋላ የሚቀረው ቢኖር ሙሉ ውክልና የወሰደበትን ቤት በዋጋ ተደራድሮና ሰዎችን አማርጦ መሸጥ ብቻ ነው። ይህን ለማድረግ ደግሞ የመኪና ሽያጭ ልምዱ ብዙ አስተምሮታል። በደላላነት የቆየበት ጊዜም ገበያ እንዴት እንደሚገኝ አሳውቆታል።
እስክንድር ይህን ዕቅዱን ሲያወጣና ሲያወረድ ቆይቷል። የቀመረው ስሌት ዳር ደርሶ የሚያይበትን ጊዜ ሲናፍቅ ዕንቅልፍ አጥቶ ያደረባቸውን ጊዜያት አይረሳም። ሰነዶቹን ሲያሰናዳ በጥንቃቄ በመሆኑ የሚያሰጋው እንደሌለ እርግጠኛ ሆኗል። ለዚህ መተማመኛም አብሮት ብዙ ያሳለፈው የቅርብ ጓደኛው አግዞታል። ከዚህ ቀድሞ በማጭበር ወንጀል የተከሰሰበትን አጋጣሚ ያስበዋል። አሁን ግን ያለፈው ክፍተት እንዲደገም አይሻም። ድርጊቱ በጥርጣሬ፣ ዕርምጃው በጥንቃቄ ሆኗል።
ቤቱን ለመሸጥ ገበያ የማፈላለጉ ሂደት ቀጥሏል። የካሬው ስፋት፣የአካባቢው ማማርና የዋጋው ሚዛናዊነት በደላሎች አፍ እየተሞካሸ ነው። ብዙ ሰዎች ከስፍራው ደርሰው ቤቱን ይመለከታሉ። በዋጋ ተደራድረው፣አድራሻ ተለዋውጠው የሚለያዩ፣ በሃሳብ ተስማምተው ቀጠሮ አስይዘው የሚነጋገሩም በርክተዋል። አንድ ቀን ሁለት ባልና ሚስት ከስፍራው ደረሱ። የጥንዶቹን የመግዛት ፍላጎት የተረዱ ደላሎች በተለመደው አቀራረብ ካለው በላይ አጋነው አደራደሯቸው። ሰዎቹ የደላሎቹን አፍ ሰምተው ቤቱን ለማየት ፈቀዱ። ዋጋውን፣ካሬውንና የቦታውን አቀማመጥ ወደዱት።
ጊዜ ማጥፋት ያልፈለጉት ባልና ሚስት ከቤቱ ትክክለኛ ሻጭ ጋር ለመነጋገር ቀጠሮ ያዙ። በተባለው ቀንም ከእስክንድር ጋር ተገናኙ። እስክንድር የሰዎቹን ፍላጎት እንዳወቀ ራሱን አግዝፎ ማንነቱን አኩራርቶ ቀረባቸው። የተዘጋውን ግቢ በዘበኛ አስከፍቶ ሲያሳያቸው ቤቱን እንደገዛውና ሙሉ ህጋዊ ውክልና
እንዳለው በተመረጡ ቃላቶች እያሳመነ ነበር። ይሄኔ ገዥዎቹ አሉ የሚባሉ ሰነዶችን ጠየቁ። እስክንድር በጥንቃቄ ካስቀመጣቸው ማስረጃዎች መሀል የተጠየቀውን ሁሉ በየተራ እየመዘዘ ደረደረላቸው። ያለምንም ጥርጣሬ የሰነዶቹን ህጋዊነት አገናዝበው በሙሉ ልብ ተቀበሉት።
በድርድራቸው መሀል ስም ማዞር ያልቻለው «አሹራ» ላለመክፈል እንደሆነ ሲነግራቸው ሰውዬው ሊቀበሉት አልፈቀዱምና ቅሬታቸውን ገለጹ። በሚቀጥለው ቀን ቤቱ በፍርድቤት መታገዱን ስለመስማታቸው ነገሩት። እስክንድር ይህን እንዳወቀ እገዳው የተነሳበትን የፍርድቤት ትዕዛዝ አቀረበላቸው። ሰውዬው በድጋሚ ውልና ማስረጃ ሄደው ቤቱ እገዳ እንዳለበት ማረጋገጣቸውን ነገሩት። አሁንም እንዲህ ስለሆነበት ምክንያቱን በጥንቃቄ ለማስረዳት ሞከረ። ቤቱን ሲገዛ ቀሪ ሠላሳሺህ ብር ያለበት መሆኑ ለመታገዱ ሰበብ ሆኖ እንደቆየ በቀላሉ አሳመናቸው።
ገዥና ሻጭ ተቀራርበዋል። አሁንም ግን አንድ ሚሊዮን ሠላሳ ሺህ ብር የተቆረጠበት ቤት ጉዳይ ዳር አልደረሰም። ቤቱን ለመረካከብ ቀሪው ሠላሳሺህ ብር ተከፍሎ ማለቅ ይኖርበታል። እስክንድር ይህን ሲያውቅ መላ ያለውን መፍትሄ አቀረበ። ሰውዬው የመኪናውን ሊብሬ ይዘው ስልሳሺህ ብር እንዲሰጡትና ከፈለጉም በግዢ እንዲወስዱት አማከራቸው። በዚህ ሃሳብ የተስማሙት ሰው አስር ሺህ ብር ጨምረው መኪናውን በስማቸው አዞሩ። ከዚህ በኋላ በመሀላቸው ያለው መተማመን ጠበቀ።
ቤቱን በተባለው ዋጋ ተረክበው በባለቤታቸው ስም የገዙት አባወራ በዕለቱ በውልና ማስረጃ የተረጋገጠ ማስረጃቸውን ተቀበሉ። በወቅቱ ቤቱን በእጃቸው ለማስገባት ህጋዊነትን የተከተለው መንገዳቸው ትክክለኛ ነበር። ለዚህም ያለፉባቸው መንግሥታዊ ተቋማትና የህጋዊ ውል ሰነዶቻቸው አረጋግጠውላቸዋል።
ጥንዶቹ ቤቱን ገዝተው ከተረከቡ በኋላ የቤቱ ትክክለኛና ህጋዊ ወኪል አቶ ቢልልኝ የሆነውን ሁሉ ከቦታው ደርሰው አረጋገጡ። አዲሷ የቤቱ ባለቤት ወይዘሮ ወርቅነሽ ለተጠየቁት ሁሉ ህጋዊ ካርታና ሰነዳቸውን አሳዩ። አግባብ ባለው ሂደት ግዢውን መፈጸማቸውንም አስረዱ። ባልታሰበ መንገድ ቤቱን የተነጠቁት አቶ ቢልልኝ ይህን ሲሰሙ «አደራዬን በላሁ» ሲሉ ደነገጡ። ፈጥነው በእስክንድር ላይ ክስ ከመመስረትና ጉዳዩን በህግ ከመያዝ ሌላ ምርጫ አልነበረቻውም።
የፖሊስ ምርመራ
ፖሊስ ከተበዳይ የሰማውን ሁሉ በመዝገገቡ አሰፈረ። ወይዘሮ ወርቅነሽን ጠርቶ ሲያነጋግርም ቤቱን በህጋዊ መንገድ ስለመግዛታቸው በቂ ማስረጃዎችን እያወጡ አሳዩት። ፖሊስ ግለሰቡን በቁጥጥር ስር ለማዋል ክትትሉን ጀመረ። ቆይቶ ግን
ተፈላጊው እስክንድር በሌላ የወንጀል ክስ ማረሚያ ቤት እንደሚገኝ አረጋገጠ።
ተጠርጣሪውን በህግ አግባብ ይዞ ለመጠየቅ የፍርድቤት ትዕዛዝ ያስፈልጋል። ደብዳቤዎችን መጻጻፍና ከሚመለከታቸው ተቋማት በቂ ማስረጃዎችን ማሰባሰብም ግድ ይላል። የሰነድና የሰው ምስክሮች፣ የፎረንሲክና የጣት አሻራዎች ሁሉ ክሱን ለመመስረት አስረጂዎች ይሆናሉ። በፖሊስ በኩል ይህ ሲጠናቀቅ ግለሰቡ የዋስ መብቱ እንዳይፈቀድለት የተደረገው ጥረትም ተሳካ።
ፖሊስ የጊዜ ቀጠሮ እየጠየቀ ማስረጃዎችን ሲያጠናክር ቆየ። ለድርጊቱ ዋንኛ ተባባሪ ነበር የተባለ ባልንጀራውንም በቁጥጥር ስር አዋለ። በፍርድ ቤት የመበርበሪያ ትዕዛዝ ቤቱን ለመፈተሽ እማኞችን የቆጠረው ፖሊስ በመኖሪያ ቤቱ በርካታ ማህተሞችን፣ ቲተሮችንና በተጠርጣሪው የተለያዩ ስሞችና በሌሎች ግለሰቦች ማንነት የተመዘገቡ የነዋሪነት መታወቂያዎችን አገኘ።
በመዝገብ ቁጥር 142/2003 የተለየው የፖሊስ የምርመራ መዝገብ በየቀኑ የሚገኙ ማስረጃዎችን ያሰፍራል። እስከአሁን በተጠርጣሪው እስክንድር አበበ ላይ አስራአንድ የሰው ምስክሮች ቆጥረዋል። አስር የተለያዩ ህገወጥ ሰነዶችም ፍጹም በሚመስሉ ህጋዊነት ስለመቀየራቸው ተረጋግጧል። ግለሰቡ ቤቱን በህገወጥ ሰነድ ከሸጠው በኋላ በባህርዳር ከተማ የገዛው መጋዘን ስለመኖሩም መረጃዎች ተያይዘዋል። የግለሰቡ ተባባሪ ነበር የተባለው ተጠርጣሪ ማስረጃ ባለመገኘቱ በነፃ እንዲሰናበት ሲደረግ፤ በተጠርጣሪው እስክንድር ላይ ደግሞ ክስ ለመመስረት የሚያስችሉ በቂ ማስረጃዎች ተሟልተው ለችሎት ቀረቡ።
ውሳኔ
በረዳት ሳጂን አድነው የሎታ የተጠናከረው የፖሊስ መዝገብ ክሱን አጠናክሮ ለዐቃቤህግ አቅርቧል። ታህሳስ 4ቀን 2004 ዓ.ም ግለሰቡ በተከሰሰበት የሰነድ ማጭበርበርና ከባድ የማታለል ወንጀል ውሳኔ ለማሰጠት ዳኞች በችሎቱ ተሰይመዋል። ተከሳሽ እስክንድር አበበ በፈጸመው የሰነድ ማጭበርበር ወንጀል በርካታ ተቋማትን አሳስቷል። ተበዳዩን ጨምሮ በሌሎች ላይ በፈጸመው ከባድ የማታለል ድርጊትም ሀብትን እስከማሳጣት የደረሰ ኪሳራ ላይ ጥሏል።
የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድቤት ስድስተኛ የወንጀል ችሎት ተከሳሽ እስክንድር አበበን ሙሉ ለሙሉ ጥፋተኛ ሆኖ አግኝቶታል። ለዚህ የወንጀል ድርጊቱም «ይገባዋል» ያለውን የአስራ ሰባት ዓመት እስር በማረሚያ ቤት እንዲያሳልፍ፣ ሦስት ዓመታት ከማንኛውም ህዝባዊ መብቱ እንዲታገድና ብር አርባ ሺህ በቅጣት ገቢ እንዲያደርግ ሲል ብይኑን አሳልፏል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 21/2011
በመልካምስራ አፈወርቅ