የወሰን ማስከበር ማለት መንገዶችን ለመገንባት በወጣለት ዲዛይን ክልል ውስጥ የሚገኝ ማንኛውም ሀብት ወይም ንብረት የማስነሳት ህጋዊ መብት ነው:: ወሰን ማስከበር ከመሬት ላይ የሚታየውን የመንግስት እና የግለሰቦች ሀብትና ንብረት አስፈላጊውን የካሳ ክፊያ ፈጽሞ የማስነሳት መብት ነው:: የመንግስት ሀብት እና ንብረት ሲባል የቴሌ መሰረተ ልማቶች፣ የውሃ መስመሮች፣ የኤሌክትሪክ መስመሮች ሊሆኑ ይችላሉ:: የግለሰብ ሀብትና ንበረት ሲባል ደግሞ ቤት እና ሌሎች ቋሚ ሀብቶች ሊሆን ይችላል:: ከመሬት በላይ ከሚታየው ሀብትና ንብረት ባሻገር ከመሬት በታች የሚገኙ የማይታዩ ንብረቶችንም ጭምር የሚያካትት ነው::
በሀገራችን በርካታ የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተካሄደ ነው:: ከነዚህ የመንገድ ፕሮጀክቶች ውስጥ ግንባታቸው በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ ያሉ ፕሮጀክቶች እንዳሉ ሁሉ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት የተጓተቱ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን በቅርቡ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት በረቂቅ የመንገድ ፖሊሲ ላይ ውይይት በተደረገበት ወቅት ገልጸዋል::
በኢትዮጵያ ውስጥ የመንገድ ስራን እጅግ ውስብስብ እና አዳጋች እያደረጉ ካሉት መሰናክሎች መካከል ከወሰን ማስከበር ጋር የተያያዙ ችግሮች ትልቁን ቦታ እንደሚይዙ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ ይናገራሉ:: አብዛኞቹ የተጓተቱ ፕሮጀክቶች ዋነኛው ችግራቸው ከወሰን ማስከበር ጋር ይያያዛል:: የመንገዶች አስተዳደር ለመንገዶች መጓተት ዋነኛው ምክንያት እየሆነ ያለው የወሰን ማስከበር ችግር እንደሆነ ሲገልጽ ይደመጣል::
በቅርቡ በሂልተን ሆቴል በተዘጋጀው የመንገድ ፖሊሲ እና የመንገድ አዋጅ ረቂቅ ሰነዶች ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፣ከሁለቱም ምክር ቤቶች ፣ ከክልል ባለድርሻ አካላት ፣ከተለያዩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፤ እንዲሁም ከልዩ ልዩ ተቋማት የተወጣጡ ተሳታፊዎች በታደሙበት መድረክ ላይ እንደተገለጸው፤ የግለሰቦች ንብረቶች እና የመንግስት ሀብቶች እና ንብረቶች በጊዜ አለመነሳት ለመንገድ ፕሮጀክቶች እንቅፋት እየሆነ ነው:: በተለይም እንደ መብራት፣ ቴሌ፣ ውሃና ፋሳሽ አገልግሎት ያሉ ተቋማት ጋር የጋራ እቅድ አውጥቶ የመስራት ችግር ለፕሮጀክቶች መጓተት ምክንያት እየሆነ ነው:: ከዚያ አልፎም ለግብአቶች ብክነትም መንስኤ እየሆነ ነው::
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በሚገነቡ የመንገድ ፕሮጀክቶች ላይ የወሰን ማስከበር ችግሮች እና ከካሳ ክፊያ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ችግሮች እንዲበራከቱ ዋነኛው መንስኤ እየሆነ ያለው በተቋሙ የሚገነቡ የመንገድ ፕሮጀክቶችን የክልል እና የወረዳዎች የመንግስት አካላት እንዲሁም ህዝቡ በውጫዊ አካል የሚገነቡ ፕሮጀክቶች አድርገው እየተመለከቱ ያሉበት ሁኔታ ነው:: የወሰን ማስከበር ችግሮች በሚከሰቱበት ወቅት አስፈላጊውን ትብብር ያለማድረግ ወይም አላስፈላጊ ካሳ በሚጠየቅበት ወቅት ችግሩን ለመቅረፍ ጥረት ከማድረግ ይልቅ የችግሩ መንስኤ የመሆን አዝማሚያዎች በእነዚህ አካላት በኩል ይታያሉ::
እንደ ወይዘሮ ጫልቱ ማብራሪያ፤ በመንገዶች አስተዳደር በሚገነቡ መንገዶች ላይ የክልሎች እና የፌዴራል መንግስት ሚና በግልጽ አለመቀመጡ በመንገዶች ግንባታ ላይ ከባድ እንቅፋት ሲፈጥር ቆይቷል:: ችግሩ በተለይም ከወሰን ማስከበር ጋር ተያይዞ ከባድ ተግዳሮት ሲሆን ተስተውሏል:: ከካሳ ክፊያ ጋር ተያይዞ ያለውን ችግርም ሲያባብስ ቆይቷል::
በአንዳንድ አካባቢዎች በፌዴራል መንግስት የሚገነቡ የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ ይካሄዳሉ ተብለው በተለዩ አካባቢዎች በአንድ ሌሊት ቤት ገንብቶ ወይም አትክልት ተክሎ የማደር ሁኔታዎች መኖራቸውን የጠቆሙት ሚኒስትሯ፣ ይህ ከተሳሳተ እሳቤ የመነጨ ተግባር መሆኑን አንስተዋል:: መሰል ችግሮች በሚፈጠሩበት ወቅት ችግሩን ለመቅረፍ ክልሎች እና ሌሎች የአካባቢ አስተዳደር መዋቅሮች የሚያደርጉት ጥረት እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነም ያስታወቁት::
በዚህም ምክንያት የመንገዶች አስተዳደር ለአላስፈላጊ ወጪ ሲዳረግ መቆየቱን የጠቆሙት ሚኒስትሯ፣ ለመንገድ ግንባታ መዋል ያለበት ገንዘብ ለካሳ እንዲውል ምክንያት እየሆነ መምጣቱን ጠቁመዋል:: አስተዳደሩ በወሰን ማስከበር እና በካሳ ምክንያት በዓመት ከ10 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ ለማድረግ እየተገደደ መሆኑን ነው የተጠቆመው::
የመንገዶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሀባታሙ ተገኝ በበኩላቸው መንገዶች አሁን እየተገነቡ ባለበት አካሄድ፤ በተለይም ክልሎች፣ እና ከክልል በታች ያሉ መዋቅሮች ከወሰን ማስከበር ጋር ተያይዞ የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽኦ በሚፈለገው ልክ ማበርከት ባልቻሉበት ሁኔታ አስተዳደሩ የመንገዶችን ግንባታ ለማስቀጠል እንደሚቸገር ነው ያስገነዘቡት::
የወሰን ማስከበር ጉዳዩች እልባት ሳያገኙ ወደ ግንባታ መግባት ችግር እየፈጠረ መሆኑንም የመድረኩ ተሳታፊዎች አንስተዋል:: የመንገዶች ግንባታ ከመጀመራቸው በፊት የወሰን ማስከበር ችግሮችን መፍታት እንደሚያስፈልግ በህግ የተደነገገ ቢሆንም በማስፈጸም አቅም ውስንነት፣ በተነሺዎች በኩል በሚኖር ዳተኝነት፣ በሌሎች ተያያዥ ችግሮች ምክንያት ወሰን ሳይከበር የመንገድ ፕሮጀክቶች ዲዛይናቸው አልቆ በቀጥታ ጨረታውን ላሸነፈው ስራ ተቋራጭ ሲሰጥ ይስታዋላል::
ተቋራጩ ግንባታውን ሲጀምር የውሃና ፋሳሽ መስመር ወይም የመብራት መስመር ይገኛል:: በዚህም ምክንያት ግንባታው ለመቆም ይገደዳል:: ወይንም ደግሞ ለግለሰቦች ይዞታ አስፈላጊውን የካሳ ክፊያ ሳይከፈል ሲቀር ንብረታቸው እንዳይነሳ ከፍርድ ቤት እግድ አምጥተው ያሳግዱታል:: በዚህ መሃል የመንገድ ፕሮጅክቱ የወሰን ማስከበር ችግር አለበት ተብሎ ይቆማል:: በተለይም ቴሌ ኮሙዩኒኬሽን፣ ውሃና ፍሳሽ፣ መብራት ሀይል፣ እንዲሁም በግንባታ ዘርፍ የተሰማሩ የመንግስት መሰረተ ልማት ተቋማት የሚሰሩት ለአንድ ሀገርና መንግስት እስካሆነ ድረስ እርስ በርስ ተናበውና ተደጋግፈው መስራት ቢችሉ ከወሰን ማስከበር ጋር ተያይዞ እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ያስችላል::
አንዳንድ የመሰረተ ልማት ዘርጊ ተቋማት ካለባቸው ከፍተኛ የማቴሪያልና የሰው ሀይል እጥረት፣ መሰረተ ልማቶቹ ያሉባቸውን ቦታዎች የሚያሳይ ግልጽ የሆነ ማስተርፕላን ካለመኖር ጋር ተያይዞ ማቴሪያሎቹ በመሬት ውስጥ የተቀበሩባቸውን ቦታዎች በአግባቡ ለይቶ ከማወቅ አንጻር ከፍተኛ ችግሮች መኖራቸውም ነው በመድረኩ ላይ የተጠቆመው::
አንዳንድ ጊዜ ምንም አይነት የወሰን ማስከበር ችግር አይኖርበትም በተባለበት የመንገድ ልማት ፕሮጀክት ሲጀመር ከመሬት ውስጥ ትላልቅ የውሃ ወይም የፍሳሽ ማስወገጃ መስመሮች የሚገኙበት ሁኔታ ያጋጥማል:: መስመሩን ለማንሳት ረጅም ጊዜ ከመውሰዱና የመንገድ ግንባታውን ከማስተጓጎሉ ባሻገር እነዚህን የውሃ መስመሮችን ከቦታው የማስወጣት ሂደት ከፍተኛ ወጪንም ይጠይቃል::
አዲስ የተዘጋጀው የመንገድ ፖሊሲ ከወሰን ማስከበር እና ከካሳ ክፊያ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን ሙሉ በሙሉ የሚቀርፍ መሆኑን በመድረኩ ላይ ረቂቅ ፖሊሲውን ያቀረቡት የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ የትምጌታ አስራት ተናግረዋል:: በአዲሱ ፖሊሲ ላይ ከመንገዶች ግንባታ ጋር ተያይዞ የክልሎች እና የፌዴራል መንግስት ሀላፊነት እና ስልጣን በግልጽ የተቀመጠ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህም ይከሰት የነበረውን የሚና መደበላለቅ እና የወሰን ማስከበር ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት እንደሚያስችል ጠቁመዋል::
እንደ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ፤ የፌዴራል መንግስት፡- በአገሮች ደረጃ ወይም በመንግስታት መካከል ያሉት ጉዳዮች በብቸኝነት የሚከናወኑት በፌዴራል መንግስት አማካይነት ነው:: በመሆኑም የፌዴራሉ መንግስት ከሌሎች ሀገሮች መንግስታት እንዲሁም በየ መንግስታት ተቋማት መካከል ላሉ የመንገድ ዘርፍ ጉዳዮች የአገናኝነት ኃላፊነት ይኖረዋል:: በተጨማሪም ለዘርፉ የሚጠበቀውን አመታዊ በጀት በመመደብ የስራ አፈፃፀሙን እንደሚገመግምም ነው ያብራሩት:: በዚሁ መሰረት፤ አዲስ አበባን ከክልሎች እና ከሌሎች ሀገሮች ጋር የሚያገናኙ መንገዶችን እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ጠቃሜታ ካላቸው አካባቢዎች ጋር የሚያገናኙ መንገዶችን በፌዴራል መንገዶች የሚገነቡ ይሆናል:: የፍጥነት መንገዶች፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ የማዕድን መቆፈሪያ ስፍራዎች መንገዶች በፌዴራል መንገዶች የሚገነቡ ይሆናል::
በብሔራዊ ክልላዊ መንግስታት እንዲከናውኑ ከሚጠበቁ ተግባራት መካከል የከተማ መንገዶች፣ የገጠር መንገዶችና የወረዳ መንገዶችን መገንባትና መንከባከብ፣ እንዲሁም የአካባቢ አየር ጥበቃ እና የትራፊክ አስተዳደር ትኩረት የሚሰጡት ይሆናል:: ከዚህ በተጨማሪ የመንገድ መሰረተ ልማት የተቀናጀና የተናበበ እንዲሆን የበኩላቸውን ሚና መወጣት ይጠበቅባቸዋል:: በዚሁ መሰረት መጋቢ መንገዶችን ደግሞ የክልል መንገዶች የሚገነቡ ይሆናል:: መዳረሻ እና መጋቢ መንገዶችን የክልል መንግስታት ራሳቸው አቅደው የሚገነቡ ከሆነ በክልል መንገዶች የሚገነቡ ይሆናል::
ለአብነት ያህል ክልሎች የሚያስገነቡት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ካሉ ወደዚያ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚገነቡ መንገዶችን ክልሎች የሚገነቡ ይሆናል፤ ራሳቸው ያስተዳድራሉም፤ የፌዴራል መንግስት የሚገነባው የኢንዱስትሪ ፓርክ ካለ ደግሞ የፌዴራል መንግስት መንገዱን ያስገነባል፤ ያስተዳድራልም:: ይህም ከዚህ ቀደም ከወሰን ማስከበር ጋር የነበሩ ችግሮችን ከመቅረፍ ባሻገር ለካሳ ክፊያ ይወጣ የነበረውን ወጪ እንደሚቀንስ ነው ያብራሩት::
እንደ አቶ የትምጌታ ማብራሪያ፤ ፓሊሲው ከክልል እና ከፌዴራል መንግስት ባሻገር የግል ሴክተር ተሳትፎንም በግልጽ ያስቀመጠ ሲሆን፤ መንግስት የግል ሴክተሩ በመንገድ መሠረተ ልማት ያለውን ተሳትፎ እንዲያሳድግ ያበረታታል:: ይህም የግል ሴክተሩ በንግድ እንቅስቃሴ ያለው ሚና በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምር ያደርጋል:: ከዚህ አንፃር መንግስት ውጤታማ የግል ሴክተርን በመዋዕለ ንዋይ ለመደገፍ አግባብነት ያላቸው የህግ፣ ተቋማዊና የቁጥጥር ማዕቀፎች በሥራ ላይ እንዲውሉ ያደርጋል:: የመንገድ መሰረተ ልማት የመጨረሻ ተጠቃሚው ሁሉም የህብረተሰቡ ክፍል ሲሆን፣ የሚገነቡትን መንገዶች በተገቢው መንገድ እንዲጠቀም እና እንዲሁም የመንገድ መሰረተ ልማትን እንዲጠብቅ ማድረግን ይጠይቃል::
ሚኒስትሯ ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ፖሊሲው በሀገር አቀፍ ደረጃ የመንገድ ልማት በተቀናጀ እና በተናበበ መልኩ እንዲከናወን ይረዳል:: ለፍትሃዊነት እና እኩል ተጠቃሚነት ጥያቄዎች መሰረታዊ ምላሽ ለመስጠት ያስችላል:: የሀገሪቱን የመንገዶች ደረጃ መወሰንና የቁጥጥር ስርዓት ማበጀት ያስችላል::
የመንገድ መሰረተ ልማት አስተዳደርና ቁጥጥርን አስመልክቶ የፌዴራል፣ የክልልና የከተማ አስተዳደር የተሰጣቸው ተግባርና ሀላፊነት በማያሻማ ሁኔታ እንዲቀመጥ መደረጉ የመንገድ ባለቤትነትን፣ የወሰን ማስከበርን በተመለከተ ሀገሪቱ የምትከተለውን አቅጣጫ የሚያመላክት በመሆኑ ለዘርፉ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ጠቁመዋል::
ሚኒስትሯ ከወሰን ማስከበር ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ችግር እንዲከሰት ምክንያት እየሆነ ያለው የማህበረሰቡ ግንዛቤ እጥረት መሆኑን ጠቁመው፤ ማህበረሰቡ የሚገነበው መሰረተ ልማት የራሱ እንደሆነ ያለመመልከት አዝማሚያዎች መኖራቸውን ይገልጻሉ፤ አዲሱ ፖሊሲ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ከፍ ለማድረግ መሰራት እንዳለበትም የሚያስቀምጥ እንደመሆኑ ፋይዳው ላቅ ያለ ነው ብለዋል::
አዲስ ፖሊሲ መቀመጡ ከወሰን ማስከበር ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን ለመቅረፍ ከፍተኛ አስተዋጽ እንደሚኖረው ቢታመንም የሌሎች ባለድርሻ አካላት ሚና እና ትብብር ወሳኝ ነው:: ስለዚህ እያንዳንዱ የልማት ተቋም የሚቀብረውን የውሃ እና የፍሰሽ፣ ኤሌክትሪክ ፣ የስልክ መስመሮችን የትና በየት በኩል እንደሚያልፍ በዘመናዊ መልክ የተቀናጀ መረጃ ሊኖረው ይገባል:: ይህ ካልሆነ ግን አንድ መሰረተ ልማት በተገነባ ማግስት የመፍረስ ሁኔታ ይቀጥላል:: ስለዚህ ከምንም በላይ የመሰረተ ልማት ገንቢ ተቋማት ስራቸውን ተናበው ሊሰሩ ይገባል::
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 30/ 2014