ዘመን አይዘምን አይባልምና መሽቶ ሲነጋ አዲስ፣ ሲውል ሲያድር ድንቅ የተባሉ መገልገያዎች ዓለማችንን ይቀላቀላሉ:: እነዚህ መገልገያዎችም በቀዳሚነት ሥራን ለማቅለል ሲቀጥልም ባለማወቅ አልያም በጥንቃቄ ጉድለት ጉዳትን ሲያስከትሉ ይስተዋላል:: ለዚህም ነው ቁጥራቸው ጥቂት በማይባሉ እቃዎች ላይ ስለ አጠቃቀማቸው፣ ስለ ጉዳት፣ ጥቅማቸውና በውስጣቸው ምን ይዘዋል የሚለውን የሚያስረዱ መረጃዎችን ወይም የወረቀት ማስታወሻዎችን የምናገኛቸው::
አንዳንድ ቁሶች ግን ምንም አይነት የማስገንዘቢያ ጽሑፍ ሳይጻፍባቸው፤ ባስ ሲልም ምንም አይነት ማሸጊያ ሳይኖራቸው ገበያ ላይ ሲወጡ እንመለከታለን:: ይህ በሆነባቸው ምርቶች ላይ ደግሞ ስለ ምርቶቹ አገልግሎትና ይዘት፣ ጥቅምና ጉዳት ዙሪያ በተጠቃሚዎች ዘንድ የግንዛቤ ክፍተት መፍጠሩ የታወቀ ነው:: ይሄን አይነት ምርቶች ደግሞ በቀጥታ ከሕጻናት ጋር ግንኙነት ሲኖራቸው ጉዳቱ ከፍ ያለ ይሆናል::
ድሮ ድሮ ክፉና ደጉን ለይተው የማያውቁ ሕጻናት በአፈርና ውሃ፣ በተለያዩ የዳንቴል አሻንጉሊቶች፣ ባለቀ ወይም በማይፈለግ ዕቃ ይጫወቱ ነበር:: አሁን አሁን ደግሞ በተለያዩ አሻንጉሊቶች እና የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች፣ ለእነርሱ ተብለው በተዘጋጁ የዘመኑ መጫወቻዎች ሲጫወቱ ይስተዋላል:: ለወላጅም ቢሆን ሕጻናት በዚህ መልኩ ጊዜያቸውን ሲያጣጥሙ ማየት ደስታን ያጭራል:: በዚህ ሂደት ታዲያ ሕጻናቱ ለጨዋታ አሊያም ለድድ ማከኪያ መጫወቻዎቻቸውን ወደ አፋቸው ሲከቱ መመልከት የተለመደ ነው::
ልብ ይበሉ!
ሊትየም/በተን ባትሪ፤ ስሪቱ ከዚንክ፣ ሊትየም፣ ሜርኩሪ፣ ማንጋኒዝ ዳይኦክሳይድ፣ ሲልቨር ኦክሳይድ እና ከመሳሰሉት መሆኑ ይነገራል:: እኛም የጉዳዩን አሳሳቢነት በመገንዘብ በዚህች ጽሑፍ ወላጆችን ልናስገነዝብም ሆነ ተጠንቀቁ ልንል ወደድን:: ምናልባት አብዛኞቻችን ይህን ባትሪ በእጅ ሰዓቶች ላይ እንደሚገኝ አስተውለን ይሆናል:: ነገር ግን በቤት የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎቻችን ማለትም እንደ ሪሞት ኮንትሮል፣ አሻንጉሊት፣ ሙዚቃ ማጫወቻ ያላቸው ካርዶች፣ ካልኩሌተር፣ ካሜራ፣ ቴርሞ ሜትር፣ የሕጻናት የሚያበሩ ጫማዎች ውስጥና መሰል ትልልቅ እና ትንንሽ ዕቃዎች ውስጥ የሚገኝና እንደ ኃይል ምንጭነት የሚያገለግል በተለይ ለሕጻናት አደገኛነት ያለው ባትሪ ነው::
በተን ባትሪ፣ በይዘቱ አናሳ በመሆኑና በስፋት ሊገኝ መቻሉ ይበልጥ አደገኛ ያደርገዋል:: ከተለያዩ ምንጮች የተገኙ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በዓለም ላይ በርካታ ሕጻናት ሕይወታቸው በሊቲየም የተነሳ ያልፋል:: በእንግሊዝ አገር ቁጥሩን በትክክል ማወቅ ባይቻልም በዓመት ቢያንስ 2 ሕጻናት ይህን ባትሪ በመዋጥ ሕይወታቸው ያልፋል፤ በአውስትራሊያም እንዲሁ ከ2 እስከ 4 የሚሆኑ ልጆች ሕይወታቸውን ያጣሉ::
ይህ እንዴት ሆነ?
በተን ባትሪ ሲዋጥ በሦስት መንገዶች ጉዳትን ያስከትላል:: አንደኛው፣ የኤሌክትሪክ ፍሰትን በመፍጠር ሲሆን፤ ሁለተኛው፣ በስስ የሠውነት ክፍሎቻችን ላይ ግፊት በማድረግ ነው:: ሦስተኛው መንገድ ደግሞ እንደ ኮስቲክ ሶዳ ያሉ መርዛማ/አደገኛ ኬሚካሎችን በመልቀቅ ነው:: አንድ ሕጻን ባትሪውን በሚውጥበት ጊዜ በሰውነቱ ውስጥ ቃጠሎን በማስከተል ከፍተኛ ጉዳትን አለፍ ሲልም ሕጻኑ በዋጠ በአማካይ ከ20 ደቂቃ እስከ አንድ ሰዓት በሆነ ጊዜ ውስጥ ሞትን ያስከትላል::
በተን ባትሪ በሚዋጥበት ጊዜ የምግብ ቧንቧ ውስጥ የማይቀመጥ ከሆነ እና በቀጥታ ወደ ሆድ ዕቃ ውስጥ ካለፈ ሰውነት ቆሻሻን በሚያስወግድበት መልኩ ሊወገድ ይችላል:: ነገር ግን ይህ የማይሆን ከሆነና በተን ባትሪው በጉሮሮ ወይም የምግብ ቧንቧ ውስጥ ተሰንቅሮ ማለፍ ካልቻለ ከላይ እንደተጠቀሰው ለከፍተኛ ቃጠሎ ብሎም ለህልፈት የሚዳርግ ይሆናል::
በምን ማወቅ እንችላለን?
እንግዲህ ይህን መሰል አደጋ ሲያጋጥም በትክክልም የበተን ባትሪ መዋጥ መሆኑን በመጀመሪያ ወይም ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ የምንመለከታቸው ምልክቶች አሉ:: እነሱም የጉሮሮ መታፈን፣ የምግብ እና የመጠጥ ፍላጎት ማጣት፤ ፍላጎት ቢኖርም የመዋጥ እክል፣ የተወሰነ ሳል የመሳሰሉትን ሲሆኑ፤ እየቆየ ግን የመተንፈስ ችግር፣ የሆድ እና ደረት አካባቢ ሕመም፣ ትኩሳትና ማንቀጥቀጥ አለፍ ሲልም ደም የማስመለስ ምልክት በሕጻናቱ ላይ የሚስተዋሉ ምልክቶች ናቸው::
ችግሩ ሲፈጠር ምን እናድርግ?
ከላይ የተጠቀሱት ምልክቶች ከታዩ እና ሕጻኑ/ኗ ባትሪውን እንደዋጠ/ች ከጠረጠርን ጉዳቱ እንዳያይል የሚሰጡ የቅድመ ሕክምና እርዳታዎች ከመስጠት መቆጠብ እንዳለብን ምንጮቻችን ያስጠነቅቃሉ:: ምክንያቱም ይሄን ማድረግ ሕጻኑ/ኗ እንድታስመልስ ከማድረግ ወይም እንደ ወተት ያሉም ሆኑ ምንም አይነት ምግብ ነክ ነገሮችን እንዲወስዱ ማድረግ ቁስለቱን እንዲጨምር ሊያደርግና የሚደረግለትን የሕክምና እርዳታ ሊያስተጓጉል ይችላል:: ስለዚህ ይህ በሚያጋጥም ጊዜ ወደ ሕክምና ተቋም መሄድ ምናልባትም አንዱና ብቸኛው አማራጭ ነው::
ሊቲዬም እነማንን ያጠቃል?
እርግጥ አንዳንድ መረጃዎች፣ የባትሪው ይዘት እና የሕጻኑ የጉሮሮ ስፋት መጠን እንዲሁም ሲዋጥ የሚኖረው አቀማመጥ የጉዳቱን መጠን እንደሚወስነው ይገልጻሉ:: ይህ ሲባል ግን የዚህ ባትሪ አደገኛነት ለሕጻናት ብቻ እንዳልሆነ ያስገነዝባሉ:: እንደ ናሽናል ካፒታል ፖይዝን ሴንተር መረጃ በአሜሪካ በዓመት ከ3ሺህ 500 በላይ የሚሆኑ በየትኛውም የእድሜ ክልል ላይ የሚገኙ ሰዎች ይህን ባትሪ የመዋጥ አደጋ ያጋጥማቸዋል:: ምናልባትም ይህ የሚሆነው አንዳንዴ ዕቃዎችን በአፍ የመያዝ ልማድና ያልተጠበቁ ክስተቶች ሲገጥሙ ቢሆንም፤ በምንም አይነት አጋጣሚ ሊቲየም/በተን ባትሪን በአፋችን ከመያዝ ልንቆጠብ ይገባል ሲሉ ያስጠነቅቃሉ::
እንደ መልዕክት
እኛም በምክራችን አንዳንዴ ይህን እና መሰል መገልገያዎች በየመንገዱ ያለምንም ማሸጊያ ሲሸጡ ወይም ጥገና ሲደረግላቸው፤ በአንጻሩ የማኅበረሰባችን ቁሳቁሶች ላይ የሚገኙ ተለጣፊ መረጃዎችን ያለማንበብ ክፍተት እንዳለ አስተውለናልና ቢታረም እንላለን::
አገልግሎታቸው ያበቁ መገልገያዎችን ግልጋሎታ ቸውን በመቀየር መልሶ ቁስ የማድረግ ጠቃሚ ባህል በማኅበረሰባችን ውስጥ እንደ ልማድ ሆኖ የሚታይ ቢሆንም፤ አላስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የማስወገድ ባሕላችንም እምብዛም ነው ማለት ይቻላል:: ስለዚህ የሚታየው አላስፈላጊና አገልግሎታቸውን የጨረሱ ዕቃዎችን በፍጥነት ያለማስወገድ ባህል እንዲሁም የግንዛቤ እጥረት እንዳይኖር ለመረጃ ቅርብ የመሆን ባህላችን ሊዳብርና ሊሻሻል ይገባል::
ጨቅላ ሕጻናት ያላቸው ወላጆችም ቢቻል ሊትየም/በተን ባትሪ የሌላቸውን መጫወቻዎች ለልጆቻቸው ቢፈቅዱ፤ ካልሆነም በጥንቃቄ የተደበቁ ባትሪዎች ባሏቸው መጫወቻዎች እንዲጫወቱ ቢያደርጉ መልካም ነው:: ከዚህ ባለፈም ይህን ባትሪ የያዙ ቁሳቁሶች ከሕጻናት ዕይታ ውጭ መሆናቸውን፤ እንዲሁም በአግባቡ መወገዳቸውን እርግጠኛ ሊሆኑ ይገባል:: ይሄም ወላጆችን ከፀፀት ይታደጋል፤ እንላለን:: ቸር ያሰንብተን!!
ጽዮን ሳምሶን
አዲስ ዘመን ሐምሌ 30/ 2014