ስለ ማዕድን ዘርፍ አጠቃላይ እንቅስቃሴ የማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ታከለ ኡማ፣ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መረጃን በሚያሰራጭበት ድረገጹ ላይና በአንድ ወቅት ከፋና ብሮድካስት ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ ከማዕድን ዘርፎች መካከል የድንጋይ ከሰል፣ብረትና ወርቅ የገበያ ሰንሰለትን በማስተካከል ምርትና ግብይቱ እንዲሳለጥ እርምጃዎች እንደሚወሰዱ አስታውቀው ነበር::
ሚኒስትሩ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ለድንጋይ ከሰልና ብረት ግዥ በአመት ከአንድ ቢሊየን ብር በላይ ታወጣለች:: ለማዳበሪያ ግዥም እንዲሁ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ይወጣል:: እነዚህ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወጭ ተደርጎባቸው ከውጭ ሀገር በግዥ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ግብአቶች ጥሬ ዕቃ በሀገር ውስጥ የሚገኙ ናቸው:: ይሁን እንጂ የሀገርን ሀብት በሀገር ማዋል ባለመቻሉ ግብአቶቹ ሁሉ ከውጭ እንዲመጡ ሆኗል::
ከማዕድን ዘርፍ ሀብቶች መካከል አንዱ የሆነውን የድንጋይ ከሰል ከውጭ ማስገባት በ2015ዓም ሙሉ ለሙሉ በማስቀረት በሀገር ውስጥ የድንጋይ ከሰል ምርት ለመተካት ማዕድን ሚኒስቴር አቅዶ ጠንክሮ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል:: ግብአቱን የሚጠቀሙት የሲሚንቶ አምራች ኢንዱስትሪዎች በአመት አንድ ነጥብ አምስት ሚሊየን ቶን የተጣራ የድንጋይ ከሰል ያስፈልጋቸዋል:: ይህን ለማሳካትም 12 ኩባንያዎች ተመርጠው በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ሁለትና ሶስት ቦታዎች ላይ የምርት ፍለጋ እንዲያካሂዱ ፈቃድ ተሰጥቷቸዋል::
ኩባንያዎቹም በማሽን ግዥ ላይ እንደሆኑና መንግሥትም አስፈላጊውን እገዛ አድርጎላቸው ወደ ሥራው እንደሚገቡ ሚኒስትሩ ማስረዳታቸው ይታወሳል:: ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ባለሀብቶች ጥሬ ሀብቱ በሚገኝበት ሥፍራ ፋብሪካ አቋቁመው ጥሬ ሀብቱን አልምተው ለአምራች ኢንዱስትሪው ማቅረብ እንዲችሉም ሁኔታዎችን ማመቻቸቱንም ከዚህ ቀደም ዘግበናል::
ሚኒስትሩ ኢንጂነር ታከለ እድገትን መመኘት ብቻውን በቂ እንዳልሆነና በእቅድ የያዙትንም ለመፈፀም መትጋት እንደሚጠብቅባቸው በወቅቱ ተናግረዋል:: ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም የተሰጠውን ኃላፊነት ለመፈፀም ቅንጅትን ዋነኛ ማዕከል አድርጎ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንና በቅንጅት የማዕድን ወጪ ንግድን እንደሚያሳድጉ ተናግረዋል:: ከውጭ የሚገቡ ምርቶችንም በሀገር ውስጥ በማምረት ለመተካት ሚኒስቴሩ በትክክለኛው መንገድ ላይ መሆኑንም አመልክተው ነበር::
የድንጋይ ከሰል ለሲሚንቶ አምራች ኢንዱስትሪዎች ለኃይል ግብአትነት የሚውል በመሆኑ በአምራቾቹ በእጅጉ ይፈለጋል:: የምርት አቅርቦቱ በሀገር ውስጥ ቢኖርም የአቅርቦት ማነስና የጥራት ጉድለት እንዳለበት በአምራቾቹ በስፋት የሚነሳ ጉዳይ በመሆኑ ከውጭ በግዥ የሚገባው በስፋት ጥቅም ላይ ሲውል መቆየቱን ነው መረጃዎች የሚጠቁሙት::
አሁን ባለው ሁኔታ ከውጭ በግዥ የሚገባው የድንጋይ ከሰል ዋጋ በመናሩና እንደ ሀገር ባጋጠመው የውጭ ምንዛሪ እጥረት የተነሳም የአቅም ውስንነት መፈጠሩ በተደጋጋሚ ይነሳል:: ይህ የአንድ ወቅት መነጋገሪያ የነበረውን የሲሚንቶ አምራቾች የድንጋይ ከሰል ጥሬ ዕቃ አቅርቦት ችግር ለመፍታት መንግሥት በቁርጠኝነት ሲያደርግ የነበረው እንቅስቃሴ ውጤት ላይ ደርሶ እንደተባለው ይነሳ ለነበረው ለአቅርቦት ችግር መፍትሄ እየሆነ ይሆን?
በጉዳዩ ላይ የሲሚንቶ አምራቾች ማህበር ፕሬዚደንት አቶ ኃይሌ አሰግዴን እንዲሁም የድንጋይ ከሰል ጥሬ ዕቃ ሀብት ክምችት ከሚገኝባቸው የኢትዮጵያ ክፍል አንዱ በሆነው በደቡብ ብሄር፣ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል በጉራጌ ዞን አበሽጌ ወረዳ ጊቤ ቀበሌ ውስጥ የድንጋይ ከሰል ማምረትና ማቀነባበር ስራ በማዕድን ሚኒስቴር ፍቃድ የተሰጠው ሰን ማይኒንግ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ የሚገኝበትን የሥራ ሁኔታ በተመለከተ በደቡብ ብሄር፣ብሄረሰቦችና ህዝቦች የጉራጌ ዞን ውሃ፣ማዕድን እና ኢኒርጂ መምሪያ ኃላፊ አቶ ፍሰሐ ዳምጠውን ሀሳብ::
በቅድሚያም አቶ ኃይሌ አሰግዴ እንዳስረዱት ሲሚንቶ ለማምረት የኃይል ግብአት ወሳኝ ነው::በሥራው ሂደት ውስጥ ለማቃጠል ጥቅም ላይ የሚውለው ኃይል ፈሳሽ ጋዝ እና የድንጋይ ከሰል ነው::በዋጋ የድንጋይ ከሰል ግብአት ቅናሽ በመሆኑ አምራች ኢንደስትሪዎቹ በቅናሽ ዋጋ የሚቀርበውን ግብአት ይጠቀማሉ::አምራች ኢንደስትሪዎቹ ቅናሽ ዋጋ ያለው ግብአት ሲጠቀሙ፤ሸማቹም በዋጋ ተጠቃሚ ይሆናል::
የግበአት ዋጋ ውድ ሲሆን፣ሸማቹ ላይ ነው የሚያርፈው::ይህ ደግሞ ኢኮኖሚያዊ ጫና ያሳድራል::እንዲህ ያለውን ችግር ለመፍታት መንግሥት የተለያዩ ጥረቶች አድርጓል::የመፍትሄ ጥረቶቹ ግን የሚፈለገውን ውጤት አስገኝቷል ለማለት አቶ ኃይሌ አልደፈሩም::
እርሳቸው እንዳሉት አምራች ኢንደስትሪዎቹ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከውጭ በግዥ ወደ ሀገር በሚገባ የድንጋይ ከሰል በመጠቀም ነው ሲሚንቶ ሲያመርቱ የቆዩት::ከውጭ በግዥ በሚገባው እና በሀገር ውስጥ ከሚመረተው የድንጋይ ከሰል ግብአት መካከል ያለውን ልዩነትም እንዳስረዱት፤ከውጭ የሚገባው የድንጋይ ከሰል የሚቀርብበት የጥራት መጠን ወይንም ለማቃጠል ያለው የኃይል መጠን የሚዋዥቅ(ፍላክችዌትአያደርግም) አይደለም:: ቢያጋጥም እንኳን በክፍተት የሚጠቀስ አይደለም::
የሀገር ውስጥ የድንጋይ ከሰል ግን የመዋዠቅ ባህሪ ያለውና የማቃጠል ኃይሉም አነስተኛ ነው:: በዋጋ ግን ከውጭ በግዥ ከሚገባው የድንጋይ ከሰል አነስተኛ ነው:: ዋጋው ቢቀንስም አገልግሎቱ አነስተኛ ከሆነ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል:: የማቃጠል ኃይሉ አነስተኛ የሆነው በተፈጥሮ ነው::
ስለዚህ‹‹በኔፊኬሽን ፕላንት) ያስፈልጋል:: ወይንም ጥሬ ዕቃውን ፈጭቶ፣አጥቦና አድርቆ የሚያቀርብ ድርጅት መኖር አለበት:: መንግሥትም በዚህ መልኩ የሚቀርብበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ነበር ጥረት ሲያደርግ የነበረው:: አቶ ሀይሌ በዚህ መልኩ እስካሁን የአምራች ኢንደስትሪውን ፍላጎት የሚያሟሉ ድርጅቶች ስለመኖራቸው እና መንግሥት በ2015ዓም ሙሉ ለሙሉ በሀገር ውስጥ አቅርቦቱን ምቹ ለማድረግ ይችላል የሚል ጥርጣሬ አላቸው::
በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ የሲሚንቶ አምራች ኢንደስትሪዎች መካከል ትላልቅ የሚባሉት ደርባ፣ሙገር፣ዳንጎቴ፣መሶቦ ኢንደስትሪዎች ሲሆኑ፣በአሁኑ ጊዜ መሶቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ በሥራ ላይ ባይሆንም እያንዳንዳቸው በቀን አምስትሺ ቶን ሲሚንቶ የማምረት አቅም ስላላቸው በቀን ወደ ሰባት መቶ ቶን (ሰባትሺ ኩንታል)፣በወር ደግሞ 20ሺ ቶን የድንጋይ ከሰል ግብአት ይፈልጋሉ:: ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካም እስከ 13ሺ ቶን ይጠቀማል::
በመሆኑም በሀገር ውስጥ ጥሬ ዕቃውን ፈጭተው፣አጥበውና አድርቀው ለኢንደስትሪዎቹ የማቅረብ አቅም ያላቸው ድርጅቶች መፍጠር ይጠበቃል:: የሀገር ውስጥ ምርትን መጠቀም ጥቅም እንዳለው ሁሉ ሊያስከትል የሚችለውንም ክፍተት ለይቶ ማወቅ ያስፈልጋል:: ግብአቱ በጥራትና በመጠን ካልቀረበ የምርት መቀነስና የዋጋ ንረት ያስከትላል::
እንደ አቶ ኃይሌ ገለጻ፣በአሁኑ ጊዜ የድንጋይ ከሰል ከውጭ በግዥ እየገባ አይደለም:: አምራቹ ቀድሞ የያዘውን ክምችትና ፈሳሽ ጋዝ በመጠቀም ነው በማምረት ላይ የሚገኘው:: ጋዝ በሊትር ወደ 49 ብር ነው የሚሸጠው፤ ይሄ ደግሞ አምራቾችን አዋጭ አያደርጋቸውም:: እንደየአምራቹ የማምረት ሁኔታ ቢለያይም በቀን እስከ 120ሺ ሊትር ጋዝ የሚያስፈልገው አምራች ድርጅት አለ:: አሁን ባለው የጋዝ በሊትር የመሸጫ ዋጋ ለማምርት አያዋጣም:: አቅርቦቱም ቢሆን የተቆራረጠ ነው:: የምርት ዋጋን ያስወድዳል:: ይህንን ተግዳሮት መቅረፍ የሚቻለው ቤኔፊኬሽን ፕላንት ላይ ጠንክሮ መሥራት ነው::የጥሬ ዕቃ ሀብቱ የሚገኝባቸው አንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎችም የፀጥታ ስጋት ያለባቸው መሆኑም የራሱ ተጽዕኖ እንዳለው ጠቁመዋል::
የሀገር ውስጥ የድንጋይከሰል የማቃጠል ኃይሉ አነስተኛ የመሆን ጉዳይ ብዙዎች የሚያነሱት ቢሆንም አቅርቦቱ ካለ አምራቾቹ በራሳቸው የኃይል ማስተካከል በማድረግ የሚጠቀሙበት ዕድል ስለመኖሩ አቶ ኃይሌ ላቀረብኩላቸው ጥያቄ በምላሻቸው ማስተካከያው የውጭውን ከሀገር ውስጥ ጋር በማቀላቀል ወይንም ደግሞ የሀገር ውስጡን ከናፍጣ ጋር በማደባለቅ የተሻለ ውጤት እንዲያመጣ በማድረግ ጥቅም ላይ ይውላል::ናፍጣ ዋጋው ውድ እየሆነ ስለሚሄድ ከናፍጣ ጋር አደባልቆ መጠቀሙ አዋጭ አይሆንም::ይሄ ጊዜያዊ ዘለቄታዊ መፍትሄ አይሆንም::
አሁን ባለው የውጭ ምንዘሪ አቅርቦት ችግር፣ከውጭ የሚገባውም የድንጋይ ከሰል ዋጋ መናርና መንግሥትም የግብአት አቅርቦቱ ሙሉ ለሙሉ በሀገር ውስጥ እንዲሆን በአቋም እያደረገ ስላለው እንቅቅስቃሴ ያላቸውን ሀሳብና እንደመፍትሄም የሚጠቁሙት ካለ አቶ ኃይሌ ላቀረብኩላቸው ጥያቄ ‹‹ዋናው መፍትሄ በሀገር ውስጥ የተጀመረውን የቤኔፊኬሽን ፕላንት ፕሮጀክት መጨረስ ነው:: ይህ ከሆነ ሳይቆራረጥ ግብአቱን ማግኘት ይቻላል››ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል::
ማዕድን ሚኒስቴር የድንጋይ ከሰል አልምተውና አቀነባብረው ለአምራች ኢንደስትሪዎች የማቅረብ አቅም ላላቸው ባለሀብቶች የድንጋይ ከሰል ሀብቱ በሚገኝባቸው የሀገሪቱ ክፍሎች ውስጥ እንዲሰሩ ፍቃድ ከሰጣቸው መካከል ሰን ማይኒንግ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ አንዱ ነው፤ ኩባንያው በደቡብ ብሄር፣ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል በጉራጌ ዞን አበሽጌ ወረዳ ጊቤ ቀበሌ ውስጥ እንዲሰራ ነው ፍቃድ የተሰጠው::
ኩባንያው የሚገነባው ፋብሪካ ተጠናቅቆ ማምረት ሲጀምር በወር ስምንት መቶ ሺ ቶን የድንጋይ ከሰል የማምረት አቅም እንደሚፈጥርና የታለመውን የውጭ ምንዛሪ ወጭ በማዳን ሚና እንደሚኖረው እንዲሁም ለአካባቢው ወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠርም የሥራ አጥነትን ክፍተት በመሙላት ድርሻ እንደሚኖረውም ሚኒስቴር መስሪያቤቱ በወቅቱ በድረገጹ ማስነበቡ ይታወሳል::
በደቡብ ብሄር፣ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል የጉራጌ ዞን ውሃ፣መአድን እና ኢነርጂ መምሪያ ኃላፊ አቶ ፍሰሐ ዳምጠውም በጉዳዩ ላይ እንዳብራሩት፤እንደሀገር የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ተብሎ ከተያዘው ዘርፍ አንዱ የማእድን ልማት እንደሆነ በመገንዘብ ዞኑም የተቀመጠውን የልማት አቅጣጫ በማሳካት ረገድ የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት በአካባቢው የሚገኝ የማእድን ህብትን ከመለየት ጀምሮ ጥቅም ላይ የሚውልበትን መንገድ በማመቻቸት ተንቀሳቅሷል::
ዞኑ ከዲላ፣ሐዋሳና አርባምንጭ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር ዞኑ ስላለው የማዕድን ሀብት ጥናት በማካሄድ ሀብቱን ለይቷል:: በጥናት ግኝቱም በስምጥ ሸለቆ ኬላ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኙ ሶዶ፣ደቡብ ሶዶ፣በከፊል መስቃን እንዲሁም በጊቤ ተፋሰስ አብሽጌና እነሞር ወረዳዎች የድንጋይ ከሰልን ጨምሮ ለኢንዱስትሪ ግብአት የሚውሉ የማዕድን ሀብቶች መኖራቸውን አረጋግጧል::
ኩባንያው ግንባታ የሚያከናውንበትን ቦታ አመቻችቷል:: የመሠረት ድንጋይም ተጥሏል:: ለቅድመ ግንባታ የሚያስፈልጉ እንደ አፈር ምርመራና የተለያዩ ተግባራት ተከናውነው ዝግጁ ሆኖ በአጭር ጊዜ ውስጥ የድንጋይ ማጠቢያ ማሽን ተከላ ተከናውኖ ወደ ምርት ይገባል የሚል እቅድ እንደነበርም አቶ ፍሰሐ ከስድስት ወር በፊትም በጉዳዩ ላይ ሰጥተውናል::
አቶ ፍሰሐ እንዳሉት፤ ተስፋ የተጣለበት የድንጋይ ከሰል አልምቶ አቀነባበር ለአምራቾች የማቅረቡ ሥራ የውሃ ሽታ ሆኖ ቀርቷል:: የዞኑ መምሪያ ኩባንያው ወደ ሥራ ያልገባበትን ምክንያት ለማጣራት ባደረገው ጥረት ኩባንያው ወደሥራ ላለመግባቱ የሚያነሳው የድንጋይ ከሰል ማጠቢያ ማሽኑን ከውጭ ለማምጣት የውጭ ምንዛሪ እጥረት ያጋጠመው መሆኑን ነው::
አቶ ፍስሐ ኩባንያው ከማዕድን ሚኒስቴር ፈቃድ ሲወስድ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ችግሩ እንደሚፈታለት ሳያረጋግጥ ወደ ሥራው አይገባም የሚል እምነት አላቸው:: የዞኑ መምሪያ ክልሉም ሆነ ማዕድን ሚኒስቴር እንዲያውቁት በቃልም በደብዳቤም በማሳወቅ መፍትሄ እንዲያገኝ እያደረገ መሆኑን ይገልጻሉ:: በግላቸውም የማዕድን ሚኒስትሩን በአካል አግኝተዋቸው በጉዳዩ ላይ መነጋገራቸውንና ሚኒስትሩም በማወያየትና ደብዳቤ በመጻፍም እርምጃ እንደሚወሰድ በቃል እንደገለጹላቸው ነው የተናገሩት:: ‹‹መሬት ለኢኮኖሚያዊ ልማት ዕድገት ታሳቦ ለኢንቨስትምንት እንዲውል ህዝብ የሚጠቀምበት መሬት ሲሰጥ ለታለመለት አላማ ካልዋለ ተጠያቂነት ያመጣል:: ይህንን መሠረት በማድረግ ነው ለሚመለከተው አካል በየደረጃው ለማሳወቅ የተገደድነው››ብለዋል::
አቶ ፍሰሐ፣በደቡብ ክልል ብሄር፣ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል የጉራጌ ዞን ውሃ፣ማዕድንና ኢነርጂ መምሪያ አወ/ ው/ 51/ 14/ ቀን 8 /11 /2014ዓም ለደቡብ ብሄር፣ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል በደብዳቤ ያሳወቀበትን፣በደቡብ ብሄር፣ቤሄረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግሥት ማዕድንና ኢነርጂ ኤጀንሲ ደግሞ በሀ/350/መ/152/በቀን 14/11/2014ዓም ለፌዴራል ማዕድን ሚኒስቴር በደብዳቤ ያሳወቀበትንም ሁኔታ ገልጸዋል::
በጉዳዩ ላይ የማእድን ሚኒስቴር የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር ሞባይል ስልክ ላይ ብንደወልም ስልኩ ሊነሳ ባለመቻሉ ምላሽ ማግኘት አልቻልንም::
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 29 ቀን 2014 ዓ.ም