‹‹ዋው ዋው! ብራቦ ! እንዲህ ዓይነቱ አለባበስ ነው የሚያስፈልገው። እየመጣ ነው ቀጣሪሽ በፍጥነት ይዞሽ ይሄድና አሁኑኑ ሥራሽን ትጀምሪያለሽ›› በአዲስ አበባ ከሚገኙ በርካታ ሥራና ሠራተኛ አገናኞች አንዱ የአስተናጋጅነት ሥራ ፈልጋ ለመጣች ወጣት ሲሰጣት የሰማሁት አድናቆት የተሞላ መልስ ነው።
አገናኙ ፍቃድ ይኑረው አይኑረው የጠየቀው ባይኖርም አምስት ኪሎ የሸዋ ዳቦ ቤት ግድግዳን ተደግፈው ከቆሙት ሥራ ፈላጊዎች አንዷ የሆነችውንና መልስ የሰጣትን ወጣት የሚያይበት አስተያየትም ልክ አልነበረም። ዓይኑ እጥረቱ የውስጥ ሱሪዋን መደበቅ እንኳን የተሳነው የሚመስለው አጭር ቀሚስ ላይ ብቻ ተተክሎ አልቀረም። ዳሌዋን፤ ባቷን እያለ እስከ እግር ጥፍሯ ወረደ። እንደ ሸቀጥም ሁሉ ከኋላዋ ዞሮ እየቃኛት ‹‹አይ መቀመጫ ሰጥቶሻል! ሲልም በአድናቆት ከማሳረጉ፤ የልጅቱ ቀጣሪ ክላክስ አደረገ። ቀጣሪውም ቢሆን ምርጫው ልጅቱ ነበረች። መኪናው ድረስ ሸኝቶ በጥድፊያ ወደ ሌሎቹ ሥራ ፈላጊዎች መለስ ያለው አገናኝ ታዲያ በየትኛውም ዓይነት ቦታና ደረጃ ላለ አስተናጋጅነት መቀጠር የሚፈልጉ የልጅቱን ዓይነት አለባበስ መከተል እንደሚገባቸው በቁም ነገር አሳሰበ። ማሳሰቢያው ትዕዛዝና ግዴታ ጭምርም ነበር።
ሆኖም የእንዲህ ዓይነቱ የአለባበስ ግዴታ ሕጋዊ መሠረት እንደሌለው ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘሁት መረጃ ያመለክታል። ከዚህ ጋር በተያያዘ ያለውን ሀሳብ በይደር ላቆየውና ሴቶች ለአስተናጋጅነት ሙያ ለመቀጠር አጭር ቀሚስ መልበስ እንዳለባቸው የሚያስገድዱት እነማን ናቸው፤ ለምንድነው የሚያስገድዱት፤ አጭር ቀሚስ ፋሽን ነው አይደለም፤ ከሆነ አንዳንድ ወንዶች ከለከፋ ጀምሮ ሴቶች ላይ ወሲባዊ ትንኮሳ ለማድረስ ይገፋፋናል የሚሉት ለምንድነው? በሚሉት ሀሳቦች ዙሪያ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሰጡኝን አስተያየት ላጋራችሁ።
አቶ ፋሲል ሞገስ ቦሌ መድኃኒዓለም አካባቢ የሚገኘው የቤስት ዌስተርን ፓላስ ኢንተርናሽናል ሆቴል ማኔጀር ናቸው። እንደሳቸው ባንክም ሆነ ሌሎች ተቋማት ላይ ዩኒፎርም የሚዘጋጅበት ምክንያት አላስፈላጊ የግል አለባበሶችን ለመከላከል ነው። የትኞቹም ተቋማት ላይ ከጉልበት በላይ የሆነ ልብስ መልበስ አይፈቀድም። በሙያቸው ሲሠሩ ሆቴሉ ሦስተኛቸው በመሆኑ ስለ አስተናጋጆች አለባበስ ያውቃሉ። ሴቶች እሳቸው በሠሩባቸው ሦስቱም ሆነ ሌሎች ኢንተርናሽናል ሆቴሎች በሙሉ ከፓንት ማይተናነስ አጭር ቀሚስ እንዲለብሱ አይገደዱም። የለበሰች ብትገኝ ከሥራ ትባረራለች። በቤስት ሆቴል የሚፈቀደው እስከ ጉልበት አንዳንዴም ከጉልበት አለፍ ያለ ቀሚስ ወይም ሰውነታቸው ላይ ያልተጣበቀ ሱሪ ነው። ምክንያቱም ደንበኞች በአለባበሳቸው ተስበው በሴቶቹ ላይ ሌላ ፍላጎት እንዲያሳድሩ አይፈለግም።
አቶ ፋሲል እንደታዘቡት ባርና ሆቴል ላይ የሚሠሩ ሴት ወጣቶች ወድደው ሳይሆን ተገድደው ነው አጭር ቀሚስ የሚለብሱት። ተግባሩ እስከ ታች ሥጋ ቤትና ትናንሽ ምግብ ቤቶች እየተለመደ መጥቷል። ካለዚያ ሥራውን አትሠሪም ይባላሉ። አሠሪዎቻቸው እንዲለብሱ የሚያስገድዷቸው እነሱን እያለ ገበያ እንዲመጣላቸው ነው። ከዚህ ባሻገር ወደ ዝሙትም እንዲገቡ ይገፋፋል። መገደዳቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ቀሚሱ በተለይ ቡና ቤት ውስጥ የበለጠ ለጥቃትም ያጋልጣቸዋል። ሆኖም እንዲለብሱ ያስገደዷቸው አሠሪዎቻቸው ጥቃቱን እንኳን አይከላከሉላቸውም።
እነሱ ሆቴል ከልብስ ጋር ተያይዞም ባይሆን በስካር መንፈስም ሆነ በሌላ ተነሳስቶ ሴት አስተናጋጆችን የተነኮሰ ለእንግድነቱ ከሚሰጠው ክብር ባሻገር በሕግ ያስጠይቀዋል። በመስተንግዶ ሥራ ከተሠማሩት ውጪ ያሉ ሴቶች አጭር ቀሚስ መልበሳቸው ክፋት የለውም። አጭር ቀሚስ አደረገች ብሎም መናገሩም አግባብ ነው ብዬ አላምንም። ሆኖም አንዳንድ ሰዎች ስሜታዊ ሲሆኑ ስለማይ ባትለብስ እመክራለሁ ይላሉም አቶ ፋሲል።
ወጣት አልማዝ ሳህሌ በዚህ ሆቴል ውስጥ ተቆጣጣሪ ነች። ከላየን ኢትዮጵያ ኮሌጅ በሆቴል ማኔጅመንት ለአራት ዓመታት የዲግሪ ትምህርቷን ተከታትላ ከተመረቀች በኋላ ካፒታል፤ ፍሬንድ ሽፕና እንቢልታ ሆቴልን ጨምሮ በተለያዩ ሆቴሎች ለአምስት ዓመታት በአስተናጋጅነት ሠርታለች። እሷን ጨምሮ በሆቴሉ የሚሠሩ ሴት አስተናጋጆች ከጉልበት አለፍ ያለ ቀሚስን ጨምሮ ሱሪ፤ ኮትና ሸሚዝ ዩኒፎርም ነው የሚለብሱት። ነገር ግን እንደታዘበችው በምሽትና በተለያዩ ቦታዎች እንዲህ ዓይነቱን አጭር ቀሚስ ካለበሳችሁ የሥራ ዕድሉን አታገኙም የተባሉ ወጣት ሴቶች ታውቃለች። ኑሯቸውን ለማሸነፍ ሲሉ እንቢ አይሉም። ሥራውን ማግኘት ግድ ስለሚላቸው ይለብሳሉ። ነገር ግን አንዳንድ ወንዶች ቀሚሱን የለበሱ ሴቶችን የመተናኮልና የማይሆን ነገር ውስጥ የማስገባት ባህርይ አላቸው። ስለዚህ ከሆቴሉ ሠራተኛ ይልቅ የሆቴል ባለቤቶች ለሴት አስተናጋጆች ለጥቃት የማያጋልጥ ዩኒፎርም ማዘጋጀት አለባቸው ትላለች።
‹‹ወድጄ ነው! ወደሽ ከተደፋሽ ቢረግጡሽ አይክፋሽ አለች አያቴ›› ያለችኝ ደግሞ አጭሩን ቀሚስ ለምን እንደለበሰችና ያም ይሄም የሚጎትታት በቀሚሱ ምክንያት መሆኑንና አለመሆኑን እንድትነግረኝ የጠየቅኳት ወጣት ናት። እንደ አሸን ከፈሉት የከተማችን ሥጋ ቤቶች በአንዱ ያገኘኋት ስሟን ልትነግረን ፈቃደኛ ያልሆነችው ወጣቷ አስተናጋጅ እንዳጫወተችኝ የ12ኛ ክፍል ትምህርት ብታጠናቅቅም ውጤት ስላልመጣላት ሁለት ዓመት ያለ ሥራ ተቀምጣለች። በዚህ መካከል ብታገባምና ሁለት ልጆች ብትወልድም ባሏ ሥራ አልነበረውም። ከዚህ በኋላ በወላጅ እርዳታ የመስተንግዶ ትምህርት ተማረች። እዚህ ሥጋ ቤት ከፓንት የማይተናነሰውን ልብስ መልበስ ግዴታ እንደሆነ በአስቀጣሪዋ ደላላ አማካኝነት ሲነገራት አቅማምታ የነበረ ቢሆንም አማራጭ በማጣቷ ተቀጠረች።
ከሥራ ዩኒፎርም ውጪ ሌላ ዓላማ ይኖረዋልም ብላ አላሰበችም። ሥጋ ቤቱ ውስጥ ድራፍትንና ቢራን ጨምሮ የተለያዩ የአልኮል መጠጦችም ይሸጣሉ። የሥጋ ቤቱ ደንበኞች በዚህ የተነሳ ለመስተንግዶ ስታልፍ ስታገድም ይጎነትሏታል። ከዚህም አልፎ አንሶላ ለመጋፈፍ የሚጠይቋት ብዙ ናቸው። እንደገባች ሰሞን ትሳደብና ትናደድ ነበር። ሴት አዳሪ ሳልሆን አስተናጋጅ ነኝ እላቸው ነበር ስትልም ታስታውሳለች። ሆኖም ባለቤቱ ለደንበኞቼ እንዲህ ዓይነት ምላሽ አትመልሺ፤ ገበያየን ታርቂብኛለሽ እያለ በተደጋጋሚ ያስጠነቅቃት እንደነበርም ታወሳለች። አማራጭ በማጣቷ እየለመደችው መጣች።ሥራ ያልነበረው ባሏ ሥራውን መሥራቷን በመቃወሙ ጥሏት ጠፍቷል። ሳታስበው የዝሙት ሥራ ውስጥ ብትገባም ለዝቅተኛ የወር ደመወዟ መደጎሚያ ሆኗታል።
አኒሳ አብዲ ትባላለች። ድሬዳዋ ብዙኃን መገናኛ ኤፍኤም ድሬ 106 ነጥብ 1 በሴቶች ብቃትና ፖለቲካዊ ተሳትፎ ላይ ትኩረት ያደረገ ብቁ ሴት የተሰኘና በአማርኛ ቋንቋ የሚተላለፍ የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ ነች። በኦሮሚያ ቋንቋ በሚተላለፈው የቴሌቪዥን ፕሮግራምም መዝናኛ ፕሮግራም አዘጋጅ ሆና እየሠራች ትገኛለች። አለባበስ እንደየ ግለሰቡ ምርጫ የሚወሰን መብት ነው የሚል አቋም አላት። ነገር ግን አጭር ቀሚስ ከባህላዊና ሃይማኖታዊ አለባበስ ጋር አይመደብም። ከውጭ የመጣና ከጊዜ ብዛት የራሳችን አድርገን የተቀበልነው ፋሽን ነው ትላለች።
ሆኖም አንዳንድ ወንዶች ራሱ ኅብረተሰቡም በብዛት ለሴቷ ከራስ እስከ ጥፍሯ ትሸፋፈን በሚል ሕግ አጥረውና ድንበር ሠርተውላታል። ሆኖም ይሄ የሴቷን መብት መጋፋት ነው። የአመለካከትና ራስን ለመቆጣጠር ያለመቻል የወንዶቹ ችግር ነው። አኒሳ ወጣት ሴቶች ይሄን ፋሽን በመከተላቸው ከለከፋ ጀምሮ ለወሲባዊ ጥቃት ይጋለጣሉ በሚለው አትስማማም። አንዲት ሴት እንደ ዘመናዊ ሴት አጭር ቀሚስ ልትለብስና ፋሽኑን ልትከተል ትችላለች። ይሄም መብቷ ነው ባይ ናት።
ከስድስት ወር ጨቅላ ሕፃናት ጀምሮ አረጋውያን፤ አካል ጉዳተኛ፤ በተለያየ ዕድሜ ደረጃ ያሉ ሴቶች የተደፈሩትና በወንዶች እየተለከፉ ያሉት አጭር ቀሚስ አድርገው ነው ወይ? ስትልም ትጠይቃለች። አጭር ቀሚስ ስላደረጉ አይደለም እየተደፈሩና ጥቃት እየደረሰባቸው ያሉትም ትላለች። ለለከፋና ለተለያዩ ወሲባዊ ጥቃቶች ስለሚያጋልጣት አትልበስ የሚለውንም የኅብረተሰቡ የአመለካከትና ራስን ለመቆጣጠር ያለመቻል የወንዶቹ ችግር ነው ባይ ነች። ይሄን ለመለወጥ ኮቪድ 19 በተስፋፋበት ሰሞን ሴቶች ላይ እንደደረሰው የቤት ውስጥ ጥቃት የአንድ ሰሞን ዘመቻ ብቻ ሳይሆን ተከታታይ ሥራ እንደሚያስፈልግም ትመክራለች። በዚህ በኩል እሷ በብቁ ሴት የሬዲዮ ፕሮግራሟ ተግታ እንደምትሠራም ታወሳለች። አሁን ያለውን ትውልድ ማትረፍ የተቻለው ተከታታይነት ባለው መልኩ በኤች አይቪ ኤድስ ላይ በመሠራቱ መሆኑን ታነሳለች።
በአዲስ ዘይቤ ዲጂታል ጋዜጣ የሚሠራው ወጣት ኢያሱ ዘካርያስ አንዲት ሴት የፈለገችውን የመልበስ መብት አላት ይላል። ራሷን ዝቅ ታድርግ የሚል ዕምነት የለኝም። በተለይ ወጣት ሴት ዕድሜ ደረጃዋ የሚፈቅደውን ፋሽን ሁሉ መከተል እንዳለባት እንደሚያምንም ያወሳል። ሆኖም በለበሰችው አጭር ቀሚስ ምክንያት ከወንዶች ከለከፋ ጀምሮ የተለያዩ ጾታዊ ትንኮሳዎች እንዲሁም ከኅብረተሰቡ መገለል ሲደርስባት አስተውሏል። ለወሲብ አነሳሳኝ የሚሉ ወንዶችም ገጥመውታል። እነዚህ ሰዎች እርቃን መሄድ ባህላቸው የሆነ ሴቶች አካባቢ ቢሄዱ ምን ሊሉ ነው? ሲልም ይጠይቃል። የባህርይንና የአመለካከት ችግርን እንዲሁም ሃይማኖትን ከፋሽንና መብት ጋር ለያይተው ማየት እንደሚገባቸው ይመክራል። በበኩሉ በምንም ያህል መጠን የሚለበስን አጭር ቀሚስ ከፋሽን ጋር ብቻ እንደሚያያይዘው ያወሳል።
ስሟ እንዲገለፅ ባትፈልግም የነቃች የበቃች የምትባል ዓይነት ሴት ናት። በምትሠራበት በኦን ላይን ሚዲያ አብዝታ ትታወቅና ትደነቃለች። እንደነገረችን አጭር ቀሚስ ለባሽ ነች። የምትለብሰው በፋሽን መልኩ ነው። ሁሉም ቀሚሶቿ ከጉልበቷ በላይ ናቸው። ፈልጋ ወድዳና ፈቅዳ እንዲሁም ለራሷ በሚመቻት መልኩ ነው የምትለብሰው። ቀሚሱን የምትገዛውም ራሷ ናት። ሁሉም ቀሚሶቿ ከጉልበቷ በላይ ናቸው። አጭር የምትለብሳቸው ለራሷ በሚመቻትና ምቾት በሚሰጣት መልኩ ነው። ሆኖም አጭር መልበሷ ለማንኛውም ጾታዊ ትንኮሳም ሆነ ለመደፈር ያጋልጠኛል የሚል ዕምነት የላትም። እንዲህ እንደ እሷ ያለ ቀሚስ የለበሰችን ሴት ልጅ ለክፈው ወይም ጾታዊ ትንኮሳ አድርሰው አጭር ቀሚስንም ሆነ ሌላ አለባበስን ምክንያት የሚያደርጉ ወንዶችን እንዲሁም አለባበስን ችግር የሚያደርጉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን አጥብቃ ትቃወማለች።
‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ወንዶችም ጋር ብዙ የአለባበስ ችግሮች አሉ›› የምትለው ወጣቷ ወንዶች ፋሽን ነው ብለው የውስጥ ሱሪያቸውን ዝቅ አድርገው እያሳዩ ይሄዱበታል። ሲክኒ ሱሪ ለብሰውና ደረታቸውን ገልብጠው ሲሄዱ እኛ ስሜታችንን ያነሳሳል አላልንም ትላለች። በመሆኑም ችግሩ አጭር መልበስ ሳይሆን የወንዶቹና የኅብረተሰቡ የአስተሳሰብ ችግር እንደሆነ ታሰምርበታለች።
እኔ አጭር ቀሚስ መልበስን በፈቃደኝነትና ከፍቃድ ውጪ በሁለት ከፍዬ አየዋለሁ የምትለው ወጣቷ በዚህ በኩል ግን ጥንቃቄ ሊወሰድ እንደሚገባ ትጠቅሳለች። ሰሞኑን በማህበራዊ ሚዲያ ሲያነጋግር የቆየውን አዲስ አበባ ከተማ ላይ የሚገኙ አብዛኞቹ ሥጋ ቤቶች አስገድደው እያስለበሷቸው ያሉ የእንስት አስተናጋጆች ጉዳይም ታነሳለች። ‹‹ሰውየው ከቤቱ ኪሱን እንጂ የልጅቱን ገላ አስቦ አይወጣም›› የምትለው ወጣቷ ድርጊታቸው የሴቷን መብት ያልጠበቀ፤ ለብርድና ቁርጥማት የሚያጋልጥ የግለሰቦችን ጥቅም የሚያስጠብቅ ከመሆኑም ባሻገር በእንስቶቹ፤ በቤተሰባቸውና በአገሪቱም ላይ ዝሙትን በማስፋፋት ታላቅ ማህበራዊ ቀውስ እንደሚያስከትልም ታስጠነቅቃለች።
ሴቷ ጭኗ ስለታየ የበለጠ ይበሉና ይጠጣሉ በሚል ሴት ወጣቶችን በመጠጥ በተሳከረ ሰው መኻል ተጋላጭ የማድረግ አለባበስ እንደ ፋሽን ወስዶ ዝም ማለት እንደማይገባና ቁርጠኛ እርምጃ እንደሚፈልግም ታሳስባለች። ሆኖም ይሄም ችግር አሁንም የሥራ አማራጭ ስላጡ የገቡበት እንስቶች ሳይሆን የአሠሪዎቻቸውና በመጠጥ በመሳከር ጥቃት የሚያደርሱ ወንዶች እንደሆነም ታወሳለች።
ትርሲት አሰፋ በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ቴሌቪዥን ዝግጅት የትምህርታዊ ፕሮግራም አርታኢ ነች። የእንስቷን አጭር ቀሚስ መልበስ አትደግፍም። ፋሽንነቱንም አታበረታታም። ሴቶች አጭር ቀሚስ ለብሰው ሳይ ራሳቸውን እንደ ጣሉ እቆጥራለሁ። ምክንያቱም ከጉልበቷ በላይ ልብስ ለበሰች ማለት ግማሽ ድረስ ያለው አካሏ እርቃን ሆነና ለትንኮሳ ራሷን አጋለጠች ማለት ነው። ክብሯንም ያዋርዳል። ወንዶችንም ያሰናክላል ትላለች።
የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ፤ ባንኮችና ትልልቅ የሚባሉት ዓለም አቀፍ ተቋማት ይሄን ልብስ እያበረታቱና እየደገፉ አስገዳጅ እያደረጉት ነው። ከዚህ ተነስቶም ልብሱ እስከ መንደር ምግብ ቤቶች እየተለመደ መጥቷል።በአስተናጋጅነት ሥራ ለመቀጠርም እንደ አንድ አስገዳጅ የቅጥር መስፈርት እየተወሰደ ነው የሚሉ እሳቤዎች በአንዳንድ ኅብረተሰብ ክፍሎች መደመጡን የምትናገረው አርታይዋ ጉዳዩ በተጨባጭ በአስተናጋጆቹ ላይ ተፅዕኖ የመፍጠሩ ዕውነታ በጥናት የሚመለስና ማጣራትን የሚፈልግ እንደሆነም ታወሳለች።
ከአጭር ቀሚስ ጋር በተያያዘም ሴቷ እስከ ባቷ ድረስ ለብሳ እየጨነቃትና ጉርዷን አስሬ ወደ ታች ዝቅ እያደረገች ስታስተናግድ ገጥሟታል። ወንዱ በፊናው ከነ ክርባቱ ሱሪና ኮቱን ገጭ አድርጎ ዘና ብሎ ሲያስተናግድ እሷ ብርድ የወለደው ቁርጥማት እግሯን እያኘካት ፊቷን ቅጭም አድርጋም ታዝባለች። ካልተመቸሽ ለምንድነው የለበሽው ስትላት የእንጀራ ጉዳይ ነው የሚል ምላሽ እንደሰጠቻትና ከዚህ ተነስታ ልብሱን እንስቶቹ በባለቤቶቹ ተገደው እንደለበሱ ለመረዳት መቻሏን ታወሳለች። አጭር ቀሚስ ካለበሰች ማስተናገድና ሕይወቷን መምራት ያለመቻሏ ጉዳይ አሳሳቢና እንደ ሴት ሴቶች ድምፃቸውን ሊያሰሙበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑንም ትጠቁማለች። ትርሲት የድሮዎቹን የእናቶች ግርማ ሞገስ ያላቸውና እስከ ጉልበት የደረሱ ሚኒስካርት የተሰኙ አጭር ቀሚሶችእንደምትደግፍም አጫውታኝ ሀሳቧን አሳርጋለች። ለመሆኑ ሴቶች ሥራ ለመቀጠር ሲሉ አጭር ቀሚስ እንዲለበሱ የሚያስገድዱ አሠሪዎችን በተመለከተ ሕጉ ምን ይላል? ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርስ ጉዳዩን እንደምን ይመለከተዋል የሚለውን ሳምንት እንመለስበታለን፡፡
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 26 ቀን 2014 ዓ.ም