የፈጠራ ሥራዎች ለአገራዊ እድገትና ለመዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግር እውን መሆን ተስፋ የሚጣልባቸው ወሳኝ ግብዓቶች እንደሆኑ ይታመናል። የፈጠራ ሥራዎቹ አገር በቀል ሲሆኑ ደግሞ ፋይዳቸው እጥፍ ድርብ ይሆናል። እነዚህ ሥራዎች አገራዊ የአምራችነት አቅምን በማሳደግና ለኅብረተሰቡ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ በመሆን በአገር እድገት ላይ ጉልህ አዎንታዊ ሚናም ይጫወታሉ።
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የሚከናወኑ የፈጠራ ሥራዎች ተማሪዎች በንድፈ ሃሳብ የጨበጡትን ግንዛቤ በተግባር የመተርጎም ብቃታቸውንና ዝግጁነታቸውን ይጠቁማሉ። ይህም ከተቋማቱ የሚመረቁ ተማሪዎች ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ፣ የአምራች ዘርፉ አቅም እንዲጎለብትና የአገር ምጣኔ ሀብት እንዲጠናክር ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ያግዛል። በዚህ ረገድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ከላይ የተጠቀሱትን ግቦች ለማሳካት የሚያግዙ የፈጠራ ሥራዎችን እውን ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች እየተረዳን ነው።
በቅርቡ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ በሜካኒካል ምህንድስና (Mechanical Engineering) የትምህርት ዘርፍ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያገኙ ስድስት ተመራቂዎችም ነዳጅን በቀላሉ ለማምረት የሚያስችል የፈጠራ ሥራ መሥራት ችለዋል። የፈጠራ ሥራውን ከሠሩት ተመራቂዎች መካከል አንዷ ስምረት ጴጥሮስ ትባላለች። ስምረት እንደምታስረዳው፣ የፈጠራ ሥራው ፓይሮላይሲስ (Pyrolysis Process) በተባለ ዘዴ አገልግሎት የማይሰጡ የፕላስቲክ ውጤቶችን ወደ ነዳጅ ምርት ለመቀየር የሚረዳ የቴክኖሎጂ ውጤት ነው። ፓይሮላይሲስ ያለምንም ኦክስጅን፣ ሙቀትን ብቻ በመጠቀም የፕላስቲክ ውጤቶች ወደ ነዳጅ ምርት የሚቀየሩበት ቴክኖሎጂ ነው።
ተመራቂዎቹ የፈጠራ ሥራውን ለመሥራት ያሰቡት ለመመረቂያ ጽሑፋቸው ሲሆን ጊዜያቸውን በአግባቡ ለመጠቀም የወረቀት/ጽሑፍ እና የተግባር/የናሙና (Prototype) ሥራውን ተከፋፍለው ያከናውኑ ነበር። የፕሮጀክቱ አማካሪ መምህር ኣብርሃ ካህሳይም በየቀኑ፣ ከተመራቂዎቹ ጋር በመገኘት እያንዳንዱን ሥራቸውን እየተመለከቱ ክትትል አድርገውላቸዋል።
በፓይላይሲስ ቴክኖሎጂ ሁሉንም ዓይነት የፕላስቲክ ውጤቶች ወደ ነዳጅ መቀየር ይቻላል። ተመራቂዎቹ ሥራቸውን በሚያከናውኑበት ጊዜ አንዳንድ የፕላስቲክ ዓይነቶች የቴክኖሎጂውን ቱቦ እየደፈኑ ያስቸግሯቸው እንደነበር በማስታወስ ‹‹በዘርፉ የተሻለ እውቀትና ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች በሥራው ሂደት የሚሳተፉ ከሆነ የፕላስቲክ ውጤቶችን ወደ ነዳጅ የመቀየር ውጤታማነት ማሳደግ ይቻላል›› ትላለች።
እንደ ስምረት ማብራሪያ፣ ማሽኑ የተሠራው በዩኒቨርሲቲው ግቢ ከሚገኙ ዕቃዎች ነው፤ ከውጭ የተገዛ ዕቃ የለም። ለምርቱ የሚያስፈልጉትን ማምረቻዎች ለመሥራት፣ ብረታ ብረቶችን እንዳስፈላጊነቱ በማጠፍና የተለያዩ ዓይነት ቅርፆችን በመስጠት፣ ዲዛይን ከተደረገ በኋላ ለምርቱ የሚፈለገውን ቅርፅ በማስያዝ ተሠርቷል።
እነ ስምረት ሃሳቡን አደራጅቶና ወደ ተግባር ለውጦ ለማጠናቀቅ ከአንድ ወር በላይ ፈጅቶባቸዋል። በእነዚህ ጊዜያትም ተመራቂዎቹ በየቀኑ እየተገናኙ ይሠሩ ነበር። ‹‹ሁሉም ነገር የተሟላለት ነው›› ባይባልም የዩኒቨርሲቲው ላቦራቶሪ ባለው አቅም በመታገዝ ሥራቸውን አከናውነዋል። የተመራቂዎቹ ምርት ጥቅም ላይ መዋል የሚችል ነዳጅ እንደሆነም ተረጋግጧል፤ በተሻለ የግብዓት አቅርቦት የተሻለ ምርት ማግኘት እንደሚቻልም ምክረ ሃሳባቸውን አስቀምጠዋል።
ስምረት ‹‹ርዕሰ ጉዳዩን የመረጥነው ከመመረቂያ ጽሑፍነት የዘለለ ትርጉምና ፋይዳ ስላለው ነው። በአሁኑ ወቅት የነዳጅ ፍላጎት መላው ዓለምን የሚመለከት ወሳኝ ጉዳይ እንደሆነ ይታወቃል። በተለይ ደግሞ የአገራችንን ኢኮኖሚና እንደ ግለሰብ እያንዳንዳችንንም በደንብ የሚነካ ጉዳይ ሆኗል። ስለሆነም ጉዳዩ ከመመረቂያ ጽሑፍነት የሚያልፍ በመሆኑ ወደ ቢዝነስ ተቋም (Startup Company) በማሳደግ ሥራውን በትልቅ መጠን ለማከናወን እቅድ አለን።›› በማለት ታብራራለች። ይህን ለማሳካት ደግሞ ሥራውን በተሻለ መጠንና ጥራት ለማከናወን የሚያስችሉ ጥናቶችንና ዝግጅቶችን ማድረግ እንደሚፈልግም ትናገራለች። የፈጠራ ሥራው ነዳጅን ከማምረት በተጨማሪ የወዳደቁ የፕላስቲክ ውጤቶችን ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችል መሆኑንም ጠቅሳ፣ ‹‹በቀጣይ ምን ማድረግ እንዳለብን እየተነጋገርን እንገኛለን›› በማለት ታብራራለች።
ተመራቂዎቹ ሥራቸውን ሲያከናውኑ ጅማ ዩኒቨርሲቲ ልዩ ልዩ ድጋፎችን አድርጎላቸዋል። ‹‹ጅማ ዩኒቨርሲቲ ዕቃዎችን አቅርቦልናል። በፈለግነው ጊዜ እየሄድን እንድንሠራ የላብራቶሪ አቅርቦትም አመቻችቶልናል። በላብራቶሪ ውስጥ ስንሠራ ለመቁረጥና ለመበየድ የሚያስፈልጉ ማሽኖችን ለሥራችን ፈቅዶልናል። በአጠቃላይ ዩኒቨርሲቲው ማቅረብ የሚችለውን ዕቃ አቅርቦልናል። ሁሉንም ሥራ ያከናወንነው ግቢው በሰጠን ማቴሪያሎች ነው›› በማለት ስምረት ዩኒቨርሲቲው ስላደረገላቸው ድጋፍ ገልፃለች።
በሌላ በኩል ‹‹ምን ትፈልጋላችሁ?›› ብለው ለጠየቋቸው አካላት የሚያስፈልጋቸውን እገዛ እንዳሳወቁም ነው የምትናገረው። እስካሁን ድረስ በይፋ ድጋፍ የሚያደርግ አካል ባይገኝም በቀጣይ ጊዜያት ግን የፕሮጀክት ሃሳቡ አሁን ካለው የበለጠ ዳብሮና ተስተካክሎ ሲዘጋጅ ድጋፍ የሚያደርጉ አካላት ይገኛሉ ብለው ተስፋ ያደርጋሉ። ለጊዜው የፈጠራ ሥራቸው የሚጠራበትና የፈጠራ ባለቤቶቹም የሚታወቁበት የቡድን ስያሜ ባይኖራቸውም፣ ሥራቸውን በማሻሻልና ለቡድናቸውም ስያሜ ለመስጠት እንደሚያስቡም ስምረት ጠቁማለች።
የተመራቂዎቹን የፈጠራ ሥራ በአማካሪነት የመሩት በጅማ ዩኒቨርሲቲ የሜካኒካል ኢንጂነሪንግ መምህር አብርሃ ካህሳይ፣ ፓይሮላይሲስ አንድን ዕቃ ያለኦክስጅን በሙቀት የማቃጠል ሂደት መሆኑን ገልጸው፤ የተመራቂዎቹ ፕሮጀክትም የፕላስቲክ ውጤቶችን ያለምንም ኦክስጅን በሙቀት በማቃጠል የነዳጅ ምርት ማስገኘት የቻለ የፈጠራ ውጤት እንደሆነ ያስረዳሉ።
እርሳቸው እንደሚሉት፣ የፈጠራ ሥራው ነዳጅን ከማምረት በተጨማሪ ሌሎች ዓላማዎችንም የሚያሳካ ፕሮጀክት ነው። አንደኛው አካባቢን የሚበክሉ ፕላስቲኮችን ለነዳጅ ምርት ግብዓት በመጠቀም ወደ ጥቅም መቀየር ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ የግብርና ተረፈ ምርቶች ፕላስቲኮችን ለማቃጠል ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማድረግ ነው።
የተመራቂዎቹ የፈጠራ ሥራ ከነዳጅ ምርት የተሻገረ ተጨማሪ ፋይዳም አለው። ቴክኖሎጂው የወዳደቁ የፕላስቲክ ውጤቶችን በመሰብሰብ ለምርት ሥራ የሚጠቀም በመሆኑ የፕላስቲክ ውጤቶች በአካባቢ ብክለት ላይ የሚኖራቸውን ድርሻ ለመቀነስና ሥነ ምኅዳርን ለመጠበቅ ያግዛል።
የፈጠራ ሥራው አሁን ከተገኘው በተሻለ መልኩ ከተሠራ፤ በነዳጅ አቅርቦት እና በአካባቢ ጥበቃ ዘርፎች ያሉትን አገራዊ ውስንነቶች ለማቃለል አስተዋፅኦ እንደሚኖረው የፈጠራ ሥራው ባለቤቶች ተስፋ ያደርጋሉ። በተመራቂዎቹ አማካኝነት የተሠራውን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ነዳጅን በብዛት ማምረት ከተቻለ በነዳጅ እጥረት ምክንያት የሚጋጥሙ ችግሮችን መቅረፍና ምርታማነትን ማሳደግ እንዲሁም አገሪቱ ለነዳጅ የምታወጣውን ወጪ መቀነስ ብሎም ማስቀረት እንደሚቻል ያምናሉ። ከዚህ በተጨማሪም የፈጠራ ሥራው አካባቢን በመበከል ችግር የሚፈጥሩ የፕላስቲክ ውጤቶችን ለነዳጅ ምርት ግብዓት እንዲሆኑ በማድረግ የችግር መፍትሄ እንጂ ችግር እንዳይሆኑ የማድረግ አቅምም እንደሚኖረው ተስፋ ተጥሎበታል።
‹‹ፓይሮላይሲስ ቴክኖሎጂ ኢትዮጵያ ውስጥ በብዛት ጥቅም ላይ አልዋለም እንጂ በሌላው ዓለም አዲስ ቴክኖሎጂ አይደለም›› የምትለው ስምረት፣ ነዳጅን የማምረት ፈጠራቸው ችግር ፈቺ ተግባራት ላይ ማተኮር እንደሚያስፈልግ ካላቸው እምነት የሚመነጭ እንደሆነ ትገለፃለች። ‹‹ፓይሮላይሲስ ቴክኖሎጂ አዲስ ቴክኖሎጂ አይደለም። የፕላስቲክ ውጤቶችን ለድጋሚ አገልግሎት ጥቅም ላይ ማዋልም የተለመደ ቢሆንም፣ ከዚህ ቀደም የፕላስቲክ ውጤቶች ለድጋሚ አገልግሎት ጥቅም ላይ የሚውሉት ተመሳሳይ ምርቶችን ለማምረት ነው። ‹ይህኛው ሥራ አሁን ለምን አስፈለገ› ብለን ብንጠይቅ ችግር ፈቺ መሆን ስላለብን ነው። ሃሳባችን አሁናዊ ችግራችንን የሚቀርፍ ከሆነ ትኩረታችንን መሰል ተግባራት ላይ አድርገን መሥራትና መጠቀም ይኖርብናል›› በማለት ታስረዳለች።
ስምረት እንደምትለው፣ ፓይሮላይሲስ ቴክኖሎጂ ኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት ጥቅም ላይ ካለመዋሉ በተጨማሪ ቴክኖሎጂውን መጠቀም የጀመሩት ሌሎች አገራትም ፕላስቲኩን ለማቃጠል የሚያስፈልገው የነዳጅ ወጪ ከፍተኛ ሆኖባቸው በፈለጉትና ባቀዱት ልክ ሊቀጥሉበት አልቻሉም። ተመራቂዎቹ የፈጠራ ባለቤቶች ይህን የነዳጅ ወጪ ለማስቀረት የተጠቀሙት ዘዴ ነዳጅን ተክተው ፕላስቲክን ለማቃጠል የሚውሉ እንደቡና ገለባ ያሉ ሌሎች ምርቶች ተረፈ ምርቶችን መጠቀም ነው።
‹‹ተመራቂዎቹ በፈጠራ ሥራቸው ያመረቱት ነዳጅ ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል እንደሆነ በሙከራ ታይቷል›› የሚሉት መምህር አብርሃ፣ የፈጠራ ሥራው ተጨማሪ የማጣራት ሂደቶችና የማሻሻያ ሥራዎች የሚከናወኑለት ስለሆነም ምርቱ በአጭር ጊዜ ወደ ገበያ ለመቅረብ እንደማይችል ያስረዳሉ። ‹‹ሌሎች የማጣራት ሂደቶችና ጥናቶች ያስፈልጉታል። ለምሳሌ ያህል የፕላስቲክ ውጤቶቹ በሙቀት በሚቀልጡበት ወቅት የሚፈጠረው ትነት ውሃ እንዲፈጠር ስለሚያደርግ ውሃውን ከነዳጁ መለየት ያስፈልጋል። አሁን ባለን የላቦራቶሪ አገልግሎት ይህን ማድረግ አልተቻለም። አሁን ባለበት ደረጃ በአንድ ጊዜ ወደሚፈለገው ደረጃ (Standard) ከፍ ማድረግ ስለማይቻል በቀላሉ በብዛት ወደ ገበያ ለማቅረብና እርግጠኛ ሆኖ ለመናገር ከባድ ይሆናል።›› ሲሉ ያብራራሉ።
ስምረት በበኩሏ ‹‹እኛ የሠራነው በትንሽ መጠን ነው። ሥራው ጊዜ ይፈልጋል። ምርቱ ወደ ገበያ ለመውጣት በብዛት መመረት አለበት። ለዚህ ደግሞ ፕላስቲክ ውጤቶችን በብዛት መሰብሰብና ማቃጠል፣ ለማምረት የሚፈጀውን ጊዜ ማሳጠር እንዲሁም ማሽኑ በብዛትና በፍጥነት እንዲያመርት የሚያስችሉ ማሻሻያዎችን ማድረግ ያስፈልጋል። በተጨማሪም ምርቱን በትልቅ ቦታ ላይ ማምረትም አስፈላጊ ነው። እነዚህ ግብዓቶችና ቅድመ ሁኔታዎች ከተሟሉ ምርቱን በተሻለ ጥራና ብዛት ለገበያ ማቅረብ ይቻላል። እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች ካልተሟሉ ምርቱን በተሻለ ጥራት፣ ፍጥነትና ብዛት ለገበያ ለማቅረብ የሚደረገውን ጥረት ያጓትተዋል›› ትላለች።
የተመራቂዎቹን የፈጠራ ሥራ ከዳር ለማድረስና ምርቱን በተሻለ ጥራትና መጠን ለገበያ ለማቅረብ የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት ዩኒቨርሲቲው የፈጠራው ባለቤቶች ጥናታቸውን እንዲቀጥሉ የሁለተኛ ዲግሪ የትምህርት ዕድል እንደሰጣቸውና ፕሮጀክቱን የሚደግፉ አካላትን ለማፈላለግ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም መምህር አብርሃ ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያውያን ስለተሠሩ በርካታ የፈጠራ ሥራዎች በተደጋጋሚ ሲነገር ሰምተናል። ይሁን እንጂ እነዚህ የፈጠራ ሥራዎች በጥራትና በብዛት ተመርተው፣ ለገበያ ቀርበው ለኅብረተሰቡ ዘላቂ መፍትሄ ሲሆኑ የምንመለከትበት አጋጣሚ ግን ብዙ አይደለም።
ዛሬ በምጣኔ ሀብታቸው የዓለም ቁንጮ የሆኑት አገራት ለዚህ ደረጃ የበቁት በአምራችነታቸው ምክንያት ነው። ስለሆነም በኢትዮጵያም በየጊዜው ለሚሠሩ የፈጠራ ሥራዎች እገዛ በማድረግ የአገሪቱን ምጣኔ ሀብት ትርጉም ባለው መጠን መደገፍና ማሳደግ ያስፈልጋል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 26 ቀን 2014 ዓ.ም