ተማሪ አሊ መሀመድ ኡመር ይባላል። የሰባተኛ ክፍል ተማሪ ነው። በአፋር ክልል በዳርሳጊታ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቤት ይማራል። በትምህርቱ ጎበዝ ከሚባሉት ተርታ ይመደባል። ይሁንና ጦርነቱ እርሱንና ቤተሰቦችን ብዙ ዋጋ አስከፍሏቸዋል። በተለይም ሕወሓት አፋር የገባበትን ጊዜ ማስታወስ ጭምር አይፈልግም። ምክንያቱም እርሱ ወደትምህርትቤት በሚመጣበት ጊዜ ትምህርትቤቱ በጥይት እየተደበደበ ነበር። ሰምቶ የማያውቀውን የመሳርያ ድምጽና የሰዎችን ሰቆቃ በመሰማቱ እንዲበረግግ አድርጎታል። በወቅቱ ባለበት ለተወሰኑ ሰዓታት ደርቆ ቀርቶ እንደነበርም ያስታውሳል።
ተማሪ አሊ ከሰመመኑ ሲነቃ በቀጥታ ወደ እናቱ ነበር እየበረረ የሄደው። ምክንያቱም በድህነት ተቆራምዳ እያሳደገችው ያለችው ብቸኛ እናቱ ናት። እናም ከዚህ ድምጽና ጩኸት ትሸሽገው ዘንድ ወደእርሷ እሮጠ። ነገር ግን በቦታው አላገኛትም ነበር። ምክንያቱም የሕወሓት ጦር እዚያም ደርሶ ነበርና ነብሴ አውጪኝ ብላ ወደጫካው ሄዳለች። በዚህ ጊዜ የሚያደርገው ጠፋው። ብቻውን ሆኖም ምን ማድረግ እንደሚገባው ግራ ገባው። እናም የአገኘውን ሰው ተከትሎ እርሱም ነፍሱን ለመታደግ ወደጫካው ሮጠ።
ወደ ጫካው ቢሄድም አላገኛትም፤ ወራት ተቆጠሩ፤ አሁንም የአሊ እናት የለችም። ገለዋት ይሆንም የሚለው ሃሳብ አቃጨለበት። እንደዋዛ ሁለት ወራት አለፉ። በዚያ መኖር እንኳን ላልጠነከረ ልጅ ለአዋቂም ያዳግታል። ምግብ የለም፤ መተኛም እንዲሁ። የሚጠጣ ውሃም ቢሆን አይታሰብም። ገና ባልጠና ጉልበቱ ይህንን መቋቋም አዳጋች ሲሆንበት ተደብቆ ወደ ከተማ እየወጣ የወዳደቀውን ምግብ እያነሳ ይመገብ እንደነበረ ይናገራል።
በጦርነቱ ወቅት አይደለም ምግብ ልብስ እንኳን መቀየር እንዳልቻለ አሊ ይናገራል። ተማሪ አሊ፤ በረሃብ ብቻ ሳይሆን በልብስ እጦትም ብዙ ተሰቃይቷል። ከምንም በላይ ደግሞ ብዙ ሰዎች ሲሞቱ ማየቱ የበለጠ ጭንቀት ፈጥሮበታል። ትምህርት ቤት የመመለስ ህልምም እንዳልነበረው ይናገራል። ምክንያቱ ደግሞ ተደብቆበት ከነበረው ጫካ በሕይወት እወጣለሁ ብሎ አለማመኑ ነው። ብዙ ጓደኞቹም በዚያ ቀርተዋል። ከጫካው ቢወጡም ለመማር ዝግጁ አልነበሩም።
ጓደኞቹ በጦርነቱ የተከሰተው ነገር ከአዕምሯቸው የሚጠፋ ነገር ስላልሆነላቸው በትምህርትቤቱ አካባቢ መድረስን እንደማይፈልጉ የሚገልጸው ተማሪ አሊ፤ አንዳንዶች ደግሞ የሚበሉት ጭምር በማጣታቸው ትምህርታቸውን አቋርጠው ለእለት ጉርሳቸው የሚሆን ሥራ ላይ ተሰማርተዋል። እነርሱንም ቢሆን አሁንም ጦርነቱ ዳግመኛ ይመጣል በሚል ስጋት ውስጥ ከቷቸዋልና በፍራቻ ውስጥ ሆነው እየተማሩ እንደሆነ ይናገራል። ጦርነቱ ትምህርትቤታቸውን ብቻ ሳይሆን ሕይወታቸውን ጭምር ያመሰቃቀለባቸው እንደሆነም ያነሳል።
‹‹ጁንታ በጫካ ሲከተን ራሳችንን ለማትረፍ ብዙ ዋጋ ከፍለናል። የተለየናቸውን ቤተሰቦች ጭምር ለማግኘት ተቸግረናል›› የሚለው ተማሪው፤ ወደቀያቸው ሊመለሱ ሁለት ቀን ሲቀራቸው እናቱን እንዳገኘና ወደ ትምህርትቤት ለመመለሱም መምህራንና የእናቱ ጉትጎታ ትልቅ ድርሻ እንደነበረው ያነሳል። አሁን ፈተና እየወሰዱ ቢሆንም ባላጠናበትና ስጋት ውስጥ ሆኖ ባለበት ሁኔታ ስለሚያደርገው ውጤታማ እንደማይሆንም ይገልጻል። የመውደቅ አደጋን ሊጋርጥበት እንደሚችልም ያስረዳል። ይሁን እንጂ ማንኛውም ውጤት ቢመጣ በጸጋ እንደሚቀበለው ይናገራል።
ሌላው አሊ ያነሳው ነገር ወደፊትም ቢሆን ለመማር ብዙ ነገሮች ያስቸግራሉ የሚለውን ነው። ይህም በየቦታው የተቀበረው ፈንጅ ጉዳይ ሲሆን፤ በቅርቡ ሦስት ህጻናት መሞታቸውን ነግሮናል። እንደልብ ለመንቀሳቀስ እየፈሩ እንዳሉም አጫውቶናል። በተመሳሳይ የአስከሬን መነሳት ጉዳይም እንደሚያሳስበው ያነሳል። ጦርነቱ በሁሉም ቦታ አስከሬን እንዲያዩ ያደረጋቸው ሲሆን፤ እያነሱ ጭምር ቀብረዋል። ነገር ግን አሁንም በየቦታው ሽታ እየፈጠረ ይገኛል። እንደውም ቤታቸው ጭምር እንዳያድሩ አድርጓቸዋል።
ከትምህርትቤት መልስም ውሏቸውም ሆነ አዳራቸው መስኪድ እንደነበር ያወሳል። ከዚያ ባሻገር ኃይለኛ ንፋስ በመኖሩ ብዙ ሰዎች እያለቁ ነውም ብሏል። ምክንያቱ ደግሞ የወዳደቀው ቆርቆሮ በንፋሱ አማካኝነት የብዙዎችን አንገት መቁረጡ ነው። እናም የሚመለከታቸው አካላት እነዚህንና መሰል ችግሮቻችንን በአፋጣኝ ፈተውልን ቀጣዩን ትምህርት በተረጋጋ ሁኔታ እንድንማር ያድርጉን ሲልም መልእክቱን ያስተላልፋል።
በዚሁ ትምህርትቤት የምታስተምረው መምህርት አረጋሽ ኢብራሂም በበኩሏ፤ በዚህ ትምህርቤት 11 ዓመታትን ስታሳልፍ እንዲህ አይነት መአት የወረደበት ጊዜን እንደማታስታውስ ትናገራለች። እንደዚህ አይነት ችግር ገጥሟትም አያውቅም። በተለይም ትምህር ቤቱ ሞዴል በመሆኑ የተሻሉ ነገሮች ሲቀርቡለትና ተማሪዎችን በጥራት ስታስተምር እንጂ እንደዚህ ወላልቆ በድንኳን ተማሪዎችን እስከማስተማር የደረሰችበትን ወቅትን በፍጹም አታስታውስም።
መምህራን የትምህርት ጥራቱን ለማሳደግና ትምህርት ቤቱም ሞዴል እንዲሆን ከማስቻል አኳያ ደፋ ሲሉ የቆዩ ናቸው። ለዚህም ማሳያው በበረሃ ውስጥ ልምላሜን ፈጥረው ቀን ሳይቀር ተማሪዎች እንዲማሩ ማስቻላቸውን ነው። በጁንታው ምክንያት ግን ይህ ሥራቸው ሙሉ ለሙሉ እንደወደመና የማስተማሪያ ክፍላቸው ጭምር እንደተሰባበረ ትገልጻለች። አሁን እያስተማሩ ያሉትም በዳስ ውስጥ መሆኑ እጅጉን እንደሚያሳምማት ታነሳለች።
ጁንታው በትምህርትቤት ውስጥ እያሉ እንደደረሰባቸውና ብዙ ስቃይን እንዳበረታባቸው የምታስረዳው መምህርት አረጋሽ፤ ጁንታው የተማረ ኃይል ያለበት አይመስለኝም ትላለች። በምክንያትነት የምታነሳው ደግሞ የአገር ሀብት ማውደሙን ነው። ተማርኩ ከሚል አካል ይህ አይጠበቅም። ነገር ግን ሆኖ አይተነዋል። ገና ብዙ እንገነባለን ያልነውን ባዶ አድርጎ ዳዴ እንድንል ፈርዶብናል። እናም አገር ከመራና አገሩን ከሚወድም ይህ በፍጹም የሚጠበቅ አይደለም። ስለሆነም ይህንን ጠላት የሆነ ቡድን ሁሉም በተሰማራበት ሙያ በርትቶ በመሥራት ከነበረው በላይ ሰርቶ በማሳየት ማሸማቀቅ እንዳለበት ትመክራለች።
እንደ መምህርት አረጋሽ ገለጻ፤ መምህራን ጠላት ካደረገው አንጻር ብዙ ተጎድተዋል። ሕወሓት ሙስሊሙ መስገጃ እንዲያጣ፣ መምህራኑ ማስተማሪያ ብቻ ሳይሆን መኖሪያ እንዳይኖራቸው ያደረገ ጨካኝ ቡድን ነው። ማንኪያ ጭምር አልተወልንም። በዚህም ዛሬ ላይ በብዙ መንገድ እንድንፈተን ሆነናል። ቤት ስለሌለን ሁለት
ሶስት ሆነን ተከራይተን እንድንኖርና ምግብ አብስለን የምንመገብበት አሳጥቶናል። ነገር ግን ተስፋ ሳንቆርጥ ተማሪዎቻችንን ከታህሳስ ጀምሮ ከያሉበት በመሰብሰብ ችግሮቻችንን በጋራ እየመከትን እያስተማርን እንገኛለን። እጅም እንደማንሰጥ በብዙ መልኩ አሳይተናል። ወደፊትም ይህ ተግባራችን ይቀጥላል።
መምህርቷ እንደምትለው፤ እኛ የተማርን ነን። አገር ወዳድና አዲስ ትውልድ የምንፈጥር ነን። በሆነው ነገር ሳንቆዝም እንሰራለን። ይሁን እንጂ እንደማንኛውም ማህበረሰብ መምህራንም የችግሩ ሰለባ ናቸውና የክልሉ ትምህር ቢሮ፤ ትምህር ሚኒስቴርና የክልሉ አስተዳደር እንዲሁም አንዳንድ ረጂ ድርጅቶች ለሌላው እንደሚያደርገው ሁሉ ለመምህራንም የቻሉትን ሊያደርጉለት ይገባል።
የዳሳጊታ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ኡመር ኢብራሂም በበኩላቸው እንዳሉት፤ ትምህርት ቤቱ ከክልሉ በተለያየ ጊዜ በሞዴልነት የሚመረጥ ነው። ብዙ ሽልማቶችንም አግኝቷል። በቅርቡ የተሰጠው የሁለተኛ ደረጃ እድገትም ከዚህ የተነሳ የመጣ ነው። ነገር ግን ትምህርት ጠል የሆነው ጁንታ ከሁሉም በበለጠ መልኩ ይህንን ትምህርትቤት መርጦ ከባድ አደጋ አድርሶበታል። የመማሪያ ክፍሎችን ብቻ ሳይሆን የመምህራንን ቤትና ንብረት ጭምር አውድሟል። በትምህርትቤቱ የነበሩ ኮንፒውተሮችንና መሰል ቁሳቁሶችንም ዘርፏል፤ አቃጥሏልም።
ጁንታውን ለመታገል ብዙ መምህራን ጥረት አድርገዋል። ለዛሬው ዳግም የመማር ሥራም መብቃት የተቻለው በተቻለው ሁሉ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይባል በመሥራቱ ነው። በተለይም ቤተሰብን አሳምኖና ተማሪዎችን አግባብቶ ወደትምህርት ገበታቸው መመለስ ትልቅ ጥረትን የጠየቀ ነበር። በዚህም ብዙውን አሳክተናል የሚሉት ርዕሰ መምህሩ፤ ጦርነቱ ብዙ ደንቃራዎችን እንዳስቀመጠባቸውም አልሸሸጉም። አንዱና ዋነኛው የስምንተኛ ክፍል የተማሪዎች ፈተና ነው። በስጋትና በውጥረት ውስጥ ሆነው ተማሪዎች እንዲማሩ፤ መምህራን እንዲያስተምሩ ሆነዋል። ከዚያም ያሉትን እንዲፈትኑም ተገደዋል። በዚህም ይፈተናሉ ተብለው የተጠበቁት 27 ተማሪዎች ሙሉ ለሙሉ እንዲፈተኑ ተደርጓል።
እንደ ትምህርትቤት 306 ተማሪዎች በትምህርት ገበታው ላይ ይገኛል ተብሎ ይታመን ነበር። ነገር ግን በጦርነቱ ምክንያት ከ150 በላይ ተማሪዎች አቋርጠዋል ያሉን አቶ ኡመር፤ ዳግመኛ ትምህርቱ ሲጀመር ባለመምጣታቸውና ትምህርቱን በአግባቡ ባለመከታተላቸው የማጠቃለያ ፈተና መውሰድ አልቻሉም። በዚህም ግባችን እንዳይሳካ አድርጓል። ይሁን እንጂ በ2015 ዓ.ም ለሚጀመረው የትምህርት መርሃግብር ተማሪዎችን ሙሉ ለሙሉ የመመለስ ሥራ ይሰራል። ማለትም በቀጣይ የትምህር ዘመን ቤተሰብን በማማከርና ያሉበትን ቦታ በማፈላለግ የስነልቦና ህክምና በመስጠት እንዲማሩ እድሉ እንደሚመቻችም አስረድተዋል።
በትምህርትቤቱ አሁን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሊከፈትላቸው በመሆኑ እጅግ ደስተኛ እንደሆኑ የሚናገሩት ርእሰ መምህሩ፤ ከዚህ ቀደም ተማሪዎቹ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ለመከታተል 25 ኪሎሜትር በእግራቸው ይጓዙ እንደነበር አንስተዋል። አሁን የተሰጠው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርትቤት የመክፈት እድል ይህንን ሁሉ የሚፈታ ብቻ ሳይሆን የማቋረጥ ምጣኔን የሚቀንስም ይሆናል ብለዋል። በተጨማሪም ተማሪዎች በቅርብ ሆነው ቤተሰቦቻቸውን እንዲያግዙና እንዲያጠኑ የሚያደርግ በመሆኑ ለሁሉም የማህበረሰብ ክፍል እፎይታን የሚፈጥር እንደሚሆንም ገልጸዋል። በተለይ ደግሞ በትምህርት ጥራቱ ላይ የሚኖረው ፋይዳ የማይተካ እንደሚሆንም አንስተዋል።
የአፋር ክልል ትምህርት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ዳሬክተር አቶ አህመድ ሰዲቅ እንደሚናገሩት፤ እንደ ክልል ጦርነቱ የተካሄደባቸው በአራት ዞንና በ22 ወረዳዎች ላይ ነው። በዞን አራትና አምስት ላይ ብቻ ከ150ሺህ በላይ ተማሪዎች እንዲፈናቀሉ ሆነዋል። ነገር ግን ተማሪዎቹ በጦርነት መንፈስ ውስጥ እንዳይቆዩ በየደረሱበት ወረዳ ላይ ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ተደርገዋል። ከጦርነቱ በኋላ ተማሪዎቹ ወደቀያቸው ሲመለሱም ቢሆን ብዙ ድጋፎችን በማድረግ ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ተደርጓል። ድጋፉ በጦርነቱ ምክንያት ቤተሰብ ለተማሪዎቹ የሚሆን ምንም የትምህርትቤት ቁሳቁስ የሚገዛበት ስላልነበረ ወጪውን በመሸፈን ቦርሳን ጨምሮ ሌሎች የትምህርት ቁሳቁሶችን እንደየክፍል ደረጃቸው እየታየ መሰጠቱን ተናግረዋል።
ድጋፉ የትምህርት ክፍሎችን አማራጭ ከመፈለግ የሚጀመር እንደነበረ የሚያነሱት ዳይሬክተሩ፤ ሙሉ ለሙሉ የፈረሱ ክፍሎችን ተማሪዎቹ እንዳይበተኑ ለማድረግ ድንኳን በመትከል የሚማሩበት አማራጭ ተመቻችቷል። ይህ ተግባር ዞን ሁለት በጁንታው ረጅም ጊዜ የተያዘ በመሆኑ ከእርሱ በስተቀር ሁሉም ላይ ተዘርግቶ ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸው እንዲገኙ መደረጉንም ጠቅሰዋል።
በወረዳው ላይ ብዙ ተማሪዎች እንደተጎዱ ሁሉ መምህራንም የችግሩ ገፈት ቀማሽ እደነበሩ ያነሱት ዳይሬክተሩ፤ ጦርነቱ ምንም እንዳይኖራቸው አድርጓል። ስለዚህም እንደ ትምህርት ቢሮ ብቻ ሳይሆን እንደ ክልልም የተቻለውን ሁሉ ለማድረግ ይሰራል። በተለይም ረጂ ድርጅቶች ቢያንስ የቤት ውስጥ ቁሳቁሶችን እንዲያሟሉላቸው ከማድረግ አንጻር ሥራዎችን ለመከወን ይሞከራል። ይህ ባይሆን እንኳን ሕወሓት ለምገባ ሥራ የሚውሉ ቁሳቁሶችን ጭምር አጥፍቶ ነበርና መልሶ ለመተካት እንደተሞከረው ለእነርሱም ቢያንስ የእለት ከእለት መጠቀሚያ የሚሆናቸው ነገር እንዲገዛ እንደሚደረግ ነግረውናል።
መምህራን በቁስ መጥፋት ብቻ ሳይሆን በስነልቦናም ተጎጂ ሆነዋል። ስለዚህም በስልጠና ራሳቸውን አግዘው ሌሎችንም እንዲረዱ ለማድረግ በቢሮ ደረጃ በሁለት ዙር 500 መምህራንን እንዲሰለጥኑ ተደርጓል። አጋዥ ድርጅቶች በሰጡት ድጋፍ ደግሞ ሁለተኛ ዙር የተጀመረ ሲሆን፤ በዚህም ከ300 በላይ እንዲሰለጥኑ ሆነዋል። ስነልቦናን ማከም የአንድ ቀን ሥራ ባለመሆኑም ቀጣይነት ያለው ተግባር እንደሚከናወንም አስረድተዋል።
በአጠቃላይ አሸባሪው ሕወሓት የትምህርት ተቋማትን በማውደም ዜጎች የጨለማ ጉዙ እንዲገፉ ለማድረግ ብዙ ሰርቷል። ትምህርት ቤቶችን አውድሟል፤ ተማሪዎችን አፈናቅሏል፤ መምህራንን ገድሏል፤ ንብረታቸውን ዘርፏል። ሆኖም ኢትዮጵያዊነት ጽኑነት ነውና ዛሬ ትምህርት ቤቶችም ሆኑ ተማሪዎችና መምህራን ችግሮችን ተቋቁመው በዕውቀት መንገድ መጓዝ ጀምረዋል። በአፋር የታየውም ይህ እውነታ ነው።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሐምሌ 25/2014