ኢትዮጵያ የስእል ሀገር ናት። ከቅጠሉ እና ከስሩ ቀምመው ቀለም የሚሰሩ እና በዚያ ስእል አስገራሚ ስእሎችን የሚሰሩ ድንቅ ሰአሊያን በየዘመኑ ተፈጥረዋል። በተለይም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉ ሰአሊያን የራሳቸውን ፍልስፍና እና የአሳሳል መንገድ መፍጠር ችለዋል። ሆኖም የኢትዮጵያ ዘመናዊ የአሳሳል ስልት በመፍጠር ረገድ ዋነኛው ተጠቃሽ አንድ ሰው ናቸው። እሳቸውም አለ ፈለገሰላም ይባላሉ። ዛሬ በአጭሩ ስለ ታላቁ ሰው ከተጻፉ ጽሁፎች የተወሰነውን ቀንጭበን አቅርበናል።
አለ ፈለገሰላም ኅሩይ በሰላሌ ፍቼ ከተማ ሐምሌ 24 ቀን 1915 ዓ.ም. ተወለዱ። ገና የሁለት ወር ጨቅላ ሳሉ አባታቸው አቶ ፈለገሰላም ኅሩይ ስለሞቱ፣ በሠዓሊው አያታቸው በአለቃ ኅሩይ ቤት አደጉ። (አለቃ ኅሩይ የዳግማዊ ምኒልክን ምሥል፣ የእንጦጦ ማርያምንና ራጉኤልን፣ የሌሎችን አብያተ ክርስቲያናት ሥዕላት ሥለዋል።) አያትየው አለቃ ኅሩይ ወደ ዲቁናው ትምህርት ወደ አዲስ አበባ ላኳቸው።
አለ ሥዕልን ያገኙት ከአጎታቸው ከብላታ እምአዕላፍ ኅሩይ ነበር። ብላታ እምአዕላፍ ኅሩይም መንፈሳዊውንም ዓለማዊውንም ሥዕል በመሥራት የሚታወቁ በብርሃንና ሰላም ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ማተሚያ ቤት ተቀጥረው ይሠሩ ከነበሩት ሠዓልያን አንዱ ነበሩ። (በዓሉ ግርማ እምአእላፍ ኅሩይ የሚል ሠዓሊ ገጸ ባሕርይ እንደጻፈ ያስታውሳል።)
ብዙ ሳይቆይ በጣሊያን ጦርነት ጊዜ እምአዕላፍ ኅሩይ በአርበኝነት ዘመቱ። ከዘመቻ መልስ እምአዕላፍ ኅሩይን አለን ወደ አዲስ አበባ መልሰው ወሰዷቸው። በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ገቡ። ግርማዊነታቸው ተማሪዎችን ለመጎብኘት ወደ ትምህርት ቤቱ በሔዱ ጊዜ ሥዕሎች ተመልክተው ሠዓሊውን ጠየቁ። አለ ነበሩ የሣሉት። በዕለቱ አለ በትምህርት ቤቱ አልነበሩምና በነጋታው ቤተ መንግሥት እሳቸው ዘንድ እንዲቀርብ አዘዙ።
በቤተ መንግሥት አስቀድሞ በትምህርታቸው አንደኛ በመውጣት ንጉሡ ሸልመዋቸው ነበር። ከሌሎች ልጆች ጋር ወደ ውጭ አገር ለትምህርት እንዲሔዱ ተብለው ነበር። ንጉሡ አስታውሰው፣ “አልሄድክም እንዴ?” ሲሉ ጠየቋቸውና፣ “በል አሁን ጥሩ ሠዓሊ ሆነህ ተገኝተሃልና ወደ ውጭ አገር ሄደህ ሥዕል ተማር፣” አሏቸው። በርሳቸው ትዕዛዝ ወዲያውኑ ወደ አሜሪካ ሔደው፣ በቺካጎ አርት ዩኒቨርሲቲ ገብተው ተማሩ።
በቺካጎ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ካገኙ በኋላ፣ በፈረንሣይ ከነበሩት የታሪክ ምሁሩ ዶ/ር ብርሃኑ አበበ ጋር በመሆን፣ በማርሴይ፣ በሮም፣ በሲሲሊ እየዞሩ፣ የነማይክል አንጄሎ፣ የነራፋይሌ፣ የነዳቪንቺን ሥዕሎችና ሐውልቶች ጎበኙ። ወደ አገር ቤት እንደገቡ፣ ወደ ጃንሆይ ቀርበው፣ “በአገራችን የሥዕል ትምህርት ቤት እንዲከፈትና እኔም በዚያ ማስተማር እፈልጋለሁ፤” አሏቸው።
በትምህርትና ሥነ ጥበብ ሚኒስቴር ተመድ በው በልጆች መማሪያ መጻሕፍት ላይ ሥዕሎችን መሥራት ቢጀምሩም፣ ትምህርት ቤት ለመክፈት የሚያስችላቸውን እንቅስቃሴም በግላቸው ያካሒዱ ነበር። በሚኖሩበት ቤት ጊቢ ውስጥ፣ በጣሊያኖች በተሠራ መጋዘን ውስጥ፣ አስፈላጊውን ቁሳቁስ በማሟላት ቅዳሜና እሑድ በነፃ ማስተማር ጀመሩ።
የተማሪዎችን ሥራዎች ይዘው፣ በልዕልት ተናኘ ወርቅ ኃይለ ሥላሴ የተመረቀ ዓውደ ርዕይ አሳዩ። በመክፈቻው ዕለት፣ “በአገራችን የሥነ ጥበብ ተግባር ብዙ ነበር፤ የአክሱም ሐውልቶችን ያነፁ፣ ላሊበላን የቀረፁ፣ በጎንደርና ጎጃም ሥዕልን የሠሩ አሁን የሉም፣ ብቅ አላሉም። በኛ ጊዜ መጥፋት የለባቸውም፤ ነፍስ እንዲዘሩ መደረግ አለበት። ወደነበርንበት ትልቅ ተግባር በዓላማ መጓዝ አለብን፤፣” በማለት ጥሪ አቀረቡ።
በዐውደ ርዕዩ የቀረቡት ሥዕሎች ተሸጡላቸው። አንድ ግሪካዊ ከበርቴ ከለገሠው 50,000 ብር ጋር 78,000 ብር ተሰበሰበ። ይህንን እንዳለ ይዘው፣ ለጃንሆይም በማስረከብ፣ ‹‹በራሴ ጥረት ይችን ገንዘብ አግኝቻለሁ፤ ተማሪ ቤት ይሥሩልን፣›› አሏቸው። ንጉሡ ከመንግሥት 150,000 ብር ተጨምሮ የአዲስ አበባ ሥነ ጥበብ ትምህር ቤት ግንባታ ተጀመረ። ሕንፃው ተጠናቅቆ፣ በንጉሠ ነገሥቱ የልደት ቀን፣ ሐምሌ 16 ቀን 1950 ዓ.ም. ትምህርት ቤቱ ተመረቀ። አለ በ1951 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ዘመነኛው የሥነ ጥበብ ትምህርት እንዲጀመር አደረጉ። የመጀመሪያው ዳይሬክተርም ሆኑ።
በሥዕሎቻቸው የኢትዮጵያን ትውፊትንና ዘመነኛውን የእውነታ አሣሣልን ያቀናጁ፣ ብሔራዊና ኢትዮጵያዊ ድባብ ያላቸው፤ ስሜትንና ህሊናን የሚገዙና የተረጋጉ መሆናቸውን ብዙዎቹ የሥነ ጥበብ ታሪክና ሒስ ምሁራን መስክረውላቸዋል።
በይዘቱና በጥራቱ እጅግ ውብ የሆነው የአዲስ አበባ ሒልተን ሲመሠረት የላሊበላውን የሰላማዊ ፍቅርና የዕድል ተምሳሌት የሆነውን መስቀለ ጌጥ ምስል (ከስዋስቲካ ምስል ጋር የሚመሳሰለውን) እንዲቀናበር የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አድርገዋል። እንደገናም በዘመነ ደርግ የዚህን መስቀለ ጌጥ ምስል ለቀን መቁጠሪያ ሥዕል፣ በሴቶች የጥበብ ልብስ ላይ ስለአደረጉት ትርጉሙ ተለውጦ የፋሺዝም (ናዚዝም) ምልክት ነው ተብለው ለእንግልት ዳርጓቸው ነበር።በተረፈ ሥዕሎቻቸውን በአሜሪካ፣ በጀርመን፣ በህንድ፣ በሶቪየት ኅብረት፣ በቼኮዝላቫኪያ፣ በግሪክና በዩጎዝላቪያ አሳይተዋል።
አለ ፈለገሰላም በ93 ዓመታቸው ሐምሌ 4 ቀን 2008 ዓ.ም አርፈው፣ ሐምሌ 5 ቀን በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የመታሰቢያ ዝግጅት ተደርጎላቸው፣ ሐምሌ 6 ቀን በደብረ ሊባኖስ ሥርዓተ ቀብራቸው ተከናውኗል። ሠዓሊና መምህር አለ ፈለገሰላም ከሙያቸው ውጪ የተለየ ክህሎት ነበራቸው። ስፖርት (ዮጋ) የመሥራት፣ ንብ የማነብና ዓሳ የማጥመድ ወዘተ። የመዝናኛ ልምድ እንደነበራቸው ይታወቃል። ሠዓሊና የሥነ ጥበብ መምህሩ አለ ፈለገሰላም ከባለቤታቸው ወ/ሮ አስቴር ክፍለእግዚእ የአንድ ሴት (መሠረት አለ) እና የአንድ ወንድ ልጅ (ቴዎድሮስ አለ) አባት ሲሆኑ፣ የሦስት የልጅ ልጆችና የአንድ ልጅ ቅድመ አያት ነበሩ። መወድስ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከስድስት ዓመት በፊት፣ አለ ፈለገሰላም ላበረከቱት የሥዕል አለኝታነት ክብር ለመግለጽ፣ የመሠረቱትን ትምህርት ቤት በስማቸው እንዲጠራ አድርጓል።
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን ሐምሌ 24 ቀን 2014 ዓ.ም