በዚህ ሳምንት የምናስታውሳቸው ሌላኛው ጀግና ሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ ናቸው። ለጣሊያን ፋሽስት ወራሪ አንገዛም ብለው ሰማዕት የሆኑ ናቸው።የእኝህን ሰማዕት ታሪክ በጥቂቱ እናስታውሳለን።
የኢትዮጵያ አርበኞች በ1928 ዓ.ም ክረምት፣ አዲስ አበባ ባለው የፋሽስት ጣልያን ጦር ላይ ከሦስት አቅጣጫ ድንገተኛ ጥቃት ፈጸሙ።ዋና ከተማዋን ነጻ ማውጣትና ፋሽስት ጣልያንን ማስወጣት የወታደራዊ ዘመቻው ዓላማ ነበር። ሆኖም ግን በተመሳሳይ ሰዓት ከተለያየ አቅጣጫ ጥቃቱን መፈጸም አልተቻለም።
ድንገተኛ ጥቃቱ ለጣልያን መንግሥት ያሳየው በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ልብ የነጻነት ህልም እንዳለ ነው፡፡የኢትዮጵያዊነትን መንፈስ የማይገፋ አለት፣ የማይጨበጥ የእሳት አሎሎ ካደረጉት ነገሮች መካከል የአንድ ኢትዮጵያዊ አባት ሚና ከፍተኛ ነበር። እኚህ አባት አቡነ ጴጥሮስ ናቸው።
ፋሽስት ጣልያን በባንዳዎች ድጋፍ አቡነ ጴጥሮስን በቁጥጥር ሥር አዋለ። የጣልያን ፋሽስት አቡነ ጴጥሮስን በምድራዊ የቅንጦት ኑሮ ሊያባብላቸው ሞከረ። እርሳቸው ግን ለነዋያት ከማይሸነፍ መንፈሳዊ ልዕልና ላይ ወጥተው ነበርና አልተሳካለትም።አቡነ ጴጥሮስ ለግል ሕይወት ብልፅግና የሚለውጧት ኢትዮጵያ፣ ለምቾት ኑሮ የሚቀይሯት አገር እንደሌላቸው አስረግጠው ተናገሩ።
የማይረታ መንፈሳቸውን ከኢትዮጵያውያን ልብ ለማስወጣት እና በምትኩ ፍርሃትን ለመትከል ለፋሽስቱ የታየው መፍትሔ ቆራጡን አቡነ ጴጥሮስ መግደል ሆነ።ሞታቸው ሲሰማ በየጓዳው ያደፈጠው የነጻነት ህልም፣ አልሸነፍ ባይነት በያለበት ይከስማል የሚል ነበር የጠላት ስሌት። ሰዎቹ ኢትዮጵያውያን ናቸውና ውጤቱ ግን የተገላቢጦሽ ሆነ!
አቡነ ጴጥሮስን ከታሠሩበት እሥር ቤት እጅና እግራቸው በሠንሠለት እንደታሰረ ወደ ፍርድ አደባባይ አወጧቸው። በማመፅና በማሳመፅ ተከሰው በዳኞች ፊት ቀረቡ።የመሐል ዳኛ የነበረው ጣልያናዊ ኮሎኔልም ‹‹ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ቄርሎስና የቤተ ክህነት ሹማምንት የኢጣልያን መንግሥት ገዢነት ተቀብለው ለጣልያን ሲያድሩ እርስዎ ለምን አመፁ?›› ሲል አቡነ ጴጥሮስን ጠየቃቸው፡፡
የቆራጡ አቡነ ጴጥሮስ መልስ ግን እንዲህ ነበር!
‹‹አቡነ ቄርሎስ ግብጻዊ ናቸው።እኔ ግን ኢትዮጵያዊ ነኝ፤ ስለ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ኃላፊነት ያለብኝ የቤተ ክርስቲያን አባት ነኝ።እኔን ግደሉኝ ተከታዮቼን ግን አትንኩ›› ሲሉ በድፍረት ተናገሩ።
አቡነ ጴጥሮስ ለዳኛው መልስ ሰጥተው ሲያበቁ ወደ ተሰበሰበው ሕዝብም መለስ ብለው፤
‹‹…ቤተ ክርስቲያንን ለማቃጠል፣ ሕዝበ ክርስቲያንን ለመግደል፣ ሃይማኖትን ለማጥፋት፣ ታሪካችንን ለማበላሸት ለመጣው ፋሽስት እንዳትገዙ፤ ስለውድ ሀገራችሁና ስለ ቀናች ሃይማኖታችሁ ተጋደሉ።ለእነዚህ አረመኔዎች የተገዛ እንኳን የኢትዮጵያ ሕዝብ መሬቷም ጠላትን ብትቀበል የተረገመች ትሁን…›› አሉ በጠላት ፊት በግርማ ሞገስ ቆመው።
ይህን ንግግራቸውን እንደ ጨረሱ መስቀላቸውን አውጥተው ሞት የፈረዱባቸውን ዳኞች ባረኩ። የሞት ፍርዱን ያነበበው ጣልያናዊ ዳኛ እጅ ይንቀጠቀጥ ነበር።ፍርሃት ከፈራጆቻቸው ፊት በቆሙት ሰማዕት አቡነ ጴጥሮስ ጋር ሳይሆን በፈራጆች ደጅ ነበረች።
ፍርዱ እንደተሰጠ ጣልያ ናዊው ኮሎኔል ወዲያውኑ አጣድፎ ወደሚገደሉበት የዛሬው አቡነ ጴጥሮስ አደባባይ ወሰዳቸው። በቦታው ሲደርሱ ሕዝብ ተሰብ ስቧል፤ ዓይናቸውን መሸፈን ይፈልጉ እንደሆን ተጠየቁ። እርሳቸው ግን በደስታ የሚሞቱላት አገርና ሕዝብ፣ ነፍሳቸውን የሚሰጡላት ሃይማኖት ያላቸው ጽኑ አባት ነበሩና ሞትን ፊት ለፊት ዓይናቸው እያየ ለመጋፈጥ አልፈሩም።መሸፈን እንደማይፈልጉ በፍርሃት ሳይሆን በድፍረት ተናገሩ።
ከጾምና ጸሎት በቀር መሣሪያ ላልታጠቁት አቡነ ጴጥሮስ፣ የክርስትና አርማ የሆነውን መስቀልን ብቻ ለያዙት አባት፣ በብረት ሠንሠለት ለተቆለፈባቸው መንፈሳዊ አርበኛ ስምንት ገዳዮች መሣሪያቸውን አቀባብለው ተዘጋጁ። ጣልያናዊው መኮንን የመጨረሻ ቃል እንዲናገሩ ዕድል ሰጣቸው። ያችን የመጨረሻ ቅጽበት ለጸሎት ተጠቀሙባት።
በቦታው ተገኝቶ ታሪካዊውን ክስተት የዘገበው ፖጃሌ የተባለ ጋዜጠኛ ‹‹በመጨረሻም ይዘውት የነበረውን መጽሐፍ ቅዱሳቸውን ተሳለሙ፤ ከዛም ሰዓታቸውን ከኪሳቸው አውጥተው ተመለከቱ›› ሲል ጽፏል፡፡
ሞት በጥቂት ርምጃ ርቀት ላይ ቁሞ አልፈሩትም። መጽሐፍ ቅዱሳቸውን ሳሙ፤ እነሆ በዚች ሰዓት ስለ ክብርህ፣ ስለ እውነተኛ ቃልህ እሠዋ ዘንድ የፈቀድክልኝ አምላክ ክበር ተመስገን አሉ።
ወዲያው ኮሎኔሉ የ‹‹ተኩስ!›› ምልክት ሰጠ።ሁሉም በአንድ ላይ አነጠጥረው ተኮሱ። የአቡነ ጴጥሮስ ነፍስ ግን ከሥጋዋ አልተለየችም ነበር። ሐኪም መጥቶ አረጋገጠ፤ አልሞቱም። በነዛ ሁሉ ተኳሾች ጥይት ተመትተው አለመሞታቸው የተኳሾቹን ሥነ ልቡና አፍ አውጥቶ የሚናገር ይመስላል።
አልተናገሩትም እንጂ መሣሪያ የታጠቁት ተኳሾቹ እውነት በታጠቁት አባት መንፈስ ተሸብረዋል። መሸበራቸው አካላዊ ቁጥጥራቸውን ሰልቦታል። ምላጭ ቢስቡም ስስ ብልት ላይ መምታት አልቻሉምና በስምንት ጥይት የተመቱት ሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ ወዲያውኑ አልሞቱም። ሐኪሙም አለመሞታቸውን አስረዳ።
ኮሎኔሉ ሌላ ጋሻ ጃግሬ አዘዘ። እሱም ቀረብ ብሎ የፋሽስቶችን አረመኔያዊነት በሚያሳይ ሁኔታ በሽጉጡ ሦስት ጊዜ ጭንቅላታቸው ላይ ተኮሰ። አሁን ጳጳሱ አልፈዋል፤ አይበገሬው የኢትዮጵያዊነት መንፈሳቸው፣ መንፈሳዊ ወኔያቸው ግን ይበልጥ በኢትዮጵያውያን ልብ እንደ ሰደድ እሳት ተቀጣጠለ። የኢትዮጵያ ጫካዎች ከዚህ ክስተት በኋላ በኢትዮጵያውያን አርበኞች ተይዘዋል።
የፋሽስቱ ኮሎኔል ሰማዕቱ ሲገደሉ በዙሪያው የነበረውን ሰው አስጨበጨበ።ጳውሎስ ኞኞ እንደጻፈው፤ ማታ ሲጨዋወቱ የፋሽስቱ ኮሎኔል ‹‹ይሄ ሕዝብ ቄሱ ስለሞቱ ደስ ብሎታል፤ አጨበጨበ እኮ!›› አለ።በኢትዮጵያ ለ30 ዓመታት ኖሮ የነበረ ግሪካዊ ‹‹ኢትዮጵያውያን ሲደሰቱ ብቻ ሳይሆን ሲከፋቸውም ማጨብጨብ ባህላቸው ነው›› አለው።
ከዚያች ክስተት በኋላ የኢትዮጵያ አርበኞች በዱር በገደል ተሰማርተው ፋሽስቱን ጣሊያን ከአገራቸው ጠራርገው አስወጡ።እኝህ ሰማዕት አባትም እነሆ ሲታወሱ ይኖራሉ።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 24 ቀን 2014 ዓ.ም