ሁለቱ ግንቦቶች

በዛሬው የመጀመሪያ የሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችን ግንቦት 8 ቀን 1981 ዓ.ም በደርግ ላይ የተደረገውን የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ እና ግንቦት 7 ቀን 1997 ዓ.ም የተደረገውን ምርጫ እንዲሁም በእዚህ ሳምንት ከእዚህ ዓለም በሞት የተለዩትን ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስን ዘርዘር አድርገን እናስታውሳለን። ከእዚያ በፊት በእዚህ ሳምንት የሚታወሱትን የታሪክ ክስተቶች በአጭር በአጭሩ እናስታውሳችሁ።

የሀገር ውስጥ የፖለቲካ ክስተቶች የሚበዙበትን የግንቦት ወር ጀምረነዋል። የግንቦት ወር የደርግ እና የኢህአዴግ፣ የደርግ እና የተቃዋሚዎቹ፣ የኢህአዴግ እና የተቃዋሚዎቹ ወር ነው ማለት ይቻላል። የታሪክ ግጥምጥሞሹ በታሪክ ክስተቶች ላይ ብቻ የተወሰነ አይደለም። የሚገርመው ገዥዎቹ እና ተቃዋሚዎቹ መሪዎች የተወለዱበትና ያረፉበት ወር ጭምር ነው። የደርግ መሪ የነበሩት ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም የተወለዱት በግንቦት ወር ነው። የደርግ መንግሥትን የታገለውና የገረሰሰው የኢህአዴግ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ የተወለዱት በግንቦት ወር ነው።

ከ68 ዓመታት በፊት በእዚህ ሳምንት ግንቦት 5 ቀን 1949 ዓ.ም የንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ እና የእቴጌ መነን አስፋው ልጅ የሆኑት ልዑል መኮንን ኃይለሥላሴ አረፉ።

ከ77 ዓመታት በፊት በእዚህ ሳምንት ግንቦት 6 ቀን 1940 ዓ.ም (በአውሮፓውያኑ 1948) እስራኤል ሉዓላዊ (ነፃ) ሀገር ሆና ተመሰረተች።

ከ41 ዓመታት በፊት በእዚህ ሳምንት ግንቦት 6 ቀን 1976 ዓ.ም (በአውሮፓውያኑ 1984) የፌስቡክ ኩባንያ (Facebook, Inc.) መስራች ማርክ ዙከርበርግ ተወለደ።

ከ157 ዓመታት በፊት በእዚህ ሳምንት ግንቦት 7 ቀን 1860 ዓ.ም የንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ ባለቤት የነበሩት እቴጌ ጥሩወርቅ ውቤ ኃይለማርያም አረፉ።

ከ9 ዓመታት በፊት በእዚህ ሳምንት ግንቦት 7 ቀን 2008 ዓ.ም አንጋፋው የአትሌቲክስ አሰልጣኝና የኢትዮጵያ ባለውለታ ዶክተር ወልደመስቀል ኮስትሬ አረፉ።

ከ116 ዓመታት በፊት በእዚህ ሳምንት ግንቦት 10 ቀን 1901 ዓ.ም ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አጼ ምኒልክ፣ ልጅ ኢያሱ ሚካኤል የዙፋናቸው ወራሽ መሆኑን በአዋጅ አሳወቁ።

በዝርዝር ወደምናያቸው ታሪኮች እንሂድ።

ግንቦት 8 ቀን 1981 ዓ.ም

ግንቦት 8 ቀን 1981 ዓ.ም ሌተናንት ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ለጉብኝት ወደ ምሥራቅ ጀርመን ሄዱ። በዕለቱም መፈንቅለ መንግሥት ለማድረግ የመጨረሻው የአድማ ስብሰባ ቦታ የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር ግቢ ነበር። መፈንቅለ መንግሥት አድራጊዎች ከመከላከያ ሚኒስትሩ ቢሮ አጠገብ ባለው አነስተኛ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ ተሰበሰቡ።

የመፈንቅለ መንግሥቱ ጠንሳሽና የአድመኞቹ ሰብሳቢ ሜጀር ጀኔራል ፋንታ በላይ ወደ ስብሰባው የመጡት ዘግይተው ነበር። ወደ አዳራሹ ሲገቡ የሰብሳቢነቱን ቦታ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ ሜጀር ጀኔራል መርዕድ ንጉሤ ይዘውታል። ሜጀር ጀኔራል መርዕድ ቦታውን መልቀቅ ሲገባቸው ዝም አሉ። ይባስ ብለውም ሜጀር ጀኔራል መርዕድ ቦታውን የመልቀቅ አዝማሚያ ሳያሳዩ ስብሰባውን መምራት ቀጠሉ። መፈንቅለ መንግሥት ለማድረግ የተሰበሰቡት የጦር አዛዦች እዚያው በእዚያው ሌላ መፈንቅለ መንግሥት አደረጉ። ሜጀር ጀኔራል ፋንታ በሁኔታው ተበሳጭተው ስብሰባውን ጥለው ወጥተው እጃቸውን ኪሳቸው ውስጥ አድርገው መንጎራደድ ጀመሩ።

በሌላ በኩል በመፈንቅለ መንግሥቱ ሴራ ውስጥ ከተሳተፉ የጦሩ አባላት መካከል አንዳንዶቹ መፈንቅለ መንግሥቱ እንደሚሳካ ቀድመው እርግጠኛ በመሆን ‹‹እዚህ አድማ ውስጥ እኔንም አካፍሉኝ እንጂ ጎበዝ! በ1953ቱ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ወቅት ሳይነግሩኝ ቀሩ። ዛሬም ልትተውኝ ነው እንዴ? …›› ብለው የተናገሩ የጦር መሪዎች እንዳሉ ስለመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው የተፃፉ ታሪኮች ያሳያሉ።

የመፈንቅለ መንግሥቱ ሴራ ጠንሳሾች ‹‹ታማኝ ናቸው›› ያሏቸውን የጦሩን አባላት ሰብስበው ሲነጋገሩ ንግግራቸው ጭቅጭቅ የበዛበት ነበር። የመንግሥቱ ኃይለማርያም አስተዳደር ተወግዶ በምትኩ በጀኔራል መኮንኖች የሚመራ አዲስ መንግሥት የማቋቋም እቅዳቸውን ተናገሩ። በብዙ ጉዳዮች ላይ መግባባትና መተማመን እያጡ በሄዱ ቁጥር ጊዜ እየመሸባቸው መሆኑን መገንዘብ አቃታቸው።

የደህንነት ሚኒስትሩ ኮሎኔል ተስፋዬ ወልደሥላሴ በሊቀመንበሩ ሽኝት ላይ ሳይገኙ የቀሩ፤ የጦር አዛዦች ሁኔታ ስላላማራቸው አዛዦቹን የሚከታተል ቡድን አደራጅተው ስለነበር እያንዳንዱን ድርጊት ይከታተሉ ነበር። ጉዳዩ የመፈንቅለ መንግሥት አድማ መሆኑን ሲያረጋግጡም ነገሩን የሊቀመንበሩ ቀኝ እጅ ለነበሩት ለሻለቃ መንግሥቱ ገመቹና ለሌተናል ጀኔራል ተስፋዬ ገብረ ኪዳን አሳወቋቸው።

ኮሎኔል አዲስ ተድላ እና ኮሎኔል ደበላ ዲንሳ በሽምግልና ወደ መከላከያ ሚኒስቴር ቢላኩም የመፈንቅለ መንግሥቱ ሴራ ጠንሳሾች ግን ‹‹ያለቀለት ነገር ስለሆነ ሽምግልናና ድርድር አያስፈልግም›› ብለው መነታረካቸውን ቀጠሉ። ለመንግሥት ታማኝ በነበረው ጦርም ተከበቡ። በሁኔታው ተስፋ የቆረጡት አንዳንድ የጦር አዛዦችም ራሳቸውን አጠፉ።

የመፈንቅለ መንግሥቱ ጠንሳሾችና መሪዎች በፈፀሙት የእቅድና የአፈፃፀም ስህተት ለአራት ዓመታት ያህል ታቅዶበት ሲውጠነጠን የነበረው መፈንቅለ መንግሥትም ሳይሳካ ቀረ።

ከመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው በኋላ በተወደሰው ርምጃ ኢትዮጵያም በርካታና ‹‹በአፍሪካ ደረጃ ምርጥ ነበሩ›› የተባሉ የጦር መሪዎቿን አጣች። ሊቀመንበር ሌተናንት ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ከግንቦት 1981 ቢተርፉም ከግንቦት 1983 ግን ሳይተርፉ ቀሩ።

ግንቦት 7

ከ20 ዓመታት በፊት በእዚህ ሳምንት ግንቦት 7 ቀን 1997 ዓ.ም ኢትዮጵያ ምርጫ አካሄደች። ይህ ምርጫ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የሚታወስ ሆነ። የምርጫውን ዕለት ክስተቶች በዕለቱ አዲስ አበባ ውስጥ የነበሩ ሰዎች ያስታውሱታል። አንዳንዶችም ራሱን የቻለ መጽሐፍ ጽፈውበታል። ከእነዚህም አንዱ የኢህአፓ መሥራችና ‹‹ኢትዮጵያ ሆይ›› በሚሉት መጽሐፎቹ የሚታወቀው ክፍሉ ታደሰ ነው። ክፍሉ ታደሰ ‹‹ግንቦት 7›› በሚለው መጽሐፉ በዕለቱ በአዲስ አበባ የተለያዩ ምርጫ ጣቢያዎች ያስተዋለውንና የታዘበውን ለታሪክ ጽፎ አስቀምጧል።

ክፍሉ ታደሰ ‹‹ግንቦት 7›› በተሰኘው መጽሐፉ፤ ምዕራፍ 5 ‹‹ግንቦት 7 ታሪካዊ ቀን›› በሚል ርዕስ እንዲህ ጽፎታል።

‹‹ግንቦት 7/1997 ዓ.ም 524 የምክር ቤት ወንበሮች ለውድድር ቀረቡ። 23 የሚሆኑት በነሐሴ ወር በሶማሌ ክልል ለሚደረገው ምርጫ ወደ ጎን ተተው።

ግንቦት 7 በተካሄደው ምርጫ ተሳትፌያለሁ። ማን ይናገር የነበረ፤ ማን ያርዳ የቀበረ እንደሚባለው፤ ያየሁትን፣ የሰማሁትን፣ የተሳተፍኩበትን ነው የማቀርበው። እኔ የእዚህ መጽሐፍ ደራሲ ታሪኩን በሦስተኛ ሰው አድርጌ ላቀርበው አስቤ ራቀብኝ። የእኔ መስሎ አልሰማህ አለኝ፤ እናም በቀጥታ ላቀርበው ወሰንኩኝ›› በማለት ደራሲው ግንቦት 7 ቀን 1997 ዓ.ም በአዲስ አበባ ውስጥ የነበረውን ሁነት በቀጥታ በመሳተፍ ያየነውን ነግሮናል።

ማለዳ 12፡00 ተነስቶ መገናኛ ሲደርስ ረጅም ሰልፍ አጋጠመው። ሰልፉ እየተጠማዘዘ ቢያንስ ከ300 ሜትር በላይ እንደሚሆን ይገምታል። ደራሲው የዕለቱን እንቅስቃሴ ማየት ፈልጎ ስለነበር ብዙ የምርጫ ጣቢያዎችን እየተዘዋወረ ተመለከተ። ሁሉም ረጃጅም ሰልፎች ያሉባቸው ናቸው።

ደራሲው ከእዚያ በፊት የነበሩ ምርጫዎችንም ያስተዋለ መሆኑን አስታውሶ፣ የእዚያን ዕለት የነበረው ተሳትፎ ግን በኢትዮጵያ ከተደረጉ ምርጫዎች ሁሉ የተለየ እንደነበር ይገልጻል። መጽሐፉ ከ2013ቱ 6ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ በፊት የተጻፈ ስለሆነ በዘመነ ብልፅግና የተደረገውን ምርጫ አያካትትም።

ደራሲው እንደሚለው፤ የምርጫው ዕለት እንደሌላ ጊዜው ‹‹ውጣ›› እየተባለ ሳይሆን፤ ሕዝቡ በራሱ ተነሳሽነት በነቂስ ወጣ። ሕዝቡ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች የሄደው በመንግሥት ካድሬዎች ቅስቀሳ ሳይሆን በተፎካካሪ ፓርቲዎችም ቅስቀሳ መሆኑን አስተውሏል።

ያም ሆኖ ግን ምርጫ 97 በእንዲህ አይነት መንገድ ተጀምሮ መጨረሻው ብዙ ወከባና ግርግር የተፈጠረበት ስለነበር በኢትዮጵያ የምርጫ ታሪክ ውስጥ ጎላ ብሎ ይታወሳል።

ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ

ሌላኛው የእዚህ ሳምንት ክስተት የፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ሕልፈተ ሕይወት ነው። የኢህአዴግን መንግሥት አምርረው ይቃወሙ የነበሩ ምሁር ናቸው። የእርሳቸው ታሪክም ከኢህአዴግ ጋር ይገናኛል ማለት ነው።

ከ26 ዓመታት በፊት በእዚህ ሳምንት ግንቦት 6 ቀን 1991ዓ.ም ነው ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ ከእዚህ ዓለም በሞት የተለዩት።

ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ የሕክምና ባለሙያ ሲሆኑ፤ ኢህአዴግን ለመታገል የፖለቲካ ፓርቲ በማቋቋም ብዙ ዋጋ የከፈሉ ናቸው። የእኝህን ሰው ሕይወት እና የፖለቲካ ውጣ ውረድ እናስታውሳለን።

አስራት ወልደየስ ከአባታቸው ከአቶ ወልደየስ አልታዬና ከእናታቸው ከወይዘሮ በሰልፍይዋሉ ጽጌ ሰኔ 12 ቀን 1920 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ተወለዱ። የአስራት አባት አቶ ወልደየስ አልታዬ በጸሐፊ ትዕዛዝ ኃይሌ ወልደሥላሴ አስተዳደር ውስጥ በጸሐፊነትና በአስተዳደር ተግባር የተሰማሩ ነበሩ። እናታቸውም በአነስተኛ ንግድ የተሰማሩ ነበሩ። ፕሮፌሰር አሥራት የሦስት ዓመት ህጻን እያሉ ወላጆቻቸው በፍች ምክንያት ስለተለያዩ ከእናታቸው ጋር ወደ ድሬዳዋ አቀኑ።

አስራት ድሬዳዋ በነበሩበት ወቅት ጣሊያን ኢትዮጵያን ትወራለች። በእዚህ ወቅት በእነ ሞገስ አስግዶምና አብርሃም ደቦጭ ግራዚያኒ ላይ የተደረገ የግድያ ሙከራን ለመበቀል ከግራዚያኒ በተላለፈ በቀል በሶስት ቀናት ውስጥ ብቻ ከ33 ሺህ በላይ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በዶማ፣ በአካፋና በገጀራ ተጨፍጭፈው ተገደሉ። የአስራት አባት አቶ ወልደየስ አልታዬም እንደ ሌሎች ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ተጨፍጭፈው በአርበኝነት ሞቱ። እናቱ ወይዘሮ በሰልፍይዋሉ ጽጌም የባለቤታቸው ሞት ተጨምሮበት ብዙም ሳይቆዩ ታመው በሞት ተለዩ።

ወላጆቹን በሞት የተነጠቀው ታዳጊ በድሬዳዋ ከአያቱ ጋር አደገ። ቄስ ትምህርት ቤት ገብተውም ጎበዝና ፈጣን ተማሪ ነበሩ ይባላል። ከጣሊያን ወረራ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ተመልሰው ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ገቡ። አንደኛ በመውጣትም ተሸላሚ ሆኑ። አንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀው ከፍተኛ ውጤት ያመጡ ወደ ውጭ ይላኩ ስለነበር አሥራት ወደ ግብጽ ተልከው ተከታትለዋል። ከእዚያም በስኮላርሽፕ እንግሊዝ ሀገር ሄደዋል። እንግሊዝ ሀገር ሕክምና ተምረው ወደ ሀገራቸው በመመለስ በሕክምና አገልግለዋል።

ዶክተር አስራት ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን የህክምና ማሰልጠኛ እንዲከፈት በመወትወታቸው ምክንያት የጥቁር አንበሳን ሆሰፒታል እውን አደረጉ። የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሲቋቋም የቴክኒክ ኮሚቴውን የመሩት ዶክተር አስራት ነበሩ። እ.ኤ.አ በ1965 ዓ.ም የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል እውን ሲሆን ፕሮፌሰር አስራት ተባባሪ ፕሮፌሰር በመሆን የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ዲን ሆኑ። ከእዚያ በፊት በውጭ ባለሙያዎች ነበር።

ፕሮፌሰር አሥራት በደርግ ዘመነ መንግሥት በተደጋጋሚ ዘመቻ የተላኩ ሲሆን፤ የሄዱበትን ዘመቻ በክብር ለመወጣት በቅተዋል። በእዚህም መሠረት በ1968 ዓ.ም በቀዳጅ ሐኪምነት በቃኘው ሆስፒታል አስመራ፣ በ1969 ዓ.ም እንደገና በቃኘው ሆስፒታል አስመራ፣ በ1970 ዓ.ም በራዛ ዘመቻ በቀዳጅ ሐኪምነት እና ቡድን መሪነት በመቀሌ ሆስፒታል፣ እንዲሁም በሰኔ 1971 ዓ.ም በቀዳጅ ሐኪምነት ምጽዋ ዘምተው ግዳጃቸውን ተወጥተዋል። የተለያዩ ዓለም አቀፍና ሀገር አቀፍ ሽልማቶችንም አግኝተዋል።

የደርግ ሥርዓት ተሸንፎ ኢህአዴግ ሀገሪቱን በተቆጣጠረበት ወቅት፤ ሰኔ 24 ቀን 1983 ዓ.ም በተደረገው የሽግግር መንግሥት ቻርተር ውይይት ላይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ወክለው የተገኙት ፕሮፌሰር አስራት ‹‹ሀገር ላስገነጥል ተወክዬ አልመጣሁም›› በማለት ተቃውሞ አሰሙ። ‹‹ይህ ጉባኤ በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ምንም ጉዳይ ሊወስን፤ ሊያግድ ወይም ሊሰርዝ አይችልም›› በማለት ጉባኤው እያደረገው ያለውን ውሳኔ ‹‹ኢ-ዲሞክራሲያዊ ነው›› ሲሉ ሞገቱ።

እንዲህ እንዲህ እያሉ ፕሮፌሰር አሥራት ወደ ፖለቲካው ገቡ። የኢህአዴግን አገዛዝ ለመታገል ፓርቲ መሥርተው መንቀሳቀስ ጀመሩ። ከኢህአዴግ ጋር አይጥና ድመት ሆኑ። ኢህአዴግም እያሳደደ ያሥራቸውና ይፈታቸው ጀመር። ኢህአዴግ እንቅስቃሴያቸውን ባየ ቁጥር እስርና እንግልቱን አጠናከረው። ለብቻቸው በማሰር ስቃይና መከራም ያደርስባቸው ጀመር።

የእስር አያያዛቸው የከፋ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በ1972 ዓ.ም የጀመራቸው የልብ ሕመም ተባብሶ እንዲሁም የስኳር መጠናቸው በመጨመሩ ከፍተኛ የጤና ችግር ላይ ወደቁ። ለብዙ በሽተኞች መድኃኒት የነበሩት አስራት ሕክምና ተከልክለው የበሽታ መጫወቻ ሆኑ። ከስኳራቸው ከፍ ማለት ጋር ተያይዞ አይናቸው ማየት አልቻለም። ሰውነታቸውም እንደፈለጉ ሊታዘዛቸው አልቻለም። የልብ ድካማቸው ጨምሯል። ሕክምና እንዲያገኙ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሳይቀር ደብዳቤ ጻፉ። መፍትሄ ግን አላገኙም። የኋላ ኋላ ሲዳከሙ ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ቢወሰዱም ሕመማቸው ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ በመሆኑ መፍትሄ ሊያገኙ አልቻሉም። በመጨረሻም እ.ኤአ ታህሳስ 27 ቀን 1998 ዓ.ም ወደ ውጭ ሀገር ሄደው እንዲታከሙ ተፈቀደ።

በከፍተኛ ሁኔታ በመድከማቸው አውሮፕላን ውስጥ በሐኪሞች እየታገዙ ወደ ለንደን ሆስፒታል በረሩ። ከ3 ቀናት ቆይታ በኋላ ወደ አሜሪካ ሆስተን አመሩ። በአሜሪካ ቅዱስ ሉቃስ ኤጲስቆጶስ ሆስፒታል በነበሩበት ወቅት እንደተሻላቸውና ከልቡ ሲያስባቸው ለነበረው ሕዝብ መልዕክት አስተላልፈው ነበር። ትንሽ እንደተሻላቸው ዘመዶቻቸው ወደሚገኙበት ፊላደልፊያ ከወር በፊት ተዛውረው በነበረበት ወቅት ባልታወቀ ምክንያት ሕመማቸው ተባብሶ ተዳከሙ።

ሞትን ድል ሲያደርጉት የኖሩት ሐኪም ግንቦት 6 ቀን 1991 ዓ.ም ፊላደልፊያ በሚገኘው ፔኒሲለቫኒያ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል በሕክምና ሲረዱ ቆይተው በዕለተ አርብ በተወለዱ በ71 ዓመታቸው አረፉ። በወቅቱ የፕሮፌሰሩን ሞት ትልልቅ የዓለም መገናኛ አውታሮች ሰፊ ሽፋን ሰጥተው ነበር። ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ የፖለቲካ ተሳትፏቸው ከሕክምና ሙያቸው በላይ እንዲታወሱ አድርጓቸዋል።

አቶ መለስ ዜናዊ እና ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ የሁለት ዓለም ሰዎች ናቸው። እንዳለመታደል ሆኖ ግን የታሪክ አቀባበል ልማዳችን ኋላቀር ነው። ታሪክን በታሪክነቱ ከማስታወስ ይልቅ መበሻሸቂያና የቡድን የፖለቲካ ፍላጎት መቀስቀሻ ሆኗል። የአቶ መለስ ዜናዊ አድናቂዎችና ደጋፊዎች የፕሮፌሰር አሥራት ስም እንዲነሳ አይፈልጉም፤ የፕሮፌሰር አሥራት ደጋፊዎች ደግሞ የአቶ መለስ ዜናዊ ስም እንዲነሳ አይፈልጉም። ይህ ኋላቀር አመለካከታችን ሊቀረፍ ይገባል። ሁሉንም በሠሩት ሥራ ታሪክ ያስታውሳቸዋል።

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን እሁድ ግንቦት 10 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You