
ባለፈው ሐሙስ ሚያዚያ 27 ቀን 84ኛው የአርበኞች ቀን በተለያዩ ስነ ሥርዓቶች ተከብሯል። በዛሬው ሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችን 84 ዓመታትን ወደኋላ መለስ ብለን ታሪካዊ ክስተቶችን እናስታውሳለን። ከዚያ በፊት ግን ሌሎች የዚህ ሳምንት ክስተቶችን በአጭሩ እናስታውስ።
ውድ አንባቢያን፤ በዕለተ እሁድ ባለፉት ቀናት የተከሰቱ ክስተቶችን ያስታውስ የነበረው ሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችን ከነገ ግንቦት 4 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በዕለተ ሰኞ የሚወጣ መሆኑን እናሳስባለን።
ወደ ታሪካዊ ክስተቶቻችን!
ከ135 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሚያዝያ 25 ቀን 1881 ዓ.ም ለዓድዋ ጦርነት ሰበብ የሆነው የውጫሌ ውል ተፈረመ።
የውጫሌ ውል በአሁኗ አምባሰል ወረዳ ውጫሌ በምትባል ቦታ በአጼ ምኒልክና በጣሊያኑ ንጉስ ኢምቤርቶ ተወካይ ኮንት አንቶሎኒ መካከል ተፈረመ። ውሉ 20 አንቀጾች ያሉት ሲሆን ከእነዚህ አንቀጾች ውስጥ ሰበበኛዋ አንቀጽ 17 ለጣሊያን የውርደት ካባ ያለበሰውን የዓድዋን ጦርነት አስከተለች፤ ለኢትዮጵያውያን ደግሞ ድል በማጎናጸፍ የጥቁርን ጀግንነት ያስመሰከረ ክስተት ሆነ።
አንቀጽ 17 በአማርኛ ‹‹የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት ከአውሮፓ ነገስታት ለሚፈልጉት ጉዳይ ሁሉ በኢጣሊያ መንግሥት አጋዥነት መላላክ ይቻላቸዋል›› የሚል ሲሆን ቀጥተኛ ትርጉሙም የኢትዮጵያ መንግስት ከፈቀደ ወይንም ከፈለገ በኢጣሊያ በኩል ከውጭ መንግሥታት ጋር ግንኙነት ማድረግ እንደሚችል የሚጠቅስ ነው፡፡
የአንቀጹ የጣሊያንኛ ትርጉም ግን ‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት ከውጭ ሀገር መንግሥታት ጋር የሚያደርገውን ግንኙነት በኢጣሊያ መንግሥት አማካኝነት ማድረግ ይገባዋል›› የሚል ነበር። ይህም የኢትዮጵያን የውጭ ግንኙነት በቀጥታ በጣሊያን በኩል እንዲከናወን የሚያስገድድ ነበር፡፡
በአንቀጽ 17 አማካኝነት ጣሊያን የውሉን ሀሳብ በጣሊያንኛ በመቀየር የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በመገርሰስ የጣሊያን ሞግዚት እንድትሆን ቀዳዳ እያበጀች ነው ብለው ነገሥታቱ እና መኳንንቱ ስለተገነዘቡ የውጫሌ ውልን እንደማይቀበሉት አሳወቁ።
የጣሊያን መንግሥት ውሉን ለማፍረስ አሻፈረኝ በሚልበት ጊዜ፣ የውጫሌ ውል እንዲፈርስና ኢትዮጵያ ለማይቀረው ጦርነት እንድትዘጋጅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካበረከቱ ግለሰቦች መካከል የዳግማዊ አጼ ምኒልክ ባለቤት የሆኑት እቴጌ ጣይቱ ብጡል እንደነበሩ ታሪክ ይናገራል፡፡
እቴጌዋ ‹‹እኔ ሴት ነኝ፣ ጦርነት አልወድም። ግን እንዲህ መሳዩን ውል ከምቀበል ጦርነት እመርጣለሁ›› ብለው የተናገሩት እነሆ ታሪክ ሆኖ ይታወሳል!
ሌላኛው የዚህ ሳምንት ክስተት ከ89 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሚያዚያ 27 1928 ዓ.ም ታዋቂው ደራሲ ስብሃት ገብረእግዚአብሔር ተወለደ። ደራሲ ስብሃት ገብረእግዚአብሔር የታሪክና የማህበራዊ ጉዳዮች አዋቂ ቢሆንም ብዙዎች የሚያውቁት ግን ‹‹ትኩሳት›› እና ‹‹ሌቱም አይነጋልኝ›› በተሰኙ ሁለት መጽሐፎች ብቻ ሆኗል። በኢትዮጵያ ባህልና ወግ ባልተለመደ ሁኔታ በእነዚህ መጻሕፍት ወሲባዊ ቃላትን በመጠቀሙ ከሌሎች መጽሐፎቹ ይልቅ በእነዚህኞቹ አጀንዳ ሆነ። ያም ሆነ ይህ ስብሃት ገብረእግዚአብሔር ለየት ባለ የሕይወት ፍልስፍናው እና በስነ ጽሑፍ ሥራዎቹ ሲታወስ ይኖራል።
ከ70 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ግንቦት 1 ቀን 1947 ዓ.ም የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ተወለዱ። ከፖለቲካ ሕይወታቸው ባሻገር ያለው የግል ሕይወታቸው ብዙም የማይታወቀው አቶ መለስ ዜናዊ በፓርላማ እና በሌሎች መድረኮች በሚያደርጓቸው ንግግሮች እነሆ አሁን ድረስ ይታወሳሉ። ዝርዝር ታሪካቸውን ከዚህ በፊት ማስታወሳችን ይታወሳል።
አሁን በዝርዝር ወደምናየው የአርበኞች የድል ታሪክ እናልፋለን።
ገጽ 8
ሳምንቱን በታሪክ
ስፖርት እና መዝናኛ
አዲስ ዘመን እሁድ ግንቦት 3 ቀን 2017 ዓ.ም
በዓድዋ ጦርነት ሽንፈት የተከናነበው ጣሊያን ለ40 ዓመታት ያህል ዝግጅት አድርጎ ዳግም ወረራ ሞክሮ ነበር። ኢትዮጵያውያን ጀግኖች በለመዱት የጀግንነት ስልትና ወኔ ባደረጉት ተጋድሎ ነፃነታቸውን አስከብረዋል። ይህ ድል የኢትዮጵያውያን የወታደራዊ ጀግንነት እና የቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ የዲፕሎማሲያዊ ጥበብ ውጤት ነበር ማለት ይቻላል።
የተክለ ጻድቅ መኩሪያ ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ ከዐፄ ቴዎድሮስ እስከ ቀዳማዊ ሀይለ ሥላሴ›› የባህሩ ዘውዴ ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1847 እስከ 1983›› መጽሐፎች በዝርዝር ይነግሩናል።
ኢትዮጵያ በአምስት ዓመቱ የፋሽስት ጣሊያን ወረራ ሰንደቅ ዓላማዋ ከታጠፈ፣ ሉዓላዊነቷ ከተደፈረ 5 ዓመታት በኋላ ነፃነቷን ያስመለሰችው ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ በ11 ሰዓት ንጉሰ ነገሥቱ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ በአርበኞች ብርታትና መስዋዕትነት የጣሊያን ባንዲራ አውርደው የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በታላቁ ቤተ መንግሥት ሲሰቅሉ ነው፡፡
የሚያዝያ 27 የንጉሰ ነገስቱ አዲስ አበባ ገብቶ ሰንደቅ ዓላማ መስቀል ሌላው ታሪካዊነቱ ከአምስት ዓመታት አስቀድሞ ሚያዝያ 27 ቀን 1928 በዚያው ቀን ወደ ኢትዮጵያ የዘመተው የጣሊያኑ ጦር አዛዥ ጄኔራል ባዶሊዩ አዲስ አበባ ገብቶ በታላቁ ቤተ መንግሥት የጣሊያንን ባንዲራ የሰቀለበት ቀን መሆኑ ነው። ጣሊያን ከዓድዋ ሽንፈቷ 40 ዓመታት በኋላ በዘመናዊ የጦር መሣሪያና በወታደራዊ ኃይል ይበልጥ ደርጅታ ኢትዮጵያን ከሦስት አቅጣጫዎች ወረረች። ከዓድዋው ዘመቻ ያልተሻለ የጦር ትጥቅ የነበራት ኢትዮጵያም የጣሊያንን ጦር በፅናት ተዋጋች፡፡
የወቅቱ ሃያላን እንግሊዝና ፈረንሳይ የጦር መሣሪያ በግዢ እንዳታገኝ ለጣሊያን ተደርበው ስላሴሩባት ኢትዮጵያ ብቻዋን ጦርነቱን በመጋፈጧ ድል ማግኘት አልቻለችም ነበር፡፡
የየግንባሮቹ የኢትዮጵያ የጦር አዛዦች ብዙዎቹ ሞተው ሠራዊቱም በመርዝ ጋዝና በአውሮኘላን ቦምብ ተደብድቦ ያለቀው አልቆ የቀረው ቀርቶ ጣሊያን ጊዜያዊ ድል አግኝታ ዋና ዋና ከተሞችን ብትቆጣጠርም ኢትዮጵያውያን ጀግኖች በገጠሩ ክፍል እምቢ ለነፃነቴ፣ እምቢ ለሀገሬ ብለው የሽምቅ ውጊያ ጀመሩ። ንጉሰ ነገስቱም ስደት ሄደው በጊዜው ለነበረው የመንግሥታቱ ማህበር (ሊግ ኦፍ ኔሽንስ) አቤቱታ አቀረቡ። የሚሰማቸው ግን አላገኙም። የኢትዮጵያ አርበኞች ግን ከቀን ወደ ቀን ድል እየተቀዳጁ የጣሊያን ወታደሮችን መፈናፈኛ፤ መግቢያ መውጫ አሳጧቸው፡፡
ከጣሊያን ወታደሮች ይማርኳቸው በነበሩ መሣሪያዎች ራሳቸውን እያደራጁ አብዛኛውን የገጠር ክፍል ተቆጣጠሩት፡፡
በዚህ መሃል እንግዲህ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት መቀስቀስ ለኢትዮጵያ ትልቅ ቦታ ነበረው። ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሲቀሰቀስ ጣሊያን የናዚ ጀርመን አጋር ሆነች። ያን ጊዜ እንግሊዞች የጣሊያን ጠላት ሆነው ኢትዮጵያን መደገፍ ጀመሩ።
ወታደራዊ ድጋፍ ሰጥተው፤ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ ረዷቸው፡፡
በጄኔራል ካኒንግሂም የሚመራው የእንግሊዝ ጦር ከኬንያ ተነስቶ በደቡብ አቅጣጫ ወደ መሀል ኢትዮጵያ ሲገሰግስ፤ በጄኔራል ፕላት የሚመራው ጦር ከሱዳን ተነስቶ ወደ አሥመራ፤ ከዚያም በሰሜን አቅጣጫ ወደ መሐል ኢትዮጵያ ተንቀሳቀሰ፡፡
በቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ የሚመራውና የአርበኞችና የእንግሊዝ አማካሪዎች የሚገኙበት ‹‹ጌዲዮን›› ተብሎ የተሰየመው ጦር ከሱዳን ተነስቶ በኦሜድላ አልፎ በጐጃም በኩል ወደ መሐል ሀገር ገሠገሠ፡፡
በመካከለኛው ኢትዮጵያ አርበኞች በጣሊያን ወታደሮች ላይ ጥቃታቸውን አፋፋሙ፡፡
ጣሊያኖች ክፉኛ ተሸነፉ። በየቦታው ድል የመሆናቸው ዜና ናኘ፡፡
ዘመቻው ከተጀመረ ሁለት ወራት ሳይሞላው፤ ጣሊያኖች አዲስ አበባን ለቀው ፈረጠጡ፡፡
መጋቢት 28 ቀን 1933 ዓ.ም የጄኔራል ካኒንግሃም ጦር አዲስ አበባን ተቆጣጠረ፡፡
እንግሊዞች ኢትዮጵያውያን አርበኞች ወደ አዲስ አበባ እንዲገቡ ስላልፈለጉ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴን በደብረ ማርቆስ ለአንድ ወር ያህል እንዲቆዩ አደረጓቸው።
ይሁንና በአዲስ አበባ በአርበኞች ተፅዕኖና ቅሬታ የተነሳ አርበኞች ወደ አዲስ አበባ እንዲገቡ ፈቀዱ። አፄ ኃይለ ሥላሴም ወደ አዲስ አበባ እንዲጓዙ ፈቀዱ። ንጉሰ ነገስቱም አዲስ አበባ በታላቁ ቤተ መንግሥት የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ሰቀሉ። አዲስ አበባ ገብተውም የሚከተለውን ንግግር አደረጉ።
‹‹ይህ የምትሰሙት ድምጽ የእኔ የንጉሳችሁ የቀዳማዊ ሀይለ ሥላሴ ነው። አባቶቻችን ደማቸዉን አፍሰዉ አጥንታቸዉን ከስክሰዉ በነፃነት ያቆዩልን ሀገራችንን ወደ ከፍተኛዉ የሥልጣኔ ደረጃ ለማራመድ የምንደክምበት ጊዜ ከጥንት ዠምሮ ስለሆነ ደመኛ ጠላታችን ኢጣሊያ ይህንን አይታ ወሰናችንን ጥሳ የግፍ ጦርነት እንዳደረገችብን ሁላችሁም የምታውቁት ነዉ። እኛም በተቻለን ከተከላከልን በኋላ ርዳታ ለመጠየቅ ወደ መንግሥታት ማሕበር ወደ ወዳጆቻችን መንግሥታቶች መጣን፤ እዚህ ስንነጋገር በቆየንበት ጊዜ የኢትዮጵያ አርበኞች ሰይፋችሁን ሳትከቱ ፊታችሁን ሳትመልሱ ሰንደቅ ዐላማችሁን ሳታጥፉ ለባዕድ አንገዛም በማለት በመሳሪያ ብዛት ከሚበልጣችሁ ጨካኝ ጠላት ጋር የባሕርይ የሆነዉን ዠግንነታችሁን መሣሪያ አድርጋችሁ በኢትዮጵያ አምላክ ብቻ ተማምናችሁ በዠግንነት ቀንና ሌሊት በዱር በገደል ስትጋደሉ ቆይታችሁ ይኸዉ አሁን እንደምታዩት የማያቋርጥ የአምስት አመት ትግላችሁ የድካማችሁንና የመሥዋዕትነታችሁን ፍሬ ለማየት እንድትበቁ አደረጋችሁ።
የሀገሬ የኢትዮጵያ ህዝብ!
ዛሬ ኢትዮጵያ እጆቹዋን ወደ እግዚያብሔር ዘርግታ እልል እያለች ምስጋናዋን የምታቀርብበት ደስታዋንም ለልጆቿ የምትገልጽበት ቀን ነው። የኢትዮጵያ ልጆች ከባድ የመከራ ቀንበርና ከዘለአለም ባርነት ነፃ የወጡበት ቀንና እኛም አምስት አመት ሙሉ ተለይተነዉ ከነበረዉ ከምንወደውና ከምንናፍቀው ሕዝባችን ጋር ለመቀላለቀል የበቃንበት ቀን ስለሆነ ይህ ቀን የተከበረና የተቀደሰ በያመቱም ታላቁ የኢትዮጵያ በዓል የሚውልበት ነዉ። በዚህም ቀን ለሚወዷት ላገራቸዉ ነፃነት ለንጉሰ ነገስታቸውና ለሰንደቅ ዐላማቸዉ ክብር ካባቶቻቸው የተላለፈውን ጥብቅ አደራ አናስወስድም በማለት መስዋዕት ሆነዉ ደማቸውን ያፈሰሱትን አጥንታቸውን የከሰከሱትን ዠግኖቻችንን እናስታውሳለን። ለዚህም ለዠግኖቻችን የኢትዮጵያ ታሪክ ምስክር ይሆናል።
ባለፈዉ አምስት አመታት ዉስጥ በዝርዝር ተነግረውና ተቆጥረዉ የማያልቁ ያገኘናቸዉ መከራና ስቃይ ትምህርት ሆነውን ሰራተኛነት አንድነት ህብረትና ፍቅር በልባችሁ ተጽፈው ለምናስበዉ ለኢትዮጵያ ጉዳይ ረዳቶች ለመሆን ዋና ትምህርት የሚሰጣችሁ ነው። ባዲሷ ኢትዮጵያ ከእንግዲህ ወዲያ የማትነጣጠሉ በሕግ ፊት ትክክልና ነፃነት ያላችሁ ሕዝቦች እንድትሆኑ እንፈልጋለን። ሀገር የሚለማበትን ሕዝብ የሚበለጽግበትን እርሻ፣ ንግድ፣ ትምህርትና ጥበብ የሚሰፋበትን የሕዝባችን ሕይወቱና ሀብቱ የሚጠበቅበትን የአገር አስተዳደርም ባዲሱ ስልጣኔ ተለውጦ ፍጹም የሚሆንበትን ይህን ለመሰለዉ ለምንደክምበት ስራ አብሮ ደካሚ መሆን አለባችሁ፡፡
የኢጣሊያ መንግስት ኢትዮጵያን ድል አድርጎ ለመያዝ ችሎታ ከሰጠዉ መሳሪያ በቀር ኢትዮጵያን ለመግዛት ሌላ ተስፋ ያደረገዉ ነገር ነበር ይኸዉም የኢትዮጵያ የነገድ ልዩነት ነዉ። የኢትዮጵያ ህዝብ እንደ እርሱ አሳብ አንደኛዉ ወገን ከሴም ዘር የመጣዉ የትግሬና የሸዋ፣ የጎጃም፣ የበጌምድር፣ በጠቅላላዉ አማራ የሚባለዉ፣ ሁለተኛዉ በኢትዮጵያ ምዕራብና ደቡብ የሚገኙትን እነወለጋ፣ እነጅማ፣ እነሲዳማ፣ እናሩሲ አነዚህን የመሳሰሉት ሀገሮች ከካም ዘር የመጡ በነገድም በቋንቋም በሃይማኖትም የተለያዩ ናቸዉ። አንደኛው ወገን ቢያምጥብኝ ሁለተኛውን ወገን ይዤ አጠፋዋለሁ የማለት ተስፋ ነበረውና ይህንንም ሊሰራበት እንደጣረ በጉልህ ታይቷል። ዳሩ ግን የ3ሺህ አመት የነፃነቱ ዘመን በታሪኩ ውስጥ ምንም የሚያሳፍር ገጽ የሌለበት የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነቱን አሳይቶ ለጠላቱ ሳይመች ቀረ።›› ብለው ነበር ንጉሡ፡፡
ይሄ የኢትዮጵያውያን የድል ብስራት የሆነው የአርበኞች ቀን ከፍተኛ ዋጋ የተከፈለበት ነው። በዚህ ጦርነት ውስጥ ምላጭ ስቦ ጥይት ከተኮሰው አርበኛ በተጨማሪ በየቤቱ ሆኖ የተባበረውም ቀላል አልነበረም። በትግሉ ጊዜ የአርበኞች ዋናው ችግር ቀለብ ነበር። ቀለባቸውን የሚያገኙትም ከአርሶ አደሩ ቤት ነው። ይሄ ነገር የሚሆነው ታዲያ በግድም በውድም ነበር። ፈቃደኛ የማይሆን አርሶ አደር ካለ ፋኖ እስከማሰማራትም ተደርሶ ነበር። በተለይም ከጠላት ጋር የሚያብሩ ሰዎችን ደግሞ እህላቸው እንዲዘረፍና ለሰራዊቱ ቀለብ እንዲሆን ተደርጓል።
ሰራዊቱ ‹‹ደረቅ ጦር›› እና ‹‹መደዴ ጦር›› ተብሎ ለሁለት ተከፍሎም ነበር። ደረቅ ጦር የተባለው ሙሉ በሙሉ ውጊያ ላይ የሚያተኩር ሲሆን ‹‹መደዴ ጦር›› የተባለው ደግሞ እንደሁኔታው የእርሻ ሥራ ላይ እንዲሰማራ ይደረጋል። ነገሩ ሲከፋ ግን አርበኞች ፍራፍሬ፣ ቅጠላቅጠልና የዱር አውሬ ሁሉ እየበሉ ተዋግተዋል። እናቶች ከሰራዊቱ ጋር አብሮ በመዝመት ምግብና ውሃ ከማቀበል በተጨማሪ ባህላዊ ህክምና እየሰጡ ሰራዊቱን ታድገዋል። የወደቀውን በማንሳት የቆሰለውን በመጠገን ተሳትፈዋል። ይህ የአርበኞች ቀን የሁሉም ኢትዮጵያዊ የተጋድሎ ድል ነው ማለት ይቻላል።
ኢትዮጵያ በዚህ ሁኔታ ነፃነቷን ማስከበሯ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ከአራቱ ልዕለ ኃያላን ሀገራት (አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ እና ሩሲያ) ጋር ለውይይት እንድትቀመጥ ክብር ሰጥቷታል። የአውሮፓውያን ቅኝ ተገዢ የነበሩ የአፍሪካ ሀገራት ዕጣ ፈንታ ምን ይሁን ተብሎ ሲመከር ኢትዮጵያ ግን የሚመከርባት ሳትሆን አብራ የምትማከር ነበረች። ሀሳቧን እንድታዋጣ የምትጠየቅ ነበረች። የአርበኞች ቀን የወታደርም የዲፕሎማሲም ድል ውጤት ነው!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን እሁድ ግንቦት 3 ቀን 2017 ዓ.ም