ከአፋቸው አንድ ቃል ለማውጣት ሲታገሉ እንባቸው ኮለል ብሎ ይወርዳል። ተረጋግተው ለማውራት ይጀምራሉ። መልሶ ውስጣዊ ሀዘን ያሸንፋቸዋል። የፊታቸው ገጽታ መከፋታቸውን እያሳበቀ ነው። የሚተናነቃቸውን እንባ ለማገድ እየዋጡ ቃላት ከአንደበታቸው ለማውጣት ይሞክራሉ።
ብሶታቸውን ሸሽገው የውስጣቸውን ላለመተንፈስ ከራሳቸው ጠብ ይዘዋል። ቆይቶ ግን እጅ ሰጡ። ስንቱን ልንገርሽ ? በሚል አይነት የሆዳቸውን መዘርገፉን ተያያዙት። ብዙ ርቀት መሄድ አልቻሉም። ልማደኛው እንባቸው እየተንቆረቆረ ገደባቸው። በደቂቃዎች እፎይታ በራሳቸው ዝምታ ተዋጡ። ታገስናቸው። ጥበቃችን ያስጨነቃቸው ይመስላል። አረፍ እንዳሉ ንግግራቸውን ቀጠሉ።
ልጅነቴ ማርናወተቴ የለም
ብርቄ ሙለታ በለምለሙ ተጂ አስጎሪ በቾ በምትባል ስፍራ ቢወለዱም ዕድገታቸው ግን በእናት አባት እጅ አልነበረም። ወላጆቻቸውን ነብስ ሳያውቁ ነበር ያጡዋቸው። ቆይቶም በአሳዳጊዎቻቸው ፈቃድና ይሁንታ እንዲያድጉ ሆነ። ብርቄ ልጅነታቸው እንደእኩዮቻቸው አልሆነም። ለምለሙን መሬት የቦረቁበት ለትንሽ ጊዜ ነበር ።
አሳዳጊዎቻቸው በእናትና አባታትነት ቢቀበሏቸውም ከልጅ እኩል የሚጫወቱበትን እድል አልሰጧቸውም። እናም ልጅነትን እንደፈለጉ ሳያጣጥሙ፣ ሳይቦርቁበት እንዲኖሩት ብቻ ተፈረደባቸው። በወቅቱ ባልጠና ጉልበታቸው ይህንን አድርጊ አይባሉም። ከፍ እስኪሉም ምንም ጎድሎባቸው አያውቅም። አሳዳጊዎቻቸው የምድሩ በረከት የተረፈላቸው ስለነበሩ በግብርናው ሲሳይ ከሚያገኙት ሁሉ ያቋድሷቸዋል።
እነሱ ለልጅ ጣፋጭና ትዝታ ይሆናል ያሉትን ሁሉ ያደርጉላቸው ነበር። ከአንድ ነገር ውጪ። እርሱም አብዝቶ መጫወት ነው። ከልጆች እኩል እንዳም ብዙ ገደቦች ይጣልባቸዋል። የብርቄ ውሎ ብቸኝነት ነበርና የልጅነት ትዝታ የላቸውም። እናትና አባት እንደሌላቸው የሚሰማቸውም በእንዲህ አይነቱ አጋጣሚ ነው። የወላጅን ፍቅር ባሰቡት ልክ አለማግኘታቸው ባይተዋርነት እንዲሰማቸው አድርጓል። ብርቄ ገና ልጅነታቸውን ሳይጠግቡ ባል እንዲያገቡ ሆነ። ትዳር መያዝ ጎጆ መውጣትን አልጠሉትም። አዲሱ ዓለም ህይወታቸውን ከብቸኝነት እንደሚታደግ አምነዋል።
ባለትዳሯ ልጅ
ብርቄ ፍቅርን ከእናት አባት ቢያጡም ከባል አገኛለሁ የሚል ሀሳብ ነበራቸው። ትዳራቸው ጣዕም አልባ እንዳይሆን በጨቅላ አዕምሯቸው ብዙ ለፍተዋል። እንዳሰቡት አልሆነም። ነገሮች ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮደግፍ›› ሆኑባቸው። አባወራቸው መጀመሪያ ላይ ጎንበስቀና እንዳላለ ቆይቶ ‹‹ዓይንሽን ላፈር›› ወደማለቱ ገባ።
ምንክንያቱን በቀላሉ መረዳት አልቻሉም። ከአሳዳጊዎቻቸው ቤት መውጣታቸው አስቆጫቸው። በዚያ ቤት ብዙ ነገሮች ሙሉ ነበሩ። እዚህ ግን የሚጎድለው ይበዛል። በዚያ ላይ የዱላው ነገር።
ለሚሰሩት ተግባር ሁሉ ምክንያት ፈላጊው ባለቤታቸው ወጥቶ በገባ ቁጥር ይደበድባቸዋል። በማያባራ ለቅሶና ሰቀቀን አንገታቸውን ደፍተው ዓመታትን ተቀመጡ። ምርጫ ቢኖራቸው ቤተሰቤ የሚሏቸው ዘንድ ይመለሱ፣ አልያም ሌላ ቦታ ይሄዱ ነበር። ይህን የሚያደርጉበት አቅም ላይ አልነበሩም። አሁን ይሆነኛል ያሉት ጎጆ ገሀነም ሆኖ እንዲኖሩበት ተገደዋል። ጠዋት ማታ በዕንባ ውለው ያደራሉ። ለትዳር ልጅ መሆናቸው ሳያንስ ዱላን ማስተናገዳቸው ውስጣቸውን ሰብሮታል።
ብርቄ በሀሳብ ይናውዛሉ። ምን ዘዴ መቀየስ እንዳለባቸው አልተረዱም። እናት አባቷን በሞት አጥታ በአሳዳጊዋ ግፊት ጎጆ እንድትወጣ የተፈረደባት ልጅ መድረሻ አይኖራትም። ነገሩን አምኖ ከመቀመጥ ውጪ። የዓመታት ዱላውን ታግሰው ጊዜ እስኪያልፍ ሲሉ ቆይተዋል።
የዱላው ብዛት ክፉኛ ጎድቷቸዋል። በታዳጊ እድሜያቸው አላምጠው እየዋጡ አይደለም። የላይኛው ጥርሳቸው በከፊል ረግፏል። ወገባቸውም ቢሆን ጉዳተኛ ነው። እንዲህ መሆኑ ጥረው ግረው ለራሳቸው እንዳይኖሩ ገድቧቸዋል። የዛኔው ብርቱ ዱላ ዛሬን ዋጋ አስከፍሏቸዋል። በስቃይ ከዘለቀ ህመም
ጋር እየኖሩ ነው። ያም ሆኖ ‹‹አምላክ ባይረዳኝ፣ በሕይወት አልወጣም›› ይላሉ የባለቤታቸውን ድርጊትና የደረሰባቸውን ስቃይ ሲያወሱ። ብርቄ የልጅነት ትዳራቸው አልዘለቀም። ስቃዩ ማቄን ጨርቄን ሳይሉ ቀዬአቸውን ለቀው ጠፉ።
ትንሿ ሰራተኛ
በባላቸው ምሬት አዲስ አበባን የተቀላቀሉት ወይዘሮ ከተማዋ እንዳሰቡት አልሆነችላቸውም። የሚያውቁት ሰው የለም፤ የሚያርፉበትም ቤት እንዲሁ። መንከራተትና መሳቀቅ የቀናት ጉዟቸው ሆነ። ደጋግ ሰዎች ግን አላጡም። ‹‹ሳይደግስ አይጣላ›› እንዲሉ ሆኖ የሚጠጉበት ሰው አገኙ። ይህ ደግሞ ያልጠነከረው ጉልበት እንዲበረታ፣ በዱላ የጎበጠው ወገብ እንዲቃና፣ ተስፋና እድል ሰጣቸው። መስራትና መለወጥን ተመኙ።
ብርቄ ወገባቸውን ታጥቀው ለስራ ሮጡ። ከእንግዲህ ማንም እንደሌላቸው አውቀዋልና ራሳቸውን ለመቻል ታገሉ። እናት አባት፣ እህት ወንድም፣ የቅርብ ወዳጅና ዘመድ በሌለበት ያገኙትን ዘመድ የማድረግ ውዴታ ግዴታቸው ሆኖ ጎንበስ ቀናውን ጀመሩት። ከእዚህ በኋላ የራሳቸው ብርታት ራሳቸው ብቻ መሆናቸውን አምነዋል። ቢወድቁ መነሳት፣ ቢረቱ ተስፋ ባለመቁረጥ በርትቶ መቆም እንዳለባቸው ቆርጠዋል። አሁን በጎ አድራጊዋን እናት ተመርኩዘው በእርሳቸው ቤት እያደሩ ኑሯቸውን ቀጥለዋል።
የኑሯቸው መግፊያ አማራጭ የጉልት ላይ ሥራ ሆኖ ቆይቷል። ሽንኩርት፣ ቲማቲምና ጎመን ኑሯቸውን ማጣፈጫና የገቢ ምንጫቸው ሆነውላቸዋል። በወዝ በላባቸው የሚያድሩበትን ሥራ በማግኘታቸውም ወጣትነታቸውን እንዲያስቡት፣ ያለፉበትን እንዳይረሱት ሆነዋል። ይህ በዚህ ከቀጠለ ኑሯቸው እንደሚቀየር፣ ሕይወታቸው እንደሚሻሻል አምነዋል።
ሁለተኛው ቤታቸው ከዚህ የተሻለና በዘመድ የታጠረ ነበር። የቆዩበትን አመስግነው ሲወጡ ብዙ አልተከፉም። አዲሱ ቤት ከአካባቢያቸው የመጣችና ዘመዴ የሚሏት መሪም ቤት ነው። በእሷ ቤት ሳሉ እስከ ስምንተኛ ክፍል ተምረዋል። አንዳቸው ለሌላቸው የሚያሳዩት መተሳሰብ ከልብ የመነጨ ነበር። ከእርሷ ጋር ሲኖሩ ከተለያዩ ሥራዎች ተገኝተዋል። በተለይ በቀላሉ ሰርተው የገቢ ምንጭ ያገኙበት እንጀራና አንባሻ ጋግሮ መሸጥ ዋነኛው ተግባራቸው ነበር። በሚያገኙት ገቢ ሁልጊዜ ደስተኛ ነበሩ። ቤታቸው ሙሉ ሆኖ ለሌላ አስኪተርፉ አትርፈዋል።
ብርቄ ሁሌም የተሻለውን ይዘው ሥራቸውን ማስፋት ያልማሉ። በወቅቱ ደግሞ ውጤታማ ሆነዋል። ይህ ሙከራ ግን እስከ መጨረሻው አልቀጠለም። እናት አባታቸውን የነጠቃቸው ሞት ዛሬም ከበራቸው ደርሶ ጓዳቸውን አንኳኳ። እናት፣ እህትና መካሪ የሆነቻቸውን ደጓን መሪም ወሰደባቸው።
ለእሳቸው ከእርሷ ሌላ ማንም አልነበራቸውም። እህት ነትን ዝምድናን ያወቁባት፤ መተሳሰብን ያዩባት ነበረች። ከእርሷ የቀረበ ዘመድ አያውቁም። ድንገቴው ሞቷ ባዶነታቸው ዳግም መለሰባቸው። ‹‹አለችኝ›› የሚሏትን እስከመጨረሻው ሲለዩዋት ሰማዩ ተደፋባቸው። ውስጣቸው እንዳይሆን ሆኖ ተሰበረ።
ከማንም ጋር ስላልነበሩና ብቻቸውን ስለቀሩ የሚያደርጉት ግራ ገባቸው። ዘመድ አዝማድ በሌለበት ሕይወትን መምራት በእጅጉ ከበዳቸው። በዚህም አዲስ አበባ መኖር አስጠላቸውና ባህር ማዶን ተመኙ፤ ተሳካላቸው።
ኑሮ በአረብ አገር
ጊዜው ውጪ አገር መሄድ ቀን ያወጣል፣ ብር ያሳፍሳል የሚባልበት ነበር። በዚህ ወቅት በተለይ አረብ አገር ሄደው የተመለሱ ጥቂቶች በብዙ መልኩ ተለውጠው ታይተዋል። ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን ለዘመድ አዝማዱም ሲተርፉ ተስተውሏል።
ይህ አይነቱ እውነት ያስቀናቸው የትናንቷ ወጣት ይሻላልን መርጠው ባህር ማዶ ተሻገሩ። አረብ አገርን ‹‹አገሬ›› አሉ። ረጅም ዓመታትን በዚያው አሳለፉ። በዓመታት ቆይታና ልፋታቸው ግን አንድም ጠብ ያደረጉት ጥሪት ሳይኖር ባከነ። የያዙት ወርቅ፣ የቋጠሩት ገንዘብ አልነበረም። የተሰቃዩበትንና ያላቸውን ገንዘብ ጨረሱ። አንድ ቀን ደግሞ ከተለየ ምሬትና ሀዘናቸው ጋር ባዶ ሻንጣቸውን ይዘው አገራቸው ተመለሱ።
በአረብ አገር ህይወት ያላሰቡትን በሽታ ሸምተዋል። ችግርን አይተዋል። በልፋት ብቻ የታጠረ ኑሮን የተስፋ መቁረጥ ቆይታን አሳልፈዋል። አገር የሌለው ሰው ማለት ምን እንደሚመስል አይተዋል። ጥቂት ልረፍት፣ ልተኛ የማይባልበት ቤት መኖርን አይተዋል። ወጥቶ መግባትን፣ በሰላም ውሎ ማደርን፣ በወጉ መተንፈስን ናፍቀዋል። በመጨረሻ ህወታቸውን አትርፈው ‹‹ የአገሬ ሰው ይብላኝ፣ ይግደለኝ›› ብለው ባዶ እጃቸውን ሲገቡ በምስጋና የአገራቸውን መሬት ለመሳም በቅተዋል።
ንፍሮ ነጋዴዋ
አሁን ብርቄ ከአረብ አገር አሰስከፊ ህይወት አምልጠው ለእናት ምድራቸው በቅተዋል። በአገር ቤት አዲስ አየር፣ አዲስ ሰላምና ተስፋ እንዳለ እየተሰማቸው ነው። ምንም ይሆን ሰርተው እንደሚያድሩ ያውቃሉ። እናት ምድራቸውን ሲረግጡ አፈሯን የመሳማቸው ምስጢር ይህ ነበር። በእርግጥ አገርቤት ሲገቡ ሁሉ ነገር ተለውጧል። በአደራ የተሰጠው ቤት ጭምር ከቦታው የለም። የትናንቱ ትናንት ሆኖ አልፏል። የሚያርፉበትን ቤት ጭምር ነጥቀዋቸዋል። ያም ሆኖ አልከፋቸውም። ዛሬ አይዞሽ፣ አለንሽ የሚላቸው የአገር ሰው ጋር ናቸው። የሚያስጠጋ፣ የሚያስጠልላቸው አያጡም።
ደርሶ የሚሰማቸው ህመም ጤና ቢነሳቸውም አንድም ቀን ተኝተውለት አያውቁም። እጅ አይሰጡትም። ከበሽታቸው እየታገሉ ኑሯቸውን ይገፋሉ። ሕመም ቢጠናባቸው እንኳን ደፋ ቀና ማለታቸውን አይተውም። ቢያንስ ጦም አያሳድረኝም ከሚሉት ሥራ ይውላሉ። አንባሻና እንጀራ እየጋገሩ ይሸጣሉ። በሚያገኙት ገንዘብ ለተጠጉበት ቤት ክፍያና ለአንዳንድ ነገሮች ይደጉማሉ።
በሽታው ፋታ ሲሰጣቸው ደግሞ አለፍ ካለ ሥራ ይገኛሉ። በተመላላሽ ሰራተኝነት ልብስ ያጥባሉ፣ እንጀራ ይጋግራሉ፤ ልጆችን ይንከባከባሉ። ፒያሳ አካባቢ ባለ ዳቦ ቤት ይሰራሉ። ለሰባት ዓመታት ሌሊት 11 ሰዓት እየወጡ ሲሰሩ ጎን ለጎን በዳቦ መጋገር ሥራ ሰርተፍኬት ጭምር አግኝተዋል።
ከዚያ ሲያልፉ ደግሞ መሳለሚያ አካባቢ ከሚገኝ ፋርማሲ በጽዳት ሥራ ተሰማርተው አገልግለዋል። ሥራው ግማሽ ቀን በመሆኑ ግማሽ ቀኑን ለሌላ ሥራ ያውሉታል። ትርፍ ቀናቸውን ለተጨማሪ የሰው ቤት ሥራዎች ማዋል ልማዳቸው ሆኖ ዘልቋል። አንዳንዴ ተስፋን የሚያጨልሙ ነገሮች በሕይወት ውስጥ ማጋጠማቸው አይቀርም። በዚህ ታታሪነታቸው መሀል ትልቅ ጋሬጣ ተደነቀረባቸው። ፋርማሲው በመንገድ ግንባታ ምክንያት ፈርሶ ሥራቸው ተቋረጠ። ብርቄ ዕድሜያቸው ቢገፋም መሥራት እንጂ መቀመጥን አያውቁም። መልሰው ለራሳቸው ሥራ ፈጠሩ።
ትኩስ ንፍሮዋቸውን ቀቅለው፣ ጠዋት፣ ማታ ገበያ ይዘው ይወጣሉ። እንዲያ ቢያደርጉም ብርዱና በሽታቸው አልስማማ ብለው አወኳቸው። ውጋት፣ ቁርጥማቱ አላስቀምጥ አላቸው። በስቃይ መሀል ሆነው እንጀራቸውን አከበሩት ሳያቋርጡ በስራው ገፉበት።
ብርቄ ለኑሮና ህይወታቸው የሚደርስላቸው የለም። ጦም ላለማደር በርሀብ ላለሞት አስከመጨረሻው ይታገላሉ። ለጎናቸው ማረፊያ ቤትን አላጡም። ይህ ባይሆን ችግራቸው ልቆ በእስተርጅና የጎዳና ተዳዳሪ ሊሆኑ ይችሉ ነበር። ደግነቱ እነ አቶ በቀለ ጉርማን ጥሎላቸው ሊኖር ከሚችል አሳዛኝ ህይወት ተረፉ።
አዛውንቷ ዛሬ
ወይዘሮ ብርቄ ዛሬ በአዲስ ከተማ ክፍለከተማ ወረዳ አራት 01 ቀበሌ በእነ አቶ በቀለ ቤት ተጠልለው ይኖራሉ። እሳቸው ቤት የገቡት በሰራተኝነት ነበር። ይሁን እንጂ ሁሉም አግብተው በመውጣታቸውና አስጠጊያቸው በመታመማቸው ከቤት ቀሩ። ብርቄ ለዚህ ቤተሰብ የተለየ ቅርበት አላቸው። ልጆቹን አሳድገው፣ ድረው ኩለዋል።
አሁን ማንም እሳቸውን ሊያስወጣ አይሻም። ዛሬን የልጅ ልጆችን እየተንከባከቡ እንዲኖሩ ተፈቅዶላቸዋል። ባለቤቱ በቤት ውስጥ ባይኖሩም ቤታቸውን እንደራሳቸው እንደሚጠብቁ ያውቃሉና ‹‹ኑሪበት፣ እረፊበት›› ብለዋቸዋል።
የቤቱ ባለቤት በጎነት ቢኖርም የእርሳቸው ካጠገባቸው ያለመኖር ብዙ አጉድሎባቸዋል። ቤቱ አሁንም ቤተሰብ የሞላበት በመሆኑ ጦማቸውን አያድሩም፤ ለወጪውና ለዕለት ጉርስም ተጨንቀው አያውቁም። እንደዛሬው አንዳንዴ ግን ነገሮች ድብልቅልቅ ይሉባቸዋል። በቤቱ የቱን ሸፍነው የቱን እንደሚተውት ያስባሉ። የቤት ኪራይ ባይከፍሉም ኑሮ ከዕድሜ ተዳምሮ ህይወት ከብዷቸዋል።
መስራትና ገቢ ማግኘት ግዴታቸው እንደሆነ ቢረዱም የአቅማቸው ማነስ ከበሽታው አላንቀሳቅስ ብሏቸዋል። ዳቦ ቤት በሚሰሩ ጊዜ ወድቀው የተሰበረው እግራቸው ዛሬን እንደልብ አላላውሰ እያላቸው ነው። ከአደጋው በኋላም በእግራቸው ጉዳት ምክንያ ትስራ የሚቀጥራቸው ሳያገኙ ቆይተዋል።
ባሉበት ቤት እንጀራና ዳቦ ቢጋግሩና እንደቀድሞው ቢሸጡ ይመርጣሉ። ይህን ለማድረግ ግን ለመብራት ክፍያው አቅም የላቸውም። ይህ ችግር እንጀራ ጋግረው እንደይበሉ ጭምር ፈተና ሆኗል። በዚህ ምክንያት የእለት ጉርሳቸው በዳቦ ይሸፈናል። እሳቸው ግን አሁንም አርቀው ያስባሉ። የተሻለ ገቢ ካገኙ ዳቦውን ወደ እንጀራ ያሳድጉታል። ይህ የሚሆነው የሚሸጡት ንፍሮ ከቲፑ ተዳምሮ ጥሩ ካገኙ ነው።
አሁን ብርቄ በሴፍትኔት መርሀግብር የቀጥታ ተረጂ ናቸው። በወር 700 ብር ያገኛሉ። ይሁንና በዚህ ገቢ ብቻ ኑሮን መግፋት ከብዷቸዋል። ብርቱዋ ወይዘሮ ደጋግመው ‹‹ለእኔ የሚሆን ሥራ ካላችሁ እባካችሁ ታደጉኝ›› ይላሉ። እኛም በጎ ማድረግ የሻቱ ሁሉ ቀርበው እንባቸውን ያብሱላቸው ዘንድ ታሪካቸውን ወደ እናንተ አድርሰናል።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሐምሌ 23 ቀን 2014 ዓ.ም