ለየት ማለት ስትወድ..
ሁሉ ነገር እሷ ጋ አዲስ ነው..
የቤታቸው ልዩዋ ሴት እሷ ናት።ከጓደኞቿ መሀል ደምቃ የምትታየው እሷ ናት።ለጠየቃት ሁሉ የምትመልሰው ትርፍ መልስ አላት፡፡
ኩራት..ንቀት ያደገችባቸው ናቸው።ትህትና ምን እንደሆነ መልኩን አታውቀውም።ለድሀ የተሳቀ ሳቅ የላትም።ሄዳ..ሄዳ ማረፊያዋ ማን አለብኝነት ላይ ነው።የአባቷ ልጅ ናት።የአባቷ ልጅ ናትም እየተባለች ነው ያደገችው።ሲበዛ ኩራተኛ፣ ሲበዛ ትምክህተኛ ናት።ኩራተኛ ባትሆን ኖሮ ከሰፈር ጓደኞቿ ቀድማ ታገባ ነበር።
ኩራተኛ ባትሆን ኖሮ እሄኔ የአንዱ ባለጸጋ ሚስት ሆና ነበር።እሄኔ ዘበናይ ነበረች።በመንገድ ስትሄድ የማያያት የለም..በረጅም ታኮ ጫማ፣ ሰንደቅ አካሏን ሰቅላ ስትውረገረግ ማንም ያያታል።ረጅም ጸጉሯን ጀርባዋ ላይ እያስጨፈረች፣ ማስቲካዋን ቀጭ እያደረገች ወዳሻት ስትራመድ የሚከጅላት ብዙ ነው።በውብ ሽቶ፣ በድንቅ አለባበስ ከግሪክ ጣኦቶች አንዷን መስላ በጎዳናው ስታገድም ሁሉም ይመኛታል።ኩል ባጌጡ፣ ቀለም በጠጡ አይንና ከንፈር ታጅባ፣ እንደ ግንቦት ጸሀይ በሚፋጅ ውበታማ ገጽ አደባባይ ስትወጣ የማንም አይን ማረፊያ ናት። ግን ኩራተኛ ናት የማንም አይደለችም፡፡
አባቷ በሽምግልና እድሜው ነው የወለዳት።በስልሳ አምስት ዓመቱ። ለሞት በቀረበ ወንድነት ውስጥ እንዲች አይነቷ ቆንጆ ሴት መጸነሷ ለመንደሩ ሰዎች ሁሉ ቡና መጠጫ ሆኖ ነበር።አባቷ በመንደሩ የሚታወቀው በኩራቱ ነው..ሰው ሲንቅ ልክ የለውም።ወንድ ሆነ እንጂ ሴት ቢሆን ኖሮ አርጦ ያለ ልጅ በቀረ ነበር እየተባለ ይታማል።ቁርጥ እሱን የሆነች ልጅ ወልዷል..ርዕግበን እማማ ሸጌ እሷን ሲያዩ ነው መሀንነታቸው ትዝ የሚላቸው።ስንት ዘመን አብሯቸው የኖረ ብቸኝነታቸው እሷን ያየ ቀን ነው ነፍስ የሚዘራው።
ስንቱን የዘመድና የጎረቤት ልጅ አጥብተውና አጥበው እንዳላሳደጉ፣ ስንቱን የመንደሩን ልጅ ኩለውና ድረው ጎጆ እንዳላወጡ ዛሬ በርዕግበ መሀንነታቸው ተሰማቸው።ጎረቤት ናቸው አጥር በሌለው ሁለት የተለያየ ግቢ ውስጥ ነው የሚኖሩት።እንደ ጀምበር ስትወጣና ስትገባ ያዩዋታል።መጥለቂያዋ እሳቸው ገጽ ላይ ነው።ሲያዩዋት ‹ምነው ለአይኔ ማረፊያ አንድ ወልጄ ቢሆን› ሲሉ ይቆጫሉ። ኩራቷ ትዝ ሲላቸው ወዲያው ‹ኤዲያ ይቺን ከመውለድ እንደ እኔ መሀን መሆን ይሻላል› ይላሉ፡፡
ጠዋትና ማታ በአጠገባቸው ስታገድም አንድም ቀን እንዴት አደሩና እንዴት ዋሉ ብላቸው አታውቅም።ከቤቷ ወጥታ ቤቷ ትገባለች።ከማርያም ስም አንዱን ወርሳ ክፉ መሆኗ ያስገርማቸዋል።ርዕግበ ሆና ርዐግበ ተብላ በወርቅ ጫማዋ ለድሀ አለማጠጣቷ ይገርማቸዋል።ከጨዋ እናቷ አንድ ሳትወርስ አባቷን ሆና መፈጠሯ ይሄም ሌላ ትዝብታቸው ነበር፡፡
እማማ ሸጌ የህይወታቸውን ግማሹን ያሳለፉት ከከብቶች ጋር ነው።አዛባ እየዛቁ።ከጥጃ ጋር እየተባረሩ.. እየተናነቁ።በዚህ የህይወት አብራክ ውስጥ ሆነው በተኮላ አይንና ከንፈር ማስቲካዋን እያላመጠች፣ በትልቅ ጫማ ላይ ሰንደቅ አካሏን ይዛ በአጠገባቸው ስታልፍ ሽቶዋ ይሸታቸዋል።ሽቶዋ አጥር ዘሎ በአዛባ ከተወዳጀ አፍንጫቸው ውስጥ ይማገዳል..።ያኔ ቀና ይላሉ..ያኔ ያስተውሏታል። ያኔ ሰበር ሰካዋን ማየት እጣ ፈንታቸው ይሆናል። መሬት የነካ..አፈር የሚልስ የመቀነታቸውን ጫፍ ከአዛባ በጸዳ አውራ ጣትና ሌባ ጣታቸው ታግዘው ወገባቸው ስር እየወሸቁ እስክትታጠፍ ድረስ ቆመው ያስተውሏታል።
‹እንዴት አደሩ እማማ ሸጌ? ብትላቸው የሚመልሱላት ብዙ መልስ ነበራቸው።በዚያ ማለዳ፣ በዚያ ከሰዐት የእሷን የእንዴት አደሩ ድምጽ የናፈቁትን ያክል ምንም ናፍቀው አያውቁም።ግን አትላቸውም..ብላቸውም አታውቅም።ቀና ባሉበት ሀሳብ ይወስዳቸዋል..ከሀሳብ የሚመልሳቸው የከብቶቻቸው እምቡዋ ነው።‹ይቺንስ ከመውለድ..እያሉ እያጎረመረሙ ወደአዛባቸው ይመለሳሉ። ማታ ሲሆን መመለሻዋ በደጃቸው ነው..ጎናቸውን ለመታከክ ምንም ባልቀረው ርምጃ በአጠገባቸው አልፋ ወደ ቤቷ ትገባለች።ያኔም ዝም ነው..‹ይቺንስ ከመውለድ.. ሲሉ እያጎረመረሙ በታዘበ አይን ወደ ቤቷ ይሸኙዋታል፡፡
እማማ ሸጌ ሁሌም አንድ አይነት ናቸው።ላሞቻቸው ጉያ ውስጥ ሆነው፣ ጭኖቻቸው ላይ ማለቢያ አስቀምጠው እያለቡ አሊያም አዛባ እየዛቁ፣ አሊያም ኩበት እያኮበቱ እንደዚህ።ቀና የሚሉት አንዴ ነው..ወይ ጠዋት ወይም ማታ አጥር ዘሎ የገባ የቆንጆ ልጅ ጠረን ከአዛባ መሀል ሲያውዳቸው።በድንቅ ርምጃ የተቃኘ ሰበር ሰካ በጆሯቸው ላይ ሲሞዝቅ እና እየጮኸ የሚላመጥ የማስቲካ ርችት ሲሰማቸው።‹ምነው አንድ እንኳን አይን ማረፊያ ወልጄ ቢሆን..እዲያ ይቺስ ተወለደች ቀረች ምን ልትሰራ?
ከአዛባ የዋለ አፍንጫቸው ጠረኗ እስኪርቀው ድረስ፣ ሰበር ሰካዋ በከብቶች እምቧ እስኪዋጥ ድረስ፣ የማስቲካዋ ጩኸት ተረት እስኪሆን ድረስ ማረመሚያቸው ናት።ተቀይመዋታል..ጡታቸውን እያጠቡ ነበር ያሳደጓት። ከአባቷ ሽሽት መደበቂያዋ የእሳቸው ጉያና ቤት ነበር። እንዴት አደሩ ብላቸው ዘሀር መስኬን ብለዋት አያውቁም፡፡
ርዕግበ..ከተመረቀች ስምንት ወሯ ነው..ዛሬም ድረስ ስራ ፈላጊ ናት።እርግጥ አብዛኞቹ ጓደኞቿ እንደ እሷ ስራ ፈላጊ ቢሆኑም የእሷን ያክል በማጣት የተሰቃየ ግን አልነበረም።እማማ ሸጌን ረግጣ ሄዳ ጥሩ ነገር ያምራታል? እንደ አመዳይ በሸበተ እውነት ላይ ተረማምዳ አርነት መውጣት ያምራታል? ብታውቀው ኖሮ እድሏ ሁሉ የተዘጋው በእኚያ አሮጊት አርምሞ ነበር፡፡
ከሰሞኑ ይቀጥረኛል ብላ ተስፋ ወደጣለችበት አንድ ድርጅት ጠዋት ነው የሄደችው።የትምህርት ማስረጃዋን ታቅፋ..ወደ መዝጋቢው ተጠጋች፡፡
‹ስምሽ ማነው? አላት መዝጋቢው ሽቅብና ቁልቁል እየቀላወጣት፡፡
‹ርዕግበ ይቤላ› ስትል መለሰችለት።ስሟ እኮ ርዕግበ ነው፡፡
‹ይሄ ሁሉ ስምሽ ነው? አልበዛም?
‹ላካፍልህ? በማያስቅ ወሬ ውስጥ ጥርሷ ፈገገ። ብሬሷ ታየ፡፡
መስጠት አትወጂም ማለት ነው› አላት መዝጋቢው። ‹እንዴት? ስትል ጠየቀችው፡፡
‹በሁለት ፊደል የሚጠሩ የስም ችግረኞች ባሉበት አገር ላይ ይሄን ሁሉ ስም ለብቻሽ መያዝሽ ነዋ›
አሳቃት..ማንም እንደዛ አስቋት አያውቅም።የጥርሷ ማብቂያ እስኪታይ ድረስ መንጋጋዋን በረገደችለት። በብሬስ የታሰሩ ጥርሶቿ ተገለጡ።ለነገሩ በሄደችበት ሁሉ እንዳገጠጠች ነው።ለብሬስ ካላት ፍቅር የተነሳ የመውለቂያ ጊዜው አልፏል።ከሳቋ መልስ..
‹ለአንተ በማዋስ ብጀምር ምን ይመስልሀል? አለችው። ‹መልሰሽ የማትወስጂብኝ ከሆነ ደስ ይለኛል..
‹አልወስድብህም..
ለድሀ የሚሆን ሳቅ የላትም..ሳቋ ሁሉ ለባለጸጋ የተሳቀና የሚሳቅ ነው፡፡
ማታ ሲሆን ወደ ቤቷ ተመለሰች…በእማማ ሸጌ አጠገብ ወጥታ ገባች፡፡
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵያ)
አዲስ ዘመን ሐምሌ 22/2022