ከዛሬው እንግዳችን ጋር በከተማዋ ያለውን የኢንተርፕራይዞች ሽግግር፣ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ጉዳይ፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የኑሮ ውድነት፣ መሰረተ ልማት ግንባታ፣ የመታወቂያና በከተማዋ የሚንቀሳቀሱ የውጭ ሀገር ዜጎች ጉዳይ፣ የከተማዋ ሠላምና ፀጥታ፣ የአገልግሎት አሰጣጥ እና ተያያዥ ጉዳዮችን በማንሳት ቆይታ አድርገናል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የሥራ፣ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር ዓባይ ለተነሱት ጥያቄ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
አዲስ ዘመን፡-የከተማ አስተዳደሩ የ2014 ዓ.ም በጀት ዓመት የስራ አፈጻፀም ግምገማ ምን ይመስላል?
አቶ ጃንጥራር፡– 2014 በጀት ዓመት እንደ ከተማ አስተዳደር በሁሉም መስክ በርካታ ስኬታማ ተግባራት ተከናውነዋል። በሠላምና ፀጥታ፤ በትምህርት፣ በመሠረተ ልማት ግንባታ፣ በጽዳት አስዳደር፣ ገቢ አሰባሰብ፤ በሥራ ዕድል ፈጠራና በሌሎች መስኮች ስኬታማ ሥራዎች ተሰርተዋል ። ይህ ማለት ግን ሁሉም ነገር ተሳክቷል ማለት ሳይሆን በመሰረታዊነት የተያዙ እቅዶችን ማሳካት ተችሏል ለማለት ነው። ከህብረተሰቡ ጥያቄ አኳያ የሚቀሩ ነገሮች ግን አሁንም እንዳሉ ታሳቢ ማድረግ ተገቢ ነው።
በበጀት ዓመቱ በጉድለት የተገመገሙ ነገሮች አሉ። በህብረተሰቡ ውስጥ አገልግሎት አሰጣጥ ከፍተኛ ደረጃ ላይ አልደረሰም። የኑሮ ውድነት ላይም የሚነሱ ጥያቄዎች አሉ። በቤት አቅርቦት፣ ትራንስፖርት አኳያ እና ሌሎች ተግባራት ላይ ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅብን ታይቷል። ህብረተሰቡ ይህን ስለሚገነዘብ ትብብር እያደረገ ነው። በርካታ ሥራዎች በጋራ እየሰራን ነው። ይህ አድናቆት የሚቸረው ተግባር ነው። በቤት ዕድሳት፣ በሠላምና ጸጥታ እና በመሳሰሉት ላይ ከህብረተሰቡ ጋር በጋራ እየሰራን ነው።
የትራንስፖርት ችግር በተመለከተ በየቦታው ብዙ ሰልፎች አሉ። ይህን ችግር ለማቃለል ከተማ አስተዳደሩ ተጨማሪ የትራንስፖርት አቅርቦት ለመፍጠር እና ተጨማሪ ተሽከርካሪ ግዥ ለመፈፀም ጥረት እያደረገ ነው። በኪራይ ወደ ሥራ ያስገባቸው ተሽከርካሪዎችም አሉ። እነዚህ ሁሉ ተግባራት ቢከናወኑም የህብተሰቡን ጥያቄ ሙሉ በሙሉ መመለስ አዳጋች ሆኗል።
አገልግሎት አሰጣጥ ላይም ህብረተሰቡ ጥያቄ ያነሳል። አገልግሎት ለማግኘት ገንዘብ እየተጠየቁ መሆኑን ይናገራሉ። ወደታች ወርደን ችግሮችን ለማቃለል ሞክረናል፤ግን አሁንም ፈታኝ ሁኔታዎች አሉ። በመደበኛ ሥራዎች በርካታ ስኬቶች ቢኖሩም ህብረተሰቡ ያልተመለሱለት ጥያቄዎች በመኖራቸው በ2015 በጀት ዓመት እና ከዚያን በኋላ ለሚመጡት ዓመታት ችግሮቹን ለዘለቄታው ለመፍታት ሳይንሳዊ እቅድ እያዘጋጁ መምራት ይጠይቃል።
አዲስ ዘመን፡- የከተማ አስተዳደሩ የትራንስፖርት ችግር ለማቃለል ዘመናዊ አውቶቡሶች ከውጪ ይገዛሉ የሚለው የቆየ መግለጫ ነው። ድጋፍ ሰጪ አውቶቡሶችም በተባለው ልክ መፍትሄ አላመጡም። ችግሩን አውቆ መፍትሄ አለመስጠቱ ቅሬታ አይፈጥርም?
አቶ ጃንጥራር፡– መፍትሄውን በተለያየ መንገድ ማየት ያስፈልጋል። የተሽከርካሪ አቅርቦት ብቻ አይደለም፤ መሠረተ ልማቱ በራሱ የተሳለጠ ነው ? የሚለውን ማየት ያስፈልጋል። ይህ ችግር በአጭር ጊዜ የሚፈታ ጉዳይ አይደለም። በአዲስ አበባ ከተማ ያለው ተሽከርካሪ ብዛት ከሌሎች የአፍሪካ ከተሞች አኳያ ሲታይ ዝቅተኛ ነው። ለህብረተሰቡ እንኳን ብናካፍለው የተሽከርካሪ ቁጥር ዝቅተኛ ነው። ነገር ግን የትራፊክ መጨናነቅ አለ። ምክንያቱ ደግሞ ይህን የሚያፋጥንና የሚሸከም መሰረተ ልማት፣ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የፍሰትና የሞብሊቲ ፕላኒንግ የለም። ይህ ወደፊት መሠራት ያለበት ነው።
ከተማ አስተዳደሩ ትራንስፖርትን በመደገፍ ያደረገው ጥረት አለ። ከተማ አስተዳደሩ የትራንስፖርትን ችግር ለማቃለል የአንበሳ አውቶቡስ፣ የሸገር አውቶቡስ፣ ድጋፍ ሰጪ አውቶቡስ እና ሌሎችን በመደጎም ወደ ሥራ አስገብቷል። ይህ ሁሉ ችግሩን ለመፍታት ነው። ከውጪ ሊገዙ የነበሩ አውቶቡሶች በተለያዩ ምክንያቶች ዘግይተዋል። ቀደም ሲል የብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ‹‹ሜቴክ›› የሚባለው ወይንም በአሁኑ ወቅት ኢትዮ-ኢንጂነሪንግ ተብሎ ከሚጠራው ድርጅት ጋር ተይዞ የነበረው የግዢ ሥርዓት ባልተጠበቀ መንገድ ችግር ውስጥ በመግባቱ ውድቅ ተደርጓል።
በዓለም ባንክ መገዛት የነበረባቸው አውቶቡሶችን ለመግዛትም ጥረት ተደርጓል። የግዢ ሥርዓቱና በባህሪ ብዙ ሂደቶች ስላሉት ዘግይቷል። እነዚህ ተሽከርካሪዎች ተገዝተው ቢገቡ ኖሮ ድጋፍ ሰጪ አውቶቡሶች አንጠቀምም ነበር። ምክንያቱም ለዚህ ከፍተኛ ወጪ እየወጣ ነው።
ተሽከርካሪዎችም ካላቸው ሥምሪት አኳያ የተወሰኑ ክፍተቶች ሊኖሩ ይችላሉ። በአሁኑ ወቅት ግን ድጋፍ ሰጪ አውቶቡሶች በጥብቅ ሥነ-ምግባር እንዲመሩ እየተደረገ ነው። ሌሎች የከተማ አውቶቡሶችም በተመሳሳይ ክትትል ይደረጋል። በከተማው ያለውን የትራንስፖርት ችግር ለህዝብ የሚተው አይደለም። አመራሩም ይህን ለመፍታት ብዙ እየለፋ ነው፤አልተኛም።
አልፎ አልፎ ችግር የሚፈጥሩትንም በመለየት አስፈላጊው ዕርምርጃ ይወሰዳል። የከተማው ትራንስፖርት ቢሮ፣ የሸገር ብሎም አንበሳ የከተማ አውቶቡስ የሚጠበቅባቸውንም እየሰሩ ነው። ትልቁ ችግር በርካታ አማራጮች ቢቀርቡም አሁንም ሙሉ ለሙሉ ችግሩን ማቃለል አልተቻለም። 3000 አውቶብሶችን ይፈልጋል። በአሁኑ ወቅት 1000 ባልሞሉ ተሽከርካሪዎች አገልግሎት እየተሰጠ ነው። ስለዚህ በአንድ ጊዜ የሚፈታ ሳይሆን ሂደት የሚጠይቅ ነው። የከተማ አስተዳደሩም በመሠረታዊነት ለመፍታት እየተንቀሳቀሰ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከአገልግሎት አኳያ የውሃና የውሃ መሰረት ልማት የከተማው ህዝብ ቀዳሚ ጥያቄ ነው። ይህ ጥያቄ አጥጋቢ መልስ የሚያገኘው መቼ ነው?
አቶ ጃንጥራር፡– በመሰረታዊነት በአስተሳሰብም ሆነ በአመለካከት ሊያዝ የሚገባው የከተማ አስተዳደሩ ቅድሚያ የሰጣቸው አንዱ የመሰረተ ልማት ግንባታ ነው። ይህ ማለት ከካፒታል በጀቱ ትልቁን ድርሻ የሚወስዱት ውሃ እና መንገድ ቀዳሚ ናቸው። ይህ የሆነበት የራሱ ምክንያት አለው። በተደጋጋሚ እንደሚገለፀው በቀን 1ነጥብ2 ሚሊዮን ኩዩቢክ ሜትር በላይ ውሃ ከተማው ለፍጆታ ያውላል። እስከ 2012 ዓ.ም ድረስ በቀን ሲቀርብ የነበረው ውሃ በቀን 574ሺ ኩዩብ ሜትር ነበር።
ባለፉት ሁለት ዓመታት በተከናወነው ተግባር ቀደም ሲል ከነበረው ግማሽ ያክል ወይንም ከ200ሺ ሜትር ኪዩብ በላይ ውሃ ወደ ሲስተም ገብቷል። ይህ የሆነው ትልቅ በጀት በመመደቡ፣ ትኩረት እና ቅድሚያ በመሰጠቱ ነው። በርካታ ጉድጓዶች ተቆፍረዋል፤ ወደ አገልግሎትም ለማስገባት ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል። በአሁኑ ወቅት ወደ 794ሺ ሜትር ኩዩብ ውሃ በቀን ለአዲስ አበባ ከተማ ለማቅረብ የሚያስችል አቅም ተፈጥሯል። ይህ ሁሉ የሆነው ከተማ አስተዳደሩ በልዩ ሁኔታ ትልቅ በጀት ለውሃ በመበጀቱ ነው።
ውሃ የማይደርስባቸው ተራራማ አካባቢዎች በተለይም የነበሩ እንደ የካ፣ ጉለሌ እና ፈረንሳይ አካባቢ ያለውን ችግር ለማቃለል የሚያስችልና በቅርቡ የመረቅነው ለገዳዲ ሁለት ባለፉት ሁለት ዓመታት በተያዘለት ጊዜና ወጪ ተጠናቆና ተመርቆ ወደ ሲስተም እንዲገባ ተደርጓል። ባለፈው ዓመትም አቃቂ፣ ቦሌ እና አያት አካባቢዎች አገልግሎት የሚሰጡ የውሃ ልማት ሥራዎች ተከናውነዋል።
ለህብረተሰቡ ግልጽ ማድረግ የሚገባው ለረጅም ዓመታት 574ሺ ሜትር ኪዩብ ውሃን በሁለት ዓመት ውስጥ ከ200ሺ ሜትር ኪዩብ በላይ ውሃ ወደ ሲስተም ገብቶ እንዲሰራጭ ተደርጓል። ነገር ግን ከህብረተሰቡ ቁጥር መጨመር አኳያ ከፍተኛ ሥራ ይጠበቃል። የከተማ እድገቱም በዚያው ልክ ከፍ ብሎ እየመጣ ነው። ይህን ፍላጎት የሚመልስ ሃብት ይፈልጋል። የከተማ አስተዳደሩ አጀንዳ ውሃን ከወረፋ ማስወጣት ነው። ሆኖም አሁንም እጥረቱ መኖሩ አልቀረም።
በቀጣይ ችግሮቹን ለማቃለል ሰፊ ሥራ መሥራት ይጠበቃል። ለዚህም አንዱ የገርቢ ፕሮጀክት ዲዛይን ተደርጎ ወደ ሥራ ለማስገባት ጥረት እየተደረገ ነው። ይህም ሆኖም ትልቅ ሃብት እና ጊዜ ይጠይቃል። ከውሃ ጋር የተያያዘ በባለስልጣኑ በኩል ወረፋ ካለ ማሳወቅ ይገባል። በአንዳንድ አካባቢዎች ግን ውሃ ብክነት አለ። ይህን ለማስቀረት አዲስ አሰራር መተግበር ይገባል። ይህንን ለማድረግ የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የተለያዩ ሥርዓቶችን መተግበር ጀምሯል፤ ይህንም ያስቀጥላል። በአጠቃላይ ከውሃ ችግር ለመላቀቅ ሰፊ ጊዜ እና ሃብት የሚጠይቅ መሆኑ ታውቆ፤ የከተማ አስተዳደሩም የሰጠው ትኩረት ቀላል አለመሆኑን መገንዘብ ይገባል።
የትራንስፖርት ችግር ለማቃለልና የህብረተሰቡን ጥያቄ ለመመለስ የመንገድ መሰረተ ልማት ስራዎች በስፋት እየተከናወኑ ነው። በቢሊዮን ተበጅቶ እየተሠራ ነው። ይህን ሁሉ ለማከናወን የከተማ አስተዳደሩ በራሱ በሚሰበስበው ገቢ የሚከናወን ነው። 98 ከመቶ የሚሆነውን ወጪ በአጠቃላይ ከከተማዋ የሚሰበሰብ ነው። ይህ መልሶ ለከተማዋ ልማት ሥራ ነው የሚውለው። ከፌደራል መንግስትና ከውጭ ብድር የሚገኘው ብዙ አይደለም።
በቤት ልማት፣ ውሃ፣ ትራንስፖርት ድጎማ፣ መሰረተ ልማቶች ጋር የተያያዘው ትልቅ ሃብት ተበጅቶ እየተሰራ ነው። ከፑሽኪን ዓደባባይ እስከ ጎተራ፣ ከቦሌ ወደ ጎሮ፣ የኮተቤ መንገድ፤ የአቃቂ መንገድ፤ የእንጦጦ መንገድ ትልቅ ሃብት ተመድቦ እየተከናወኑ ነው። ውስጥ ለውስጥም በርካታ መንገዶችን ገንብተናል፤ ጠግነናል። ባለፉት ሁለት ዓመታት ተጀምረው የነበሩ በርካታ የመንገድ እና ውሃ መሠረተ ልማቶች በጣም ስኬታማ በሆነ መንገድ የተጠናቀቁ ናቸው፤ ከፍተኛ ሃብትም የተመደበለት ነው። ይሁንና አሁንም ቢሆን የልማት ፍላጎቶችና ጥያቄዎች አሉ፤ በመሆኑም ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል።
አዲስ ዘመን፡- በመንገድ ግንባታ ስኬታማ ሥራዎች ቢኖሩም ለዓመታት የተጓተቱና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ምንጭ የሆኑበት ምክንያት ምንድን ነው?
አቶ ጃንጥራር፡– በአንዳንድ ፕሮጀክቶች መዘግየት ምክንያት ሕብረተሰቡ የሚያነሳው ትክክል ነው። ነገር ግን ምክንያቶቹን ማወቅ ተገቢ ነው። ለምሳሌ የኮተቤን መንገድ ብንወስደው ይዞት የነበረው ሥራ ተቋራጭ በሀገሪቱ ውስጥ በነበረው ነባራዊ ሁኔታ አቋርጦ ጥሎ የጠፋ በመሆኑ እንደገና ውሉን አቋጦ ወደሥራ ማስገባት ይጠይቅ ነበር። ይህም በለውጥ ሂደት ካጋጠሙ ችግሮች እንደ አንድ የሚወሰድ ነው። ‹‹አድቫንስ›› ገንዘብ ወስደው አቋርጠው የቀሩና ፕሮጀክቶችን ያጓቱ ተቋራጮች ነበሩ።
በለውጡ ምክንያት አድራሻቸውን ለማግኘት ያስቸገሩ አሉ። በዚህም ረጅም ጊዜ የወሰዱ አሉ። የኮተቤው መንገድም ብዙ ሂደቶች አልፈው ወደ መንግስት ገብቶ ለማጠናቀቅ እየተሞከረ ነው። ከዚህም በተጨማሪ የወሰን ማስከበርና ሌሎች ችግሮችም ነበሩ። በዚህ ዓመት መጠናቀቅ አለበት ተብሎ እየተከናወነ ነው፤ ሥራውን ለማጠናቀቅም ርብርብር እየተደረገ ነው።
ሌላኛው የአቃቂ-ቱሉ ዲምቱ-ያለው መንገድ በህብረተሰቡ ዘንድ ቅሬታ ፈጥሯል፤ አይካድም። መንገዱ ሲጀመር ከቻይናው ኢግዚም ባንክ በብድር ነበር። ይህን ችግር ለመፍታት ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር ብዙ ውይይት ተደርጓል። ባንኩ ገንዘቡን ባለመልቀቁ ማጠናቀቅ አልተቻለም። ውል ሲገባ ደግሞ በውጭ ገንዘብና በሀገር ውስጥ ገንዘብ ስለነበርና ይህ ባለመቻሉ መንግስት ከራሱ ሃብት መድቦ የህብረተሰቡን ጥያቄ ለመመለስ እየሠራ ነው። መሰል ፈተናዎች ያጋጥማሉ። መሰል የብድር ውሎች ብዙ ውጣ ውረዶች ያሉበት መሆኑን ማወቅ ይገባል። ነገር ግን ባለፉት ሁለት ዓመታት ኮንትራት ሰጥተናቸው የቆሙ የሉም። ምናልባት የዘገዩ ሊኖሩ ይችላሉ።
አዲስ ዘመን፡- ባለስልጣንን ተገን በማድረግ በከተማዋ የመሬት ወረራ እየተበራከተ ስለመሆኑ ህብረተሰቡ ቅሬታ እየሰማ ነው። በከተማ ዙሪያም በተመሳሳይ ቅሬታ አለ። ከተማ አስተዳደሩ ምን እየሠራ ነው?
አቶ ጃንጥራር፡– በመጀመሪያ መታወቅ ያለበት ጉዳይ መሬት እንዴት ይሰጣል፤ ለማን ይሰጣል ለሚለው አሠራር አለ። ይህ የሚመራው ግልጽ በሆነ ህግ ነው። መሬት በጨረታ ወይንም በምድባ ነው የሚሰጠው። በምደባ ሊሰጥ የሚችለው ለከተማ ከንቲባ ቀርቦ ተገቢነቱ ሲታመንበት በከንቲባ ኮሚቴ ተወስኖ ነው። ከዚህ ውጭ ለሥራ ዕድል ፈጠራ የሚሰጠው የመሬት ልማትና ማናጅመንት ቢሮ ከሚመለከተው ተቋም በሊዝ አስረክቦ በተለይም ለከተማ ግብርና የታሰቡና ለመሳሰሉት ጉዳዮች ቦታዎች ይሰጣሉ። ይህም በጊዜያዊ ሊዝ ምደባ ይሰጣሉ። ለመንግስት ተቋማት ግንባታ ተመሳሳይ በመሬት ልማት ማናጅመንት ‹‹ፕሮሰስ ካውንስል›› የከንቲባ ከንቲባ ውክልና ሲሰጥ ሊታይ ይችላል።
ከዚህ ውጭ ህገ-ወጥነት የባለስልጣን ሥም በመጥራት ወይንም በሌላ መንገድ የሚደረግ ሙከራ ሊኖር ይችላል። ነገር ግን እኔ እስከሚገባኝ ድረስ በየአካባቢው ያለው አመራርና አስተዳደር ግንባታ ሲከናወን ሙሉ ኃላፊነት አለበት። ይህ ከሆነም ባለስልጣን ታዝዤ ነው በሚል ያለሰነድ የሚስያተናግድ አመራር ለእኔ አመራር አይደለም። በአሰራሩም አይፈቀድም። የተፈቀደልትን ሰነድ ወይንም ደብዳቤ ሳይዝ መስተናገድ የለበትም።
በባለስልጣን ሥም ብዙ ወንጀሎች ሊሰሩ ይችላሉ። ነገር ግን ባለስልጣኑ በምን ህግ ነው የሚያዘው፣ በምን ለምን ያዛል የሚለውን መጠየቅ ይገባል። ማንም ብድግ ብሎ ማዘዝ አይችልም። እንኳንስ አሁን በፊውዳሉ ዘመንም የራሱ አመራር አለው። ውሳኔያችን የጋራ ውሳኔ ተደርጎ ይተገበራል። ሳይፈቀድ የሚታጠር መሬት ካለ በአካባቢው ያለ አመራር፣ ደንብ አስከባሪ እና የፀጥታ መዋቅር ምን ይሠራል?
ይሄ የጉልበተኛ ሀገር አይደለም። የምንተዳደረው በህግ ነው። እኔ እስከማውቀው ድረስ እንደ ከተማ አስተዳደር የወሰንናቸው መሬቶች አሉ። እነዚህም በአሰራር መሰረት በካቢኔ የተወሰኑ ናቸው። እነዚህ የተፈቀደላቸው አካላት በዝርዝር ይታወቃሉ። ከዚህ ውጭ የተስተናገዱ ካሉ በህግ መጠየቅ ይገባል። ከዚህ ውጭ ህገ-ወጥ ግንባታዎች በተገኙ ጊዜ ፈርሰዋልም፤ ይፈርሳሉም። በየአካባቢ ያለው መሬት ሲታጠር በቅርበት ያለው አስተዳደር ማወቅ አለበት። ከዚህ ወጭ ከሆኑ ጉልበተኝነት ነው። ከዚህ በተረፈ አመራር ፈቅዶ ነው የሚል አሉባልታ ተቀባይነት የለውም። የከተማ አስተዳደሩ ግልጽ አቅጣጫ አስቀምጧል። ህገ ወጥነትን ቀድመን መከላከል ከዚህ አልፎም የተገኘ በህግ መጠየቅና እርምጃ መውሰድ ይገባል።
ህገ-ወጥነትን የሚያስተናግድ ሥነ-ምህዳር የለም። በአመራር ሥም የሚነግድ ወንጀለኛ ነው። ለክፍለ ከተማ አመራሮች እርምጃ ወስዳችሁ አስተካክሉ ብለን አመራር ሰጥተናል። ይህን ያላስፈፀመ የክፍለ ከተማ አመራር ተጠያቂ ነው፤ ወረዳም ተጠያቂ ነው። ህገ ወጥነትን የማይከላከል አመራር፤አመራር አይደለም። ህገ-ወጥነትን የማይከላከል ክፍለ ከተማ እንጠይቃለን።
የአርሶ አደር ይዞታም ቢሆን ተመዝግቦ አርሶ አደር መሆኑ ታውቆ እንዴት እንደሚስተናገድ ዝርዝር መመሪያ አለ። ከዚህ ውጭ ወደ መሬት ባንክ ያልገባውንም ሆነ የገባውን የመቀራመት ሁኔታ ካለ ይጠየቃል። መሬት አጥሮ ስለተቀመጠ ሊቀጥል አይችልም። በተደረሰበት ጊዜ እርምጃ ይወሰደል። በአጠቃላይ ከህግ ውጭ የሚሆን ነገር መኖር የለበትም። ሁሉም ነገር በህግ፣ ደንብና መመሪያ የሚመራና የሚፈፀም ነው።
አዲስ ዘመን፡- ኮንደሚኒየም ቤቶች ያለ ዕጣ ለካቢኔዎች እና ዕጣ ላልወጣላቸው እየታደለ ነው የሚለውን ቅሬታ ህብረተሰቡ ያቀርባል። እርስዎ ምን ይላሉ?
አቶ ጃንጥራር፡- አመራርን በተመለከተ በየደረጃው ያለው አመራር ቤት ያስፈልገዋል። ለምን የሚለውን በደንብ ማጤን ይገባል። የቤት አበል የሚሰጣቸው የተወሰኑ አመራሮች ናቸው። መታወቅ ያለበት ህዝብን የሚመራ አመራር ደህንነቱ የተጠበቀ፣ መሰረታዊ ፍላጎቱ የተሟላ መሆን አለበት። ይህም የራሱ ሥነ-ምግባርና ደህንነት አኳያ ጠቀሜታው የጎላ ነው። ቢያንስ መጠለያ ያስፈልገዋል። እዚህ ሀገር የኢኮኖሚ እጥረት ስላለ እንጂ አንድ አመራር ቤት አግኝቶ ህዝብ ቢመራ ይህን ያክል አጀንዳ መሆን አልነበረበትም።
ችግሩ አቅርቦቱ ዝቅተኛ በመሆኑና ህዝቡ ከፍተኛ ፍላጎት ስላለው እንጂ በዚህ ደረጃ አይነሳም ነበር። ተከራይ ሆኖ ለመኖር ደግሞ ገቢው ዝቅተኛ ነው። በየመድረኩ አመራሩ የሚያነሳው ነገር ቢኖር የቤት ጉዳይ ነው። ይህ ችግር እስካሁን አልተፈታም። እንደከተማ የተወሰኑ ሰዎችን አስተናግደናል። ነገር ግን እነዚህ አመራሮች ከሚሰጡት አገልግሎትና ደህንነት አኳያ ሲታይ ምንም ማለት አይደለም። ይህ ማለት ግን ህብረተሰቡን ገንዘብ መንጠቅ አለበት ማለት አይደለም። የሕብረተሰቡ ጥያቄም ረጅም ጊዜ ቆጥበን አላገኘንም ከሚለው እንጂ አመራሩ ቤት አይኑረው ከሚለው የመነጨ አይደለም። ከችግሩ ጎን ለጎን በፍትሃዊነት መመለስ ይገባል።
የቤት ጥያቄ ከማስተናገድ አኳያ በጋራ መኖሪያ ቤታችን ዕጣ የራሱ አሰራር አለው። ለአካል ጉዳተኞች፣ ሴቶችና መንግስት ሰራተኞች እያለ ይገለፃል። ከጋራ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ 30 ከመቶ ለመንግስት ሠራተኛ ነው። አመራሩም ደግሞ የመንግስት ሠራተኛ ነው። የአመራር የቤት ችግር በከፍተኛ ሁኔታ በሚሰቃይበት እንዴት ይመራል የሚለው ለእኛ ራስ ምታት ሆኖብናል። ስለዚህ የኪራይ ቤት የምናቀርብበት፤ የቆጠበው ደግሞ በአሰራሩ የሚስተናገድበት አሰራር እየሄድንበት ነው። ባለፉት ሁለት ዓመታት በጎላ መልኩ ለሁሉም አመራር ቤት አልሰጠንም። የተወሰኑ አመራሮች ተስተናገደው ይሆናል። አሁንም ጥያቄዎች አሉ፤ይህን መመለስ አለብን ብለን እየሰራን ነው።
አዲስ ዘመን፡- አመራር ሆኖ የቤት ኪራይ ገንዘብ የሚሰጠው፤ የቀበሌ ቤትና የግል ቤት ያለው አለ። ከዚህም በተጨማሪ የመንግስት የኪራይ ቤትም ይዞ ይኖራሉ ሲል ህብረተሰቡ ቅሬታ ያቀርባል። እርስዎ ምን ይላሉ?
አቶ ጃንጥራር፡– ኮንደሚኒየም ቤት ዕጣ ደርሶት የቀበሌ ቤት የያዘ፤ ሌላ ቤት እያለው ተጨማሪ የሚይዘው የመረጃ ሥርዓታችን ችግር የወለደው ነው። ይህ መስተካከል አለበት ብዬ ነው የማምነው። አንድ ግለሰብ በአንዱ ብቻ ነው መጠቀም ያለበት። ይህ ከሆነ የሙስና ሥርዓት ነው። ግለሰቦችም ከማጭበርበር ራሳቸውን ማቀብ አለባቸው።
አሁን የሚደረጉ ጥናቶች ብሄራዊ መታወቂያ ካርድ ጨምሮ ሥርዓት ካልያዘ አስቸጋሪ ነው። ክፍለ ሀገር ሆነው አዲስ አበባ የጋራ መኖሪያ ቤት ዕጣ ተጠቃሚ የሆኑ አሉ። ሌላ ክልል እየኖረ አዲስ አበባ ቤት የተመዘገበና የተጠቀመ አለ። ይህ መስተካከል አለበት። ነገር ግን በአንድ ዓመት ውስጥ የሚከናወን አይደለም። መረጃዎች እየጠሩና የቤት ምዝገባ ስርዓቱ እየተስተካከለ ሲሄዱ ሁሉም ይስተካከላሉ።
አዲስ ዘመን፡- ከጥቂት ዓመታት በፊት እርስዎ የሥራና ከተማ ልማት ሚኒስትር ነበሩ። በአሁኑ ወቅትም እንደ ከተማ አስተዳደር የሚያውቁት ጉዳይ ነው። የቤት ጉዳይ ለምን መፍትሄ አጣ?
አቶ ጃንጥራር፡- ጥያቄዎችን አንድ በአንድ ማየት ተገቢ ነው። ሚኒስቴሩን እየመራሁ በነበረ ጊዜ ተጀምረው የተቀበልናቸው ቤቶች አሉ። በሰዓቱም ከነበሩት ከንቲባ ጋር ያጠናቀቅናቸው አሉ። ነገር ግን መጀመሪያ ሲሰጡ ብዙ ጉድለቶች ነበሩ። የቤቶች ልማት ሥራና ጥናት እኛ ሥራ ስንጀምር የተጀመሩ ሳይሆኑ ቀደም ብለው የተጀመሩ ናቸው። የዛሬውን አመራር መውቀስ ተገቢ አይደለም። አራብሳ ኮንደሚኒየም ሲገነባ ያለውን ነገር ብናይ የሚወገደውን ቆሻሻ ማከሚያ ፕሮጀክት አልነበረውም። ይህ ትልቅ ኢንቨስትመንት የሚጠይቅ ነው። በወቅቱ ስንመጣ ባንክ ቤቶቹ ላይ ያለው ገንዘብ ባለመመለሱ ገንዘብ ለማስፈቀድ ከፍተኛ ችግር ነበር። የሚፈቀደውም የገንዘብ ብድር ቤቶችን ለማጠናቀቅ በቂ አልነበረም። ከጊዜ ወደ ጊዜ እየወረደ አምስት ቢሊዮን ብር በታች ነበር የሚፈቀደው።
በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ ቤቶችም 54 ቢሊዮን ብር በላይ ዕዳ አለበት። በወቅቱ ሲሚንቶ፣ ብረትና ሌሎች ግብዓቶች እንዴት ይገዙ እንደነበር ሲታሰብ በጣም ውስብስብ ታሪኮች ያሉበት ነው። ይህን መመርመር ያለበት አካል መመርመር አለበት። ሚኒስቴሩን እየመራሁ ሆነ አዲስ አበባ ከተማ እያለሁ ያንን ውስብስብ ችግር ለመፍታት ነው ጥረት የተደረገው። ከዚያም በኋላ ትንሽ ብር ሲፈቀድ የተጀመሩት ይጠናቀቅ ብለን ነው የገባነው። አዲስ ቤት ለመጀመር የተጀመሩት ተጠናቀውና ተሸጠው ከዚያ የሚገኘው ገንዘብ ወደ ባንክ ተመልሶና ባንክ ብድር መፍቀድ አለበት።
በቤቶቹ አካባቢ ያለውን በሚገባ ስንመለከት ብዙ ቦታ ላይ የተጀመረው መሰረተ ልማት እንዴት ይከናወናል፤ ውስጥ ለውስጥ ላንድ ስኬፕ ምን ይሁን፣ የቆሻሻ አወጋገድና የማጣሪያ ሥርዓቱ የት ይገነባል፣ በምን ያክል ካፒታል ይገነባል የሚሉት ቀሪ ሥራዎች ሰፊ ነበሩ። ያንን ለመፍታት ባለፉት ዓመታት ሚኒስቴሩን እየመራሁ ለመፍታት በጋራ ሙከራዎች ተደርገዋል። በዚህም ችግር ውስጥ በርካታ ቤቶችን ለማጠናቀቅ ተችሏል። የመጣንበት መንገድ በአንድ ጊዜ ግን ከፍተኛ ገንዘብ አግኝቶ ቤቶቹን ማጠናቀቅ አልተቻለም።
ቤት ለመገንባት ሃብት መኖር አለበት። ለዚህ ደግሞ የባንክ ዕዳ መዘጋት አለበት። በመሆኑም ታሪኩን ከኋላ መረዳት ይገባል። ይህ አሁን ያለው የአመራር ድክመት የወለደው ችግር አይደለም። ሆኖም እኛ ያለፈውን እየወቀስን መሄድ አንችልም። የተጀመሩትን ነገሮች ለማጠናከር እየሰራን ነው። ችግሮቹን በአንድ ጊዜ መፍታት ባንችል እንኳን በየዓመቱ እየቃለልን ነው። የቀሩትን ቤቶች አጠናቀን ሌሎች አዳዲስ ቤቶችን ለመገንባት ጥረት እየተደረገ ነው። ብዙ የውጭ ኩባንያዎችንም ለማነጋገር ጥረት ተደርጓል። አንዳንዶቹ የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ምክንያት በማድረግ ከመጡ በኋላ ተመልሰው የሄዱ አሉ። ሌሎች ምክንያቶችን ፈጥረው የሄዱ አሉ። ባለፈው ደግሞ የሀገሪቱን የፀጥታ ሁኔታ እንደትልቅ ጉዳይ ቆጥረው ጥለው ሄደዋል። እኛ ግን ጥረት እያደረግን ነው።
አዲስ ዘመን፡- የአዲስ አበባን የመኖሪያ ቤት ችግር ባለሃብቶች ሳይሳተፉ መንግስት ብቻውን መፍታት ይችላል?
አቶ ጃንጥራር፡– በቤት ግንባታ ለመሳተፍ ሐሳቡም ፍላጎቱም ያለው አልተከለከለም፤ ዕድሉንም ሰጥተናል። በዚያው ልክ ደግሞ ገበያን የምንቆጣጠርበት መንገድ መኖር አለበት። አንዳንድ ጊዜ መንግስት በቤት ግንባታ ላይ ጣልቃ ገባ ተብሎ ይወቀሳል። በሌላ በኩል ባለሃብቱ ዋጋውን ሰቀለ ተብሎም ይወቀሳል። በርካታ ሪል ስቴት አልሚዎች አሉ፤ በዚያው ልክ ገዥ አለ። ግን የዋጋ ጣሪያ እናዳናስቀምጥ የምንከተለው የፖለቲካ ኢኮኖሚ ሥርዓት አይፈቅድም። ስለዚህ በአስተሳሰብ ደረጃ መያዝ ያለበት የቤት አቅርቦት እንዲበራከት አማራጮችን ማስቀመጥና መሥራት እንጂ ዋጋ በመቁረጥ አይሆንም። መንግስትም ብዙ አማራጮችን አስቀምጧል።
አዲስ ዘመን፡- የኑሮ ውድነቱ መላውን ህዝብ እየተፈታተነ ነው ለችግሩ መፍትሄ ለማፈላለግ ከተማ አስተዳደሩ ምን እየሠራ ነው?
አቶ ጃንጥራር፡– የኑሮ ውድነቱ ሀገር አቀፋዊ እና ዓለም አቀፋዊ ገፅታ አለው። አዲስ አበባ የዚህ ተጋላጭ ናት። እንደ ከተማ ችግሩን ለመፍታት ብዙ ጥረት እየተደረገ ነው። ከዚህም ውስጥ አቅርቦቱን ለማሳለጥ የሚያስችል ስርዓት መፍጠር በሚል እየሰራን ነው። የግብርና ምርት አቅርቦት ማህበራት እንዲያቀርቡና ራሳቸውን ሪፎርም እንዲያደርጉ በካቢኔ ውሳኔ 1ነጥብ4 ቢሊዮን ብር ድጎማ አድርገናል። ከለውጡ ጀምሮ በተለይም በ2013 እና 2014 ዓ.ም ችግሩን ለማቃለል ጥረት ተደርጓል።
ሌላው በኑሮ ውድነቱ የተፈጠረውን ጫና ለማቃለል በየትምህርት ቤቱ ከ600ሺ በላይ ተማሪዎች ምገባ ሥርዓት ዘርግተናል። የምገባ ማዕከላትንም እያሰፋን ነው። ከሸገር ዳቦ ፋብሪካ በተጨማሪም በሌሎች አካባቢዎች አነስተኛ የዳቦ መጋገሪያዎችን እንዲኖሩ እየሰራን ነው። ፋብሪካዎች ትንሽ የዘገዩ ቢሆንም ወደ ሥራ እየገቡ ናቸው።
የገበያ ንረት ለማምጣት የሚጥሩትን አካላት በግብረ ኃይል እየተቆጣጠርን ነው። ሆኖም ችግሩን ሙሉ ለሙሉ አልተቀረፈም። ችግሩ ዋጋ አንዴ አስቀምጦ በዚያው ማስቀጠል ይታያል። በሀገሪቷ ዋጋ አንዴ ከጨመረ አይወርድም። በጣም የሚገርም ባህሪ ነው ያለው። ትርፍ ምርት ተመርቶ የሚቀንስ አይደለም። ማህበራትም ብዙ ትርፍ ሳያተርፉ ለተጠቃሚዎች እንዲያቀርቡ እያደረግን ነው። ማህበራት ከዩኒዮኖች ነው የሚገዙት። ነገር ግን እኛ አንድ ደረጃ አልፈን ከመሰረታዊ ማህበራት ለመግዛት ተሞክሯል። ይህ ሁሉ የሚደረገው የከተማዋን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት ነው።
የኑሮ ውድነት የጥቅል ውጤት ነው። ለምሳሌ እኛ የቤት ኪራይ ላይ ገደብ ጥለናል። የቤት ኪራይ፣ ትራንስፖርት ውድ ነው። ችግሩን ለማቃለል የኢንዱስትሪ ምርት አቅርቦትን ማሳደግ፣ ቤት አቅርቦት ማስፋት ይገባል። በሁሉም መስክ ምርት ማምረት ይገባል። በግብዓት እጥረት፣ በኃይል አቅርቦት፣ በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምርት የሚያቆሙ ኢንዱስትሪዎች አሉ።
በቅርብ ጊዜ አዲስ አበባ ያሉ ኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ለማወቅ ጥናት አድርገናል። በአማካይ የማምረት አቅማቸው 53 ከመቶ ላይ ናቸው። ይህም የሆነው በግብዓት እጥረት፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረትና በመሳሰሉት የተከሰተ ነው። የከተማ አስተዳደሩ ችግሮቹን ስለሚገነዘብና ጉዳዩ ስለሚያሳስበው በተቻለ አቅም ሁሉ እየሠራ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች የኑሮ ውድነት መፍትሄ ካልተበጀለት የከፋ ሁኔታ ያመጣል የሚል ምክረ ሃሳብ ይሰጣሉ። ይህ ከተማ አስተዳደሩን ያሳስበዋል?
አቶ ጃንጥራር፡- እኔ የባለሙያዎቹን ሐሳብ መቃወም አልችልም፤ የራሳቸው ጥናት ሊኖራቸው ይችላል። በግሌ የምረዳው ግን እነርሱ ባሉት ልክ ይሆናል ብዬ አልገምትም። ምክንያቱም በእኛ ሀገር አሁን ባለው ሁኔታ የኑሮ ውድነቱን ለመቀነስ የሚያስችል ዕድል አለን። ዕድሉ ደግሞ በግብርና ምርት በስፋት ከተንቀሳቀስን አብዛኛውን ችግር እንፈታለን። ማዳበሪያም ከሆነ ወደ ሀገር ውስጥ አስገብተናል። ስንዴ፤የጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ ምርት በሰፊ ማምረት እንችላለን። የሚጠይቀው ቁርጠኝነትና ተጨማሪ ጉልበት ነው። ከዚህ በተረፈ የአመጋገብ ሥርዓታችን ላይ የባህል ለውጥ ማምጣት ይገባል።
ዘይት እና ስንዴ የሚመጣው ከሩሲያ እና ዩክሬን ስለሚመጣ የተወሰነ ጫና ሊኖረው ይችላል። ነገር ግን ሀገር ውስጥ ያለው የግብርና እንቅስቃሴ ይህን ችግር ይፈታል፤ ይቻላልም። በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባ ከተማ ወይንም በሌሎች ከተሞች ውስጥ ውድ ቢሆንም በቆሎ እና አትክልት በስፋት ይገኛል። የአጠቃቀም ሥርዓታችን እንጀራ በወጥ ብቻ እንደምግብ ስለሚታይ እንደጫና ሊቆጠር ይችላል።
ይህ ለኑሮ ውድነቱ ጫና ይኖረዋል እንጂ ወደሌላ ብጥብጥ የሚወስድና ተስፋ የሚያሳጣ ነገር አለ ብዬ አልገምትም፤ ሊኖርም አይችልም። አቅሙ አለን ብዬ አምናለሁ። አሁን ባለው ነበራዊ ሁኔታ የውጪው ጫና እንደተጠበቀ ሆኖ ዋጋ ላይ ንረት ሊፈጥር ይችላል እንጂ ሌላ ችግር ይወልዳል ብሎ ማሰብ አይቻልም። የእኛ አብዛኛው ፍጆታችን ከግንባታ እና አልባሳት ውጭ ያለው የምግብ ፍጆታችን እዚህ ሀገር ውስጥ በምናመርተው መተካት ይቻላል፤ ዕድሉም አለን። የባህል ለውጥ ማምጣትና ዕድሉን መጠቀም ከተቻለ ሌላ ቀውስ ያመጣል የሚል ዕምነት የለኝም።
አዲስ ዘመን፡- የከተማዋ የሥራ ዕድል ፈጠራ ሌላኛው የዜጎች ጥያቄ መሆኑ ይታወቃል። ችግሩን ለማቃለል የከተማ አስተዳደሩ በበጀት ዓመቱ ምን ሰርቷል?
አቶ ጃንጥራር፡- በበጀት ዓመቱ ይዘን የነበረው ዕቅድ 350ሺ ዜጎች የሥራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው ታስቦ ነበር። ይህም በግሉ ዘርፍ፤ በመንግስት ተቋማት በቅጥር እና በመሳሰሉት ውስጥ እንዲሳተፉ ነው። ይሁንና በበጀት ዓመቱ 405ሺ536 ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል። ይህም ከእቅድ ባይ ስኬታማ ነው። ይህ ማለት ግን 405ሺ ዜጎች ሼድ ሰጥተናል፤ መሥሪያ ቦታ ሰጥተናል ማለት አይደለም። ከዚህ ውስጥ በቅጥር የተገኘ የሥራ ዕድል አለ።
በራሳቸው ኢንተርፕራይዝ የመሰረቱ፤ በንግድና አገልግሎት የተሰማሩ፣ በፋብሪካዎች የተቀጠሩና የመሳሰሉትን ያቀፈ ነው። ከእነዚህም መካከል 65ሺ107 የሚሆኑት ዜጎች የዩኒቨርሲቲ እና ኮሌጅ ምሩቃን ናቸው። በእነዚህ የሥራ ዕድል ፈጠራዎች ሰዎች ተለጣፊ ሱቆችን ታሳቢ ሊያደርግ ይችላል። እኛ ይህን አሠራርን ወደ ሌላ እየቀየርነው ነው። ከዚህ የመውጣት ሂደት ነው። የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ እያደገ ሲሄድ አነስተኛውን ደመወዝ እየወሰንን እንሄዳለን እንጂ ወደፊትም ቢሆን ተቀጣሪ መኖሩ አይቀርም። ኢንርፕራይዝ ሆኖ ኢኮኖሚውን መደገፉ እንዳለ ሆኖ ችሎታው ያላቸው ዜጎች ኢንዱስትሪ ላይ እንዲገባ ይፈለጋል። በዚህም መሠረት የተገኙ የሥራ ስምሪቶች መሆናቸውንም ታሳቢ ማድረግ ያስፈልጋል።
ይህን ሁሉ ስናደርግ ሼዶችን በሚመለከት ቢሯችን ሁለት ነገሮችን ወስኖ እየሠራ ነው። አንደኛው እኛ የሥራ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ የሚያስተዳድራቸው ከአምስት ዓመት በላይ የሆኑ ኢንተርፕራይዞች የያዙትን ሼድ እንዲለቁ ውሳኔ አሳልፈናል፤ እየተገበርነው ነው። ስንቶቹ ለቀዋል የሚለው አሁን የምንፈትሸው ይሆናል። እስከ ሰኔ 30 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ የሦስት ወር ማስጠንቀቂያ ሰጥተናቸው እንዲለቁ ውሳኔ የተላለፈባቸውም አሉ።
ስድስት ወር እንዲሁም ለአንድ ዓመት ማስጠንቀቂያ ሰጥተናቸው እንዲለቁ የተደረጉ አሉ። ሌሎች ደግሞ እንደየባህሪያቸው የሚቀጥሉ ይሆናል። አምራች ሆነው ብዙ ሰው አቅፈው የያዙና ውጤታማ የሆኑ ሌላ ተጨማሪ ሽግግር እስካላደረግንላቸው ድረስ የሚቆዩ ይሆናሉ። ምክንያቱም 200 እና 300 ሰዎችን የሚይዝ ኢንተርፕራይዝ ካልተሸጋገሩ እነዚህን ሰዎች መበተን አይቻልም። እነዚህን ነገሮች በዝርዝር ጥናት አድርገን ወስነናል። ከ4000 በላይ የሚሆኑና አምስት ዓመት እና ከዚያ በላይ የሞላቸው ኢንተርፕራይዞች ዝርዝር ጥናት አድርገን ውሳኔ አሳልፈናል። በዚህ ምክንያት አላተረፍንም፣ ውጤታማ አልሆንንም በሚል ቅሬታ የሚያቀርቡ አሉ።
አዲስ ዘመን፡- በ4000 ኢንተርፕራይዞች ላይ የተላለፈው ውሳኔ ምንድን ነው?
አቶ ጃንጥራር፡- አንደኛው የሚሸጋገሩ እና የሚለቁ አሉ። ይህ ጥሪት ማፍሪያ እና ወደ ሌላ የሚሸጋገሩበት እንጂ መንግስት እየሠራና እያቀረበ ሊቀጥሉ አይደለም። የሆነ ቦታ የሚሰጠው ከአምስት ዓመት በኋላ ወደ ሌላ ምዕራፍ በመሸጋገር እንዲሰሩ ወይንም ወደ ግሉ ገብተው ራሳቸውን እንዲችሉ እንጂ አምስት ዓመት ሲጠናቀቅ የግድ ሌላ ቦታ መሰጠት አለበት የሚል ህግ እና አሰራር የለም። ሽግግሩ በአምስት ዓመት ማዕቀፍ ውስጥ የሚከናወን ነው። አምስት ዓመት ሲሞላው መንግስት መሬት እያቀረበ አይሄድም፤ሊደረግም አይችልም። በእነዚህ ዓመታት ጥሪት ለማፍራትና ወደ ሌላ ለመሸጋገር የሚሆን ጊዜ ነው። በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ አሳልፈን እየተተገበረ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ካለው የሥራ ፈላጊና የኢንተርፕራይዞች ቦታ ይሰጥን ጥያቄ አኳያ ለኢተርፕራይዞች ሽግግር አምስት ዓመት የሚለው አዲስ መመሪያ ያስፈልገው ይሆን?
አቶ ጃንጥራር፡– አምስት ዓመት የሚለው ስትራቴጂክ ዕቅዱ ላይ የተቀመጠው ነው እንጂ ዝም ብሎ የመጣ አይደለም። አዲስ መመሪያ ብናወጣም አንድ ዓመት መጨመር ወይንም መቀነስ አይደለም ዓብይ ጉዳይ የሚሆነው። 10 ዓመትም ቆይተው ያልተሸጋገሩ አሉ። አምስት ዓመት አንድ የስትራቴጂክ ጊዜ ነው። ለሁሉም ነገር ምክንያትና አመክንዮ ያስፈልጋል። ወደ ሥራ ሲገቡም ከአምስት ዓመት በኋላ የት እንደሚደርሱ ከሚያቀርቡት ቢዝነስ ፕላን መረዳት ይቻላል። በዚህ ውስጥ በጣም ውጤታማ ሆነው ለሥራ የተጉ አሉ።
ሌሎች ደግሞ የተሰጣቸውን አከራይተው የጠፉ እና ኢ-መደበኛ ሥራ የሚሰሩ ይኖራሉ። አምስት ዓመቱ ለሁሉም ገዥ ነው። አንድ ኢንተርፕራይዝ በዚህ መሠረት ካልሰራ ይወጣል። ይህ የሚደረገው ደግሞ የማዘን እና አለማዘን አይደለም። ሌሎች ወጣቶች የመስሪያ ቦታ ስጡን ብለው ይጠይቃሉ። ብዙ ዳቦ ፈላጊ አለ። ስለዚህ ይህን ለማጣጣም በህጉ መሰረት መሥራት አለብን። ይህ ሲደረግ ቀደም ሲል የነበረው የመገናኛ ብዙሃን ወቀሳ አምስት ዓመት የሞላቸው ለምን አይለቁም የሚል ነው።
በሌላ ጎኑ ደግሞ አምስት ዓመት የሞላቸውን ስናስወጣ ዕድሜውን፤ ምርት ዓመቱን ብታዩ ይሉናል። ይህ ወቀሳ መንግስት ለመምራትም ግራ ይሆንበታል። በመሆኑም መሰል ውሳኔዎች የሚወሰኑት በዝርዝር ጥናት እንጂ በግብታዊነት አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- የከተማ አስተዳደሩ የጀመረው የትምህርት ቤት ምገባ እና የሴፍትኔት መርሐ ግብር ይቋረጥ ይሆን የሚል ስጋት አለ። ከተማ አስዳደሩ ምን ይላል?
አቶ ጃንጥራር፡– አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጀመረው የትምህርት ቤት ምገባ ሞዴል ሆኖ ወደ ሌሎች ክልሎች እየሰፋ ነው ፤አይቆምም። በዚህ መንገድ ሕብረተሰቡ ስጋት ውስጥ ሊገባ አይገባም። የከተማ አስተዳደሩ የፈለገውን ያክል ጫና ቢደርስበትም ለእናቶች፣ ህፃናት የደረሰን ፕሮጀክት አይቋረጥም። ከዘለቄታዊነት አኳያ እነዚህ ዜጎች አዕምሯቸው የበለፀገ እንዲሆን፣ እውነትም ብልጽግና ለሚያስብ ዜጋ ትልቅ ተስፋ ያለው ነው። ምክንያቱም ባልተመገበ እና በቀነጨረ አዕምሮ የሚቀበሉት ትምህርት በዚያው ልክ የቀነጨረ ነው። ይህ ሳይንሳዊ ነው። በመሆኑም የከተማ አስተዳደሩ የትምህርት ቤት ምገባ መርሐ-ግብርን አያቆምም፤ ስጋትም እንዲገባቸው አንፈልግም።
ሌላው በ2009 ዓ.ም የጀመረው የከተማ ሴፍትኔት መርሐ-ግብር መስከረም 30 የመጀመሪው ምዕራፍ ይዘጋል። ሁለተኛው ምዕራፍ ይቀጥላል፤ በ2014 ዓ.ም የጀመርነውም ቀጥሏል። ይህ ማለት በየዙሩ ይመረቃሉ። በአሁኑ ሦስተኛ ዙር ተመራቂዎች አሉ። በአሁኑ ወቅት 109ሺ የሚሆኑ ዜጎችን በ‹‹ፐብሊክ ወርክ›› እያሳተፍን ነው፤ ይህም ይቀጥላል። የሚመረቁት ግን ወደ ዘላቂ ልማት መሸጋገር አለባቸው። ወደ ዘላቂ ልማት ሲሸጋገሩ የመስሪያ ቦታ ያስፈልጋቸዋል። ለዚያም የሚሆን አበረታች ሥራ አከናውነናል።
ተጨማሪ ሼዶችን ገንብተን እነዚህ ዜጎች ተጠቃሚ የሚሆኑበትን እቅድ ይዘን እየሰራን ነው። በመሆኑም ይህ መርሐ-ግብር የሚቆም አይደለም። በዚህ መርሐ- ግብር ብዙ ሥራ አከናውነናል። ለአብነት በዚህ በጀት ዓመት ብቻ 125 ትምህርት ቤቶች ሴፍቲ ታንኮችን ግንባታ እየተጠናቀቅን ነው። ከዚህም በተጨማሪ 19 ሼዶችን ለመገንባትና በጀቱን በአግባቡ ሥራ ላይ ለማዋል የሚያስችል ሥራ እየተከናወነ ነው። በመሆኑም የተማሪዎችን ምገባ፣ የሴፍትኔት መርሐ-ግብሩን እና ወደ ዘላቂ ልማት የሚገቡትን ዜጎች ሥራ አጣጥመን እየሰራን ነው፤ይህም ተጠናክሮ የሚቀጥል ነው።
አዲስ ዘመን፡- በዚህ ዓመት የከተማ አስተዳደሩ ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› የሚል እንቅስቃሴም ሲያደርግ ነበር። ይህ ለአምራች ኢንዱስትሪው ምን አስገኘ?
አቶ ጃንጥራር፡- ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› የሚለው ንቅናቄ የሥራ የኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት የተሠራ ሲሆን ጥሩ ውጤት ማየት ተችሏል። በዚህ ንቅናቄ ከ3ሺ300 በላይ ኢንዱስትሪዎችን ጎብኝተናል። ይህን ጉብኝት ስናደርግ ከ6000 በላይ ችግሮችን አግኝተናል። ከእነዚህ ውስጥ 4000 በላይ የሚሆኑ ችግሮችን መፍትሄ አበጅተናል። ቀሪዎቹ 2000 ችግሮች ደግሞ ገና ያልተፈቱ አሉ። ለችግሮቹ ባለቤቱ ማነው ብለን ለይተናል።
ለምሳሌ የማስፋፊያ መሬት፣ የውጭ ምንዛሪ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት፣ ኤል.ሲ፣ ግብዓት አቅርቦት፣ የፋይናንስ አቅርቦት፣ የማሽን አቅርቦትና ሌሎች ጥያቄዎች የሚያቀርቡ አሉ። የትኛው ማንን ይመለከታል ለሚለው ደግሞ ለይተን ለተቋማት አሳውቀናል። ልማት ባንክ፣ ብሄራዊ ባንክ እና የከተማ መሬት አስተዳደር የሚፈቱትን ልከናል። በእኛ እጅ ያለው የውሃ፣ መንገድ እና የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ደግሞ ለመፍታት ጥረት አድርገናል።
ይህ ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› የሚለው ንቅናቄ የአንድ ዓመት ሳይሆን የአስር ዓመት እቅድ በመሆኑ ይቀጥላል። የምርታማነትን ምጣኔ 80 ከመቶ ለማድረስ ታቅዷል። እኛ ስንጀምር የምርታማነት ምጣኔ ከ53 እስከ 54 ከመቶ ነበር የተባለው። ይህን ቁጥር የሚቃወሙ እና የአዲስ አበባ 42 ከመቶ ነው የሚሉ አሉ። እኛ 53 ከመቶ እንዲደርስ ልኬታ ወስደናል። 1ሺ600 ኢንዱስትሪዎችን ልኬታ አድርገን የማምረት አቅማቸው 53 ከመቶ ደርሰ ዋል።
ይህ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትና መሰል ችግሮች በመፈታታቸው የተገኘ ነው። ከዚህ በዘለለ ክህሎት ያለው ባለሙያ ማቅረብና የመሳሰሉትን መጠየቃቸው ስለማይቀር በቀጣይ የምንፈታቸው ይሆናሉ።
ዋናው የኢንዱስትሪዎችን ችግር ቀረብ ብሎ ማገዝ፣ መደገፍና መፍታት ነው። 10ሺ የሚደርሱ አምራች ኢንዱስትሪዎች አሉን። ከእነዚህም ከፍተኛ፣ መካከለኛ፣ አነስተኛ እና ማይክሮዎች ይታወቃሉ። አብዛኞቹ ማይክሮ ናቸው፤ ከፍተኛዎቹ ጥቂት ናቸው። ዘግተው የጠፉ አሉ። እነዚህም መፈታት አለባቸው።
ከግላቸው ከመነጨ ችግር ካልሆነ በስተቀር በመንግስት በኩል ያለው ችግር እየተፈታ ነው። ከከተማ አስተዳደሩ በላይ የሆኑ ችግሮችን ደግሞ ወደ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እና በፌደራል መንግስት የሚፈታ ነው። ለምሳሌ የገበያ ማፈላለግ፣ ኤል.ሲ የማግኘት ጉዳይ፣ ትልቅ የኃይል አቅርቦት የሚጠይቁ እና የመሳሰሉ ጥያቄዎች ያሏቸው አሉ። የእነዚህን ዳታ በአግባቡ መዝግበን ይዘናል።
አዲስ ዘመን፡- የሌላ ሀገር ስደተኞች ሆነው ሳለ መታወቂያ ያላቸውና በአዲስ አበባ ንግድ ቤትም ጭምር ከፍተው በኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ አሉ። ይህ አግባብ ነው?
አቶ ጃንጥራር፡- የውጭ ስደተኞች መታወቂያ አላቸው የሚለው በትክክል መጥራት አለበት፤ እንደዚህ እየተደረገ ስለመሆኑ መረጃ የለኝም። እንዴት ተፈቀደ የሚለውንም ማወቅ አለብኝ። በህገ ወጥ መንገድ የተሰጠ ከሆነም እርምጃ መውሰድ አለበት።
አዲስ ዘመን፡- መልካም አስተዳደር ከማስፈንና የህብረተሰቡን ቅሬታ ለመፍታትስ ቁርጠኝነቱ እስከምን ድረስ ነው?
አቶ ጃንጥራር፡– የመልካም አስተዳደር ጉዳይን በተመለከተ፤ ይህን ከመፍታት በስተቀር ከተማ አስተዳደሩ ሌላ አጀንዳ የለንም። የመልካም አስተዳደር ጥያቄን በልማት እና በምንሰጠው አገልግሎት ነው የምንመልሰው። ይህን ካላሳካን የትኛውንም ልማት ብናለማ በህዝብ ውስጥ ተቀባይነት አናገኝም። በህዝብ ውስጥ ተቀባይነት የሌለው መንግስት ደግሞ የፖለቲካ ልዕልና ካጣ መንግስት አይደለም።
ፎቶ ግራፍ ሰቅለን ወይንም በሚዲያ ታይተን የምንመራው ሳይሆን ህዝብ ተጨባጭ ነገር ካላገኘ ይጥላል። እኛ ኮንትራታችን የአምስት ዓመት ነው። አንድ ዓመት አጠናቀን የቀረን አራት ዓመት ነው። ያንን እያሰብን ነው የምንሠራው። መልካም አስተዳደር ችግር ከመንግስት የሚጠበቀውን አለማድረግ ነው። እኔን ጨምሮ በቢሮዬ ይህን የማንፈታ ከሆነ አግባብ አይደለም። ከሃብት እጥረት በስተቀር በንዝህላልነት እና በቆራጥነት ማነስና በአመራር ሥነ-ምግባር ጉድለት የማንፈታው ችግር መኖር የለበትም የሚል ተግባቦት አለ። ለምሳሌ በቤት አቅርቦት ብናይ፤ 600ሺ ተመዝጋቢዎች ባሉበት ቤት በወቅቱ ይሰጠን ብሎ መጠየቅ ከመብት አኳያ አግባብ ነው፤ ነገር ግን ከመንግስት አቅም አኳያ ደግሞ አስቸጋሪ ነው። ከመልካም አስተዳደር አኳያ የሚሸጋገሩ ችግሮች ይኖራሉ ለማለት ነው። የኑሮ ውድነቱን ጥያቄ ለመመለስ በተመሳሳይ ሁኔታ ምርታማነትን በብዙ እጥፍ በመጨመር የሚመለስ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ሥም አመሰግናለሁ። የሚጨምሩት ሐሳብ አለ?
አቶ ጃንጥራር፡– እኔም አመሰግናለሁ። እንደከተማ አስተዳደር ሆነ እኔም እንደምክትል ከንቲባ በምንሰራቸው ሥራዎች ሁሉ አቅማችን ህዝባችን ነው። ህዝቡ ችግሩን፣ብሶቱን፣ መከራውንም ጦርነቱንም ተቋቁሞ ከመንግስት ጎን በመሆን የልማት ሥራዎቹን እያከናወነ ነው፤ በ2015 በጀት ዓመትም ይህ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። አሁንም ያልተፈቱ ችግሮች አሉ። በተሟላ ድጋፍና ትዕግስት ችግሮችን ይፈታሉ። አመራሩ ላይ የጎደሉትን ማንሳትና መገሠፅ አግባብ ነው። የቀረው አብሮ በመስራት ህብረተሰቡ ድጋፉን እንዲያጠናክር እንጠይቃለን።
ለሥራችን ትልቅ አቅም ነው። በክረምት የሚታደሱ ቤቶች ህዝብና ባለሃብቱ ድጋፍ እያደረገ ነው። ለአብነት በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ እኔ በቅርበት የምከታተለው 350 በላይ ቤቶች እየተጠገኑ ነው። በዚህ ብዙ እናቶችን መታደግ እየተቻለ ነው። ይህ በሁሉም ክፍለ ከተሞች አለ። ሰው ተኮር ፕሮጀክቶችን ማሳካት ላይ ህብረተሰቡ ድጋፉን ማጠናከር አለበት። ሌላው የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የችግሮች ማባባሻ መንገዶች ላይ ማተኮር የለባቸውም ብዬ አምናለሁ። ጥፋት ይሸፈን ማለቴም አይደለም። ነገር ግን ልማትን የሚያሳንስ መሆን የለበትም። ሁሉንም ሚዛናዊ በሆነ መንገድ መሥራት አለበት ብዬ አምናለሁ። ይህ መልዕክት ለአንተም ጭምር ነው።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ሐምሌ 21/2014