ትናንት በተጠናቀቀውና በአሜሪካ ኦሪገን ባለፉት አስራ አንድ ቀናት ሲካሄድ በቆየው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በድል ላይ ድል ደርበዋል። አሜሪካንን ተከትለውም ከአለም ሁለተኛ ሆነው ያጠናቀቁበትን 4 የወርቅ፣4 የብርና 2 የነሐስ ሜዳሊያ አስመዝግበዋል። በዚህም የኢትዮጵያ ስም በአትሌቲክሱ መንደር ገናና ሆኗል። ሰንደቅአላማዋም ከፍ ብሎ ተውለብልቧል። ሕዝብም ተደስቷል። ስለሩጫ ስናነሳ ፈር ቀዳጁ አበበ ቢቂላ ነው። አበበ በሮም የመጀመሪያ ድሉን ቀጥሎም በቶኪዮ ኦሊምፒክ ሁለተኛ የማራቶን ክብሩን ተቀዳጅቷል። አበበ ሁለተኛውን ድል ሲያስመዘግብ በወቅቱ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ድሉን ሮይተርስን ጠቅሶ ያስነበበውን ዘገባ አካተናል። ከአደጋ ከወንጀልና ከልማት ነክ ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ዘገባዎችም አሉን።
አበበ ቢቂላ ለሁለተኛ ጊዜ አሸናፊ ሆነ
ቅልጥሞቹ እንደ ብረት የሚጠነክሩት ኢትዮጵያዊው አበበ ቢቂላ በቶኪዮ የማራቶን ውድድር ከሚደረግበት ሥፍራ አንስቶ እስከ መጨረሻው ድረስ ይታይበት የነበረው ፈገግታ ፍጹም አልተለወጠም ነበር ሲል ሮይተርስ አስረድቷል። የአበበ አሸናፊነት በዓለም መዝገብ ውስጥ እስከ ዘላለም የሚኖር ቋሚ ትዝታ አትርፏል። አበበን በየመንገዱ ከ፪ ሚሊዮን ፭፻ሺህ ሕዝብ በላይ ተሰልፎ የጋለ ስሜቱን ይገልጥለት ነበር።
በ፲፰ ኛው የኦሎምፒክ የማራቶን ውድድር፤ አበበ ቢቂላ ለሁለተኛ ጊዜ በማሸነፍ የወርቅ ሜዳሊያ አግኝቷል። አበበ ቢቂላ እስከ ዛሬ ድረስ ተደርጎ የማይታወቅ የማራቶን ውጤት ከማስገኘቱም በላይ፤ አንድ ሰው ሁለት ጊዜ በመድገም የማራቶን አሸናፊ የሆነ እስካሁን ድረስ በዓለም እንደሌለ ሮይተርስ ባስተላለፈው ወሬ ገልጧል።
አበበ የቶኪዮውን ማራቶን ሩጫ ያሸነፈው፤ በ2ሰዓት ከ12 ደቂቃ ከ11.2 ሰከንድ ሲሆን፤ በሚሮጥበት ጊዜ ተወዳዳሪ የሆኑት ፸፱ ሯጮች በሙሉ ሩጫው ከተጀመረበት አንስቶ እስከ ፍፃሜው ድረስ በመምራት ሁለተኛ የሆነውንና ፩ ሺህ ሜትር ያህል ቀድሞት ገብቷል። አበበ ግዴታውን ማለት ፵፪ ኪሎ ሜትር ከ፩፻፺፬ ሜትሩን ጨርሶ አላረፈም። መቼ ሥራ ፈታና ሰውነቱን በማፍታታት ልዩ ልዩ ዓይነት ጅምናስቲክ በመሥራት ጓደኞቹን ሲጠብቅ ነበር።
የማራቶን ውድድር ለመመልከት ከ፹ሺህ ሕዝብ በላይ ተገኝቶ አበበን በማድነቅ በደመቀና በጣም በሚያስተጋባ ጭብጨባ ደስታውን በመግለጥ የሚሠራውን ጅምናስቲክ ተመልክቷል።
አበበ ቢቂላ ከሮም አሸናፊነቱ በኋላ ወደ ልዩ ልዩ አገሮች ተጋብዞ በመሄድ እየሮጠ አሸናፊነቱን በሚገባ አስመስክሯል።በግብዣ የሮጠባቸው አገሮች ቼኮስላቫኪያ፤ አሜሪካ፤ ዑጋንዳ፤ ስፔን፤ ጃፓንና የቀሩትም አገሮች ናቸው።
የሃምሳ አለቃ አበበ ቢቂላ የቶኪዮን ማራቶን ከማሸነፉ ፴፭ ቀን በፊት (መስከረም 6 ቀን 1957) በትርፍ አንጀት ምክንያት በሀገሪቱ ሆስፒታል ኦፕራሲዮን ተደርጎለት ነበር።
(ጥቅምት 12 ቀን 1957 የታተመው አዲስ ዘመን )
በከሰል ጭስ ሁለት ሴቶች ሞቱ
በዚህ ሰሞን ሁለት ሴቶች በአዲስ አበባ ባቡር ጣቢያ አካባቢ በከሰል ጢስ ምክንያት የሞት አደጋ ደርሶባቸዋል።
እንዲሁም ሌላ ፫ኛ ሴት የዚሁ አደጋ ደርሶባት ወደ ዳግማዊ ምኒሊክ ሆስፒታል ከገባች በኋላ፤ የህክምና ዕርዳታ ተደርጎላት ለመዳን ችላለች።እነዚሁ ፫ ሴቶች በግርድና ተቀጥረው ይሠሩ እንደነበረና የሚኖሩትም ቀጣሪያቸው በሰጡዋቸው ጠባብ የግንብ ቤት ውስጥ መሆኑ ተገልጧል። ከሞቱት ውስጥ አንደኛዋ በቤት ውስጥ ሞታ ስትገኝ፤ ሁለተኛዋ ግን ወደ ዳግማዊ ምኒሊክ ሆስፒታል ስትደርስ በሕክምና ለመረዳት ከሚቻልበት ደረጃ ያለፈች ስለነበር ሞታለች።
(መስከረም 8 ቀን 1957 የታተመው አዲስ ዘመን)
የገንዘብ ቁጠባ ማኅበር ፶ ቤቶች ሠርቶ ያስረክባል
የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት የመኖሪያ ቤትና የገንዘብ ቁጠባ ማኅበር በዚህ ዓመት ከ፵ እስከ ፶ የሚደርሱ መኖሪያ ቤቶች በ1,000,000 ብር ሠርቶ ለሕዝብ እንደሚያስረክብ የማኅበሩ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ጌታቸው ተሰማ በሰጡት ወሬ ለመረዳት ተችሏል።
ማኅበሩ 600,000 ብር ተቀማጭ ሲኖረው ባለፈው ፶፮ ዓ.ም ፳፭ ቤቶች አስጀምሮ ዘጠኙን ጨርሶ ሲሰጥ፤ ለማሠሪያው 500,000 ብር ወጪ ማድረጉ ተገልጧል። እንዲሁም ባለፉት ሦስት ወራት ፩፻፳፯ ሰዎች 200,000 ብር በመክፈል የማኅበሩ አባል ሆነዋል።በጠቅላላው የማኅበሩ አባሎች ፱፻፳፯ መድረሳቸውን ወሬው አስረድቷል።
በጥንቱ ኤሮፕላን ማረፊያ በነበረው 100,000 ስኩየር ሜትር ቦታ ላይ ለልዩ ልዩ ቤተሰቦች መኖሪያ ቤቶች እንዲሠሩ ፕላን መውጣቱ ታውቋል።
ማኅበሩ ከላይ የተጠቀሰውን አንድ ሚሊየን ብር የሚያገኘው ባለፈው ዓመት በ500,000 ብር ካሠራቸው ቤቶች ከሚያስገባው ወለድና የብድር ተመላሽ ሲሆን ቀሪውን 100,000 ብር አበድሮ ወለዱን በመቀበል ነው ሲል በተጨማሪ አስገንዝቧል።
(መስከረም 12 ቀን 1957 የታተመው አዲስ ዘመን)
ያልተመረመሩ ከብቶች ያረዱ በ6 ወር እስራት ተቀጡ
አዲስ አበባ፤(ኢ-ዜ-አ-) አቶ ሰይድ ዋቅቶሌ የተባሉ የአዲስ አበባ ከተማ ኗሪ በመጋዘናቸው ውስጥ ሽታው የአካባቢውን ሕዝብ ጤና የሚያውክ ርጥብና ደረቅ ቆዳ ከማጠራቀም አልፈው፤ ጤንነቱ ያልተመረመረ ከብት በዚሁ ግቢ ከሕግ ውጪ እየደጋገሙ በማረዳቸው በስድስት ወር እስራት እንዲቀጡ የተፈረደባቸው መሆኑን ከአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት የተገኘው ዜና ገለጠ።
አቶ ሰይድ ዋቅ ቶሌ በአካባቢው ኗሪና እንዲሁም በጠቅላላው ሕዝብ ጤንነት ላይ ጠንቅ የሚያስከትሉን ድርጊቶች የፈጸሙት አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ፭ ጊዜ መሆኑንና በዚህም ከ፳ ብር እስከ ፩፻፶ ብር ተቀጥተው እንደነበረ ዜናው ገልጧል።
አቶ ሰይድ ዋቅቶሌ ፍርድ ቤት ቀርበው የሰጡት መከራከሪያ ማስረጃ “በገዛ ርስቴ ላይ ፤የፈለግሁትን ብሠራ አልከለከልም” የሚል ብቻ እንደነበርና ፍርድ ቤቱም በገዛ ርስት ላይ ተቀምጦ ሕዝብን የሚጎዳ ሥራ መሥራት በሕግ የሚያስጠይቅ ሥራ መሆኑን ገልጦ በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ቁጥር ፰ና-፯፻፳፬ በተከሳሹ ላይ የ፮ ወር እስራት መፍረዱን የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት የማስታወቂያ ክፍል ገልጧል።
አቶ ሰይድ ዋቅ ቶሌ የእስራት ጊዜያቸውን እንደጨረሱ የቆዳ መጋዘናቸውን የሕዝብ መኖሪያ ከሆነው አካባቢ አንስተው ለኢንዱስትሪ በተመደበው ቀበሌ ካላዛወሩ በቀር ባሉበት ቦታ ላይ እንዳይገለገሉበት ፍርድ ቤቱ በተጨማሪ ጥብቅ ትዕዛዝ መስጠቱ ታውቋል።
(ሐምሌ 3 ቀን 19 62 ከወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ)
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 18/2014