በኢትዮጵያ የአገልግሎት አሰጣጥ ዘርፉን ለማዘመን የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት ግንባታዎች በመንግስትና በግል ተቋማት ጭምር የማካሄዱ ስራ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠጨመረ መጥቷል። እነዚህ አማራጮች አንድን ጉዳይ ለማስፈጸም ይወስድ የነበረውን ጊዜን በከፍተኛ ሁኔታ በማሳጠር፣ አላስፈላጊ የገንዘብ ወጪን በማስቀረት እንዲሁም ጉልበትን እየቀነሱ ተገልጋዩን ከእንግልት እየታደጉት ይገኛሉ።
ከሁሉም በላይ በዲጂታል አማራጭ የሚሰጡ የመንግስት አገልግሎቶች ጥራትን እንዲሁም የቁጥጥር ስርዓቱን ማቀላጠፍ እየቻሉም ናቸው። ዜጎች ዘመናዊ ኑሮን ለመምራት የሚያስችል ንቃተ ህሊና እንዲኖራቸውና ወደ እዚህ ስርዓት መግባት እንዲችሉ መንገድ ጠራጊ እንደሆኑም ይታሰባል።
ለእዚህም በፋይናንስ ቴክኖሎጂው (ፋይንቴክ) ረገድ በባንኮች የተጀመሩ ዲጅታል የክፍያ አማራጮችን ጥሩ ማሳያ አድርጎ መውሰድ ይቻላል። በሞባይል ባንኪንግ መተግበሪያ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ በግል ባንኮችና በኢትዮ ቴሌኮም አማካኝነት የሚቀርቡ የፋይናንስ መተግበሪያዎች ረጅም ሰልፎችን ከማስቀረታቸውም በላይ ጊዜንና ከዚያ ጋር ተያይዞ የሚደርስ ብክነትን እና እንግልትን ያስቀሩ እንደሆነ ይታመናል።
የአገልግሎት ዘርፉን በቴክኖሎጂ የሚደግፉ ሌሎች ዲጂታል አማራጮችም እንዲሁ የዚሁ አካል ናቸው። ከሁሉም በላይ ግን ኢትዮጵያ እያደረገች ያለችውን ዲጂታል ሽግግር የሚደግፍ ቀዳሚ ዲጂታል መሰረተ ልማት ስለመሆናቸው የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ይመሰክሩላቸዋል። የዝግጅት ክፍላችን በዛሬው የሳይንስና ቴክኖሎጂ አምዱ ላይም ከላይ ከጠቀስናቸው የዲጂታል ስርዓቶች ውስጥ የሚካተት አንድ መረጃ ይዞላችሁ ቀርቧል።
እንደሚታወቀው በገበያ ስርዓት ውስጥ “ደረሰኝ” የሽያጭ አማራጭ እንደሆነ ይታወቃል። መንግስትም ሆነ ዜጎች በዚህ ማስተማመኛ የገንዘብ ልውውጥ በማድረግ ህጋዊ አካሄድን የተከተለ ግብይት ይፈፅማሉ። ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ውስጥ የደረሰኝ ጥቅም “በማንዋል” አሊያም በወረቀት ሽያጭ የሚካሄድ ነው። ይህም ማለት በካሽ ሬጅስተር (በወረቀት ሽያጭ) አሊያም ደግሞ በእጅ የሚቆረጥ ደረሰኝን የሚያካትት ነው።
ይህ አካሄድ ደግሞ ግብይት ለሚያደርገው ተጠቃሚ ምቹ አይደለም። ለመንግስትም ይህን ስርዓት ተከትሎ የሚፈለገውን ቁጥጥር ለማድረግ የሚያስችል አጋጣሚን የሚፈጥር አይደለም። በዚህ ምክንያት ዲጂታል ደረሰኝ አሊያም ኤሌክትሮኒክ ደረሰኝን የመጠቀም አማራጭ አሁን አሁን አስፈላጊ እየሆነ መጥቷል።
ብሩክ ገብረየስ የተቀናጀ የደራሽ ፕላትፎርም ዲቪዥን ዳይሬክተር ነው። ከዚህ ቀደም “በደራሽ” ፕላትፎርም ላይ ማብራሪያ ሰጥተውናል፤ አሁን ደግሞ በኤሌክትሮኒክስ ደረሰኝ አስፈላጊነትና በኢትዮጵያ ውስጥ በምን መንገድ ተግባራዊ ለማድረግ በመሰራት ላይ እንዳለ ያጋሩንን ማብራሪያ ይዘን ቀርበናል።
እንደ አቶ ብሩክ ገለፃ፤ ግብይትን ህጋዊ ከሚያደርጉ ስርዓቶች መካከል ደረሰኝ ዋንኛው ነው። ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ጥቅም ላይ እየዋለ ያለበት መንገድ በማንዋል አሊያም የወረቀት ልውውጥን ተከትሎ የሚካሄድ በመሆኑ ለተጠቃሚውም ሆነ ለመንግስት ምቹ አይደለም። በተለይ በመንግስት በኩል አስፈላጊውን ግብር ለመሰብሰብ እንዳላስቻለ ይገለጻል። ይህም ህገወጥ ነጋዴዎች ግብርን እንዲሸሽጉና እንዲያጭበረብሩ ምቹ ሁኔታ እንዲኖር አድርጓል።
“በአገራችን ከፍተኛ የሆነ የግብር መሸሸግ ወይም ማጭበርበር ይካሄዳል” የሚሉት የዲቪዥኑ ዳይሬክተር፤ በብዙ ቢሊየን ብሮች ለግብር ስወራና ማጭበርበር ተጋላጭ መሆናቸውን ይናገራሉ። ይህም ህዝብንና መንግስትን በከፍተኛ ደረጃ ተጎጂ እንዳደረገ ይገልፃሉ። በተለይ በወጪና ገቢ ንግዱ ላይ ከፍ ያለ ካፒታል በህገወጥ መንገድ ከአገር እንዲወጣ ምክንያት ሊሆን መቻሉን ነው የሚያስረዱት፡፡
በተለይ በወጪና ገቢ ንግዱ ላይ ከፍ ያለ ካፒታል በህገወጥ መንገድ ከአገር እንዲወጣ ምክንያት ሊሆን መቻሉንም ያስረዳሉ። በዚህ ምክንያት ኤሌክትሮኒክ ደረሰኝን በመጠቀምና በግብይት ስርዓት ውስጥ በቴክኖሎጂ አማራጭ ተፈፃሚ እንዲሆን በማስቻል ችግሩን ለማቃለል መንግስት እየሰራ መሆኑን ይገልጻሉ።
“እስካሁን በተቀናጀ የደራሽ ፕላትፎርም ደረሰኝ በዲጅታል አማራጭ እየቀረበ ይገኛል” የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ ይህንን እንደ አንድ የቴክኖሎጂ አቅምና ተሞክሮ በመጠቀም በዋናነት በኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረገውን ግብይት የተሳለጠ ለማድረግ የኤሌክትሮኒክስ ደረሰኝ ጥቅም ላይ ለማዋል እየተሰራ መሆኑን ያመለክታሉ። በዋናነትም የተለያዩ አገሮች ልምድን በመውሰድ በአገር ውስጥ የቴክኖሎጂ ፕላትፎርም አበልፃጊዎች በዋናነትም በኢንፎርሜሽን መረጃ መረብ ደህንነት አስተዳደር አማካኝነት መፍትሄ ለመስጠትና ኤሌክትሮኒክ ደረሰኝ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን ያስረዳሉ።
“ልክ እንደ ደራሽ ፕላትፎርም ለዜጎች የሚደርሱ አገልግሎቶች ኢንሳ ያቀርባል ማለት አይደለም” የሚሉት የዲቪዥኑ ዳይሬክተር፣ ይሁን እንጂ ይህን የዲጂታል አማራጭ ለግል ዘርፉ በአገር ውስጥ አቅም ያለማንም አካልና የቴክኖሎጂ ጥገኝነት ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን ነው የጠቆሙት።
እሳቸው አንደሚሉት፤ ከዚህ ቀደም በደራሽ ፕላትፎርም ተከታታይ ቁጥር ያላቸው የመንግስት አገልግሎት የሚሰጡ ደረሰኞችን የማቅረብ ስራ ለማከናወን ቴክኖሎጂውን በኢንሳ በኩል የማበልፀግ ስራ ተከናውኗል፤ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ይፋ በሚደረገው “ኤሌክትሮኒክስ ደረሰኝ” ደግሞ ማንኛውንም ግብይት አሊያም ሽያጭና ግዥን የሚፈፅም አካልን የሚያገናኝ ዲጅታል አማራጭ ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ ነው። ከመጀመሪያው ፕላትፎርምም በተጠቃሚና በሚሰጠው ግልጋሎት ይለያል።
ቴክኖሎጂው ከማንዋል የደረሰኝ ስርዓት የሚለየው የወረቀት አሰራርን በማስቀረቱና ለቁጥጥር ምቹ አማራጭ በመፍጠሩ ነው የሚሉት አቶ ብሩክ፣ በዋናነት ግን ህጋዊ የደረሰኝ መዋቅርን የተከተለ መሆኑንም ይገልፃሉ። ከባንክ “የፋይን ቴክ” ወይም እንደ ቴሌ ብር ያሉ መተግበሪያዎች እነዚህን ደረሰኞች ተጠቅመው ክፍያ ለመፈፀም የሚያስችሉ ይሆናል ይላሉ።
“ክፍያን ያለ ደረሰኝ በማንኛውም አገልግሎት መስጫ ተቋም ማስተናገድ በህግ የተከለከለ ነው” የሚሉት አቶ ብሩክ፣ በቴክኖሎጂ አማካኝነት የሚፈፀሙ ክፍያዎች ደረሰኝ ሲኖር ብቻ ህጋዊ እንደሚሆኑ ይናገራሉ። በዚህ ምክንያትም በዲጂታል አማራጭ በኢትዮጵያ ውስጥ እስከ ዛሬ ተሞክሮ በማያውቅ መልኩ የኤሌክትሮኒክስ ደረሰኝ ጥቅም ላይ እንዲውል የመሰረተ ልማት ግንባታና ሌሎች አስቻይ ሁኔታዎች እየተዘረጉ መሆናቸውን ያብራራሉ።
እንደ አቶ ብሩክ ገለፃ፤ የኤሌክትሮኒክስ ደረሰኝ በግብይት ስርዓት ውስጥ በቀላል አማራጭና ለተጠቃሚ ምቹ በሆነ መልኩ ለማቅረብ በኢንሳ በኩል እየተሰራ ይገኛል። በዚህ ስርዓት ውስጥ ተጠቃሚ የሚሆኑት አካላት በርከት ያሉ እንደመሆናቸው መጠንም ሰፊ የሆነ የቴክኖሎጂ አቅም የሚፈልግና የሚፈጥር ይሆናል። ከዚህም ባለፈ እጅግ በርከት ያሉ የንግድ ተቋማትን ከማስተሳሰሩም በላይ መንግስት የግብይት ስርዓቱን በቴክኖሎጂ አማካኝነት በቀላሉ ለመቆጣጠር ይጠቅማል።
የመረጃ መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢንሳ) ከተለያዩ ባባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በቅርብ ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ የሚያደርገው ኤሌክትሮኒክስ ደረሰኝ የንግድ ድርጅቶችም ሆኖ ክፍያን የሚፈፅሙ ማናቸውም ተቋማት በስርዓቱ ግብይትና ህጋዊ ደረሰኝ ልውውጥ እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። እየበለፀገ የሚገኘው ሲስተምም ዋስትናው በተጠበቀ መልኩ የደረሰኝ አቅርቦት እንዲኖር ያስችላል።
“ይህ የዲጂታል ደረሰኝ በገበያ ስርዓት ውስጥ እንዲያልፍ ሲደረግ የሚያጋጥሙ ችግሮች አሉ” የሚሉት ዳይሬክተሩ፣ በተለይ ሁሉም የንግድ ተቋማትም ሆኑ ዜጎች ሙሉ ለሙሉ ተጠቃሚ እስኪሆኑ ድረስ ብዙ ውጣ ውረዶች ሊያልፍ እንደሚችል ያስረዳሉ። ይሁን እንጂ በቴክኖሎጂ ዙሪያ የሚሰሩ እንዲሁም ዲጂታል ደረሰኝ የሚያስፈልጋቸው ግብይት የሚያካሂዱ ተቋማት ቀዳሚ ተጠቃሚ እንደሚሆኑና ቀስ በቀስ እንደሚለመድ ያስገነዝባሉ።
እንደ አቶ ብሩክ ገለፃ፤ በኦላይን አማራጭ የዲጂታል ደረሰኝን የመሰሉ ፕላትፎርሞች ሲቀርቡ ብዙ አይነት አደጋን ሊያስከትሉ የሚችሉ አካላት ያጋጥማሉ። ይህን መሰል አገልግሎት በበይነ መረብ እስካቀረብክ ድረስ ተጋላጭነትህም ሰፊ ይሆናል። በተለይ ከፋይናንስ ጋር በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ግንኙነት ያለው ከሆነ ለጥቃት የመዳረግ ሁኔታው ከፍተኛ ነው። ይህን መሰል ፕሮግራሞችን ለማጥቃት ፍላጎት ያላቸው አካላትም በስፋት በዓለማችን ላይ አሉ። ይህን ጥቃት ለመከላከል ፕላትፎርሙን ዲዛይን ከማድረግ ጀምሮ ሊሰነዘሩ የሚችሉ ጥቃቶች ምን ሊሆኑ እንደሚችሉ ታስቦ ነው የሚሰራው። ስለዚህ ከስሪቱ ጀምሮ ይህን ታሳቢ በማድረግ ነው እየተሰራ ያለው።
እንደ መውጫ
ጉዳይ ኖሮን ወደ አንድ የመንግስትም ሆነ የግል ተቋም ስንሄድ በቅድሚያ የሚያሳስበን ነገር አገልግሎት ለማግኘት ስንል የሚያጋጥመን “ወረፋ ጥበቃ” ነው። ባለን ውስን ሰዓት ከአንድ በላይ ጉዳይ መፈፀም ሲኖርብን ደግሞ ጊዜያችንን የሚያቃጥለውን ወረፋ ባይገጥመን እንመርጣለን። በተለይ በመንግስት አገልግሎት ሰጪዎችና የክፍያ ቦታዎች ይህን መሰል ችግር በስፋት ያጋጥማል።
በዓለማችን የጊዜና ገንዘብ ብክነትንና እንግልትን ለማስቀረት የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችና የክፍያ ስርዓቶች በስፋት ይታወቃሉ። የአሰራር ስርዓት የሚፈጥረውን እንግልት የሚቀንሱ ፕላትፎርሞች፣ መተግበሪያዎችና ሲስተሞችም ተመራጭነታቸው የሰፋና ጥቅም ላይ እየዋሉ የሚገኙ የዘመኑ አማራጮች ናቸው። ይህን መሰል ዲጂታል አገልግሎት በአገራችን እምብዛም አይታወቅም። አሁን አሁን የተሻሉ ሙከራዎች ይኑሩ እንጂ ቴክኖሎጂውን ለማበልፀግ የሚሰሩ ተቋማት ማግኘትም ያስቸግራል።
በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ብዙ ገንዘብ መሰብሰቢያ ተቋማት አሁንም በእጅ አሠራር ላይ የተመሰረቱ ናቸው፤ ደንበኞቻቸውንም ሒሳብ ለመክፈል በአካል እንዲቀርቡ ይጠይቃሉ። ይህ በሁለቱም በኩል ብዙ ችግሮችን አስከትሏል። ምክንያቱም ሰዎች እስከ አገልግሎት ሰጪዎች ቢሮ ድረስ መሄድ አለባቸው። በአብዛኛዎቹ ጉዳዮች ለፍጆታ፣ ለግብር እና ለሌሎች አገልግሎቶች ሂሳባቸውን ለመክፈል ረጅም ወረፋ ይጠብቃሉ። አንዳንድ ጊዜ የኢንተርኔት ግንኙነት፣ የመብራት መቆራረጥ ወይም በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ባሉ ሌሎች ምክንያቶች አገልግሎቱን በብቃት ማግኘት አይችሉም።
ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ግን በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢንሳ) አማካኝነት የሚደረጉ ሙከራዎች አበረታች ውጤቶች እያሳዩ ነው። ከእነዚህ መካከል የክፍያ ደረሰኞችን ለባንኮች ተደራሽ የሚያደርግ መድረክ እንዲሁም የኤሌክትሮኒክስ ደረሰኝ ተዘጋጅቶ አገልግሎት ላይ እንዲውል እየተሰራ መሆኑ እንደ ምሳሌ መውሰድ እንችላለን።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 18/2014