የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ተቋማዊ ለውጥና አንድነት ሁለተኛ ዙር አገር አቀፍ ጉባኤ በቅርቡ ተካሂዷል። በወቅቱም ጉባኤው የአመራሮች ምርጫ ያካሄደ ሲሆን፤ ሼህ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋን ፕሬዚዳንት፣
ሼህ አብዱል ከሪም፤ ሼክ በድረዲን እና ሼክ አብዱላዚዝ አብዱል ወሊ ምክትል ፕሬዚዳንት አድርጎ መርጧል። በዕለቱም ከሁሉም ክልል የተውጣጡ ሰላሳ የጠቅላላ ጉባኤ አባላት የተመረጡ ሲሆኑ አስራ አራቱ የሥራ አስፈፃሚ ሆነው ተመርጠዋል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡትን ሼህ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋን የዛሬው የ‹‹ወቅታዊ›› አምድ እንግዳችን አድርገናችዋል። መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፡- በቅድሚያ ስለተመረጡ እንኳን ደስ አሎት ለማለት እወዳለሁ። እስኪ ለአንባቢዎቻችን ሼህ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ ማናቸው የሚለውን ይግለጹልን?
ሼህ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ፡- ታሪኬ ሰፊ ነው። ከብዙ በጥቂቱ ለመግለፅ ያህል እኔ የኦሮሚያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት በመሆን ለሦስት አመት ተኩል አገልግያለሁ። ከዚያ በፊት ደግሞ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የኡለማዎች ምክር ቤት ከሃያ ስድስቱ ኡለማዎች አንዱ ነበርኩ። ሚያዝያ ሃያ ሦስት ቀን 2011 ዓ.ም በሸራተን አዲስ ሆቴል በተደረገ ጉባኤ የኡለማዎች አባል በመሆን ተመርጬ ነበር።
የተወለድኩት በ1941 ዓ.ም በአርሲ ዞን አርባ ጉጉ አውራጃ ነው። በልጀኔቴ እኩዮቼ የቀለም ትምህርትን ፍለጋ ሲሄዱ የእኔ ምርጫ ግን ዲን (የሃይማኖት ትምህርት ላይ ማተኮር) ነበር። በወቅቱ የአርባ ጉጉ አውራጃ ከተማ የሆነችው አቦምሳ ከተማ ውስጥ ትምህርት ቤት ተከፍቶ እኩዮቼ ሲመዘገቡ እኔ ግን አንድ ቁርኣንን በማስተማር ከታወቀ ሼህ ወደ መንደራችን መጥተው በመስፈራቸው እሳቸው እግር ስር ለመማር ተመዘገብኩ።
ለእስልምና ትልልቅ ትምህርት የተባሉትን ፈቄና ሀዲስንም በአካባቢያችንና ከአካባቢያችን ርቀው ያሉ ታዋቂ ኡስታዞች ዘንድ እየተዘዋወረኩ ቀራሁ። በልጅነቴም እንደ ዕድሜ እኩዮቼ ከብት አግጃለሁ፤ እርሻን አርሻለሁ፤ ብዙ የገጠር ልጅ ሠርቶ የሚያደገውን ሥራ በሙሉ ሠርቻለሁ። የአካባቢዬ ልጆች የሚጫወቱትንም ጨዋታ ተጫውቼ ነው ያሳለፍኩት። ጥሩ የልጅነት ጊዜ ነበረኝ።
ከአካባቢዬ ልጆች ጋር ለቂራት ወደ ሐረር ሄጄ ቀርቻለሁ። ከተለያዩ ኡስታዞች ስር ተምሬ ቂራቴን ከጨርስኩ በኋላ በአርሲ ክፍለ ሀገር ለሦስት አመታት አስተምሬያለሁ። የዚህ መጅሊስም ከመጀመሪያዎቹ መስራቾች አንዱ ነኝ። መነሻዬ ግን የአርሲ ዞን በጉና ወረዳ የእስልምና ጉዳዮች ሰብሳቢ መሆን ነበር። ከዚያም በአውራጃ ደረጃ የአርባ ጉጉ አውረጃ የእስልምና ጉዳይ ሰብሳቢ፤ በመቀጠል የአርሲ ዞን የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ሰብሳቢ፤ በመቀጠል የኦሮሚያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ሰብሳቢ የነበርኩ ሲሆን፤ አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሆኛለሁ።
ከታች ጀምሬ በታሪኬ እንደምትመለከቱት በተለያዩ ኃላፊነት ደረጃዎች አልፌ የመጣሁ ሰው ነኝ። በዚህ ከፍተኛ የሕይወትና የሥራ ልምድ ያካበትኩኝ፤ በሸሪኣ እውቀት ብዙ አመታትን ሳስተምር የኖርኩ ነኝ። ይህንን የሕይወት ልምድ እና እውቀት በመጠቀም ኢሰላም ሰላም እንደመሆኑ ሰላም ለማስፈን እሠራለሁ።
አዲስ ዘመን፡- የምርጫ ሂደቱ ምን ይመስል ነበር?
ሼህ ሀጂ ኢብራሂም፡– እንደነገርኳችሁ ለዚህ መጅሊስ አዲስ አይደለሁም ነባር ነኝ። ከመሠረቱ ጀምሮ አብሬ የነበርኩ ነኝ። በመካከል ሂደቱ ሲበላሽ አቋርጩ ወደ ሃያ አመታት አካባቢ ከመጅሊሱ የተገለልኩበት ጊዜ ነበር። በወቅቱ አባሽ የሚባል ድርጅት መራሽ እንቅስቃሴ ሲመጣ በአገራችን ያልነበረ ሀሳብ በመጅሊሱ ሲንቀሳቀስ ሳንግባባ ቀረተን ትቼው ወጥቼ ነበር። አሁን ለውጡ ሲመጣ ልመለስ ችያለሁ።
ይህ የለውጥ መንግሥት የፍትሃዊነት መንግሥት እንደመሆኑ መጠን ሕዝባችን መልሶን እንድንመረጥ አደረገ። በዚያ መሠረት ነው ወደዚህ የመጣነው። ስለምርጫው ከጠየቅሽኝ የአሁኑ ምርጫ ከሁሉም ጊዜ በላይ ለየት ያለ ነበር። እንዴት ቢባል አካታችነት፤ አቃፊነት ያለው፤ ሁሉንም ክልል ያካተተ ምርጫ በመካሄዱ የተነሳ ነው። የሁሉም ክልል ተወካይ በውስጡ የያዘ ለአንዱ ያልወገነ ሁሉንም ያቀፈ ምርጫ ነው የተካሄደው።
በአሁኑ ጊዜ ያሉ አስራ አንድ ክልሎችና ሁለት የከተማ መስተዳድሮች አጠቃላይ አስራ ሦስት ክልሎች በአባልነት ብቻ ሳይሆን በሥራ አስፈፃሚነት የተካተቱበት፤ ፍትሃዊ የሆነ ምርጫ እንዲደረግ ሁሉም ራሱን መጥቶ የሚያነብበት የራሱን ተወካይ የሚያይበት ምርጫ የተካሄደበት ነበር።
ሲመረጥም ሁሉም ክልል የራሱን ተወካይ ልኮ፤ የራሱ ተወካይም ለሥራ አስፈፃሚ የሚሆነውን ከራሱ ውስጥ መርጦ ለፌዴራል አስተላልፎ፤ የየክልሉ ተወካይ አንድ ላይ በመሆን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ተብሎ የሚጠራ ስብስብ ተዋቅሯል።
ከዚህ በፊት በዚህ መልክ ምርጫ ተካሂዶ አያውቅም። ሂደቱም ያለ ምንም መንጫጫት ያለ ምንም ውጣ ወረድ ሁሉም የአገራችን ኡለማዎች፤ የአገራችን ባለሀብቶች፤ የአገራችን ወጣቶች፤ የአገራችን ሴቶች ተወካዮች ባሉበት እንዲያውም ታዋቂ ግለሰቦች ባሉበት ተደርጓል። የራሱ አስመራጭ ኮሚቴ ተቀምጦ በራሱ ኮሚቴ አስመራጭነት ተመርጦ ስልጣኑን የተረከበ አካል ነው እዚህ ያለው። ግልፅና ምንም መሸፋፈን የሌለበት የተሳካ የተባለለት የምርጫ ሂደትን ነበር ያሳለፍነው። ይህም ለምክር ቤቱ አዲስ ልምምድ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የስልጣን ርክክቡስ ምን መልክ ነበረው?
ሼህ ሀጂ ኢብራሂም፡– የስልጣን ርክክቡ ጅማሮ ላይ እያለ ነው ወደ ጽሕፈት ቤታችን የመጣችሁት። ያው ርክክቡ ተጀምሯል። ይህ ሲባል የቀድሞ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ጂላን ከድር ቢሮውን አዳራሹን የሥራ ሂደቱን በሙሉ በደስታ አስረክበዋል። የተቀሩት ያላስረከቡት ወደ ሀጂ የሄዱ አሉ፤ አገር ውስጥ ሆነው ሰምተው ይሁን ባለመስማት ያልቀረቡም አሉ። እነዚህ አካላት በሰላማዊ አካሄድ መጥተው የሥራ ርክክብ እንዲያደርጉ ደብዳቤ እየተፃፃፍን እንገኛለን።
የመጀመሪያው ሂደት ላይ የስልጣን ርክክብ ሂደቱ ተጠናቋል ባይባልም አሁን ባለው ሁኔታ በሰላማዊ አካሄድ የርክክብ ሂደቱ እየተጓዘ መሆኑን ለመግለፅ እወዳለሁ።
አዲስ ዘመን፡- አዲሱ አመራር በቀጣይ ሙስሊሙን ማኅበረሰብ አንድ አድርጎ ለመሄድ ምን አስቧል?
ሼህ ሀጂ ኢብራሂም፡– ሙስሊሙን ማኅበረሰብ አንድ አድርጎ ማስቀጠል ከአዲሱ አመራር አላማዎች መካከል አንዱ ነው። ይህ ትልቁና ዋነኛው አላማችንን ለማስቀጠል ምንም ቅድመ ሁኔታ አይኖርም። ይህ አዲስ ወደ ኃላፊነት የመጣው አካል ከዚህ ቀደምም ለአንድነት የቆመ ለአንድነት የሚታገልና ሙስሊሙን አንድ ለማድረግ የሚሠራ ነው። አዲሱ ምክር ቤት ወደ ስልጣን ሳይመጣም ለአንድነት ሲጨነቅ የቆየ ነው።
በሙስሊሙ ማኅበረሰብ ላይ ያለፉት ሥርዓቶች የጣሉብን ጠበሳ አለ፤ ሙስሊሙን አከፋፍሎ የተለያየ ታርጋ ለጥፎበት፤ የተለያየ ስያሜ ሰጥተውት ከፋፍለህ ግዛ እንደሚባለው ሁሉ እኛን ከፋፍሎ ለመግዛት ያልተሠራ ሥራ፤ ያልተገለበጠ ድንጋይ አልነበረም።
እኛ አመጣጣችን ትልቁና ዋነኛው ያንን ጠባሳ ለማከም ነው፤ ያንን በሽታ ለማዳን ነው። አይደለም ሙስሊም የተለያዩ ሃይማኖቶች በአገራችን በአንድነት፣ በፍቅር እና በትብብር የሚኖሩባት አገር ናት። ይህ ሁሉ ጉዳይ ግን ጥያቄ ውስጥ የገባበት ጊዜ ላይ እንገኛለን። ይህ ጉዳይ ጠርቶ ሁሉም ሕዝበ ሙስሊም በአንድ የሚቆምበትን አካሄድ ለመፍጠር ይሠራል።
ክርስትያኑን ሙስሊም ላይ በማነሳሳት፤ ሙስሊሙን ተነስና በጋራ ቁም በማለት እኔ ሙስሊሞችን እወጋለሁ፤ እናንተም ከእኔ ጋራ ተዋጉ ማለት ከፍተኛ አደጋ ነው። እዚህ ላይ የመንግሥታችን ሆደ ሰፊነትም ይታያል። ይሄንን አባባል ሆነ አሠራር ለማስወገድ አላማ አድርገን የመጣን ሰዎች ነን። ሃይማኖት ከሃይማኖት ጋር እንዳይጋጭ ቢጋጭም እንኳን ቶሎ እንዲታረቅ ማድረግ አላማችን ነው።
እንደተለመደው በአገራችን ሕዝቡ ተቃቅፎ ተባብሮ ተስማምቶ ሁሉም በራሱ ሃይማኖት ኮርቶ እንዲኖር መሥራት የእኛ አላማ ነው። ስለዚህ ተለጣፊ ስሞች ከዚህ ከምርጫ በኋላ ቦታ አይኖራቸውም፤ ተቀብሯል እንኳን ባንልም ክፍፍሉ ታሟል፤ ከዚያ ደግሞ ይሞታል። በዚህም ሙስሊሙ አንድ ይሆናል ኢንሽ አላህ።
አዲስ ዘመን፡- ሃይማኖታዊ አክራሪነትና ፅንፈኝነትን ለመወጋት አዲሱ አመራር ያለው ቁርጠኝነት እንዴት ይገለፃል?
ሼህ ሀጂ ኢብራሂም፡– የሃይማኖት ፅንፈኝነትና አክራሪነት ስለሚባለው እንሰማለን እንጂ ምን እንደሆነ እኛ አናውቅም። ሃይማኖት በተለይ በእስልምና አጠራር እስላም ማለት ሰላም ነው። ይህ አክራሪነትና ፅንፈኝነት ትርጉሙን አናውቅም ግን ጥያቄሽ በሰላም ዙሪያ ከሆነ ሰላም ስለማስፈን እኛ አንጋፋዎች ነን። ሙስሊሞች ሰላም አያደፈርሱም ማለቴ ግን አይደለም፤ በሙስሊም ስም የሚነግዱ አንዳንዶች አሉ። የተለያዩ ስም ያላቸው ከውጭ የምንሰማቸው አሉ። እነዚህ ግን በአገራችን አይታወቁም። እስልምና ሰላማዊነት ነው።
እስልምና ወደ አገራችን ሲመጣ በዲፕሎማሲ መልክ ነው የመጣው። ከታሪኩ ስንሳ፤ ልዑካኖች ከመካ ወደ ኢትዮጵያ ነብያችን ሰላለህ ወአሊህ ወሰለም (ሰ.ወ.ወ) ሲልኳቸው ፍትሃዊና አደራ ተቀባይ አገር ኢትዮጵያ ናትና ሂዱ፤ እዚያ ሄዳችሁ እረፉ ብለዋቸው ወደ አገራችን ሲገቡ የኢትዮጵያ መንግሥት በሰላም ተቀብሎ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ በፍቅር በክብር እንግዳ ተቀባይ አገር መሆኗን አገራችን አስመስክራለች።
እኛም የእነሱ ልጆች እንደመሆናችን መጠን የምናውቀው ሰላምና ሰላምን ነው፤ ፅንፈኝነትና አክራሪነት የሚለውን አናውቀውም። ይህ ከሰላም ውጪ የሆነ አስተሳሰብ ግን በአገራችን አይፈቀድም ሊሞከርም አይችልም። አገራችን ሁሉን ሃይማኖቶች በአንድነት አቅፋ አስማምታ የምትኖር አገር ናት። ስለዚህ በአገራችን አክራሪነትና ፅንፈኝነት አይበቅልም።
አዲስ ዘመን፡- በተቋሙ አካባቢ አለ የሚባለውን የመልካም አስተዳደር ችግር በምን መልክ ለመቅረፍ ታስቧል?
ሼህ ሀጂ ኢብራሂም፡– ለወደፊት መንገዱ ብሩህ ነው። አንድነቱን ጠብቀን አገራችንን ለማልማት ዝግጁ ነን። አንድነቱን ጠብቀን ዲሞክራሲ ለማስፈን ዝግጁ ነን፤ አንድነቱን ጠብቀን ፍትሃዊነትን ለማስፈን ተዘጋጅተናል። እዚህ ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥተን እንሠራለን፤ አደርባይነት፣ አምባገነንነት፣ ቢሮክራሲ በእኛ ውስጥ አይኖርም፤ ቁርኣኑ እንደሚያዘው በፍትሃዊነት ለመሥራት ቆርጠናል። ይሄንን ካልሠራን ለዲን አልሠራንም፤ ለእስልምና አልተሠራም ማለት ነው፤ መርሃችንም አላማችንም ተግባራችንም ከብልሹ አሠራር የፀዳ ፍትሀዊነትን መከተል ነው፤ በአላህ ፍቃድ ይሄንን እናሳካዋለን።
አዲስ ዘመን፡- ሁሉም ክልሎች በምክር ቤቱ ተወክሏል ብለዋል የትግራይ ክልል ተወካይስ ነበሩ?
ሼህ ሀጂ ኢብራሂም፡- የትግራይ ክልል እንደ ማንኛውም ክልል ተወካይ አለው። አንድ አገር ናት ያለችው፤ ዲን ነው። እስልምና አንድ እምነት ነው፤ የትግራይ ሕዝብ ወገናችን ነው፤ የትግራይ ልጆች ኢትዮጵያውያን ናቸው፤ የትግራይ ተወላጆች እንደማንኛውም ክልል ተወካዮቻቸው ተሳተፈዋል፤ ኮታቸውን አግኝተዋል። ሥራ አስፈፃሚ ውስጥም ሆነ ጠቅላላ ጉባኤ ውስጥ ተከታዮቻቸው አሉ። እኛ ይሄንን ነው የምናውቀው።
አዲስ ዘመን፡- እርሶ የሃይማኖት አባት ነዎት፤ ኢስላም ማለት ሰላም ነው ብለዋል፤ እርሶ ከመጡ በኋላ ለሰላም የሚያደርጉትን ጥረት ቢነግሩን? እስካሁንስ ለሰላም ምን ሠርተዋል?
ሼህ ሀጂ ኢብራሂም፡– እኔ በግሌ ለሰላም የሠሯኋቸው ሥራዎች በሕይወት ዘመን ካከናወንኳቸው ተግባራት መካከል በጉልህ ቀለም የተፃፈ ነው። እኔ የአገር ሽማግሌ ነበርኩ። አገር ማረጋጋት ላይ ስሰራ ነበርኩኝ። በሽምግልና በኩል ደግሞ እንደ ኦሮሚያ ለሰላምና ለማረጋጋት ለማቀራረብ ፓርቲዎች ሳይቀሩ እንዲቀራረቡ ለማድረግ ሠርቻለሁ። ኦነግና ኦህዲድ መሀል ገብቼ ለማስታረቅ በርካታ ሥራዎች ሠርቻለሁ። አንድ ክልል የሰላም አምባሳደርነት ወረቀት እንስጥህ ብለውኝ ነበር። እኔ የምሠራው ለአላህና ለአገሬ በመሆኑ እውቅና አያሻኝም በማለት አልተቀበልኩም።
ብዙ ጊዜ ግጭቶችን የፈታሁበት ሁኔታ አለ። ለሠራኋቸው ሥራዎች ወረቀት አልወሰደኩም የምሠራው ለአገሬ ለህሊናዬ በመሆኑ ማስረጃዎች የለኝም። አሁንም በበለጠ ለአገሬ ሰላም፣ ለአገሬ አንድነት፣ ለአገሬ መረጋጋት ልክ ለሃይማኖቴ እንደምሠራው ለአገሬም እሠራለሁ። ሥራዎቼን በሃይማኖታዊ አባትነት ከፖለቲካ ውጪ በሆነ መንገድ ለአገር ሰላም ልሠራ ወስኛለሁ።
አዲስ ዘመን፡- የአሠራር ግልፀኝነትን ማስፈን ለአመራሩ ታማኝነት ከሚኖረው አስተዋፅኦ አንፃር የታሰበ አሠራር ካለ ቢነገሩን?
ሼህ ሀጂ ኢብራሂም፡– እንደ እኔ ግልፀኝነት ትልቁ ባህሪዬ ነው። ግልፀኝነት ከሌለ ሌብነት አለ ማለት ነው፤ ሌብነት ካለ ደግሞ ጥፋተኝነት አለ ማለት ነው። ይሄ ዲናችንም ሃይማኖታችንም ያዛል። ግልፀኝነት ግድ ነው እኛጋ። ስለዚህም ይህን አሠራር ለማስፈን ወደ ኋላ አንልም።
አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻ ለሕዝበ ሙስሊሙም ሆነ ለቀረው የአገሪቱ ሕዝብ የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ?
ሼህ ሀጂ ኢብራሂም፡– የማስተላልፈው መልዕክት በአጠቃላይ ሙስሊሙ ኅብረተሰብ ከአንድነት ውጪ የሚያዋጣው ነገር አለመኖሩን ተረድቶ ሀዲስና ቁርኣንን መሠረት በማድረግ በአንድነት እንዲቆም ነው። የነብዩ መሐመድን ፈለግ በመከተል አንድነትና ኅብረት መፍጠር ተገቢ ነው። የነብዩ መሐመድን ፈለግ፤ የሱሀቦችን ፈለግ በመከተል አንድነትን በመፍጠር አገሪቱን ወደ ሰላም ማምጣት ተገቢ ነው። አገራችን ኢትዮጵያ በኡለማ የበለፀገች አገር ነችና ኡለማዎቻችን የሚሉትን በመስማት መተግበር አስፈላጊ ነው።
የሌሎች እምነት ተከታዮችም የራሳችሁን እምነት እንደምታከብሩ ሁሉ የሌላውን እምነት ማክበር ተገቢ ነው። መጀመሪያ ከራስ እምነት እኩል የሌሎችን እምነት ማክበር አለባችሁ። የሌላውን እምነት ሳያከብሩ ግን እምነቴን አከብራለሁ ማለት ትክክል አይደለም።
ቤተክርስትያን እየተቃጠለ መስጊዴ አይነካም፤ መስጊድ እየተቃጠለ ቤተክርስቲያኔ አይነካ ማለት አይቻልም። ለሁሉም ሰላም፤ ሁሉም ተከባብሮ ተባብሮ ተቻችሎ መኖር ነው የሚያዋጣው። አንድ አገር ውስጥ አንዱ ጎጂ አንዱ ተጎጂ ሆኖ አሸናፊ ይኖራል ማለት አይቻልም፤ ሁሉም ተሸናፊ ይሆናል። ደም እየፈሰሰ ባለበት አገር ሰላም ይኖራል ማለት ስህተት ነው።
ሰው የሰው ልጅ በመሆኑ ብቻ ክቡር መሆኑን በእስልምና አስተምህሮት ውስጥ በጉልህ ተቀምጧል። ሰው በሃይማኖቱ ሳይሆን ሰው በመሆኑ ብቻ ተከብሮ መኖር ይገባዋል። መጽሐፉ የሰው ልጅን አክብረነዋል ሲል ኢስላም ክርስቲያን ብሎ አልለየም፤ ሁሉም የሰው ልጅ ክቡር ነው። በሃይማኖት መነጣጠል፤ በማንነት ደም መፋሰስ ይብቃ፤ አይደለም ደም ማፍሰስ የሰው ልጅን መበደልም ተገቢ አለመሆኑን ሃይማኖቱ ያስተምራል። እንደ ሸሪአ በሃይማኖት መከፋፈል፤ በማንነት መነጣጠል፤ በማንነት ደም ማፍሰስ ይብቃ። በሰላም ተከባብረን ተፈቃቅረን እንደተለመደው እንደኖርንበት ልማዳችን እንኑር።
አዲስ ዘመን፡- ውድ ጊዜዎን ሰውተው ሀሳብዎትን ስለካፈሉን ከልብ እናመሰግናለን። መልካም የሥራ ዘመን እንዲሆንልዎ እንመኛለን።
ሼህ ሀጂ ኢብራሂም፡– እኔም አመሰግናለሁ።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ሐምሌ 18/2014