ኢትዮጵያ አስገራሚ የተቃርኖ አገር ናት። ብዙ እርስ በርሳቸው የሚላተሙ ነገሮች፤ ሀሳቦች እና ተግባራትን አንድ ላይ የያዘች። ሃይማኖተኛ ሕዝብ የሞላባት ነገር ግን በዚያው ልክ የሰው ልጅ እንደ ትንኝ በየቦታው እርስ በእርስ የሚገደልባት፤ የአፍሪካ የውሀ ማማ የምትባል ነገር ግን ድርቅ በቋሚነት የሚጎበኛት፤ ብዙ ውብ ታሪክ ያላት ነገር ግን የጋራ ጀግና መፍጠር ያቃታት ወዘተ…። እነዚህ ሁሉ ተቃርኖዎች በየጊዜው በብዙዎች ብዙ ተብሎባቸዋል፤ ተቃርኖዎቹን ለማረቅም ብዙ ተሞክሯል። ነገር ግን ብዙም ስኬት አልተገኘም። የዛሬው ጽሑፍም ስለ እነዚህ ተቃርኖዎች ለማውራት ሳይሆን ሌላኛውን ተቃርኖ ለማሳየት እና መፍትሄ ሊሆን የሚችል ሀሳብን ለመጠቆም ነው።
ኢትዮጵያ የተቋማት አገር ናት። ይህን ስል ብዙዎች ሊገርማቸው ይችላል። ነገር ግን ሀቁ ይሄ ነው። ሊያውም ትውልዶችን የተሻገሩ ተቋማት አገር። እስኪ ተመልከቱ አብያተ ክርስቲያናቱን፤ ገዳማቱን፤ መስጊዶቹን፤ እድሮቹን፤ ሰንበቴዎቹን…። እነዚህ ተቋማት ናቸው። አብዛኞቹ ከአንድ በትንሹ ከአንድ ትውልድ በላይ በትልቁ ደግሞ ለክፍለ ዘመናት የቆዩ ናቸው። እስኪ በአቅራቢያችን ያለውን ቤተ ክርስቲያን እንመልከት፤ ስንት አመቱ ነው ለምሳሌ እኔ ባለሁበት አካባቢ ካሉት አብያተ ክርስቲያናት መሀከል ሁለቱ አንድ ክፍለ ዘመን (መቶ አመት) በላይ ዕድሜ ያላቸው ናቸው።
የቤተሰቦቼ እድር ከ70 አመት በላይ አልፎታል። ጎርቤታችን የሚጠጡት ጽዋ ከእናታቸው የተረከቡት ነው። እነዚህ የትውልዶች እድሜ ያላቸው ተቋማት የምኖርበትን አካባቢ ቅርጽ በማስያዝ፤ ትውልድን በማነጽ፤ ባህልን በመገንባት ወዘተ አስተዋጽኦቸው ላቅ ያለ ነው። እነዚህን ተቋማት እንዴት ፈጠርናቸው? በምንስ ዓይነት ጥበብ አጸናናቸው? ይህ ወሳኝ ጥያቄ ነው። እንዲህ ትውልድን የሚሻገሩ ተቋማትን የፈጠረ እና ለዘመናት ያስቀጠለ ሕዝብ ወደ መንግሥታዊ ተቋማትስ ሲመጣ ምን ችግር ገጥሞት ነው ተቋማቱ አልበረክት ያሉት? ባለ ብዙ ጠንካራ እና አንጋፋ ተቋም አገር በተቋማት አለመኖር የመቸገር ተቃርኖ ውስጥስ የገባችው እንዴት ነው? እነዚህ ጥያቄዎች ወሳኝ ጥያቄዎች ናቸው።
ተቋማትን በመፍጠር ሂደት ዋነኛው እና ከባዱ ሥራ ተቋምን ሕዝባዊ ማድረግ ነው። ለምሳሌ ከላይ የጠቀስናቸውን ተቋማት እንመልከት። እኛ ጋር ከ100 አመት በላይ እድሜ አላቸው ያልኳችሁ ተቋማት ባለቤትነታቸው የሕዝብ ነው። በየጊዜው አዳዲስ አለቆች፤ አዳዲስ ካህናት፤ አዳዲስ ዲያቆናት ይመጣሉ፤ ይመራሉ፤ ያገለግላሉ፤ ጊዜው ሲደርስ ግን ለተረኛ ቦታ ለቀው ይሄዳሉ። ከደብሩ ጋር የሚቀረው ሕዝብ ብቻ ነው። ሕዝብ በጊዜያዊነት የመጡት አለቆችም ይሁን አገልጋዮች የተላኩበትን አገልግሎት እንዲያገለግሉ እንጂ ከዚያ ባለፈ ያለ ነገር እንዲያደርጉ አይፈቅድላቸውም። ለምሳሌ አንድ አዲስ አለቃ መጥተው የጸሎቱን ሰዓት ከዚህ ወደዚያ አሻግሬዋለሁ ቢሉ የሚቀየረው የጸሎቱ ሰዓት ሳይሆን አለቃው ናቸው። በነዚህ አድባራት ያለው ትልቁ ቁምነገር ሕዝብ ለተቋሙ የባለቤትነት ስሜቱ ከፍ እንዲል ማደረጉ ነው። በዚህም የተነሳ በአድባራቱ የሚካሄድ ማንኛውም ልማት በሌላ አካል በጀት የሚከናወን ሳይሆን በሕዝብ ተሳትፎ ብቻ የሚከናወን ነው።
ይህን ሁኔታ ወደ አገር ስናመጣው ግን ነገሩ የተገላቢጦሽ ሆኖ እናገኘዋለን። ሕዝብ የእኔ ነው የሚለው ተቋም ብዙም አይገኝም። ተቋማቱ በሙሉ ስልጣን ላይ ያለው አካል ነው። በዚህም የተነሳ ነው የደርግ ወታደር፤ የኢህአዴግ ወታደር፤ የብልጽግና ወታደር ወዘተ የተፈጠረው። ማንም ስልጣን ላይ ያለ አካል ተቋማቱን በሕዝብ መልክ ሳይሆን በራሱ መልክ ለመስራት ስለሚሞክር ሕዝቡ በተቋማቱ ውስጥ የራሱን መልክ ያጣዋል። በዚህም የተነሳ ቢፈርሱም ቢኖሩም አብሯቸው የሚቆም ሕዝብ የለም።
ሁለተኛው ከላይ የጠቀስኳቸው ተቋማት የቆሙበት ጥበብ ደንብ እና አሠራር ነው። በየጊዜው የማይቀያየር፤ በግለሰብ ልክ ያልተሰፋ ፤ ዘመንን እንዲሻገር ሆኖ የተቀመረ ደንብ እና ሥርዓት አላቸው። ለምሳሌ የጎረቤታችንን ማህበር ማየት እንችላለን። ማህበሩ ድሮ እናትየው እያሉም ሆነ አሁን ልጃቸው እያለች ሥርዓቱ ያው ነው። የተጻፈም ባይሆን የሚታወቅ አካሄድ አለ። የማህበሩ ሙሴ መብት እና ግዴታ፤ የማህበሩ አባላት መብት እና ግዴታ፤ የአዲስ ገቢ አቀባበል፤ የነባር አባላት ስንብት ወዘተ..ሁሉም ሕግ እና ሥርዓት አለው። ያን ሥርዓት በዘፈቀደ መነካካት እና መቀያየር አይቻልም። ይህን ለማድረግ የሚፈልግ አካል ቢኖር እንኳ ተቋማቱ ቀድሞውንም ግለሰቦችን ሳይሆን መላው አባላቶቻቸውን ዋነኛ የስልጣን ባለቤት ያደረጉ በመሆናቸው እንዲሁ በቀላሉ መቀየር አይቻልም።
ወደ ተቋማቶቻችን ስንመጣ ታሪኩ ሌላ ነው። ሕግ ሁሌም ይረቃል፤ ሕግ ሁሌም ይሻራል። ተቋሙን የሚመራው አካል አሠራሩን በሕጉ ልክ ከማድረግ ይልቅ ሕጉን መሪው በሚመቸው ልክ እንዲስተካከል ይደረጋል። ቀጥሎ የሚመጣውም ሰው እንዲሁ ያደርጋል። ሁሉም እንዲህ እያደረገ ሰለሚሄድ ሕጉ ለወጉ ያህል የተቀመጠ እንደሆነ ይታወቃል። ሕግ አውጪውም ፤ ሕግ አጽዳቂውም ፤ ሕግ አስፈጻሚውም ፤ ራሱ ሕጉም ግለሰብ ይሆናል። ስለዚህ መቼም ቢሆን በሕግ የሚመራ ተቋም ማግኘት ብርቅ ይሆንብናል።
እንደዚያ ስል አገሪቱ ምንም ዓይነት ተቋም የላትም ማለት አይደለም። እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ያሉ ነፍስ ያላቸው ተቋማት አሉ። ተቋም የመፍጠር ሙከራም የለም ማለት አይቻልም። በተለይ በጸጥታ ተቋማት በኩል ጠንካራ ሙከራ እንዳለ የሚታይ ነው። ነገር ግን አሁንም ሁለቱን መሠረታዊ ነገሮች ከግንዛቤ ካልከተትን ነገሩ አስቸጋሪ ይሆናል። ጠንካራ ተቋም ለመመስረት ሕዝባዊ ማድረግ እና በሕግ መመራት ወሳኝ ናቸው። እንደዚያ ካልሆኑ ተቋም ሳይሆን መስሪያ ቤት ነው የሚኖረን።
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን ሐምሌ 18/2014